‹‹የልብ ናፍቆት››

 የንባብ ከፍል፡- ኢዮብ 19

 ‹‹እኔ ራሴ አየዋለሁ ዓይኖቼም ይመለከቱታል፣

 ከእኔም ሌላ አይደለም ልቤ በመናፈቅ ዝሎአል›› ቁ. 27

ሰው ከሚያውቀው ወዳጁ ለጥቂት ጊዜ ቢራራቅ ሁለቱም በናፍቆትና በጉጉት ‹‹መቼ እንገናኝ ይሆን?›› በማለት በተስፋ ይጠባበቃሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ናፈቆት ሲይዛቸው ምግብ መብላት፣ ውኃ መጠጣት፣ ሌሊት መተኛት፣ ቀን መሥራት በፍጹም ያቅታቸዋል፡፡ ሐሳባቸው በሙሉ ያለው በተለያቸው ሰው ላይ ስለሆነ የልባቸው ናፍቆት እጅግ ትልቅ ነው፡፡

ኢዮብ በደረሰበት መከራና ችግር ሳይበገር፣ የሚያፅናኑትን ሰዎች ስድብ ሁሉ ችሎ፣ ቢገድለኝም እንኳን በትዕግሥት እጠብቃለሁ ካለ በኋላ ክብር ያለው የናፍቆት ተስፋ በልቡ ውስጥ እንዳለ ይናገራል፡፡ አሁን የለበሰው ከአዳም ያገኘው ሥጋ ጠፍቶ በሚለወጠው ሥጋው እግዚአብሔርን እንደሚያየው፣ የሚያየውም እንግዳ ሆኖ ሳይሆን ራሱ በዓይኖቹ እንደሚመለከተው ይገልጻል፡፡

 ለእኛም ለክርስቲያኖች ያለን ትልቅ የክብር ተስፋ ከመከራችን፣ ከችግራችንና ከፈተናችን በኋላ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት ማየት ነው፡፡ ይህ በራሳችን ኃይል ሳይሆን በክርስቶስ ኃይል ነው፡፡ ክርስቶስ ከሙታን በኵር ሆኖ በመነሳቱና ወደ አባቱ በመሄዱ ለእኛም መንገዱን አዘጋጅቶልናል፡፡ መንገድ ማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን ቤትም እያዘጋጀልን ነው፡፡ ወዳዘጋጀልንም ቤት ሊወስደን አንድ ቀን ያመጣል፡፡ ወንድሜና እህቴ ጌታን ለማየት ምን ያህል ናፍቆት አላችሁ?

ጸሎት፡- አምላኬ ሆይ ባንተ ያለኝን የክብር ተስፋ እንድናፍቅ እርዳኝ፡፡

‹‹የማስተዋል መንፈስ››

የንባብ ክፍል፡- ኢዮብ 32

 ‹‹ሁሉንም የሚችል የአምላክ እስትንፋስ

  ማስተዋልን ይሰጣል›› ቁ. 8

ኢዮብ በደረሰበት መከራና ችግር በፊቱ ያለውን የመጽናናት ጊዜ እያሰበ ለመጽናናት ቢሞክርም ለማጽናናት የመጡት ሰዎች የባሰ ራሱን ጻድቅ በማድረግ በአምልኩ ላይ ክፉ ቃል እንዲናገር አደረጉት፡፡ ብዙ ሰዎች የሚስቱትና ውድቀት ላይ የሚደርሱት ክፉን በክፉ ለመመለስ ሲነሱ ነው፡፡ ኢዮብ ለእነርሱ መልስ እመልሳለሁ ሲል አምላኩን ወደ ማሳዘን ደረሰ፡፡

ኤሊሁ የኢዮብን መመጻደቅ የጓደኞቹንም የማይረባ ማጽናናት ከሰማ በኋላ ያለውን ሐሳብ በማከታተል ዘረዘረ፡፡ እንደ ተናገረውም በሰው ውስጥ መንፈስ አለ፤ ስለዚህም ከእግዚአብሔር መንፈስ ጋር በማገናኘት ዝም ብሎ የአምላኩን ፈቃድ ቢጠብቅ ብዙ እውቀትና ማስተዋል ሊያገኝ ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ሰውን በፈጠረበት ጊዜ የሕይወትን እስትንፋስ እፍ ብሎበት ስለ ነበረ ሰው ሥጋ፣ ነፍስና መንፈስ ያለው ሆነ፡፡ ሰው በመንፈሱ ከአምላኩ ጋር ሊገናኝ ሲችል ሳለ፣ በአዳም ኃጢአት ምክንያት የሰውና የእግዚአብሔር ግንኙነት ተቋረጠ፡፡ አሁን ግን ያን ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነት ለማደስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጣ፡፡

ስለዚህ ሁልጊዜ በመንፈስ ከክርስቶስ ጋር የምንገናኝ ከሆነ አምላካችንንም ሰውንም ሳንበድልና ሳናስቀይም በማስተዋል ልንመላለስ እንችላለን፡፡ ወደ ፊት ባለን ተስፋ ሁሉ ልንታመን የምንችለውም የማስተዋል መንፈስ ሲኖረን ነው፡፡

ጸሎት፡- ጌታ ሆይ! ያለ አንተ ማስተዋል የለኝም፤ ሁሉንም ስለምትችል ጥበብንና ማስተዋልን እንድትሰጠኝ እለምንሃለሁ፡፡

‹‹ጌታን ብቻ ማየት››

 የንባብ ክፍል፡- ኢዮብ 34

   ‹‹ሥጋ ለባሽ ሁሉ በአንድነት ይጠፋል፤

    ሰውም ወደ አፈር ይመለሳል›› ቁ. 15

ለሰው ሕይወትንና እስትንፋስ የሰጠው እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለሆነም የሰጠውን መልሶ መውሰድ ይችላል፡፡ በተለይም ሰው ሲበድለው፣ ሲያማርረው፣ ሲያምፅበት በመቆጣት ወዲያውኑ የሰጠውን መንፈስና እስትንፋስ አይወስድም፡፡ ነገር ግን በትዕግሥት ሰው በጥፋቱ ተፀፅቶ እስኪመለስ ድረስ ያጠብቀዋል፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ ሰው ከምድረ ገጽ በጠፋ ነበር፡፡

እኛም ራሳችን ብንሆን እንኳ እግዚአብሔር በትዕግሥት ባይጠብቀን በንስሐ ወደ እርሱ መምጣትና ማመን አንችልም ነበር፡፡ በጸጋውና በምሕረቱ ሥር ሆነን ሳለ ሰውን መመልከት ትተን እርሱን ብቻ ተስፋ ብናደርግ በይበልጥ ፍቅሩን ልንረዳ እንችላለን፡፡ ስንበድለውና በኃጢአት ስንወድቅ በትዕግሥት ጠብቆን ሊያነሳን እጁን ወደ እኛ ይዘረጋል፡፡

ኤሊሁ ለኢዮብና ጓደኞቹ ስለ እግዚአብሔር የነገራቸውና ያስረዳቸው ስለዚህ ትዕግሥትና ቸርነት ነበር፡፡ እግዚአብሔር ቢፈልግ ለሰው የሰጠውን መንፈስ የመውሰድ ችሎታ እንዳለው አስረዳቸው፡፡

ብዙ ጊዜ በክርስትና ሕይወታችን በሚደርሱብን ነገሮች እናጕረመርማለን፡፡ እግዚአብሔር ለምን ይህንንና ያንን ይፈቅዳል? ለምን ዝም ብሎ ያየኛል? ኃጢአት ሳልሠራ ለምን መከራ ይመጣብኛል? እያልን ጌታን እንደማያስብልን እንደጨካኝ እናደርገዋለን፡፡ ጌታ ግን በዚያ ውስጥ እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንድናውቅና እንድናይ ይፈልጋል ጸሎት፡- ጌታ ሆይ አንተ በመከራ ውስጥ ድል አድርገሃል፤ እኔ በመከራዬ ያንተን ኃይል እንዳይ እርዳኝ፡፡      


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *