‹‹የተለወጠ ሕይወት››

 የንባብ ክፍል፡- መዝሙር 38 

   ‹‹አቤቱ ፈቃዴ ሁሉ በፊትህ ነው

   ጭንቀቴም ከአንተ አይሰወርም›› ቁ .9

ሕይወታችን በእግዚአብሔር ፊት የተገለጠ ነው፤ አንዲትም የተሠወረ ነገር በፊቱ የለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ዓይኖች በከፍታ ብንሆን በዝቅታ እግዚአብሔር ይመለከተናል፡፡ ክፉ ቢሆን መልካም ሥራችን በእርሱ ፊት የተገለጠ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ያለምነውንና የወጠንነውን እንኳ እርሱ ያውቃል፡፡ ስለዚህ ዳዊት ‹‹ፈቃዴ ሁሉ በፊትህ ነው›› ይላል፡፡

ከዚህ ጥቅስ እንድናተኩርበት የሚያስፈልገው ጭንቀታችንም ቢሆን ከእግዚአብሔር ፊት አለመሰወሩን ነው፡፡ ጌታ እንደረሳህ ጭንቀትህንም እንደማይመለከት የመሰለህ ጊዜ የለምን? ለችግርህ መፍትሔ ፈልገህ ግራ ተጋብተህ ስትጨነቅ እምነትህ አልተፈተነምን? በዚህ ሁሉ ጌታ ችግርህን ያውቃል፤ ጭንቀትህም ከዓይኑ ፊት አልተሰወረም፡፡ ሳታስበው ድንገት በችግርህ ይደርስልሃል፡፡

በክርስቲያንነትህ ልትማረው ከሚያስፈልግህ ቁም ነገር አንዱ የሚያስጨንቅህን ሁሉ በጌታ ላይ መጣል ነው፤ በዚህ ዓለም ስንኖር አእምሮአችንን በጭንቀት የሚሞላ ብዙ ነገር ይገጥመናል፡፡ ያን ጊዜ ነው ሃሳባችንን በጌታ እጅ ላይ መጣል የሚገባን፡፡ ዛሬ በሕይወትህ የሚያስጨንቅህ ነገር ምንድነው? መንፈስህ የተረበሸበት አእምሮህ የተጨነቀበት ነገር ካለ ለጌታ አሳልፈህ ስጥ፡፡

 ጸሎት፡- ጌታ ሆይ! ጭንቀቴን ሁሉ በእጅህ አሳልፌ እንድሰጥ ጸጋህን አብዛልኝ፡፡

‹‹እግዚአብሔርን መጠበቅ››

 የንባብ ክፍል፡- መዝሙር 40 

 ‹‹ቆይቼ እግዚአብሔርን ደጅ ጠናሁት፣

   እርሱም ዘንበል አለልኝ

    ጩኸቴንም ሰማኝ›› ቁ. 1

ብዙ ሰዎች ይጸልያሉ፣ ምን ያህሉ ግን በትዕግሥት ጌታን እንደሚጠባበቁ አላውቅም፡፡ ጌታ ኢየሱስ የጸለይነውን እስኪመልስልን በትዕግሥት እንድንጠብቅ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 18 ላይ የሰጠው ምሳሌ ትልቅ ትምህርት ይሰጠናል፡፡ እግዚአብሔር በፍጥነት ለጸሎታችን መልስ የሚሰጥበት ትክክለኛ ጊዜ ያውቃል፡፡ ስለዚህ በቆይታ ከእግዚአብሔር መጠበቅ የጌታን ፈቃድ ማድረግ ነው ብዬ እገምታለሁ፡፡

በተለይ አሁን ባለንበት ዘመን እግዚአብሔርን ከመጠበቅ ይልቅ ከአንድ ነቢይ የጸሎት መልስ መጠበቅ ይቀለናል፡፡ እግዚአብሔርን መጠበቅ አይደለም ወደ እግዚአብሔር መቅረቡንም ብዙዎቻችን ትተነዋል፡፡ እግዚዘአብሔር እንዲህ አለኝ ከማለት ነቢዩ እንዲህ ብሎኛል የሚለውን ማለት ይቀለናል፡፡ ተፈውሰሃል ተብለው ያልተፈወሱ፤ የሞቱ እንዳሉ ሁላችንም በየአካባቢያችን የምንሰማው ሀቅ ነው፡፡ ለእንግዳ ማረፊያ ለሦስት ቀን አስራ ስምንት ሺህ ብር ከፍሎ፣ እናቱ በአራተኛው ቀን የሞቱበት ሲናገር ‹‹ ከእናቴ ወይ ከብሬ አልሆንኩ›› ብሎ የተናገረውን ወንድም ታሪክ ሰምቼ ተገርሜአለሁ፡፡

በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 2 ላይ ኢየሱስ በተወለደ ጊዜ ሰብአ ሰገል መጥተው ሰግደውና ስጦታ ሰጥተው ከተመለሱ በኋላ፣ ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድው ባሰበ ጊዜ ‹‹እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፣ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ አለው›› (ማቴ . 2፡13)፡፡ እግዚአብሔር የተላከውን መልአክ ሄደህ ሄሮድስን በሰይፍ በለው፣ ዲዳ፣ ሽባ አድርገው ማለት ሲችል በመጀመሪያ የተጻፈው የትንቢቱ ቃል ይፈጸም ዘንድ፣ ዮሴፍ ቤተ ሰቡን ይዞ እንዲሸሽ አደረገው፤ ሁለተኛ ከእኔ ምሪት ሳታገኝ ወዴትም እንዳትንቀሳስ አለው፡፡ በዚህ ሥፍራ የእግዚአብሔርን ድምጽ መስማትና ምሪቱን መቀበል አስፈላጊ እንደሆነ እንማራለን፡፡ ዳዊትም እግዚአብሔርን መጠበቅ በሕይወቱ አስተምሮናል፡፡ ዘማሪውም እግዚአብሔርን በመጠበቅ ከዚህ ዓለም አልፎ ስለ ወዲያኛው ዓለም መጠበቅን ያስተምረናል፡፡

  ‹‹ልቆይ ልታገስ ገና አይቀርም ተስፋዬ፣

   ሊወስደኝ ወደ እርሱ ይመጣል የሱሴ፣

   አሁን በእምነት ብቻ ያለኝን ንብረቴን፣

   ይሰጠኛል በሙሉ ስደርስ ወዳገሬ፣

     ግሩም፣ ግሩም ነው ተስፋዬ፣

     ወዲያ ስመለከት ይግላል ደስታዬ››

‹‹ጥ – ማ – ት››

 የንባብ ክፍል፡- መዝሙር 42 

    ‹‹ነፍሴ ወደ ሕያው አምላክ ተጠማች፡-

     መቼ እደርሳለሁ ?

     የአምላክንስ ፊት መቼ አያለሁ? ቁ. 2

 ሰዎች መንፈሳዊ በረከትን ለማግኘት ከሚያስፈልጋቸው ነገር አንዱ ‹‹ጥማት›› ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ሲያስተምር ‹‹ጽድቅን የሚራቡ ብፁዓን ናቸው ይጠግባሉና›› ሲል ተናግሮአል፡፡ ጥማት የሌለው ሰው ውሃ ፍለጋ አይሄድም፤ ያልተራበ እንጀራ አይፈልግም፡፡ ስለዚህ ከሁሉ በፊት መንፈሳዊ ጥማት ያስፈልጋል፡፡ ዳዊት እጅግ ስለ ተጠማ ‹‹ነፍሴ ወደ ሕያው አምላክ ተጠማች›› ይላል፡፡

መንፈሳዊ ሰው ወደ ጌታ እየቀረበ ሲሄድ፣ በዚያው መጠን እየተጠማ ይሄዳል፡፡ ሰማያዊ በረከትና ልምምድ ተነግሮ የማያልቅ ተዝቆ የማይገመስ ነው፡፡ ስለዚህ ምንም ጊዜ ወደ ነገር ሁሉ ፍጻሜ ደርሰናል ለማለት አንችልም፡፡ እንዲህ የምናስብ ከሆነ መንፈሳዊ ጥማት ይጐድለናል፡፡ ሰዎች የተለያየ ነገር ይጠማሉ ለሀብት፣ ለእውቀት፣ ለዝና፣ መንፈሳዊ ሰው ግን እነዚህን ሁሉ የሚመለከተው በሁለተኛ ደረጃ ነው፡፡

ዛሬ ወደ ጌታ ስትቀርብ የፍቅሩን፣ የኃይሉን ስፋትና ጥልቀት እንድታውቅ ከትላንቱ ወደ በለጠ ልምምድ እንድትገባ ጸልይ፡፡ ክርስቲያን የሚረካው በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ትንሣኤ ያገኘውን የጌታውን ፊት ሲያይ ነው፡፡ እስከዚያ ድረስ ጥማቱ አይረካም፣ ልቡም ሙሉ አይሆንም፣ ዛሬ የጌታን ፊት ለማየት ትጓጓለህ? በመስቀል የተሰቀለውን ጌታ በእምነት ለማየት ጥማት ይኑርህ፤ አንድ ቀን ግን ጌታን ፊት ለፊት ታየዋለህ፡፡  ጸሎት፡- ጌታ ሆይ! ጥማቴን አርካ፣ የበለጠ ጥማትም ስጠኝ፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *