‹‹በመቅደስ ማቅረባቸው››
የንባብ ክፍል፡- ሉቃስ 2፡22-38
‹‹በጌታ ፊት ሊያቀርቡት ወደ
ኢየሩሳሌም አመጡት›› ቁ.22
ይህ ድርጊት በሕፃኑ ኢየሱስ ሕይወት የመጀመሪያ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ለዓለም ያለውን ፍቅር ለመግለጽ ማርያምና ዮሴፍ ኢየሱስን ወደ መቅደስ አመጡት፡፡ ይህ ለመልካሙ ምሥራች ምስክሮች ለመሆን ለሚፈልጉ የመጀመሪያ ሥፍራ መሆኑን ታውቃላችሁ? ሁላችንም ሕይወታችንን ለጌታ በማቅረብ እንጀምር፡፡ በየቀኑ ለጥቂት ሰዓት ያለንን የአምልኮ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሕይወታችንን በሙሉ እናስረክበው፡፡
ኢየሱስ በተወለደ ጊዜ ከበረቱ ውጭ ቆሞ ስለ ነበረ ልጅ የተነገረ ታሪክ አለ፡፡ ጠቢባኑ ያመጡትን ስጦታ በአንክሮ ሲመለከት ቆየ፡፡ ጠቢባኑ ስጦታቸውን አበርክተው ሲወጡ እናንተ በጣም ደስተኛ ሰዎች ለኢየሱስ የምትሰጡት ብዙ ነገር አላችሁ፡፡ እኔ ግን ምስኪን እረኛ ስለሆንኩ ምንም የምሰጠው ነገር የለኝም እያለ አለቀሰ፡፡ ከጠቢባኑ አንዱ ‹‹አታልቅስ ልጄ ምክንያቱም ከእኛ ይልቅ አንተ ለኢየሱስ ብዙ መስጠት ትችላለህ፡፡ እኛ አርጅተናል፤ አንተ ግን ገና ልጅ ነህ ስለዚህም ለዚህ ለተወለደው ንጉሥ በሚመጡት ዘመናት ብዙ መስጠት ትችላለህ፡፡ ከሁሉም ይልቅ ደስተኛ ትሆናለህ›› አለው፡፡
በየዓመቱ የክርስቶስን ልደት በዓል በምናከብርበት ጊዜ፣ ጌታ ሕይወቱን እንደሰጠን፣ እኛም ከሕይወታችን የበለጠ ታላቅና የከበረ ስጦታ የለም፡፡ ያለምንም ሁኔታ በዓሉን በምናከብርበት ጊዜ፣ አስቀድመን ሕይወታችንን ለኢየሱስ አንስጥ፡፡ የኢየሱስ ቤተ ሰቦች ወደ ቤተ መቅደስ ወስደው እንዳስረከቡት፣ እኛም ራሳችንን ለጌታ እናስረክብ፡፡
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ! ራሴን ሁልጊዜ ለአንተ እንዳቀርብ እርዳኝ፡፡
‹‹የትውልድ ሐረግ››
የንባብ ክፍል፡- ሉቃስ 20፡41-47
‹‹ክርስቶስ የዳዊት ልጅ … ›› ቁ.41
አይሁዶች ስለ መሲህ የሚያስቡት ብዙ ነገር ነበር፤ ቢሆንም ሁሉም የትውልድ ሐረጉ ከንጉሥ ዳዊት ከተማ በቤተ ልሔም እንደሚወለድ ተስማምተዋል፡፡ ይህም ተፈጸመ፤ ምድራዊ ወላጆቹ ከንጉሥ ዳዊት ዘር ነበሩ፡፡ ነገር ግን ከመወለዱ ከጥቂት ቀናት በፊት ዮሴፍና ማርያም ከቤተ ልሔም በጣም ርቀው በናዝሬት መሆናቸው የሚያስደንቅ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ጊዜ ሰከንድ እንኳ ዝንፍ አይልም፡፡ ልክ በአስፈላጊው ጊዜ የሮማ መንግሥት የግብር አዋጅ በማወጁ ዮሴፍና ማርያም ሳይቀሩ ሕዝብ ሁሉ በፍጥነት ወደ ቤተ ልሔም ለቆጠራ ተሰበሰቡ፡፡
ኢየሱስ ራሱ ኃያሉ እግዚአብሔር ቢሆንም እንኳ ራሱን በጣም ዝቅ በማድረግ የሰውን ሥጋ ይዞ በምስኪን ሁኔታ ተወለደ፡፡ አምላክ ራሱን ዝቅ አድርጎ በሰው ደረጃ ስለወረደ ማንም ሰው ቢሆን እግዚአብሔርና ድነት ልደርስባቸው የማልችል ነገሮች ናቸው ሊል አይችልም፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ራሱን በእያንዳንዱ ሰው ሁኔታ በመግለጡ የተነሣ፣ የሰው ልጆች ሊረዱት የሚችሉት ነበር፡፡
ሌላ የሚያስደንቀኝ ነገር አለ፤ እግዚአብሔር በጣም ብዙ መላእክትና የሰማይ ሠራዊት ቢኖሩትም እንኳ፣ ማርያምና ዮሴፍን ለኢየሱስ አሳዳጊነት እንደመረጣቸው ሁሉ እኛንም ስለ ኢየሱስ የምሥራች እንድንናገር መርጦናል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በ2ቆሮንቶስ 5፡17-20 እንደሚናገረው በእኛ የማስታረቅ ቃል በማኖሩ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን የምንናገር መልእክተኞች ነን፡፡ ለዚህ ታላቅ ነገር ምስክሮች ያደረገን ፍጹማንና ከሰዎች የተለየን በመሆናችን ሳይሆን በምሕረቱ ብቻ ነው፡፡
ጸሎት፡- አምላኬ ሆይ! ስለ ልጅህ አዳኝነት እንድናገር ስለ መረጥከኝ አመሰግንሃለሁ፡፡
‹‹መጻሕፍትን ተረጐመላቸው››
የንባብ ክፍል፡- ሉቃስ 24፡13-27
‹‹ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ
በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን
ተረጐመላቸው›› ቁ. 27
መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርሱ የማይጣላ ነው፤ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ አንድ ዓላማ፣ አንድ ቁም ነገር አለው፡፡ ኢየሱስ የሰው ልጆች ሁሉ አዳኝ መሆኑን ይተርካል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በተለያየ ጊዜ በኖሩና እርስ በርሳቸው በማይተዋወቁ 40 በሚያህሉ ደራሲያን የተጻፈ ሆኖ ሳለ እርስ በርሱ የማይጋጭ መሆኑ፣ ይህ ሁሉ ተዓምር ነው፡፡ ኢየሱስ በኤማሁስ መንገድ ላገኛቸው ሁለት ደቀ መዛሙርት መጻሕፍትን ሲተረጐምላቸው በብሉይ ስለ እርሱ የተነገረው ምሳሌ ሁሉ በትክክል መፈጸሙን በማሳየት ነበር፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከሰጠው ስጦታዎች ሁለተኛው ታላቅ ስጦታ ነው፡፡ ያለ መጽሐፍ ቅዱስ ገለጻ የመጀመሪያው ታላቅ ስጦታ ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ለማወቅ አንችልም፡፡ ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ ስለ ኢየሱስና ሥራው እንዲገለጽልን በመጸለይ ይህን ጥልቅ የሆነ ጉድጓድ እንቆፍር፡፡ በተጨማሪም እንደ ቃሉ መኖር የሚገባን መሆኑን እናስተውል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ ትርጉም መልእክቱን በሕይወታችን በተግባር ያዋልነው እንደሆነ ነው፡፡ በክርስቶስ ያለንን እምነት ለመመስከር ቃላት ሁልጊዜ አስፈላጊ አይደሉም፡፡ የየዕለት ኑሮአችን ጋር የሚስማማ ሲሆን ያ ከሁሉ የሚበልጥ ኃይል ያለው ምስክርነት ነው፡፡
ጸሎት፡- ከዳዊት ጋር እንዲህ ብለን እንጸልይ ‹‹ዓይኖቼን ክፈት ከሕግህ ተአምራትን አያለሁ››
0 Comments