‹‹የኢየሱስ መፈተን››

 የንባብ ክፍል፡- ሉቃስ 4፡1-13

 ‹‹ዲያብሎስም ፈተናውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ

   እስከ ጊዜው ከእርሱ ተለየው›› ቁ.13

ኢየሱስ ልክ እንደ እኛ ከኃጢአት በስተቀር በሁሉ ነገር ተፈትኗል፡፡ ፈተና ሰብዓዊ እስከ ሆንን ድረስ የመኖራችን ክፍል ነው፡፡ ኃጢአት የዓመፅና የራስ ፈቃደኝነት ውጤት ነው፡፡ የራሳቸውን ፈቃድ የሚያደርጉት እግዚአብሔር የተናገረውን ስለሚያውቁ ላለመታዘዝ ነው፡፡ የኢየሱስ ፈተና በቀጥታ ከከሳሹ ከሰይጣን የቀረበለት ነበር፡፡ ኢየሱስ በሥጋው በኩል ተፈትኗል፤ ትክክለኛና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ርሃቡን እንዲያስታግስና እንዲያረካ፤ እንዲሁም ለመብላት የፍላጐቱ ተገዢ እንዲሆን በዲያብሎስ ተፈትኗል፡፡ በመጨረሻም ሊሸሹት ሊያመልጡት ከማይቻልበት ፈተና ውስጥ ገብቶ፤ በሥጋው ብቻ ሳይሆን በነፍሱም፣ በመንፈሱም በመፈተን ድል አድርጐ ወጣ፡፡ 

የእግዚአብሔርን ቃል ባያውቅ ኖሮ በእነዚህ ጮሌ በሆኑ ፈተናዎች ከረሃቡ ለመዳን ሲል ይሸነፍ ነበር፤ ከዚያም ለመስቀል ሞት የተዘጋጀ አይሆንም ነበር፡፡ እርሱ ግን የመንፈስን ኃይል ለሥጋው መጠቀሚያ አላደረገም፡፡ ምናልባት የእኛ ፈተና ሰይጣን ለኢየሱስ  እንዳቀረበለት ዓይነት ላይሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ለእኛ ምንም ትምህርት አናገኝበትም ብለን እናስብ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ክርስቶስ በውስጣችን ያለን ሁሉ ሰይጣንን እንድንቃወመው ተነግሮናል፡፡ ኢየሱስም በቃሉና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ማሸነፉና ድል ማድረጉ ትልቅ ብርታትና መፅናናት ይሰጠናል፡፡ እርሱ ድሉን ያገኘው በሥጋ፣ በዓለምና በዲያብሎስ ላይ ነው፡፡ ድሉ የእኛም ይሁን፡፡

 ጸሎት፡- ጌታ ሆይ አንተ ድል እንዳደረግህ በፈተና ጊዜ ድል እንዳደርግ እርዳኝ፡፡

‹‹የኢየሱስ መናቅ››

 የንባብ ክፍል፡- ሉቃስ 4፡16-30

 ‹‹…ቁጣ ሞላባቸው ተነሥተውም ከከተማ

     ወደ ውጭ አወጡት›› ቁ.28

ኢየሱስ ወደ ናዝሬት ምኵራብ ሄዶ የተገለጸለትን መግለጽ ጀመረ፡፡ አብዛኛውን ምድራዊ ሕይወቱን ያሳለፈው በናዝሬት ነበር፡፡ እነርሱ ኢየሱስን የዮሴፍ ልጅ የመንደራቸው አናጢ ብቻ አድርገው ገምተውታል፡፡ ስለዚህም ከእርሱ ከንፈር ትምህርት ወይም ከእጆቹ ተዓምራት ያደርጋል ብለው አልጠበቁትም፡፡

ይሁንና ስለ ኤልያስና ኤልሣዕ  ለመበለቲቱና ለንዕማን ያደረጉትን በሚነግራቸው ጊዜ በልባቸው ያለማመን ማዕበል ስለነበረ ከከተማቸው አስወጡት፡፡ ነቢያትም እራሳቸው ያደረጉትን ሳይሆን የእግዚአብሔር ውሳኔ ነበር፤ እንዲሁም ኢየሱስ በመንፈስ ይመራ ነበር፡፡ በሌላ ሥፍራ ያደረገውን ለምን አላደረገውም በማለትና በመጨረሻም ራሱን ከኤልያስና ከኤልሣዕ ጋር ያልነፁትን ለምፃሞች ከእነርሱ ጋር ስላወዳደረ ቁጣ ሞላባቸው፡፡ ዋና ሐሳባቸው እርሱ የናቃቸው አስመስለው እርሱን መናቃቸው ነበር፡፡

የማያምኑ አዳኝነቱን ይክዳሉ፤ ሃይማኖታውያን ጌታ መሆኑን ይክዳሉ፡፡ ነገር ግን እናስታውስ! ‹‹ለተቀበሉት በስሙ ለሚያምኑት የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣን ሰጣቸው›› የሚለውን፡፡ በመካዳቸው ያጡት የእግዚአብሔርን ልጅነት ነው፡፡

 ጸሎት፡- ጌታ ሆይ በአገርህና በከተማህ ሰዎች ተንቀሃል፤ ፈቃድህ ቢሆን ባላመኑ ሰዎች ስናቅ እርዳኝ፡፡

‹‹የክርስቶስ መከራ››

 የንባብ ክፍል፡- 1 ጴጥሮስ 2፡11-25  

  ‹‹… ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና››  ቁ. 21

ክርስቶስ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን ስለ ኃጢአታችን መከራን ተቀብሎአል፤ መከራ የተቀበለው በደሙ ከእግዚአብሔር ጋር እንድንታረቅ ነው፡፡ በመከራ እርሱ ምሳሌያችን ነው፡፡ በትክክል እኛም ስለ ክርስቶስ መከራ በምንቀበልበት ጊዜ የእርሱ ባሕርይ በእኛ ውስጥ ይባዛል፡፡

የክርስቶስ ተከታይ ከሆንን ለምን መከራ መቀበል አስፈላጊ እንደሆነ በሥጋዊ አእምሮአችን ለመረዳት ቀላል አይደለም፡፡ ነገር ግን ክርስቶስ መከራውን ሁሉ ፈቃር ለሆነው አባቱ አሳልፎ ሰጠ፡፡ እኛም በእምነት ራሳችንን ክርስቶስ እንዳደረገ አሳልፈን መስጠት አለብን፡፡ ስድብን በስድብ፣ ዛቻን በዛቻ በሚለው በዓለማዊ መንገድ ሳይሆን፣ እርሱ ያደረገውን በየዋህነት ማድረግ አለብን፡፡

መከራ የምንቀበለው በሁለት መንገድ ነው፤ አንደኛው በራሳችን ኃጢአት ምክንያት ሲሆን፣ ሁለተኛው እኛ ስለ እውነት ስንሰደድ የሌሎች ኃጢአት ስለሚገለጥ መከራን እንቀበላለን፡፡ በዓለም ውስጥ ያለው መንፈስ በእኛ ውስጥ ያለውን መንፈስ አይወድም፡፡ ክርስቶስ በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ በመስጠቱ በመከራ ላይ ድልን አግኝቷል፡፡ እኛም እንደ እርሱ ራሳችንን ለጌታ አሳልፈን ብንሰጥ፣ በእርሱ አሸናፊዎች እንሆናለን፡፡

 ጸሎት፡-ጌታ ኢየሱስ ፈቃድህ ቢሆን አንተ ለእኔ መከራን እንደተቀበልህ እኔም ላንተ መከራን እንድቀበል እርዳኝ፡፡ 


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *