‹‹ራስን ማስረከብ››
የንባብ ክፍል፡- ሮሜ 12፡1-9
‹‹ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው
ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ›› ቁ.1
ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማወቅ ከእርሱ ጋር ለሚኖረን ግንኙነት (ሕብረት) ጠቃሚ ነው፡፡ ብዙ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅና እርሱን ለማስደሰት በመጀመሪያ ምን እርምጃ መውሰድ እንደሚገባቸው ማወቅ ይፈልጋሉ፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ሮሜ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ የእግዚአብሔርን ፈቃድ አውቀን ልንመላለስ ስለምንችልበት ሁኔታ መለኰታዊ መመሪያ ይሰጣል፡፡ ቁጥር 1፣ 2 ላይ ስናተኩር ሰውነታችንን ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ፣ ሕያውና ቅዱስ መሥዋዕት አድርጐ በማቅረብ በጎና ደስ የሚያሰኘውንና ፍጹም የሆነውን ፈቃዱን ፈትነን ለማወቅ እንደምንችል ያብራራል፡፡ ነገር ግን ልባችንን ብቻ ሰጥተነው የቀረውን አካላችንን ለእኛ አገልግሎት ስናውለው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማወቅ አንችልም፡፡ እግዚአብሔር ሕያው መሥዋዕት እንድናቀርብለት ይፈልጋል፡፡ ዳሩ ግን ይህን ማድረግ ጠልተን፣ አሁንም ዓለምን በመምሰል ስንመላለስ፣ ፍጹም ፈቃዱን ከመለየት እንታገዳለን፡፡ ፈቃዱንም በራሳችን ጥረትና ድካም ማድረግ አንችልም፡፡
የእግዚአብሔርን ፍጹም ፈቃድ ማወቅ ከፈለግን ጠቅላላ እኛነታችንን ሕያውና ቅዱስ ስጦታ አድርገን ለእግዚአብሔር እናቅርብ፡፡ ይህ የሚሆነው በርኅራኄው (በምህረቱ) ነው፤ በሮሜ 8፡1 ላይ ‹‹እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት፣ አሁን ኵነኔ የለባቸውም›› ተብሎ በታወጀው ምሕረት መሠረት ራሳችንን ማቅረብ ስንችል ተቀባይነት እናገኛለን፡፡ ያን ጊዜ ፈቃዱን እናውቃለን፡፡
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ!! ከዚህ በፊት ልቤን ሰጥቼህ ነበር፤ አሁን ደግሞ ጠቅላላ እኔነቴን አስረክብሃለሁ፡፡
‹‹እንደ ፈቃድህ ይሁን››
የንባብ ክፍል፡- ሉቃስ 1፡26-45
‹‹እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ›› ቁ.3
በአንዲት አነስተኛ መንደር ውስጥ አንዲት ክርስቲያን አግብታና አንድ ልጅ ወልዳ በደስታ ትኖር ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላ ቧሏ በድንገት ታሞ ሞተ፡፡ ከሟች ባሏም የወለደችው ሕፃን ልጅ በተጨማሪ ታሞ ከሞት አፋፍ ደረሰ፡፡ የዚህን ጊዜ በልጇ ሕመም ተበሳጭታ የሚከተለውን የብስጭት ጸሎት ጸለየች፡፡ ‹‹ጌታ ሆይ! አይደረግም! የእኔ ልጅ አይሞትም! በፍጹም!! ከመዳኑ በቀር የምቀበልህ ፈቃድ የለም›› አለች፡፡እግዚአብሔርም ስለ ጠንካራ ፈቃዷ ልጇን ፈወሰው፡፡ ያ ልጅ ሲያድግ፣ ሕግ አፍራሽ በመሆኑ ተይዞ ሞት ተፈረደበትና ተገደለ፡፡ እናቲቱም ሕፃን ሆኖ ሳለ ሲታመም የጸለየችው ጸሎት የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚቃወም ስለ ነበር ተጸጸተች፡፡ በኑሮዋ ሁሉ ያንን በማስታወስ በመቆጨት ኖረች ይባላል፡፡
‹‹የእኔ ፈቃድ አይሁን ያንተ እንጂ›› ማለት በፍጹም እሽታ የእግዚአብሔርን ፈቃድ መቀበል ነው፡፡ ጌታ በዚያ የመጨረሻ ሰዓቱ ሲጸልይ ‹‹የእኔ ፈቃድ አይሁን ያንተ እንጂ›› አለ፡፡
የጌታ መልአክ ለማርያም የክርስቶስን ከእርስዋ መወለድ ሲነግራት ‹‹ለባሪያህ እንደ ቃልህ ይሁን›› ብላ መለሰች፡፡ በሕይወታችን እግዚአብሔር ለመፈጸም የሚፈልገው ነገር መኖሩን ስንረዳ ከማርያም ሕይወት ምሳሌ አግኝተን ‹‹እንደ ፈቃድህ ይሁን›› ማለትን እንማር፡፡ በሕይወታችን የሚያልፈው ነገር የቱንም ያህል ከባድ ቢሆንም፤ ራሳችንን ለጌታ ስናስረክብ እንደ ቃልህ ይሁን ማለት ይቀለናል፡፡
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ!! በሕይወቴ ማድረግ የምትፈልገውን በደስታ እንድቀበል ፈቃዴን ለፈቃድህ ማስገዛት አስተምረኝ፡፡
‹‹ሐሴት አድርግ››
የንባብ ክፍል፡- ሉቃስ 1፡46-56
‹‹ነፍሴ ጌታን ተከብረዋለች፣ መንፈሴም በአምላኬ
በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፣ የባሪያይቱን
ውርደት ተመልክቶአልና›› ቁ. 47.
የእግዚአብሔርን ታላቅነት፣ በማሰብ ብዙ ሰዎች የምስጋና መዝሙር ዘምረዋል፡፡ የዛሬው የንባብ ክፍል እንደዚህ ካሉት መዝሙሮች አንዱ ነው፡፡
የማርያም መዝሙር መጀመሪያ ምስጋና ነው፤ ‹‹ነፍሴ እግዚአብሔርን ታከብረዋለች በአምላኬም በመድኃኒቴም ሐሴት አደርጋለሁ›› ብላ ዘመረች፡፡ ምስጋና የመዝሙርዋ መጀመሪያ ሲሆን፣ ‹‹በአምላኬ በመድኃኒቴ ደስ ይለኛል›› ያለችው ቃል ደግሞ ከፍተኛ ቁም ነገር ያዘለ ነው፡፡ ማርያም ከሴቶች ሁሉ ክብር ያላት የጌታ እናት ለመሆን የተመረጠች ብትሆንም ሰው ነበረች፡፡ ለዚህ ነው እኔም በመድኃኒቴ በአምላኬ ደስ ይለኛል ያለችው፡፡ መልአኩም የምሥራች ሲያበስርላት ያቀረበችው ምስጋና የክርስቶስን ወደ ዓለም መምጣት ዓላማ ያብራራዋል፡፡
የአዳም ዘር የሆኑ ሁሉ የጌታችን አዳኝነት ያስፈልጋቸዋል፡፡ እግዚአብሔር አንድ መንገድና አንድ አዳኝ ብቻ ነው ያዘጋጀው፡፡ ስለዚህ እንደ ማርያም ‹‹በአምላኬ በመድኃኒቴ ደስ ይለኛል›› ለማለትና ለመዘመር ብንችል፣ በኃጢአት የተጐሳቆለውን ሕይወታችን ይፈወሳል፡፡ ‹‹መዳን በሌላ በማንም የለም እንድንበት ዘንድ የተገባ ከሰማይ በታች ሌላ ስም የለምና›› የሐዋ. 4፡12. ለዚህ ለተሰጠን አዳኝ ሐሴት እናድርግ፡፡
ጸሎት፡- እግዚአብሔር ሆይ! በሰጠኸኝ አንድ አዳኝ በኢየሱስ ክርስቶስ ደስ ይለኛል፣ ሐሴትም አደርጋለሁ፡፡
0 Comments