‹‹የሚገኝ ጥበብ››
የንባብ ክፍል፡- ያዕቆብ 1፡1-7
‹‹ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጐድለው ሳይነቅፍ
በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፣
ለእርሱም ይሰጠዋል›› ቁ. 5
ያዕቆብ ለሚጠይቅ ሰው ጥበብ እንደሚገኝ ይናገራል፡፡ ‹‹ማንም ጥበብ የጐደለው እግዚአብሔርን ይለምን›› በዕለት ኑሮው ሆነ ወይም ከሌሎች ጋር በሚኖረው ኑሮና ችግር ሁሉ ጥበብ አለኝ አያስፈልገኝም የሚል ሰው ማነው? የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያውቅና የሚታዘዝ ሰው በማንኛውም ሁናቴ ጥበበኛ ነው፡፡ ጥበብን የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው፤ ሰው ሊያመዛዝን ይችል ይሆናል፤ እግዚአብሔር ግን ያውቃል፡፡ ከጠየቅነው አስፈላጊውን ዕውቀት ሊሰጠን ይችላል፡፡ ያለዚህ ዕውቀት እውነተኛ ጠቢባን ልንሆን አንችልም፡፡
ነገር ግን በምንጠይቅበት ጊዜ ለመስጠት ዝግጁና ፈቃደኛ መሆኑን ማመን አለብን፡፡ ያዕቆብ የሚፈለግብን ይህ ብቻ መሆኑን ያስገነዝበናል፤ ልንቀበል የምንችለው በእምነት ነውና፡፡ ጥርጣሬ እንዳንቀበል ያደርገናል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር መስጠት እንደማይችል ወይም ፈቃደኛ እንዳልሆነ ማድረጋችን ነው፡፡
ጥበብ የሚገኝ ነው፤ ካወቅንና ፍላጐታችንን ከተረዳን እግዚአብሔርን መጠየቅ አለብን፡፡ ዓለም መልካም ሥፍራ ፈቃዱን እየጠየቅን፣ በፈቃዱ ብንመላለስ፣ ዓለም መልካም ሥፍራ ትሆን ነበር፡፡ የቤተ ክርስቲያንና የእኛም ችግሮች መፍትሔ አግኝተው ኑሮአችን የሰውን ጥበብ ሳይሆን የእግዚአብሔርን ጥበብ ያንጸባርቅ ነበር፡፡
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ ጥበብህን ለመስጠት ፈቃደኛ ነህ፣ ያለማመኔን እርዳኝ፣ የምፈልገውንም ጥበብ ስጠኝ፡፡
‹‹በጥበብ ማደግ››
የንባብ ክፍል፡- ሉቃስ 2፡39-52
‹‹ኢየሱስም ደግሞ በጥበብና በቁመት በሞገስም
በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ያድግ ነበር›› ቁ. 52
ኢየሱስም ልጅ ሳለ እንኳን በጥበብ የተሞላ ነበር፡፡ እርግጠኛ ነኝ በያመቱ ማንኛውም በዚያን ዕድሜ ካሉት ልጆች ሁሉ እንከን የሌለበት እንደ ነበር፡፡ በወላጆቹ በወንድሞቹና በእህቶቹ በጓደኞቹ ዘንድ በጥበብ የሚመላለስበት አስፈላጊ ጥበብ ነበረው፡፡ አንድ ሰው እንደዚህ በማሰብ ሊፈተን ይችላል፡፡ ቤተ ሰቦቹን ትቶ በቤተ መቅደስ መቆየቱ ያለ ጥበብ ያደረገውና ማርያምና ዮሴፍም የማይጨነቁ መስሎት ያለ ማሰብ ያደረገው ነው ብሎ ያስብ ይሆናል፡፡ ለገሠጹትም ግሳጼ መልስ ሲሰጣቸው እንደ ተረዱት አስቦአል፡፡ በቁጥር 50 ላይ እንደምናነበው ከሆነ በፍጹም አልተረዱትም፡፡ የኢየሱስ ትልቁ ጥበቡ ለወላጆቹ ይታዘዝበት እስከ ነበረበት ዕድሜው ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ተገልጦአል፡፡ ራሱን ለቤተ ሰቦቹ አስገዝቶአል፡፡
ኢየሱስ በጥበብ መንገድ አደገ፡፡ ቁ. 52 የሚያሳየን በጥበብ ማደጉን ነው፡፡ በአእምሮ አስተሳሰቡ ማንኛውም ሰው ሁልጊዜ እንደሚያስበው በጣም ሰፊ ነበር፤ በጥበብና በማስተዋል አደገ፡፡ በዚህ መንገድ ለማደግ ኢየሱስ ማጥናት ነበረበት፡፡ አንድ ሰው ካላጠናና ካላሰበ በስተቀር በጥበብ ማደግ በፍጹም አይችልም፡፡
መንፈሳዊ ዕድገቱ በተደበቁት ዓመታት ውስጥ የተገኙ ፍሬአቸውም በአገልግሎቱ ዘመን ውስጥ በግልጽ ታይተዋል፡፡ መጻሕፍትን በደንብ ያጠና ስለነበር ማስረጃዎችን ሁሉ በደንቡ በግልጽ ያቀርብ ነበር፡፡ መጻሕፍትን በማስተማርና በመተርጐም ጥበቡ ተገልጦአል፡፡
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ በመንፈሳዊ ሕይወቴ በጥበብ እንዳድግ እርዳኝ፡፡
‹‹ቃሌ አያልፍም››
የንባብ ክፍል፡- ኢሳይያስ 40፡1-8
‹‹ሣሩ ይደርቃል፣ አበባውም ይረግፋል የአምላካችን ቃል
ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች›› ቁ. 8.
ሰዎች ምድር ሳሉ ለሠሩት ኃጢአት ቅጣቱን በሰማይ ቤት ብቻ የሚያገኙት ይመስላቸዋል፡፡ ነገር ግን ኃጢአት በምድራዊ ሕይወት ጕስቁልና ያመጣል፡፡ ኢየሩሳሌም ትልቅ ምሳሌ ልትሆነን ትችላለች፤ የአምላኳን ቃል ቸል በማለቷና በመዘንጋቷ ኃጢአትን አደረገች፤ ስለዚህም እግዚአብሔር ከእጁ ጣላት፡፡ ስለሠራችውም ኃጢአት ሁለት እጥፍ ተቀበለች፡፡ በዚህ በኃጢአት ምክንያት በገጠማት ጕስቁልና ታዝንና እሮሮን ታሰማ ጀመር፤ አጽናኝ፡- ይበቃል የሚላት ሰው ትፈልግ ነበር፡፡
ስለሆነም ይቅር ባይና አዳኝ እንደሚመጣ የሚያበስርላት ሰው አስቀድሞ አስፈለገ፡፡ ታዲያ ኢሳይያስ ስለዚህ የምሥራች አብሳሪ ነበር፤ በዘመኑ ለሚገኙ ሰዎች የተነበየው፤ ሆኖም በዘመኑ የማይፈታ እንቆቅልሽ ነበር፡፡ ኢሳይያስ ግን አንድ ነገር ያውቅ ነበር፤ የአምላኩ ቃል እንደማያረጅና ሳይፈጸም እንደማያልፍ፡፡ ታዲያ ትንቢቱ ውሎ ይደር እንጂ በእግዚአብሔር ጊዜና ቀን (ቁ. 2ን ተመልከት) ከ600 መቶ ዓመታት በኋላ የትንቢቱ ቃል የነበረው መጥምቁ ዮሐንስ መንገድ ጠራጊው ተወልዶ፣ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ ሆነ፡፡
ዛሬም እግዚአብሔር በቃሉ የተናገራቸው ሁሉ ይፈጸማሉ፤ ስለዚህ የሚፈጸመውን ቃሉን ብንጠብቀውና ብንታዘዘው ጥበብና በረከት በምድርም በሰማይም ይሆንልናል፡፡ ጸሎት፡- ጌታ ሆይ የተስፋ ቃልህን እንዳምን እርዳኝ፤ በጥበብም ያሳድገኝ፡፡
0 Comments