‹‹በኋለኛው ዘመን››
የንባብ ክፍል፡- 1ጢሞቴዎስ 4፡12
‹‹በቃልና በኑሮ በፍቅርም በእምነትም
በንጽሕናም ለሚያምኑቱ ምሳሌ ሁን እንጂ
ማንም ታናሽነትህን አይናቀው››
ሰው ራሱን ወዳድ ሲሆን፣ ፍቅር እየቀዘቀዘና እየጠፋ ይመጣል፡፡ ሰውም በተፈጥሮው መወደድን ይፈልጋል፤ ስለዚህም አንዱ ከሌላው መወደድን ካላገኘ፣ ሁሉም ራሱን ብቻ ወዳድ ከሆነ ፍቅር ሊኖረው አይችልም፡፡ ከፍቅር ይልቅ ክፋት፣ ተንኮል፣ ምቀኝነት፣ ጥላቻ በሰው ላይ ነግሦ ይታያል፡፡
በዛሬው ምንባባችን ለዚህ ነው ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በቃል፣ በኑሮ፣ በፍቅር፣ በእምነት፣ በንጽሕና ምሳሌ ሁን ሲል መልእክቱን የጻፈለት፡፡ ጢሞቴዎስ በነበረበት ጊዜ እውነትን በሐሰት የሚለውጡና ራሳቸውን መውደድ ስለሚያጠቃቸው ለገንዘብ ሲሉ በግብዝነት የሚሠሩ ድሃውንና መበለሊቱን የሚበድሉ ነበሩ፡፡
በዘመናችንም ቢሆን በየትኛውም አገርና ሕብረተ ሰብ ውስጥ ለቤተ ሰባቸው፣ ለሕብረተ ሰባቸውና ለአገራቸው ታማኝ የሆኑና ለእውነት የሚቆሙ ከላይ በጠቀስናቸው ነገሮች ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎች ያስፈልጋሉ፡፡ በተለይም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በቃል፣ በኑሮ፣ በፍቅር፣ በእምነትና በንጽህና ለሚያምኑቱ ሁሉ ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎች (መሪዎች) ያስፈልጋሉ፡፡ በኋለኛው ዘመን ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ቢሆንም በክርስቶስ ሕይወታቸው የተለወጠና የታደሰ የጌታ ፍቅር በሕይወታቸው የፈሰሰ፣ ከራሳቸው ይልቅ ሌላውን የሚወዱ አይጠፉም፡፡ እነርሱም የዓለም ብርሃንና የምድር ጨው መሆን ይኖርባቸዋል፡፡
ወንድሞችና እህቶች ዛሬ ለወንድማችንና ለእህታችን ፍቅር ይኖረን ይሆን? ፍቅር ላለማሳየት በራስ ወዳድነት ወጥመድ ተይዘንስ ይሆን? የኃጢአት ሁሉ ሥር የሆነው ገንዘብ ሕይወታችንን ገዝቶት ይሆን? ራሳችንን ብንጠይቅና ለጌታ ብናስረክብ ከዚህ ሁሉ እስራት ሊፈታን ይችላል (2ጢሞ.3፡1-9)፡፡
ጸሎት፡-አምላኬ ሆይ አንተን እንድወድ ቀጥሎም
ወንድሜን እንደ ራሴ አድርጌ እንድወድ
ጸጋህን አብዛልኝ፡፡
‹‹በአሁኑ ዘመን››
የንባብ ክፍል፡- ቲቶ 2፡12
‹‹ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም
በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፡፡
ድነትን ልናገኝ የቻልነው በእግዚአብሔር ጸጋ እንጂ፣ እኛ ባረገረነው በጎ ሥራ አለመሆኑ በተለይ በክርስቲያኖች ዘንድ የታወቀ እውነት ነው፡፡ ከድነት በኋላ በክርስትና ሕይወት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድና ሐሳብ በመመራት መመላለስ የምንችለው በድካማችንና በጥረታችን ሳይሆን በዚያው ድነትን ባገኘንበት ጸጋ ነው፡፡
የእግዚአብሔር ጸጋ ባለንበት ዘመን እንዴት እንደምንኖር የሚያስተምረን መሆኑን ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ በቲቶ መልእክት ላይ ይገልጸዋል፡፡ ከዚህም ከገለጻቸው ውስጥ አንዱ ኃጢአተኛነትንና ዓለማዊ ምኞትን መካድ ነው፡፡ ዓለማዊ ምኞትን የምንክደው ሐሳባችንን ከዓለማዊ ነገሮች ላይ ስናነሣ፣ የሚያቀርቡልን ደስታን እንድናደርግ የሚያጓጉንን ለነፍሳችን እሾህ የሆኑ ድርጊቶችን ነቅለን ስንጥላቸው ነው፡፡
ዓለማዊ ምኞቶች የምንላቸው በገላትያ 5፡19-21፣ ኤፌሶን 2፡3፣ 1ዮሐንስ 2፡15-17 ላይ የተዘረዘሩት ናቸው፡፡ ዓለማዊ ምኞትን ስንክድ በአንጻሩ ሌላ የምንጓጓለትና የምንናፍቀው ነገር እንዳለ እንመለከታለን፡፡ ይህም የታላቁ አምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ ነው፡፡ እርሱን ስናስብ በማያቋረጥ ጉጉትና በደስታ ስንጠብቅ ልባችን ከዓለምና ከምኞቷ ላይ ሁሉ ይነሣል፡፡
ዘማሪው እንዲህ ይላል፡-
‹‹ግሩም ግሩም ነው ተስፋዬ፣
ወዲያ ስመለከት ይግላል ደስታዬ››
አሁን ደግሞ ጳውሎስ ሌላ ልናደርገው የሚገባንን ነገር ያሳየናል፤ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንድንኖር እነዚህ ሦስት ቃሎች በሦስት አቅጣጫ ያሉንን ግንኙነት ያመለክታሉ፡፡ ራስን በመግዛት ከራሳችን ጋር ያለንን ግንኙነት ያመለክታል፤ ራስን መግዛት ቀላል ነገር አይደለም፣ የማያቋርጥ ዲሲፕሊን ያስፈልገዋል፡፡ በተለይም በዚህ መንገድ ከጸጋ የምናገኘው ትምህርት ለሥጋችን ደስ የሚያሰኘው ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በመንፈስ በኩል በሥርዓት እንድንታነጽ ያደርገናል፡፡ በጽድቅ ሲል ደግሞ ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት ሲያመለክት፣ እግዚአብሔርን በመምሰል የሚለው ደግሞ ከአምላካችን ጋር ያለንን ግንኙነት ያሳያል፡፡
በአሁኑ ዘመን በእነዚህ ሦስት እውነቶች እንድንኖር ጌታ ይጠብቅብናል፤ እኛም እንደሚጠበቅብን ለመኖር ሊረዳን ወደሚችለው ወደ ጸጋው ዙፋን ዕለት ዕለት እንቅረብ፡፡
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ በዚህ በአሁኑ በመጨረሻው ዘመን አንተን አስከብሬ እንዳልፍ እርዳኝ፡፡
‹‹የሰማነውን አጥብቀን እንያዝ››
የንባብ ክፍል፡- ዕብራውያን 2፡1
‹‹ስለዚህ ከሰማነው ነገር ምናልባት እንዳንወሰድ
ለእርሱ አብልጠን ልንጠነቀቅ ይገባል››
ዛሬ ከእግዚአብሔር የሰማነውንና በደስታ የተቀበልነውን እውነት እንድንጥል ለማድረግ የጽድቅና የእውነት ሁሉ ጠላት የሆነው ዲያቢሎስ በብርቱ እየተዋጋን ያለበት አስከፊ ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ ሐዋርያው ጳውሎስ ለዚህ የሚሆን የምክርም የማስጠንቀቂያ የሆነ ቃል አለው፡፡ ‹‹ስለዚህ ከሰማነው ነገር ምናልባት እንዳንወሰድ ለእርሱ አብልጠን ልንጠነቀቅ ይገባል››፡፡
በብሉይ ኪዳን ውስጥ ሰፍሮ የምናገኘው የሙሴ ሕግ በእግዚአብሔር ለሙሴ የተሰጠው በመላእክት አማካኝነት ነበር፡፡ ይህንን ለሙሴ የተሰጠውን አምላካዊ ሕግ የተላለፉና ያልታዘዙ ሁሉ የሚገባቸውን ቅጣት ተቀብለዋል፤ ለዚህም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ወደ ወንጌል መለስ ብለን ስንመለከት፣ ወንጌል በመጀመሪያ የተነገረው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በራሱ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህም ደግሞ የበለጠ የከበረ ያደርገዋል፡፡ ጳውሎስ እንደሚለው በመላእክት በኩል የተሰጠው ቃል ጽኑ ነበር፡፡ ታዲያ በጌታ በኢየሱስ በኩል የተነገረው ቃል ምን ያህል ጽኑ ነው? ይህን ለሚተላለፍና ባለማስተዋል ለሚያልፈውስ ቅጣቱ ምን ያህል የበረታ ይሆን? በጌታ በራሱ የተሰጠውን ድነትን ችላ በማለት አሁን የተሰጠንን የሥጋ ሕይወት ብቻ ብንኖር፣ በምንም ዓይነት መንገድ ከፍርድ ነፃ መሆንና ማምለጥ አንችልም፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን ከጥንት ጀምሮ ለሰዎች በተለያየ ሁኔታ ሲናገራቸው ቆይቶአል፤ እግዚአብሔር በመላእክት በኩል ተናግሮአል፣ በነቢያትም ተናግሮአል፡፡ ነገር ግን በመጨረሻ የሚወደውን አንድያ ልጁን በመላክ ተናገረን፡፡ ልጁም ኢየሱስ በመስቀል ላይ በመሞት ፍቅሩን ገለጠልን፡፡ ይህንንም ፍቅሩን ዛሬ ውድና ክቡር በሆነው ቃሉ በኩል ይገልጣል፣ ለሰዎች ሁሉ ያውጃል፡፡ ታዲያ አንተስ ይህን ታላቅ መዳን ስንት ጊዜ እየደጋገምህ ችላ በማለት አልፈኸዋል እስቲ ረጋ ብለህ አስብበት፡፡
አንተስ ክርስቲያን ወንድሜ ለምትሰማውና ለምታነበው የእግዚአብሔር ቃል ያለህ ጥንቃቄ ምን ያህል ነው? የሰማሃውን አጥብቀህ ያዝ፡፡ ቃሉ ወደ ፍርድ እንዳያመጣን እንስማው፣ እንታዘዘው፡፡
ጸሎት፡- ውድ አባት ሆይ ለመስማት ፈጣን ነኝ፣ ነገር ግን ቃልህን ለመርሳትና በሐሰት ለመወሰድ ደግሞ
እንዳልፈጥን እግሮቼን ተቆጣጠራቸው፡፡
‹‹ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ››
የንባብ ክፍል ያዕቆብ 1፡22
‹‹ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳቸሁን
እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ››
የእግዚአብሔርን ቃል መስማት በጣም የሚያስደስት ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ቃሉን ስንሰማ የሰማነውን የመፈጸም ኃላፊነት እንዳለብን ልንዘነጋ አይገባም፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር የሚደሰትባቸው ቃሉን ሰሚዎች ብቻ የሆኑትን አይደለም፣ ቃሉን ሰምተው የሚያደርጉትን እንደ ቃሉ የሚኖሩትን እንጂ፡፡ በዚህ ጥቅስ መሠረት ብፁዓን የሚያሰኘን መስማቱ ብቻ ሳይሆን መጠበቁ ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ በተሰጠው በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የተዘረዘረው ልዩ የሆነ በረከት ተካፋዮች የሚሆኑት ቃሉን የሚጠብቁ፣ ዘወትር የሚያስቡት፣ የሕይወታቸው መመሪያ ያደረጉት ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ቤታቸውን በዓለት ላይ የመሠረቱ በጊዜው ነፋስና ጐርፍ ቢመቱም የማይወድቁ ጽኑዎች ናቸው፡፡ ለእነርሱ የአምላካቸው ቃል ከወርቅና ከዕንቊ የከበረ ዋጋ አለው፤ ቃሉን የሚተካ ምንም ዓይነት ፍልስፍና የላቸውም፡፡
ከጌታ ጋር ብዙ ጊዜ ያሳለፈው ያዕቆብ በዘመኑ የነበሩትን ክርስቲያኖች ሲመክር ‹‹ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ›› ይላል፡፡ ከዚያም ሐሳቡን በማስፋት በቃሉ የሚጽናና ሰምቶ የማይረሳው ሰው በሥራው ሁሉ የተባረከ እንደሚሆን ያረጋግጣል (ያዕ. 1፡22-25)፡፡ ሰሚዎች ቃሉን ለመስማት፣ ለማንበብና ለማወቅ እንደምንጓጓ ሁሉ በቃሉ ለመኖርም ያንኑ ያህል ፍላጐትና ጥረት ከሌለን ምን ይጠቅመናል? እግዚአብሔር ሊያፈስልን የገባው ብዙ የበረከት ቃል ኪዳን አለ፣ ወደፊትም ከዚህ ሕይወት በኋላ ዘላለማዊ በረከቶች አሉን፡፡ በዚህ ሁሉ ተካፋይ የሚሆኑ ግን ቃሉን የሚጠብቁ ናቸውና እንደ ቃሉ እንኑር፡፡ እስቲ ረጋ ብለህ ዘወትር የምትሰማውን የእግዚአብሔር ቃል ምን ያህል እንደምትጠብቀው አሰላስል፡፡ ሁልጊዜ ይህን በማሰብ ራስህን ብትመረምር እንደ ቃሉ ለመኖር የበለጠ ትጠነቀቃለህ፡፡ ጸሎት፡- ጌታ ሆይ ቃልህን ባለመጠበቃችን ካንተ ዘንድ ያለውን በረከት እንዳናጣ ጸጋህን አብዛልን፡፡
0 Comments