‹‹ዘመኑ አልደረሰም››
የንባብ ክፍል፡- ሐጌ 1፡6
‹‹ብዙ ዘራችሁ፣ ጥቂትም አገባችሁ፣
በላችሁ ነገር ግን አልጠገባችሁም፣
ጠጣችሁ ነገር ግን አልረካችሁም፣
ለበሳችሁ ነገር ግን አልሞቃችሁም፣
ደመወዙን የተቀበለ ሰው በቀዳዳ ከረጢት
ያደርገው ዘንድ ደመወዙን ተቀበለ››
በዛሬው ዕለት የምንመለከተው የምንባብ ክፍላችን፣ ስለ አይሁድ ሕዝብ ሁኔታ የሚያስረዳና እግዚአብሔር በነቢዩ በሐጌ በኩል መልእክቱን ሲያስተላልፍ የሚያሳይ ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር መልእክቱን ከማስተላለፉ በፊት አይሁድ በባቢሎን ተማርከው፣ ለብዙ ጊዜ ከቆዩ በኋላ፣ በዘሩባቤል መሪነት ወደ አገራቸው መግባት ጀምረው ነበር፡፡ ሕዝቡ በምርኮ በተወሰዱበት ጊዜ ቤተ መቅደሳቸውና የኢየሩሳሌም ቅጥር ሁሉ ፈርሰውባቸው ነበር፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቦቹ ተበታትነውና ተጥለው ማየት ስላልወደደ እንደገና ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አደረገ፡፡ አስቀድሞ ወደ ምርኮ የተወሰዱት በኃጢአታቸው ምክንያት ነበር፡፡
አሁን ከምርኮ የተመለሱት ቤቱን እንዲሠሩ ነበር፤ እነርሱ ግን ወደ አገራቸው ከገቡ በኋላም የእግዚአብሔር ቤት ፈርሶ እያለ ዝም ብለው ይመለከቱት ነበር፡፡ ‹‹ይህ ሕዝብ ዘመኑ አልደረሰም፣ የእግዚአብሔር ቤት የሚሠራበት ዘመን አልደረሰም›› (ቁ. 2) እያሉ ቁጭ ባሉበት ጊዜ እግዚአብሔር መልእክቱን በነቢዩ ማስተላለፍ ጀመረ፡፡ በቁጥር 6 ላይ የምንመለከታቸው ሊደርስባቸው የቻለው ሕዝቡ ሁሉም ወደ የቤታቸው ለመሥራት እየሮጡ፣ የእርሱ ቤት ፈርሶ ስለ ተቀመጠ ነበር፡፡ በመጨረሻም ልባቸውን በመንገዳቸው ላይ እንዲያደርጉና ወደ ተራራው በመሄድ እንጨት እያመጡ፣ እግዚአብሔር ቤቱን እንዲሠሩ አዘዛቸው፡፡
ወንድሜ ሆይ የእግዚአብሔርን ቤት እየሠራህ ነው? ወይስ ዘመኑ አልደረሰም እያልክ ይሆን? መቼ ነው የእግዚአብሔርን ቤት የምትሠራው? የምትሠራበት ዘመን ገና ይመስልሃልን?
ጸሎት፡- አምላኬ ሆይ ቤትህን እሠራ ዘንድ
የፈረሰውን ሥፍራ አሳየኝ፡፡
‹‹የንግግር ጊዜ››
የንባብ ክፍል፡- ዘካርያስ 7፡13
‹‹እኔ በጠራሁ ጊዜ እነርሱ እንዳልሰሙኝ፣
እንዲሁ እነርሱ በሚጠሩበት ጊዜ እኔ አልሰማም››፡፡
በሁለት ሰዎች መካከል ንግግር በሚደረግበት መደማመጥና መልስ መስጠት አለ፤ አንዱ ሲጠራ ሌላው አቤት ይላል፣ አንዱ ሲጠይቅ ሌላው መልስ ይሰጣል፤ አንዱ ሲያመሰግን ሌላው ይቀበላል፡፡ ንግግር ሰዎች አሳባቸውን ከሚገልጹበት መንገድ አንዱ ነው፡፡
እግዚአብሔርም ሰዎችን ከፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ከፈጠራቸው ሰዎች ጋር ብዙ ጊዜ ንግግር ሲያደርግ በቃሉ ውስጥ እንመለከታለን፡፡ እግዚአብሔር የጠፋውን አዳምን ለመፈለግ ‹‹አዳም የት ነህ››? ብሎ ተጣራ፤ አዳምም ለእግዚአብሔር መልስ ሰጥቷል፡፡ እግዚአብሔር ከአብርሃም፣ ከይስሐቅ፣ ከያዕቆብና ከሙሴ ጋር እንዲሁም በየዘመናቱ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ንግግር አድርጓል፡፡ ዛሬም እግዚአብሔር ከእያንዳንዳችን ጋር በመንፈሱ ሊያነጋግረን ፈቃደኛ ነው፡፡
እግዚአብሔር የአይሁድን ሕዝብ ሊያነጋግር ሲጠራቸው፣ እነርሱ ለመስማት ፈቃደኛ አልነበሩም፤ በራሳቸው አሳብና መንገድ፣ በራሳቸው ምኞትና ዕቅድ ይጓዙ ስለ ነበር፣ የአምላካቸውን ድምጽ ለመስማት አልፈለጉም፡፡ በትዕቢት ተይዘው ስለ ነበረ፣ እግዚአብሔርን ለመታዘዝ አልፈለጉም፡፡ ነገር ግን ችግርና መከራ በያዛቸው ጊዜ ወደ አምላካቸው መጣራትና መጮህ ጀመሩ፡፡ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ጩኸታቸውን ሰምቶ እንደገና ሰበሰባቸው፡፡ ከምርኮ አገር ከባቢሎን ወደ አገራቸው ኢየሩሳሌም እንዲገቡ አደረጋቸው፡፡
ዛሬ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር በቃሉ ሊነጋገር በሚችልበት ጊዜ ወደ እርሱ እንቅረብ፡፡ በልጁ በኢሱስ በኩል ሆኖ ይጣራል፤ ሲጠራንም ድምጹን ሰምተን መልስ እንስጠው፡፡ ኃጢአተኛና በደለኛ መሆናችንንም እንንገረው፤ እርሱም ይሰማናል፣ መልስም ይሰጠናል፡፡
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ ንግግሬንም አድምጥ፣
እኔም ስታናግረኝ ልስማህ፡፡
‹‹የዘመኑ ምልክት››
የንባብ ክፍል፡- ማቴዎስ 16፡27
‹‹የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር
ይመጣ ዘንድ አለውና፣ ያን ጊዜም
ለሁሉ እንደ ሥራው ያስረክበዋል››
አይሁዶች ዘመናትን በሁለት ከፍለው የጨለማውና ወርቃማው ዘመን በማለት ይጠሩታል፡፡ በተለይም ከባቢሎን ምርኮ ጀምሮ ያለውን የጨለማው ዘመን ብለው ሲጠሩት፣ መሲህ ይገለፃል ብለው ከሚያስቡበት ጊዜ ጀምሮ ወርቃማው ዘመን እንደሚሆንላቸው ይናገራሉ፡፡
ስለዚህም ዘመናትን መመርመር ይወዳሉ፤ ዘመናትን ሲመረምሩ የቀኑን ሁናቴ ሁሉ ስለሚመለከቱ ስለ ዝናብ፣ ስለ ድርቅ፣ ስለ ክረምትና በጋ … ሁሉ የሰማዩን ፊት በማየት ምን እንደሚከሰት ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን በዚህ ምንባባችን ስንመለከት ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ቀርበው ምልክት እንዲያሳቸው ይለምኑታል፡፡ ኢየሱስም ‹‹የሰማዩን ፊትማ መለየት ታውቃላችሁ፣ የዘመኑንስ ምልክት መለየት አትችሉምን? አላቸው፡፡
አይሁዶች ዘመናትን እንመረምራለን ብለው ቢናገሩና ቢያስቡም፣ የዘመኑን ምልክት ማወቅና መረዳት አልቻሉም፡፡ ለወርቃማው ዘመን መምጣት ምክንያት የሚሆነው ክርስቶስ ሲሆን፣ እርሱን ግን አውቀው አልተቀበሉትም፡፡ የዘመናት ጌታ የሆነውን ትተው ዘመኑን ብቻ ይጠብቁ ነበር፤ በዚያን ጊዜ የነበሩ ሰዎች ስለ ኢየሱስ የተለያየ ግምትና አስተሳሰብ እንደ ነበራቸው ቁ. 14 ላይ ይናገራል፡፡ እርሱ ግን ስለ ማንነቱ በደንብ ገልጾ ነገራቸው፡፡ የገሃነም ደጆች የማይችሏት ቤተ ክርስቲያን እንደሚመሠርትና በዚያች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉትንም፣ በክብሩ ሲመጣ እንደሚወስዳቸውና ከእርሱ ጋር እንደሚሆኑና እንደሚኖሩ ተናገረ፡፡
ወንድሜ ሆይ ክርስቶስ ይመጣል ተብሎ ከተነገረ ብዙ ዘመናት አልፈዋል፤ አይሁዶች የመጀመሪያውን መምጣቱን ምልክቶች ካለማወቃቸው የተነሣ ሳይቀበሉት ቀሩ፡፡ እኔ፣ አንተ፣ አንቺ፣ እኛ ሁላችን የዘመኑን ምልክት እየመረመርን ነው? ማቴዎስ 24 ላይ ብንመለከትና ብናጠናው የዘመኑን ምልክት ማወቅና መረዳት እንችላለን፡፡
ጸሎት፡- አምላኬ ሆይ የመምጣትህን ምልክቱን
ማወቅና መረዳት እንድችል ማስተዋልና
ጥበብ ስጠኝ፡፡
0 Comments