‹‹ምቹ ጊዜ››
የንባብ ክፍል፡- መዝ. 32፡6
‹‹…ቅዱስ ሁሉ በምቹ ጊዜ ወደ አንተ ይለምናል፣
ብዙ የጥፋት ውኃም ወደ እርሱ አይቀርብም››፡፡
በዛሬው የምንባብ ክፍላችን መዝሙረኛው ዳዊት በኃጢአቱ ምክንያት ይጨነቅና ይጮህ እንደነበረ፣ ከዚያ ከጩኸቱ የተነሣ ደክሞት ዝም ባለ ጊዜ፣ አጥንቶቹ ሁሉ እንደ ተበላሹ እንመለከታለን፡፡
ኃጢአት ሰውን የሚያስጨንቅ የነፍስ በሽታ ነው፡፡ ሰው ሥጋው ቢታመም ምድራዊ መድኃኒት ማግኘት ይችላል፤ ለነፍሱ በራሱ መድኃኒት ፈልጎ ማግኘት አይችልም፡፡ መድኃኒት ሊያገኝ የሚችለው ከፈጣሪው እግዚአብሔር ጋር በመታረቅ ብቻ ፈውስ ሊያገኝ ሲችል ነው፡፡ ያም በምቹ ጊዜ ወደ አምላኩ ቢለምንና ንስሐ ቢገባ፣ የኃጢአት ይቅርታ እንደሚያገኝ ቃሉ ይናገራል፡፡ እግዚአብሔር ሊሰማና ሊመለከት፣ ሊጐበኝ በሚችልበት ምሕረትና ጸጋ ባለበት በምቹ ጊዜ ወደ እርሱ መመለስ ያስፈልጋል፡፡
ዳዊት ኃጢአቱን ሳይደብቅ ለእግዚአብሔር በማስታወቅ ወደ እርሱ ስለ ቀረበ የኃጢአት ይቅርታን ሊያገኝ ቻለ፡፡ ኢሳይያስም ‹‹እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፣ ቀርቦም ሳለ ጥሩት ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም አሳቡን ይተው፤ ወደ እግዚአብሔር ይመለስ፣ እርሱም ይምረዋል፣ ይቅርታውም ብዙ ነውና ወደ አምላካችን ይመለስ›› (55፡6) በማለት ይገልጻል፡፡ እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለጠጋ ስለሆነ ወደ እርሱ ለሚቀርቡት ሁሉ ምሐረትንና ይቅርታን ሁልጊዜ ይሰጣል፡፡
እኛም ዛሬ በምቹ ጊዜ ንስሐ በመግባት ወደ እርሱ ልንጠጋና ከእርሱ ጋር አብረን በመኖር ልናገለግለው በሕይወታችን እርሱን ከፍ ከፍ ልናደርገው ይገባናል፡፡ እርሱም በምንሄድበት መንገድ መሪያችን፣ አስተማሪያችን፣ መካሪያችንና ጠባቂያችን ይሆናል (ቁ. 8)፡፡ ‹‹…በልባብና በልጓም ጉንጫቸውን እንደሚለጕሙአቸው ልብ እንደሌላቸው እንደ ፈረስና እንደ በቅሎ አትሁኑ›› (ቁ. 9) ስለሚል ቃሉ፣ በተሰጠን አእምሮ መልካሙንና ክፉን ለመለየት፣ በምቹ ጊዜ ምሕረቱንና ይቅርታውን ለመጠየቅ እንጠቀምበት፡፡
ጸሎት፡- አምላኬ ሆይ፡- ለእኔ መሸሸጊያዬ ነህ፣ ከከበበኝ ጣር ታድነኝ ዘንድ ደስታዬ ነህ፡፡
‹‹ዘመኖቼ››
የንባብ ክፍል፡- መዝ. 39፡4-5
‹‹ አቤቱ ፍጻሜዬን አስታውቀኝ፣
የዘመኔ ቍጥሮች ምን ያህል እንደሆኑ፣
እኔም ምን ያህል ወደ ኋላ እንደምቀር አውቅ ዘንድ፡፡
እነሆ ዘመኖቼን አስረጀሃቸው፣
አካሌም በፊትህ እንደ ኢምንት ነው፡፡
ሕያው የሆነ ሰው ሁሉ በእውነት ከንቱ ብቻ ነው››፡፡
ብዙ ሰዎች ለምን እንደ ተፈጠሩ፣ ለምን እንደሚኖሩ፣ ወዴት እንደሚሄዱ መጨረሻቸው ምን እንደሆነ ሳያውቁ፤ እንዲሁ የሕይወት ዘመናቸውን ጨርሰው የሚያልፉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ብዙዎች በመጠጥ ብዛት እና በሐሺሽ ራሳቸውን በጉዳት ላይ የጣሉ፣ በክፋትና በተንኮል በመመላለስ ከመከራ ውስጥ ገብተው ሕይወታቸው በጉስቁልና ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ የተነሳ የተሰጣቸውን የሕይወት ዘመን ጣዕም ያለው፣ ሰላምና ደስታ ያለው ኑሮ ሳይኖሩ በከንቱ ዘመናቸውን የሚያሳልፉ ብዙዎች ናቸው፡፡
ዳዊት ስለዚህ ነው፣ ‹‹አቤቱ ፍጻሜዬን አስታውቀኝ›› እያለ አምላኩን የሚጠይቀው፤ የዘመኑ ቁጥሮች ምን ያህል እንደሆኑ፣ ለማወቅና ለመረዳት ይፈልጋል፡፡ ምክንያቱም የተሰጠውን ዘመን ምን ያህል እንደ ተጠቀመበት፣ ምን ያህሉን በከንቱ እንዳባከነ፣ ለወደፊትስ ምን ያህል ጊዜ እንደ ቀረው ለማወቅና ለመረዳት ይፈልጋል፡፡ በዚህም በጥያቄው መሠረት የራሱን የኃጢአት ብዛት ሲመለከት ሰው ከንቱ እንደሆነ፣ ለእርሱ ግን እግዚአብሔር ብቻ ተስፋው እንደ ሆነ ይናገራል፡፡
ወንድሜ ሆይ፡- በተሰጠህ የሕይወት ዘመን ምን ሠርተሃል? ሳትሠራው ያለፈብህ፣ ሳትጠቀምበት ያለፈብህ ጊዜ አለን? ለምን እንደ ተፈጠርክ፣ ለምን እንደምትኖር፣ ወዴት እንደምትሄድ መጨረሻህ የት እንደ ሆነ ታውቃለህ? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ከቻልክ ዘመንህን በሚገባ ልትጠቀምበት ትችላለህ ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁን ‹‹ላለፈው ክረምት ቤት አይሠራም›› እንደሚባለው ያለፈውን ትተህ ለወደፊቱ በፊትህ ላለው ዘመን ሕይወትህን ለጌታ ስጥና ከእርሱ ጋር ተስማምተህና ታርቀህ ኑር፤ አማኝ ከሆንክ ደግሞ፣ እንደ ዳዊት ቀሪ ዘመንህን አስታውቀኝ ብለህ በመጠየቅ፤ ዘመንህን ጌታን እንደሚገባ ለማገልገል ቁርጥ ያለ ውሳኔ አድርግ፡፡ ጊዜህን በአልባሌ ቦታ አታጥፋ፤ የሠራኸውን ሳታውቅ ዘመንህ እንደ ሸማኔ መወርወሪያ እንዳያልፍብህ ተጠቀምበት፡፡
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ፡- ዘመኔን የምዋጅበትና አንተን የማገለግልበት ጸጋና ኃይል ስጠኝ፡፡
‹‹ክፉ ቀን››
የንባብ ክፍል፡- መዝ. 41፡1-3 ‹‹… እግዚአብሔር በክፉ ቀን ያድነዋል፡፡
…እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፤
መኝታውን ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል፡፡
ሰው ራሱን ሊረዳበት የማይችልበት፣ ያሰበውን ሊያደርግና ያቀደውን ሊፈጽም ቢጥር የማይችልበት ክፉ ቀን በሕይወቱ ያጋጥመዋል፡፡ በዚያን ጊዜ ሰው ቢወድም ባይወድም የሌላውን እርዳታ የሚፈልግበት ጊዜ ይሆናል፡፡ በዚህ መንገድ ራብ እንደ ብርድ ያቆራመዳቸው፣ በሽታ የአልጋ ቁራኛ ያደረጋቸው፣ ችግር እንደ አለንጋ የገረፋቸው፣… በጐረቤታችን፣ በአካባቢያችንና በአገራችን ይኖራሉ፡፡
መዝሙረኛው በመዝሙሩ የሚገልጸው፣ እነዚህን ለመሰሉ ሰዎች ሁሉ በሕይወታቸው ክፉ ቀን ሲመጣ፣ እግዚአብሔር ለመርዳትና ለመታደግ የሚፈልግ የምሕረት አምላክ መሆኑን ይገልጻል/ያሳየናል፡፡ ኃጢአታቸውንና ድካማቸውን ወደ እርሱ ለሚያመጡት ርኅሩኅ አምላክ መሆኑን፣ ምሕረትና ይቅርታ በማድረጉ በሥራው ለመረዳት እንችላለን፡፡ እንደዚሁም በእርሱ የሚታመኑና እርሱን የሚከተሉ ሁሉ፣ በሌሎች ላይ ክፉ ቀን ሲከሰት በርኅራኄ ለመርዳት ልናደርገው የሚገባ እንደሆነ ያመለክተናል፡፡
ሰብዓዊ የሆነ ሰው ሁሉ በሕይወት ዘመኑ ሲኖር ክፉ ቀን ያጋጥመዋል፤ በዚህ ጊዜ ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ፣ የሚጸልይ፣ የሚያበላና የሚያጠጣ… እግዚአብሔር ከክፉ ቀን እንደሚያድነው፣ እንደሚጠብቀው፣ ለጠላቶችም አሳልፎ እንደማይሰጠው፣ በደዌውና በበሽታው ጊዜ ሁሉ እንደሚረዳው ቃሉ ይናገራል፡፡ ሰው በዚያ ክፉ ቀን ለመቆምና ለማለፍ የሚችለው አምላኩን ብቻ ሲተማመን ነው፤ በክፉ ቀን መውደቃችንን የሚጠብቁ፣ የምንታመንባቸው እንኳን ሳይቀሩ ሊነሱብንና በመከራ ላይ መከራ ሊጨምሩብን ይዘጋጃሉ፡፡
ወንድሞችና እህቶች ዛሬ ምናልባት ክፉ ቀን ባጋጠመን ጊዜ ሰው ባለው ዐቅም ሁሉ ሊረዳን ጥረት ያደርጋል፡፡ አንድ ቀን ግን ከእግዚአብሔር በስተቀር ማንም ሊረዳን የማይችልበት ክፉ ቀን ሊገጥመን ይችላል፡፡ ስለዚህ ዛሬ ከዚያ ክፉ ቀን ለመዳን ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወታችን አዳኝ አድርገን በእምነት መቀበል አለብን፡፡ አማኞች ሌሎች ሰዎች ክፉ ቀን ሲደርስባቸው ለመርዳት ራሳችንን አዘጋጅተን፣ በተግባር እንግለጸው፡፡
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ በክፉ ቀን በፊትህ መቆም እንድችል ሕይወቴን ተረከብ፤ ሌሎችንም መርዳት እንድችል እርዳኝ፡፡
0 Comments