ስለ ፍርድ ስናነሳ የተለያዩ ፍርዶች እንዳሉ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡ ቀደም ብለን የተመለከትናቸው አመለካከቶች ሁሉም ፍርድ እንዳለ ያምናሉ፡፡ የአመኑም ያላመኑም ሁሉም ፍርድ እንዳአለባቸው በቃሉ ውስጥ እናገኛለን፤ የፍርዱ ዓይነት ግን ይለያያል፡፡ አማኞች በሥራቸው ለሽልማት ሲፈረድባቸው ያላመኑት ደግሞ ባለማመናቸው ምክንያት ፍርዱ ለጥፋትና ለቅጣት ይሆንባቸዋል፡፡
ሀ) የመስቀል ፍርድ፡- መጽሐፍ ቅዱስ ፍርድ ዛሬውኑ እንደሚጀምር ያስተምረናል፤ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 3፡18 ላይ እንዲህ ይላል ‹‹በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል›› መስቀሉ የዓለምን ሕዝብ የተፈረደበትና ያልተፈረደበት በማለት ለሁለት ከፍሎት እናገኛለን፡፡ ‹‹እውነት እውነት እላችኋለሁ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበትም ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው›› (5፡25) በማለት የተፈረደባቸውን ሙታን ብሎ ይጠራቸዋል፤ እነዚህ ሙታን ድምፁን ቢሰሙ፣ ማለት በክርስቶስ ቢያምኑ ፍርዱ ይነሳላቸዋል፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል ፍርድ ከዚሁ ከምድር እንደሚጀምር ያመለክተናል፡፡
ለ) ዕለታዊ የአማኞች ፍርድ፡- ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ‹‹እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም›› (ሮሜ 8፡1) ብሎ በሚናገረው መሠረት፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ካመንን ወደ ገሃነመ እሳት ከሚያስጥለው ከዘላለም ኩነኔ ፍርድ ነፃ ሆነናል፡፡ የድነትን ትምህርት ስንማር እንዳየነው፣ ድነትን ካገኘን በኋላ በየዕለቱ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ኃጢአት እንሠራለን፡፡ በዚህ ኃጢአት ወደ ፍርድ እንዳንገባ በኃጢአታችን ላይ በመፍረድ ንስሐ መግባት ይኖርብናል፡፡ ‹‹ራሳችንን ብንመረምር ግን ባልተፈረደብንም ነበር፣ ነገር ግን በተፈረደብን ጊዜ ከዓለም ጋር እንዳንኮነን በጌታ እንገሠጻለን›› (1ቆሮ. 11፡31-32) በማለት የቆሮንቶስ አማኞች ወደ ጌታ ፍርድ ከመግባታቸው በፊት፣ ራሳቸውን እየመረመሩ በራሳቸው ላይ መፍረድ እንዳለባቸው ያሳያቸዋል፡፡
በራሳችን ባንፈርድ ሐዋርያው ጳውሎስ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ሆኖ፣ የአባቱን ሚስት አግብቶ በተቀመጠው ላይ ንስሐ ባለመግባቱ እንደ ፈረደበት፤ ዛሬም ቤተ ክርስቲያን ንስሐ ባንገባ ትፈርድብናለች፡፡ ይህ መቼም ጎልቶ የወጣ ኃጢአት ስለሆነ ነው፤ በቤተ ክርስቲያን ይፋ ሆነው የማይታወቁ ብዙ ኃጢአቶች አሉ፤ ቤተ ክርስቲያን አላወቀችም ብለን ዝም ማለት የለብንም፤ መንፈስ ቅዱስ በቃሉ ሲወቅሰን ወዲያውኑ በራሳችን ላይ በመፍረድ ንስሐ መግባት አለብን፡፡ ይህ በራሳችን ላይ የምንፈርደው ዕለታዊ ፍርድ ይባላል፡፡
ሐ) የአማኞች የሥራ ፍርድ፡- ከዕለታዊ ፍርድ ቀጥሎ አማኞችን የሚጠብቃቸው፣ የአማኞች የሥራ ፍርድ/ የክርስቶስ የፍርድ ወንበር ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህ ፍርድ የሚከናወነው ጌታ ሲመጣ፣ ቤተ ክርስቲያን ጌታን ለመቀበል በአየር ላይ ተነጥቃ፣ የበጉ ሠርግ ከመሆኑ በፊት፣ በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በጻፈላቸው መልእክቱ ‹‹… ሁላችን በክርስቶስ ፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለንና … እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን›› (ሮሜ 14፡10፣12) ብሎአቸዋል፤ እንዲሁም ለቆሮንቶስ ሰዎች ‹‹መልካም ቢሆን ወይም ክፉ እንዳደረገ እያንዳንዱ በሥጋው የተሠራውን በብድራት ይቀበል ዘንድ ሁላችን በክርስቶስ በፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናል›› (2ቆሮ. 5፡10) በማለት ሰዎች ስለሚናገሩትና ስለሚሠሩት መጠንቀቅ እንዳለባቸው ያሳስባቸዋል፡፡
‹‹ ማንም ግን በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ ቢሆን በብርም በከበረ ድንጋይም በእንጨትም በሣርም ወይም በአገዳ ቢያንጽ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል፤ በእሳት ስለሚገለጥ ያ ቀን ያሳያልና፣ የእያንዳንዱም ሥራ እንዴት መሆኑን እሳቱ ይፈትነዋል፡፡ ማንም በእርሱ ላይ ያነጸው ሥራ ቢጸናለት ደመወዙን ይቀበላል የማንም ሥራ የተቃጠለበት ቢሆን ይጎዳበታል፣ እርሱ ራሱ ግን ይድናል ነገር ግን በእሳት እንደሚድን ይሆናል›› (1ቆሮ.3፡12-15)፡፡
ከዚህ በላይ እንደተመለከትነው አማኞች በጌታ ፊት ቀርበው በተናገሩትና በሠሩት ሥራ መሠረት ለሽልማት ለመቅረብ፣ በፊቱ ለፍርድ ይቀርባሉ፡፡ ስለዚህ እኛም በዚህ የክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት ስለምንቀርብ ዛሬ በምንኖረው ሕይወታችን በጥንቃቄና በአገባብ ልንመላለስ ይገባናል፡፡
መ) የአይሁድ ፍርድ፡- በአየር ላይ የአማኞች ፍርድ ሲከናወን፣ በምድር ላይ ደግሞ በአይሁድ ላይ ፍርድ ይሆናል፤ ቤተ ክርስቲያን ከምድር በምትወሰድበት ጊዜ የሚቀሩት ያላመኑ አይሁድና አይሁድ ያልሆኑ (አህዛብ) ናቸው፡፡ አይሁድ ክርስቶስ በሥጋ ወደዚህ ምድር በመጣ ጊዜ አልተቀበሉትም፤ በዚህ ምክንያት በዚያን ጊዜ በታላቁ የሰባት ዓመት መከራ ውስጥ ያልፋሉ፡፡ ይህ በትንቢተ ዳንኤል በሰባ ሱባኤ መሠረት ስልሳ ዘጠኙ ሱባኤ ተፈጽሞ፣ ቀሪው አንድ ሱባኤ እየተጠበቀ ነው (ዳን. 9፡20-27)፡፡ በስልሳ ዘጠኙና በአንዱ ሱባኤ መካከል ለዳንኤል ምስጢር በነበረው በቤተ ክርስቲያን ዘመን ውስጥ እንገኛለን፡፡ ይህ የሰባት ዓመት መከራ የያዕቆብ መከራ ተብሎ ይጠራል፤ አይሁድ በዚህ ጊዜ ለመዳን ታላቅ ዋጋ እስከ ሞት ድረስ ይከፍላሉ፡፡ በዚህ መከራ ጊዜ ሕይወታቸውን ለጌታ ያልሰጡ ቢኖሩ፣ ጌታ ሲመጣ ለፍርድ ይቀርባሉ፡፡
ሠ) የአሕዛብ ፍርድ፡- በማቴዎስ ምዕራፍ 25 31-46 ላይ ‹‹የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፣ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል በጎቹን በቀኙ ፍየሎቹንም በግራው ያቆማቸዋል›› የሚለው ሐሳብ በታላቁ መከራ ጊዜ አይሁዶች በታላቅ መከራ ውስጥ በሚያልፉበት ጊዜ እነርሱን ያበላ፣ ያጠጣ፣ የጠየቀ፣ መልካም ያደረገ ሁሉ በጣም ከባድ ቅጣት ይደርስበታል፡፡ ማንኛውንም የሚደርስባቸውን ዋጋ ከፍለው ሲያልፉ ለክርስቶስ እንዳደረጉት ተቆጥሮላቸው ዋጋቸውን ያገኙበታል፡፡ እነዚህን በጎ ድርጊቶች የሚፈጽም ሰው ካለ፣ በዚያ ሕይወት በአዲስ ለውጥ ለመኖሩ (ለማግኘቱ) ማስረጃ ይሆናል፡፡ በሌላ አነጋገር እነዚህ አሕዛብ ለአይሁድ፣ ለክርስቶስ ወንድሞች የሚያደርጉት መልካም ሥራ፣ ዳግም ለመወለዳቸው ምልክት ነው፡፡ ዳግም በመወለዳቸው ይድናሉ፤ መልካሙም ተግባራቸው የመወለዳቸው ማረጋገጫ ይሆናል፡፡ በዚህ መሠረት ክርስቶስን ያልተቀበሉና በድርጊታቸው ለአይሁድ ምንም ያላደረጉ ጌታ ሲመጣ ዋጋቸውን ለመቀበል ወደ ፍርድ ይመጣሉ፡፡
ረ) የወደቁ መላእክት ፍርድ፡- በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንደምናገኘው ሰይጣን እንደ እግዚአብሔር እሆናለሁ ብሎ ካመጸበት ጊዜ ጀምሮ፣ የዓመፁ ተባባሪ የሆኑ መላእክት ሁሉ ከክብራቸው ከእርሱ ጋር ተጥለዋል፡፡ በዚህ ምድር ላይ ለሚካሄደው ዓመጽ ሁሉ አለቃና ገዥ በመሆን የዓመፅ ሥራ እየሠራ ይገኛል፡፡ የበግ ሠርግ በአየር ላይ ካለቀ በኋላ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሳኑ ጋር የሺህ ዓመቱን ግዛት ለመጀመር፣ ወደ ምድር በሚመጣበት ጊዜ፣ ጌታ ግዛቱን ከመጀመሩ በፊት ሰይጣን ሰዎችን እንዳያስት ለሺህ ዓመት ይታሠራል፡፡ ከዚህ እሥራት በኋላ ለጥቂት ጊዜ ይፈታና ከእርሱ ጋር አብረው ከክብራቸው ከወደቁ መላእክት ጋር ሆኖ ለዓመፅ ይነሳል፡፡ በዚህ ጊዜ ከሰይጣን ጋር ለዓመፅ የተነሱትን አጋንንት ሁሉ ጌታ ይፈርድባቸዋል፡፡
‹‹ሺሁም ዓመት ሲፈጸም ሰይጣን ከእስራቱ ይፈታል፣ በአራቱም በምድር ማዕዘን ያሉትን አሕዛብ፣ ጎግንና ማጎግን፣ እንዲያስታቸው ለሰልፍም እንዲያስከትታቸው ይወጣል፤ ቍጥራቸውም እንደ ባሕር አሸዋ የሚያህል ነው፡፡ ወደ ምድርም ስፋት ወጡ የቅዱሳንንም ሰፈርና የተወደደችውን ከተማ ከበቡ፤ እሳትም ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወርዳ በላቻቸው፡፡ ያሳታቸውም ዲያቢሎስ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፣ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ቀንና ሌሊት ይሣቀያሉ›› (ራዕ. 20፡7-10)፡፡ ከዚህ በኋላ የነጩ ዙፋን ፍርድ ይቀጥላል፡፡
ሰ) የነጩ ዙፋን ፍርድ፡- በዚህ በነጩ ዙፋን ፊት ቀርበው የሚፈረድባቸው ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በእግዚአብሔርና በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ያላመኑ ሁሉ በፊቱ ቀርበው ፍርዳቸውን የሚቀበሉበት ጊዜ ነው፡፡ በዮሐንስ ወንጌል ‹‹የሰው ልጅም ስለሆነ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን ሰጠው ›› (ዮሐ. 5፡27-29) ባለው መሠረት በመቃብር ያሉቱና በሕይወት ያሉቱ ሁሉ ወደ ፍርድ የሚቀርቡበት ጊዜ ነው፡፡ ክርስቶስን ባለማመናቸው የሕይወት መጽሐፍ ሲከፈት ስማቸው ባለመገኘቱና ሥራቸው ተጽፎ እንደተገኘው ፍርዳቸውን ይቀበላሉ፡፡ ይህ ፍርድ ከእግዚአብሔር ለዘላለም መለየትን የሚያመጣ ወደ ገሃነም እሳት የመጣል ፍርድ ነው (ራዕ.20፡1-15)፡፡
መንግሥተ ሰማይ፡- መንግሥተ ሰማይና ገሃነመ እሳት የሰው ልጆች የመጨረሻ ሥፍራ ናቸው፡፡ ጌታ በወንጌሉ ‹‹ልባችሁ አይታወክ ፣ በእግዚአብሔር አመኑ፣ በእኔም ደግሞ እመኑ፡፡ በአባቴ ቤት፣ ብዙ መኖሪያ አለ፣ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፣ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፣ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ›› (ዮሐ. 14፡1-3) ባለው መሠረት፣ መንግሥተ ሰማይ የአማኞች/የጻድቃን ውብ ስፍራ፣ ቅዱስ ስፍራ፣ ስለሆነ ለመኖሪያና እግዚአብሔርን ለማምለኪያ የተዘጋጀ ነው፡፡ ከጌታ ጋር ኅብረት እያደረግን ለሥራና ለትዳር ሳናስብ በደስታና በሐሴት በአዲስ አመለካከት ለዘላለም ከእግዚአብሔር ጋር የምንኖርበት የሰዎች ቃላት የማይገልጸው ድንቅ ሥፍራ ነው (ዕብ. 12፡22-24፣ ራዕይ 21፡1-4)፡፡
ገሃነመ እሳት፡- የመንግሥተ ሰማይ ተቃራኒ ገሃነመ እሳት ነው፤ ያላመኑ/የኃጥአን ከሲኦል (የመቃብር፣ የመቆያና፣ ጊዜአዊ ሥፍራ) ቀጥሎ የመጨረሻው የሥቃይ፣ የልቅሶና የቅጣት ሥፍራ በመሆኑ ለዘላለም ከእግዚአብሔር ተለይተው በእሳት እየተቀጡ የሚኖሩበት ሥፍራ ነው፡፡ ገሃነም እሳት ዘላለማዊ የቅጣትና የሥቃይ ቦታ በመሆኑ፣ በአንድ ጊዜ ተቀጥተው የሚወጡበት ሳይሆን ለዘላለም ያለማቋረጥ የሚቀጡበት አስከፊና አሰቃቂ ሥፍራ ነው (ኢሳ. 66፡24፣ ማቴ. 8፡12፣ 2ጴጥ. 2፡4፣ ራዕ. 14፡10-11፣ 20፡10,15)፡፡
አስተምህሮዎቼ በቅድመ-ሺህ-ዓመት አመለካከት (Premillennialism) ላይ የተመሠረቱ ናቸው፤ የቅድመ-ሺህ ዓመት አመለካከት እንደሚከተለው ይተነተናል፡፡ የቅድመ-ሺህ ዓመት አመለካከት ያለን አማኞች ሁሉ ክርስቶስ በምድር ላይ ከቅዱሳኑ ጋር ሺህ ዓመት ይነግሣል ብለን አናምናለን፡፡ ጌታ በምድር ላይ ሺህ ዓመት ከመንገሡ በፊት አማኞችን ለመውሰድ ደመና ድረስ ይመጣል፡፡ በዚህ ጊዜ ለቤተ ክርስቲያን መነጠቅ ሲሆን፣ የሞቱ ከሙታን በመነሣት፣ በሕይወት ያሉት ከመቅጽበተ ዓይን በመለወጥ ክርስቶስን በአየር ለመቀበል መነጠቅ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡
ቤተ ክርስቲያን (አማኞች) በአየር ላይ የበጉ ሠርግና የአማኞችም ፍርድ እየተከናወነ ሁሉም እንደ ሥራው ሽልማቱን የሚያገኝበት ጊዜ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ በሰማይ እነዚህ ሁለት ታላላቅ ድርጊቶች እየተከናወኑ ሳለ በምድር ላይ ደግሞ ለሰባት ዓመት ታላቅ የመከራ ጊዜ ሲሆን፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአየር ላይ ለሰባት ዓመት ቆይታ አድርጎ ወደ ምድር ከቅዱሳኑ ጋር በመምጣት ለአንድ ሺህ ዓመት ይነግሣል፡፡ በዚህ ጊዜ ሰይጣን ዓለምን እንዳያስት ለአንድ ሺህ ዓመት በሚታሰርበት ጊዜ በምድር ላይ ትልቅ ሰላም ይሆናል፡፡ ከሰባት ዓመት ታላቅ መከራ በኋላ ሰይጣን ለጥቂት ጊዜ ይፈታና ዓመፅ ካካሄደ በኋላ ይፈረድበትና ወደ ገሃነመ እሳት ለዘላለም እንደሚጣል አምናለሁ፡፡ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ያሉ ኃጢአተኞች በነጩ ዙፋን ፊት ቀርበው እንደሚፈረድባቸውም አምናለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ በአዲስ ሰማይና ምድር ከእግዚአብሔር ዘንድ በምትመጣው፣ በዚያ ለዘላለም ከእግዚአብሔር ጋር መኖር እንደሚጀመር አምናለሁ፡፡ ይህን ጥናት አስጀምሮ ላስጨረሰኝ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ በሌላ ጥናት እስከምንገናኝ በጸሎታችሁ አስቡኝ፡፡
0 Comments