- የተለያዩ አመለካከቶች
በክርስቶስ ተመልሶ በመምጣቱና በምልክቶች ብዙዎች ቤተ እምነቶች ቢስማሙም፤ በመከራው ዘመን፣ በሺህ ዓመት ግዛት፣ በሙታን ትንሣኤ፣ በፍርድ፣ በመንግሥተ ሰማይና በገሃነመ እሳት የተለያዩ አመለካከቶች አሉዋቸው፡፡ እነዚህ አመለካከቶች የሚለያዩት ሺህ ዓመት አለና የለም በሚሉት ሐሳቦች ላይ ሲሆን፤ የሺህ ዓመት አገዛዝ ካለ፣ የሚሆነው/የሚፈጸመው ከክርስቶስ ዳግም ምጽዓት በፊት ነው ወይስ በኋላ? በሚለው ሐሳብ መለያየታቸው በሌሎችም ነገሮች እንዲለያዩ አድርጓቸዋል፡፡ ሁሉም አመለካከቶች የሚደግፏቸውን ጥቅሶች ለመጥቀስ ይሞክራሉ፡፡ ወደፊት በሚሆኑ ነገሮች ላይ መቶ በመቶ እርግጠኛ መሆን ቢያስቸግርም ከመቶ ሃምሳ እርግጠኞች የሚሆኑበትን ሁሉም አመለካከቶች ለማቅረብ ይሞክራሉ፡፡ ዛሬ ለእኛ ልክ ናቸው ብለን የምናስባቸውን አምነን መቀበልና መከተል እንችላለን፤ ሆኖም ጌታ ሲመጣ ከሦስት አንዳቸው እርግጠኞች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የተለየዩ አመለካከቶቹም እነሆ፡- በፊታችን ቀርበዋል፤ ጊዜ ሰጥተን እንመልከታቸው፡፡
ሀ) የድህረ- ሺህ ዓመት አመለካከት (Postmillennialism)
ለ) የአልቦ- ሺህ ዓመት አመለካከት (Amillennialism)
ሐ) የቅድመ-ሺህ- ዓመት አመለካከት (Premillennialism)
ሀ) የድህረ- ሺህ ዓመት አመለካከት (Postmillennialism)
የድህረ-ሺህ ዓመት አመለካከት ያላቸው የክርስቶስ የሺህ ዓመት አገዛዝ እንዳለ ይቀበላሉ፤ ነገር ግን ስለ ጊዜው ሲናገሩ ክርስቶስ ሺህ ዓመት የሚገዛው በዚህ በምድር በቤተ ክርስቲያን ዘመን ነው ብለው ነው የሚናገሩት፤ የጊዜው ርዝመት ወሰን የለውም፡፡ ወንጌልን ለሺሁ ዓመት ቅድመ ሁኔታ አድርገው ስለሚያስቀምጡት፣ ወንጌል እየተሰበከና እያሸነፈ ሲሄድ በዓለም ላይ ትልቅ ሰላም ይመጣል፣ ክፋትም እየጠፋ ይሄዳል፤ ያን ጊዜ ክርስቶስ ይመጣል ብለው ያስተምራሉ፡፡ ያን ጊዜ ያመኑና ያላመኑ ሙታን ይነሣሉ፣ ፍርድም ይሰጥና ዐዲስ ሰማይና ዐዲስ ምድር ይመጣና ዘላለማዊ የክርስቶስ መንግሥት ይጀምራል ብለው ያምናሉ፡፡ ነገር ግን የአንደኛውና የሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጥቶ ጉድ አደረጋቸው፤ ዛሬም በዓለም ላይ ሰላም ሊመጣ አልቻለም፣ ምክንያቱም እየተካሄዱ ያሉት ጦርነቶች ሁሉ እንደ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት ባይቆጠሩም ይህን አመለካከት እየተፈታተኑት ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ በዚህ አመለካከት ውስጥ ያሉ አማኞች በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡
ለ) የአልቦ- ሺህ ዓመት አመለካከት (Amillennialism)
የአልቦ- ሺህ ዓመት አመለካከት ያላቸው አማኞች ክርስቶስ በምድር ላይ ሺህ ዓመት አይገዛም ቢሉም፤ በማቴዎስ 28፡18 ላይ ‹‹ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ›› የሚለውን መሠረት በማድረግ አሁን ክርስቶስ እየገዛ ያለው በሰማይ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ስለዚህ ወደፊት በምድር ላይ በአካል የሚገዛው ነገር የለም፣ ምክንያቱም በራዕይ ምዕራፍ 20 መሠረት ክርስቶስ በቤተ ክርሰቲያን በኩል ለዳዊት የተገባለትን ቃል ኪዳን አሁን በሰማይ የሺህ ዓመቱን ግዛት እየፈጸመ ይገኛል ይላሉ፡፡ በብሉይ ኪዳን ለእሥራኤል የተሰጠውን ተስፋ በቤተ ክርስቲያን በኩል እየፈጸመ ይገኛል በማለት ያስተምራሉ፡፡ የሺህ ዓመት ግዛት የለም የሚሉትም በቁጥር እንዳለ ሳይሆን የሚወስዱት ምሳሌያዊ መግለጫ እንደሆነ አድርገው ስለሚወስዱት ነው፡፡ ሰይጣን ታስሯል የታሰረውም በወንጌል ነው፤ ባይታሰር ቤተ ክርስቲያን ወንጌል በመስበክ ሰዎችን ነፃ ማድረግ አትችልም ነበር ብለው ያምናሉ፡፡ ምክንያት ሲሰጡ የማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 3፡27 ሐሳብ በመውሰድ የኃይለኛውን ቤት ለመዝረፍ አስቀድሞ ኃይለኛውን ማሠር ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ ስለዚህ የቤተ ክርስቲያን ዘመን ሲያበቃ ክርስቶስ ይመጣል፡፡ ወዲያውኑ የአማኞችና የማያምኑ ትንሣኤ ይሆንና የአማኞች የሥራ ፍርድና ያላመኑ ሁሉ በክርስቶስ ባለማመናቸው ምክንያት ፍርድ ይሰጥና በዐዲስ ሰማይና ምድር የክርስቶስ የዘላለም መንግሥት ይጀመራል ብለው ያምናሉ፡፡
ሐ) የቅድመ-ሺህ ዓመት አመለካከት (Premillennialism)
የቅድመ- ሺህ ዓመት አመለካከት ያላቸው አማኞች ክርስቶስ በምድር ላይ ከቅዱሳኑ ጋር ሺህ ዓመት ይነግሣል ብለው ያምናሉ፡፡ በአንደኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15፡51 ላይ ‹‹… ሁላችን በድንገት በቅጽበተ ዓይን እንለወጣለን›› በአንደኛ ተሰሎንቄ ምዕራፍ 4፡17 ‹‹ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፣ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን›› የሚለውን ቃል መሠረት በማድረግ፤ በምድር ላይ ሺህ ዓመት ከመንገሡ በፊት አማኞችን ለመውሰድ ደመና ድረስ ይመጣል፤ በዚህ ጊዜ ክርስቶስ የራሱ የሆኑትን ለመውሰድ የሚመጣበት ጊዜ፣ ለቤተ ክርስቲያን መነጠቅ ሲሆን፣ የሞቱ ከሙታን በመነሣት፣ በሕይወት ያሉት ከመቅጽበተ ዓይን በመለወጥ ክርስቶስን በአየር ለመቀበል መነጠቅ ይሆናል ብለው ያምናሉ (1ተሰ. 4፡13-17)፡፡
ቤተ ክርስቲያን (አማኞች) በአየር ላይ የበጉ ሠርግና የአማኞችም ፍርድ እየተከናወነ ሁሉም እንደ ሥራው ሽልማቱን የሚያገኝበት ጊዜ እንደሚሆን አስተምህሮአቸው ያሳያል፡፡ በሰማይ እነዚህ ሁለት ታላላቅ ድርጊቶች እየተከናወኑ በምድር ላይ ለሰባት ዓመት ታላቅ የመከራ ጊዜ ይሆናል ይላሉ፡፡ ከዚያም የጌታ ዳግም ምፅዓት ይሆናል፤ ማለት ክርስቶስ ከቅዱሳኑ ጋር በድል አድራጊነትና በክብር ወደ ምድር የሚመለስበት ወቅት መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ይህን የሰባት ዓመት ቀመር በብሉይ ኪዳን በትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ 9 ላይ እናገኘዋለን፡፡ ዳንኤል የሰባውን ዓመት የምርኮ ጊዜ፣ በተመለከተ የእሥራኤል ሕዝብ ከምርኮ እንዲመለስ ወደ እግዚአብሔር መጸለይ በጀመረበት ጊዜ ወዲያውኑ የጸሎት መልስ መጣለት፡፡ የጸሎት መልሱ ፍጻሜ እንዲያገኝ ሰባ ሱባኤ እንደ ተቀጠረበት ተነገረው፡፡ ይህ ሰባ ሱባኤ በሰባት፣ በስልሳ ሁለትና በአንድ ሱባኤ በሦስት የተከፈለ ነበር፡፡ ስልሳ ዘጠኝ ሱባኤዎች ተፈጽመው አንድ ሱባኤ ይቀራል፡፡ በስልሳ ዘጠኝና በአንድ ሱባኤዎች መካከል ለዳንኤል ያልተገለጠለት አሁን ያለንበት የቤተ ክርስቲያን ዘመን ጣልቃ ገብቶ መጨረሻው ላይ እንገኛለን፡፡
ይህቺ የቀረችው አንድ ሱባኤ ማለት ሰባት ዓመት ማለት ነው፡፡ (ሱባኤ ማለት ሰባት ማለት ነው) ይህ ሰባት ዓመት ለሁለት ይከፈላል፡፡ ሐሰተኛው ክርስቶስ ከእሥራኤል ጋር ለሰባት ዓመት ቃል ኪዳን ይገባቡና ለሦስት ዓመት ተኩል በሰላም ከኖሩ በኋላ ሁለተኛውን ሦስት ዓመት ተኩል ቃል ኪዳናቸው ይፈርስና ይጣላሉ፡፡ በዚህ ምክንያት እሥራኤል ታላቅ መከራ ውስጥ ትገባለች፣ ይህ መከራ የያዕቆብ መከራ ተብሎ ይጠራል (ኤር.30፡7)፡፡ በተለይም እሥራኤል ክርስቶስ ሊያድናት መጥቶ ባለመቀበሏ ምክንያት የምትቀጣበት ጊዜ ነው፡፡ እውነተኛውን ክርስቶስ መቀበል ሲገባት፣ ሐሰተኛውን ክርስቶስ ተቀብላ ስምምነት በማድረጓ የምትቀበለው መከራ ነው፡፡
በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24፡30፣ ‹‹በዚያን ጊዜ የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፣ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፣ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል››፤ በራዕይ ምዕራፍ 1፡7 ላይም እንዲህ በማለት ሐሳቡን ይደግመዋል ‹‹እነሆ ከደመና ጋር ይመጣል ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፣ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ›› ይላል፡፡ እንዲሁም በትንቢተ ዘካርያስ ምዕራፍ 12፡10 ላይ ‹‹…ወደ እርሱም ወደ ወጉት ይመለከታሉ፣ ሰውም ለአንድያ ልጁ እንደሚያለቅስ ያለቅሱለታል፣ ሰውም ለበኵር ልጁ እንደሚያዝን በመራራ ኀዘን ያዝኑለታል›› የሚለው ትንቢት ይፈጸማል፡፡ በእነዚህ ቃሎች መሠረት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአየር ላይ ለሰባት ዓመት ቆይታ አድርጎ ወደ ምድር ከቅዱሳኑ ጋር በመምጣት ለአንድ ሺህ ዓመት ይነግሣል፡፡ እንዲሁም በዚህ ጊዜ ሰይጣን ዓለምን እንዳያስት ለአንድ ሺህ ዓመት በሚታሰርበት ጊዜ በምድር ላይ ትልቅ ሰላም ይሆናል ብለው ያምናሉ፡፡
በሺህ ዓመቱ እንደሚለያዩ እንዲሁ፣ በመከራው ዘመን ላይም ሁሉም የተለያየ አቋም አላቸው፡፡ የድህረ-ሺህና የአልቦ ሺህ ዓመት አመለካከት ያላቸው አቋም ቤተ ክርስቲያን በታላቁ መከራ ውስጥ ታልፋለች ብለው ያምናሉ፡፡ ምክንያቱም ሺህ ዓመቱን ድህረ-ሺህ ዓመቶች ቤተ ክርስቲያን አሁን በምድር እያለች በሺሁ ዓመት አገዛዝ ውስጥ እያለፈች ነው ሲሉ የአልቦ-ሺህ ዓመቶች ደግሞ ሺህ ዓመቱን በሰማይ ሆኖ እየገዛ ነው ብለው ስለሚያምኑ ነው፡፡
የቅድመ-ሺህ ዓመት አመለካከት ያላቸው ደግሞ በሦስት የተከፈለ አቋም አላቸው፡፡ ስለ መከራው ዘመን መኖር ሁሉም እርግጠኞች ሆነው ስለ ሚፈጽምበት ጊዜ ላይ ግን የተለያየ አቋም አላቸው፡፡ ሀ) ቤተ ክርስቲያን በመከራው ውስጥ ታልፋለች የሚሉት ድህረ- ፍዳ ሲባሉ፤ ለ) ቤተ ክርስቲያን በግማሽ መከራ ውስጥ ታልፋለች የሚሉት ግማሽ ድኅረ- ፍዳ (ማዕከላዊ የፍዳ ዘመን) ሲባሉ፤ ሐ) ቤተ ክርስቲያን ከመከራው በፊት ትነጠቃለች የሚሉት ቅድመ- ፍዳ ዘመን ተብለው ይጠራሉ፡፡
እኔም ቤተ ክርስቲያን ከመከራው በፊት ትወሰዳለች ብዬ አምናለሁ፤ በራዕይ ምዕራፍ 3፡10 ላይ ‹‹የትዕግሥቴን ቃል ስለ ጠበቅህ እኔ ደግሞ በምድር የሚኖሩትን ይፈትናቸው ዘንድ በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው ከፈተናው ሰዓት እጠብቅሃለሁ›› ይላል፡፡ እንዲሁም በ1ኛ ተሰሎንቄ ምዕራፍ 5፡1-9 ላይ ‹‹እግዚአብሔር ለቁጣ አልመረጠንምና፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መዳንን ለማግኘት ነው እንጂ›› በማለት አማኞች በብርሃን እንጂ በጨለማ ስለ አይደሉ ለመከራና ለቁጣ እንዳልተመረጡ ይናገራል፡፡ በሉቃስም ምዕራፍ 21፡36 ላይ ስለ ዳግም ምፅዓቱ በተናገረበትም ጊዜ ‹‹እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፣ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁልጊዜ ትጉ›› በማለት ከመከራው ማምለጥ እንዲችሉ ያሳስባቸዋል፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ከመከራው በፊት ወደ ጌታ በአየር በመነጠቅ፣ የመከራውን ጊዜ በሰማይ ላይ ከበጉ ጋር ሠርጓን በማድረግ ታሳልፋለች፡፡ የሥራዋን ፍርድ በመቀበል የበጉ ሙሽራ ሆና ትሞሸራለች፡፡
የተለያዩ አመለካከቶች ቢኖሩም አንዱን መርጦ፣ ማመንና መከተል ይቻላል፤ መቶ ፐርሰንት እርግጠኞች በማንሆንበት ጉዳይ ላይ መለያየትና መጠላላት አያስፈልግም፡፡ ባለን አመለካከት ተከባብረን፤ ጌታችን የሚመጣበትን ቀን በትዕግስትና በፅናት ልንጠብቀው ይገባናል፡፡ በኢ.ቲ.ሲ (ኢቫንጀሊካል ቲኦሎጂካል ኮሌጅ) ስማር ካገኘሁት ትልቅ ነገር አንዱ፣ ባለን አመለካከት መከባበርና መቀባበልን ነው፡፡ በዚህ ለመኖር ሁላችንንም ጌታ ይርዳን፡፡
0 Comments