የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶችን በሁለት ከፍለን እናጠናቸዋለን፤ በጌታ በራሱ የተሰጡና ቤተ ክርስቲያን በልምምድ ካሳለፈችው በመነሳት ያስፈልጋሉ ብላ ያመነችባቸውንና ከቃሉ ጋር አይጋጭም በማለት የተለማመደቻቸውን አካታ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች/ሚስጢራት ብላ በማካሄድ ላይ ትገኛለች፡፡
በጌታ የተሰጡ ሥርዓቶች፡- በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በጌታ ተሰጥተው የምናገኛቸው ሥርዓቶች ሁለት ሲሆኑ፤ እነርሱም ሀ) የውኃ ጥምቀትና ለ) የጌታ ራት/ቅዱስ ቁርባን የምንላቸው ናቸው፡፡ እነዚህም ሥርዓቶች በማን፣ ለምን፣ መቼና እንዴት እንደ ተሰጡ፤ አማኝ ቢፈጽማቸው ድነትን ሳይሆን በረከትን እንደሚያገኝባቸው ከቃሉ እንመለከታለን፣
ሀ) የውኃ ጥምቀት፡- ጥምቀት የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃቀም ስንመለከተው ለውኃና ለመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት አገልግሎት ላይ ውሎ እናገኘዋለን፡፡ ጌታ በማቴዎስ ወንጌል 28፡18-20 ላይ ‹‹እያጠመቃችሁ›› ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው ሲል የውኃ ጥምቀትን ሲያመለክት፣ በ1ቆሮንቶስ 12፡13 ላይ ‹‹አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና›› የሚለው የመንፈስ ቅዱስን ጥምቀት ያመለክታል፡፡ ከአውዱ በሚገባ ጥናት ካላደረግንበት የውኃ ወይም የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ይሁን አይሁን፣ በቀላሉ የማንረዳቸው ጥቅሶች የሚከተሉት ናቸው፤ (ሮሜ 6፡1-11፣ ኤፌ. 4፡5፣ ቆላ 2፡12፣ ገላ. 3፡27)፡፡
ቃሉ በግሪክኛው ‹‹ባፕቲዞ›› የሚል ሲሆን፣ ትርጉሙም ‹‹መጥለቅ›› ወይም ‹‹መስመጥ››ን ያመለክታል፡፡ በወንጌሎቹ መጀመሪያ ምዕራፎች ላይ ስንመለከት፣ የንስሐ ጥምቀት ጀማሪ መጥምቁ ዮሐንስ ነበርና፤ በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳና በዮርዳኖስ ዙሪያ ካለው አገር ሁሉ ወደ እርሱ የሚመጡትን ኃጢአታቸውን እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ በውኃ እንዲጠመቁ ያደርግ እንደ ነበር ይናገራሉ፡፡ በማቴ 3፡16፣ በማር. 1፡10 እና በሉቃ. 3፡21 ላይ ሰዎች በዮርዳኖስ ወንዝ ይጠመቁ እንደ ነበረ ይናገርና በመቀጠልም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መጠመቅ ሲናገር እንዲህ ይላል ‹‹ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃው ወጣ›› የሚለው አባባል በውኃ ውስጥ በመጥለቅ መጠመቁን ያሳየናል፡፡ ኢየሱስ ተጠምቆ አገልግሎት ከጀመረ በኋላ፣ በዮሐንስ ወንጌል 4፡2 ላይ እንደምናገኘው ደቀ መዛሙርቱ ማጥመቅ እንደ ጀመሩ ቃሉ ያመለክተናል፡፡ ስለዚህ የጥምቀቱ ጀማሪ ክርስቶስ ራሱ ሲሆን፤ በመቀጠል ደቀ መዛሙርቱ በተሰጣቸው ታላቁ ተልዕኮ መሠረት እነርሱ እንደሆኑ ቃሉ ያስተምረናል፡፡ ይህ ማለት ጥምቀት ሁልጊዜ በወንዝ ውስጥ መካሄድ አለበት ማለት አይደለም፤ ዋናው ነገር ውኃው ሰውነትን ሙሉ በሙሉ መሸፈን አለበት ማለት እንጂ፡፡
ኢየሱስ የተጠመቀው ጥምቀቱ ጀማሪ ለመሆን ብቻ ሳይሆን ዓላማም አለው፤ ዓላማውም ከክርስቶስ ጋር በሁሉ ነገር ለመተባበር እንድንችል ነው፡፡ ‹‹ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን? እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን፡፡ ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን›› (ሮሜ 6፡3-5፣ ቈላ. 2፡12፣)፡፡ ከዚህ ጥቅስ የምንረዳው ነገር ቢኖር የውኃ ጥምቀት መውሰድ ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ጋር መተባበር እንደ ሆነ የሚያሳይ ማስረጃ ነው ማለት እንችላለን፡፡ ለመዳን ሳይሆን ስለ ዳንንና ትእዛዝ ስለሆነ ነው የምንጠመቀው፡፡ ውሃ በመርጨት ወይም በማፍሰስ የሚፈጸም ጥምቀት ግን ይህን ምሳሌነት ቢያጣም፤ የውኃ ችግር ባለበት አካባቢ በእምነት ቢደረግ ጌታ ይቀበለዋል፡፡ በጌታ ቀኝ የተሰቀለው ወንበዴ እንኳ ሳይጠመቅ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ ተብሎአል፡፡
የውኃ ጥምቀት በሰዎች የተጀመረ ሳይሆን የጌታ ትእዛዝ እንደሆነ ከማቴዎስ ወንጌል 28፡18-20 ባለው ክፍል ላይ ‹‹ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ፡፡ እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን (ሕዝቦችን) ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው›› በማለት ጌታ ራሱ የጀመረውን የጥምቀት ሥርዓት ለሚያምኑት ሁሉ እያስፈጸሙ በዓለም ሁሉ እንዲዞሩ ታላቁን ተልዕኮ ለደቀ መዛሙርት እንደ ሰጣቸው እንመለከታለን፡፡ በዮሐንስ ወንጌል 20፡21 ላይ ‹‹አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ›› በማለት የተልዕኮ ሽግግር ሲያደርግ ቃሉ ያመለክተናል፡፡ ሰው ከኃጢአቱ ንስሐ ገብቶ ኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝና ጌታ አድርጎ ሲያምንና ሲቀበል፣ የጌታ ትእዛዝ የሆነውን ጥምቀት ሊፈጽም፣ የውስጥ እምነቱንም በሕዝብ ፊት ሊገልጽ በውኃ ውስጥ በመግባት በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም ጠልቆ በመግባትና በመውጣት የውኃ ጥምቀት ሊወስድ ይገባዋል፡፡
በማንኛውም እድሜ ላይ ያለ ሰው ኢየሱስ ክርስቶስን አምኖ ሕይወቱን ለጌታ ለመስጠት የሚችልበት ዕድሜ ላይ የደረሰ ሁሉ ሊጠመቅ ይችላል፡፡ በቃሉ ውስጥ የተፈጸሙትን ታሪኮች ስንመለከት ማመን አስፈላጊ መሆኑን እንመለከታለን፡፡ በበዓለ ኀምሳ ቀን የጴጥሮስን ስብከት የሰሙ ሁሉ ‹‹ቃሉን የተቀበሉትም ተጠመቁ በዚያን ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ›› (የሐዋ. 2፡41)፣ ‹‹ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እየሰበከላቸው ፊልጶስን ባመኑት ጊዜ ፣ (አምነው በመቀበላቸው አ.መ.ት) ወንዶችም ሴቶችም ተጠመቁ›› ይላል (8፡12)፡፡ በሁለቱም ሥፍራ የምንመለከተው ለመጠመቅ በእውነተኛ እምነት ፈቃደኛ ሆነው ክርስቶስን መቀበል አስፈላጊ መሆኑን ነው፡፡
የውኃ ጥምቀት የወሰድን ሁሉ በውስጣዊ ሕይወታችን ያገኘነውን ለውጥ በውጫዊ በሚታይ መልኩ መዳናችንን፣ ዳግም ልደት ማግኘታችንን፣ አዲስ ፍጥረት መሆናችንንና፣ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን የምንመሰክርበት ሥርዓት ነው፡፡ የገላትያ መጽሐፍ 3፡27 ላይ ‹‹ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁላችሁ ክርስቶስን ለብሳችሁታል›› ብሎ የሚናገረው የውኃ ይሁን ወይም የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ይሁን መለየት አስቸጋሪ መሆኑን ቀደም ብለን ካየናቸው ጥቅሶች አንዱ እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ ጳውሎስ የገላትያ ሰዎች በውስጣዊ ሕይወታቸው ለውጥ ማግኘታቸውን ያስረዳቸዋል፡፡ በውኃ የምንጠመቀው በውስጡ ሕይወታችን በመንፈስ ቅዱስ የተጠመቅነውን ጥምቀት ለመግለጽ ነው፤ ስለዚህ በሁለቱም ብንወስደው፤ ጥምቀት የዳግም ልደት ማስረጃ ነው፡፡ ጌታ በሰጠው በታላቁ ተልዕኮ መሠረት፣ ቤተ ክርስቲያን ጌታን አምነውና ተቀብለው የሚመጡትን ሁሉ በውኃ ውስጥ በማጥለቅ፣ በሞቱና በትንሣኤው በመተባበር፣ የጌታን ትእዛዝ ለመፈጸም የወሰኑትን አባል አድርጋ ልትቀበላቸው ኃላፊነትና የጌታ አደራ አለባት፡፡
ለ) የጌታ ራት፡- በጌታ ከተሰጡት ሥርዓቶች የመጀመሪያውና አንዱ የጌታ ራት (ቅዱስ ቁርባን) የምንለው ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር በነበረበት ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ሦስት ዓመት ተኩል ያህል በማሰልጠን ካሳለፈ በኋላ፣ ራሱን ለሞት አሳልፎ ለመስጠት ወደ መስቀል መሄዱ የሚታወቅ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ጊዜ እስራኤላውያን የሚያከብሩት የነበረውን የፋሲካን በዓል፣ ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜ አብሮአቸው በየዓመቱ ከእነርሱ ጋር እየተካፈለ ቆይቶአል፤ ለመጨረሻ ጊዜ አብሮአቸው ተካፍሎ፤ በመቀጠልም ‹‹ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንስቶ ባረከ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ፡፡ ጽዋንም አንስቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ፡- ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው፡፡ ነገር ግን እላችኋለሁ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋር ከዚህ ከወይን ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ከዛሬ ጀምሬ አልጠጣውም›› (ማቴ. 26፡26-29፣ ማር. 14፡22-25፣ ሉቃ. 22፡14-20) አላቸው፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን ይህንን አዲስ ሥርዓት ለምዕመናኗ እየሰጠችና እያካፈለች ትገኛለች፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስም ከሃያ ዓመት በኋላ፣ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ያለውን ችግር ለማስወገድ ስለ ጌታ እራት አንስቶ ሲጽፍላት፤ ‹‹ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና ጌታ ኢየሱስ አልፎ በተሰጠባት በዚያች ሌሊት እንጀራን አንስቶ አመሰገነ፣ ቆርሶም፡- እንኳችሁ ብሉ ይህ ስለ እናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ፡፡ እንደዚሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን ደግሞ አንስቶ፡- ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው በጠጣችሁት ጊዜ ሁሉ ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ፡፡ ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እሰኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁ›› (1ቆሮ. 11፡23-26)፡፡ የጌታን እራት የምንወስደው ከዚህ በላይ እንደ ተገለጸው የክርስቶስን መከራ፣ ሞቱንና ትንሣኤውን በጠቅላላ በመስቀል ላይ ያደረገልንን በማሰብ አዳኝነቱን ላልዳኑ ሰዎች እንድንናገር ነው፡፡ የጌታ እራትን የምንወስደው ለድነት ሳይሆን መንፈሳዊ ብርታት እንድናገኝበት ነው፡፡ ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር ያለንን ሕብረትም እንገልጽበታለን፡፡ አንዱን ሕብስት በመቁረስና ከአንዱ ጽዋ በመጠጣት በክርስቶስ ያገኘነውን ሕብረት እንገልጻለን (1ቆሮ. 10፡16-17)፡፡
በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 6፡54 ላይ ‹‹ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት›› አለው በማለት የሚናገረውን ክፍል በመውሰድ የጌታን ራት በመውሰድ ድነት/ደህንነት እንደሚገኝ የሚያስተምሩ ክፍሎች አሉ፡፡ ክፍሉ የሚያስተምረው ስለ ጌታ ራት ሳይሆን ኢየሱስ ክርስቶስን በእምነት ስለ መቀበል፣ ስለ መብላትና መጠጣት ነው የሚናገረው፡፡ በቁጥር 63 ላይ ‹‹ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው ሥጋ ምንም አይጠቅምም እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው›› በማለት ከላይ ምንም ስለማይጠቅመው አብረው ስለ ቆረሱት ምድራዊ እንጀራ ከተናገረ በኋላ በእምነት መብላትና መጠጣት ስላለባቸው ሥጋውና ደሙ ተናገረ፡፡
ቤተ ክርስቲያን ከክርስቶስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በሳለፈችው ታሪኳ፤ ስለ ጌታ እራት የተለያዩ ቤተ እምነቶች የተለያዩ ወደ አራት የሚደርሱ አመለካከቶች አሏቸው፡፡ የሁሉንም አመለካከቶች በዝርዝር አንመለከትም፡፡
- ይለወጣል (Transubstantiation) የመጀመሪያዎቹ እንጀራውና ወይኑ በእውን የክርስቶስ ሥጋና ደም ወደ መሆን ይለወጣል ብለው ያምናሉ፡፡ እንጀራና ወይኑ ሙሉ በሙሉ የክርስቶስ አካል ይሆናል ተብሎ ስለሚታሰብ፣ ለአያሌ ምዕተ ዓመታት ቤተ ክርስቲያን ተራ አባሎች እንጀራውን እንዲበሉ እንጂ ከወይኑ እንዲጠጡ (የክርስቶስ ደም ዐጉል ቦታ ድንገት እንዳይንጠባጠብ በመፍራት) አትፈቅድም ነበር፡፡
- በውስጥ ዐብሮ (Consubstantiation) ሁለተኛዎቹ በእንጀራውና በወይኑ ውስጥ ከእንጀራውና ከወይኑ ጋር ያለ እውነተኛ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም ነው፤ ክርስቲያኖች ይህን እንበላና እንጠጣ ዘንድ የደነገገ ክርስቶስ ራሱ ነው የሚለውን ይጠቅሳሉ፡፡ የጌታን እራት አስመልክቶ የክርስቶስ ሥጋና ደም በእውነት መገኘቱን፣ ይህን የጌታን እራት ለሚበሉ ሁሉ እንደሚዳረስ ያስተምራሉ፡፡
- በመንፈስ (Spiritially) የሦስተኛዎቹ አመለከከት እንጀራውንና ወይኑን በምንካፈልበት ጊዜ ክርስቶስ በአካል ይገኛል ባይሉም፤ በመንፈሳዊ ሁኔታ በመንፈስ በመካከላችን ይገኛል ብለው ያምናሉ፡፡
- መታሰቢያ (Memoreial) የመጨረሻው አመለካከት ያላቸው አብያተ ክርስቲያናት የሉቃስ ወንጌልንና የቆሮንቶስ መልእክትን መሠረት በማድረግ የጌታ እራት መታሰቢያ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ‹‹እንጀራንም አንስቶ አመሰገነ ቆርሶም ሰጣቸውና ስለ እናንተ የሚሰጠው ሥጋዬ ይህ ነው ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ›› (ሉቃስ 22፡19) የሚለውን ወንጌል የጻፈው ሉቃስ ሲሆን ጌታ የተናገረውን በቀጥታ በመጥቀስ አስፍሮ እናገኛለን፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስም በመልእክቱ ለቆሮንቶስ አማኞች ስለ ጌታ እራት ያላቸውን የተሳሳተ አመለካከት ለማስተካከል ሲጽፍላቸው ‹‹ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና ጌታ ኢየሱስ አልፎ በተሰጠባት በዚያች ሌሊት እንጀራን አንስቶ አመሰገነ ቆርሶም፡- እንካችሁ ብሉ ይህ ስለ እናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው ይህን ለመታሰቢየዬ አድርጉት አለ፡፡ እንደዚሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን ደግሞ አንስቶ፤- ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው በጠጣችሁት ጊዜ ሁሉ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ፡፡ ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና›› (1ቆሮ. 11፡23-26)፡፡
ቃሉ እንደሚናገረው የጌታ እራት ክርስቶስ በምድር በነበረበት ጊዜ በመስቀል ላይ ያደረገልንን የምናስታውስበት ‹መታሰቢያ› ሲሆን ተመልሶ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ መከራውን፣ ሞቱንና ትንሣኤውን ላላመኑ ሰዎች የምናውጅበት ሥርዓት መሆኑን እቀበላለሁ፤ ቤተ ክርስቲያኔም ትቀበላለች፡፡ በቤተ ክርስቲያን የወጡ ሥርዓቶች፡- ቀደም ብለን በጌታ የተሰጡትን የጥምቀትና የጌታ እራት ሥርዓቶችን ተመልክተናል፤ በመቀጠል በጌታ ባይሰጡም፣ ቤተ ክርስቲያን ከልምድ (EXPERIENCE) ባገኘችው፣ ከተለያዩ አባሎች ጋር በሚደረግ ግንኙነት (RELATIONSHIP) መሠረት በማስፈለጋቸው ምክንያት የሹመት፣ የጋብቻ፣ ልጅ የማስረከብ፣ የቀብርና የምርቃት ሥርዓት ታከናውናለች፡፡ ከቃሉ ጋር እስካልተጋጨ ጊዜ ድረስ መፈጸማቸው ምንም ችግር የለውም፤ ነገር ግን እነዚህን አለመፈጸም ድነትን ሊያሳጣ፣ ወይም ድነትን ሊያስገኝ ይችላል የሚል አንድምታ ካላቸው፣ እነዚህን መቀበል አስቸጋሪ ይሆናል፡፡
0 Comments