5. የቤተ ክርስቲያን መሪዎች
ሀ) ሐዋርያት፡- ስለ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች፣ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በምናጠናበት ጊዜ የምናገኛቸው መሪዎች፣ ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜ፣ አገልግሎት እንደ ጀመረ፣ ቀደም ብሎ ሐዋርያትን መርጦ አገልግሎት ማስጀመሩ የሚታወቅ ነው፡፡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተመርጠው ሕይወታቸውን ለጌታ በማስረከብ ተከታዮቹ፣ ደቀ መዛሙርትና አገልጋዮቹ ሆነው በማለፋቸው፤ ከትንሣኤም በኋላ የመሪነቱን ሥፍራ ይዘው መቆየታቸውን የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ያረጋግጥልናል፡፡ ቀደም ብዬ ባለፈው ጥናቴ እንደገለጥኩት በመካከላቸው በተፈጠረው ችግር በሐዋ. 6፡1-6 ላይ ረዳት አገልጋዮችም መመረጣቸውምና ሐዋርያት በቃሉ ለማገልገል፤ የተመረጡት አገልጋዮች ደግሞ በማዕድ ለማገልገል አገልግሎት በመከፋፈል ተመዳድበው እንደነበር በግልጽ የሚታወቅ ነው፡፡
ሐዋርያ የሚለው የቃሉን ትርጉም በመሠረታዊ ቋንቋው በግሪክኛው ‹‹አፖስቶሎስ›› የሚለውን ቃል ስንመለከተው ‹‹የተላከ፣ መልእክተኛ›› ማለት ነው፡፡ በዚህ ቃል ሐዋርያት ከመጠራታቸውም በፊት፣ ግሪኮች ቃሉን ይጠቀሙበት ነበር፡፡ በዚህ መሠረት ቃሉ ደቀ መዛሙርትን ብቻ ከማመልከት ውጭም ኢየሱስም፣ ጳውሎስም ተጠቅመውበት እናገኛለን፡፡ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ መልእክቱ 2፡25 ላይ አፍሮዲጡ ‹‹የእናንተ መልእክተኛ›› መባሉን፤ እንዲሁም በ2ኛ ቆሮንቶስ 8፡23 ላይ ስለ ወንጌል ጓደኞቹ (ስለ ጢሞቴዎስና ስልዋኖስ 1፡19) ሲናገር ‹‹የአብያተ ክርስቲያናት መልእክተኞች›› ብሎ መጥራቱን እንመለከታለን፡፡ ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ‹‹መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም›› (ዮሐ. 13፡16) ብሎ ቃሉን መጠቀሙን ያመለክተናል፡፡
ከዚህ በላይ ያሉትን ጥቅሶች እንደ ተመለከትነው፣ ቃሉ ሐዋርያትን ለመሰየም አዲስ የወጣና ሥራ ላይ የዋለ ብቸኛ ቃል ሳይሆን፣ የተለያዩ ሰዎችን ለመጥራት ጥቅም ላይ ውሎ እናገኘዋለን፡፡ ነገር ግን ሐዋርያትን ልዩ የሚያደርጋቸው፣ 1) በኢየሱስ ክርስቶስ በራሱ መመረጣቸው (ማቴ. 10፡1-5)፣ 2) የኢየሱስ ክርስቶስን ከሞት መነሳት በዓይናቸው በማየታቸውና የትንሣኤው ምስክር መሆን መቻላቸው (የሐዋ. 1፡22)፣ 3) መከራ ቢኖርበትም ወስነው በፅናት መከተላቸው ነው፡፡
የሐዋርያት ሥራ ጥናትን እየቀጠልን ስንሄድ፣ ቀደም ብዬ እንደገለጥኩት የመጀመሪያቱን ቤተ ክርስቲያን የሚመሯት ሐዋርያት እንደነበሩና በመቀጠልም የሚረዷቸውን አገልጋዮችንም መርጠው እንደነበር መግለጤ ይታወቃል፡፡ በመቀጠል ጥናታችንን ስንቀጥል ሐዋርያት የታላቁ ተልዕኮ ጀማሪዎች በመሆናቸው ሽማግሌዎችንና ዲያቆናትን መቼ እንዳስመረጡ መጽሐፉ አይነግረንም፤ በተሰጣቸው ተልዕኮ መሠረት አሥር ዓመት ያህል ከኢየሩሳሌም ሳይወጡ፣ ቤተ ክርስቲያንን ሲመሩ ከቆዩ በኋላ ለሽማግሌዎች እንዳስረከቡ ማየት እንችላለን፡፡ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 11፡30 ጀምሮ የሽማግሌዎች ስም ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቅሶ እናገኛለን፤ በመቀጠልም ሐዋርያትና ሽማግሌዎች እያለ ሲጠቅሳቸው እናገኛለን (የሐዋ. 15፡6፣22፣23)፡፡ ከዚህ በኋላ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች አብረው ሲሰበሰቡ፣ ሲወስኑና አገልጋዮችን ሲልኩ እንመለከታለን፡፡ ሐዋርያት የተጠሩት የአንድ አጥቢያ ሐዋርያ ሆነው ለመቀመጥ ሳይሆን በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳ፣ በሰማርያና በዓለም ዳርቻ ወንጌልን ይዘው እንዲሄዱ በመታዘዛቸው ምክንያት፣ ቢዘገዩም ሽማግሌዎችን በማስመረጥ ካደራጁ በኋላ፣ ሥፍራውን ለቀው ወደ ተቀበሉት ታላቁ ተልዕኮ እንደ ተመለሱ ከቤተ ክርስቲያን ታሪክም ማየትና መረዳት እንችላለን፡፡
የሚስዮናዊ አገልግሎት ጀማሪ የሆነችው የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ጳውሎስንና በርናባስን ለወንጌል ሥራ ልካቸው አገልግሎት መስጠት በጀመሩበት ጊዜ፤ በሐዋ. 14፡23 ላይ እንደምናገኘው ሽማግሌዎችን እየሾሙና ለጌታ አደራ እየሰጡ ጉዞ እንዳደረጉ እንመለከታለን፡፡ ከተወሰነ ዓመት በኋላ እነጳውሎስ ከወንጌል ጓደኖቹ ጋር ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም በወጣ ጊዜ፣ የሄደውና የተቀበሉት የቤተ ክርስቲያን የሽማግሌዎች ሰብሳቢ የነበረው ያዕቆብና ሽማግሌዎች እንዳስተናገዱት ይገልጻል (የሐዋ. 15፡13፣21፡18፣ ገላ. 1፡19)፡፡
ከላይ ባየነው መሥፈርት መሠረት አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት በኢየሱስ ምርጫ ያገኙትን ሥልጣን ከዚያ በኋላ ያንን ዕድል ሊያገኝ የሚችል አይኖርም፤ ምክንያቱም ጌታ በአካል ተገኝቶ ሁለተኛ ምርጫ ስለማያደርግ፡፡ የትንሣኤው ምሥክር የነበሩት ግን ሐዋርያ ተብለው እንደ ተጠሩ ከቃሉ እናነባለን፡፡ ማትያስ በይሁዳ ቦታ የተተካው፣ (የሐዋ. 1፡24-26) ጳውሎስና በርናባስ (የሐዋ. 14፡14)፣ ስልዋኖስ (ሲላስ) እና ጢሞቴዎስም ‹‹የክርስቶስም ሐዋርያት እንደ መሆናችን ልንከብድባችሁ ስንችል …›› (1ተሰ. 2፡6) ላይ ሐዋርያት ተብለው መጠራታቸውን ቃሉ ያመለክተናል፡፡ የጌታ ወንድም ያዕቆብ ሐዋርያ ተብሎ የቤተ ክርስቲያኒቱም ሰብሳቢ ሆኖ ማገልገሉን ማየት ይቻላል (ገላ. 1፡19፣ 2፡9፣ የሐዋ. 15፡13-21)፡፡ ስለዚህ በሐዋርያት ሥራ ጥናት መሠረት ጌታ በአካል ተገኝቶ ባይሾምም ከአስራ ሁለቱ ሌላ ይህን የአገልግሎት መጠሪያ ተጠቅመውበት እንደነበረ እንረዳለን፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክቱ 4፡11 ላይ ለቤተ ክርስቲያን በተሰጡ የጸጋ ስጦታዎች መሠረት ይህ ስጦታ ሊኖራቸው የሚችሉ አገልጋዮች እንዳሉ ይናገራል፤ ያ ማለት እንደ አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ይሆናሉ ወይም ይቆጠራሉ ማለት ሳይሆን፤ ከየትኛውም የጸጋ ስጦታዎች ከተሰጣቸው አገልጋዮች ሳይበልጡ፤ ከሌሎቹ እኩል ሆነው ሊያገለግሉ እንደሚችሉ መረዳትና ማስተዋል ይቻላል፡፡ አሁንም ያ ጸጋ ያላቸው አገልጋዮች ታላቁን ተልዕኮ ይዘው መውጣት አለባቸው እንጂ፣ በአጥቢያ ተወስነው ሐዋርያ ነን ቢሉ ስጦታውን ያለ ቦታው መጠቀም ስለሚሆን ዋጋ ያሳጡታል፡፡ ሐዋርያት ከዮሐንስ በስተቀር ሁሉም በተለያየ ሥፍራ ለወንጌል ሥራ ተሰማርተው መስዋዕት ሆነው እንዳለፉ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ መረዳት እንችላለን፡፡
ለ) ሽማግሌዎች፡- የሽማግሌዎች አገልግሎት ከሐዋርያት እንደ ቀጠለ በጥናታችን ተመልክተናል፤ አብረው ሲያገለግሉ ቆይተው፣ ሙሉ በሙሉ የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነቱን ለሽማግሌዎች እንዳስረከቡ፤ ሽማግሌዎች አገልግሎቱን በምርጫ ከሐዋርያት ተረክበው ሲያገለግሉ መቆየታቸውን ቀደም ባለው ጥናታችን ተመልክተናል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በሚስዮናዊ አገልግሎቱ አንደኛውን የወንጌል ጉዞ እያደረገ በዞረባቸው ከተማዎች ሁሉ ወንጌልን ሰብኮ እንደገና በሚጎበኛቸው ጊዜ ሽማግሌዎችን እየሾመ መዞሩን ተመልክተናል (የሐዋ. 14፡23)፡፡ ጳውሎስ ይህንን የሽማግሌዎች የመሾም ሥርዓት ያደርግ የነበረው እርሱ ብቻ ሳይሆን የአገልግሎቱ ረዳቶች የነበሩት ጢሞቴዎስና ቲቶ እንዳደረጉት ከቃሉ እናነባለን፡፡ ‹‹ስለዚህ ምክንያት የቀረውን እንድታደራጅ በየከተማውም፣ እኔ አንተን እንዳዘዝሁ ሽማግሌዎችን እንድትሾም በቀርጤስ ተውሁህ›› (ቲቶ 1፡5) በማለት ቲቶን ሲያሳስበው እናያለን፡፡ እነጳውሎስ ሽማግሌዎችን እያስመረጡ ኃላፊነት እየሰጡና እያስረከቡ ጉዞአቸውን ይቀጥሉ እንደነበር የታወቀ ነው፡፡
ሐዋርያው ያዕቆብም ‹‹ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ በጌታም ስም ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት›› (ያዕ. 5፡14)፣ ሐዋርያው ጴጥሮስም በመልእክቱ ‹‹በመካከላቸው ያሉትን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ፣ በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ›› (1ጴጥ. 5፡1-2) በማለት ለቤተ ክርስቲያን የበላይ ጠባቂዎችና መሪዎች ለነበሩት ሽማግሌዎች መልእክቱን ያስተላልፋል፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያንን በቡድን ሲመሩ የምናያቸው ሽማግሌዎች መሆናቸውን ቃሉ ያረጋግጥልናል፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስም ሆነ ሌሎች የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ቃላትን እየለዋወጡ ሽማግሌ፣ እረኛና ኤጲስ ቆጶስ እያሉ ተጠቅመውበታል እንጂ፣ ለአንድ አገልግሎት የተስጡ ስሞች መሆናቸውን ማየት እንችላለን፡፡ በግሪክኛው አጠራር ‹‹ፕሪስባቴሮስ›› ሽማግሌ የሚለውን ቃል በብዙ ቦታ ተጠቅመውበታል፡፡ እረኛ በግሪክኛው አጠራር ‹‹ፖይሜን›› የሚለው ይህ ቃል ተጠቅሶ የምናገኘው በሁለት ሥፍራ ብቻ ላይ ነው፡፡ (ኤፌ. 4፡11፣ 1ጴጥ. 5፡2) በተረፈ እኛ ዛሬ ‹‹መጋቢ›› ወይም ‹‹ፓስተር›› እያልን የምንጠቀምበትን ቃል የ1962 እና የመደበኛው ትርጉሞች ‹‹ባለ ዐደራ›› ብለው ተርጉመውታል (1ጢሞ. 1፡4፣ ቲቶ 1፡7) ተመልከቱ፡፡
ኤጲስ ቆጶስ የሚለውን ቃል ግሪክኛ ሲሆን፤ አማርኛው የግሪክኛውን ቃል ራሱን በመውሰድ ኤጲስ ቆጶስና በአማርኛችን ‹‹ጳጳስ›› ብሎ ተጠቅሞበታል፡፡ እንግሊዝኛው (Overseer or Bishop) የሚለውን ማለት ነው፤ ሐዋርያው ጳውሎስም ሆነ ጴጥሮስ ሽማግሌ ያሉትን እረኛ፣ ወይም ኤጲስ ቆጶስ እያሉ እያቀያየሩ ተጠቅመውበታል፡፡ ‹‹ከሚሊጢንም ወደ ኤፌሶን ልኮ የቤተ ክርስቲያንን ሽማግሌዎች አስጠራቸው… በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ›› (የሐዋ. 20፡17፣28፤ ቲቶ 1፡5፣ 7፣ ፊልጵ. 1፡1፣ 1ኛጢሞ. 3፡1)፡፡
ጴጥሮስም በመልእክቱ ሽማግሌና እረኛ እያለ በማለዋወጥ ተጠቅሞአል፡፡ ‹‹ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ (ፕሪስባይቴሮስ)… በመካከላቸው ያሉትን ሽማግሌዎች (እረኞች) እመክራቸዋለሁ… ለሽማግሌዎች (ፕሪስባይቴሮስ) ተገዙ›› (1ጴጥ. 5፡1፣5)፡፡ ስለዚህ ሦስቱም ቃሎች አንድን አገልግሎት የሚያገለግሉ አገልጋዮችን ለመጥራት የዋሉ የተለያዩ የግሪክ ቃላት ናቸው፡፡ በተለይም አዲስ ኪዳንን ስንመለከት ሽማግሌዎች ሆነው ያገለገሉት በሙሉ ጊዜአቸው እንደሆነ ከሚከተሉት ጥቅሶች መረዳት አያስቸግርም፡፡ ‹‹በመልካም የሚያስተዳድሩ ሽማግሌዎች ይልቁንም በመስበክና በማስተማር የሚደክሙት እጥፍ ክብር ይገባቸዋል፡፡ መጽሐፍም፡- የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር፣ ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል ይላልና›› (1ጢሞ. 5፡17-18) የሚለውን የብሉይ ኪዳን ጥቅስ በመጥቀስ ጽፏል፡፡ ከዚህ ጥቅስ ብዙ እውነቶችን ማውጣት እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው የሽማግሌዎች ኃላፊነት ቤተ ክርስቲያንን ማስተዳደር፣ ሁለተኛው በመስበክና በማስተማር መድከም፣ ሲሆን ሦስተኛው ሽማግሌዎች ከቤተ ክርስቲያን ቀለብ ይሰፈርላቸው እንደ ነበረ ያመለክተናል፡፡
የምርጫ መመዘኛዎች፡- ሽማግሌዎች ለአገልግሎት ለምርጫ የሚመዘኑበት መስፈርት በቃሉ ውስጥ ተቀምጦአል፤ ስለዚህ በቤተ ክርስቲያን ለአግልግሎት በሚመረጡበት ጊዜ በቃሉ ውስጥ በተቀመጡት መስፈርቶች መሆን እንዳለበት እንገነዘባለን፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጢሞቴዎስና ቲቶ በየከተማው ሽማግሌዎችን በሚሾሙበት ጊዜ ያስቀመጠላቸውን መለኪያዎች በዝርዝር ከሚከተሉት ጥቅሶች እንመልከት፡፡ መስፈርቶቹም በ1ኛ. ጢሞቴዎስ ምዕራፍ 3፡1-7 ቲቶ 1፡5- 9) ባለው ክፍል ውስጥ እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል፡፡
‹‹ማንም ኤጲስ ቆጶስነትን ቢፈልግ መልካምን ሥራ ይመኛል የሚለው ቃል የታመነ ነው፡፡ እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል የማይነቀፍ፣ የአንዲት ሚስት ባል፣ ልከኛ፣ ራሱን የሚገዛ፣ እንደሚገባው የሚሠራ፣ እንግዳ ተቀባይ፣ ለማስተማር የሚበቃ፣ የማይሰክር፣ የማይጨቃጨቅ ነገር ግን ገር የሆነ፣ የማይከራከር፣ ገንዘብን የማይወድ፣ ልጆቹን በጭምትነት ሁሉ እየገዛ የራሱን ቤት በመልካም የሚያስተዳድር፣ ሰው ግን የራሱን ቤት እንዲያስተዳድር ባያውቅ፣ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ይጠብቃታል? በትዕቢት ተነፍቶ በዲያቢሎስ ፍርድ እንዳይወድቅ፣ አዲስ ክርስቲያን አይሁን፡፡ በዲያቢሎስ ነቀፋና ወጥመድም እንዳይወድቅ፣ በውጭ ካሉት ሰዎች ደግሞ መልካም ምስክር ሊኖረው ይገባል››፡፡
መመዘኛዎቹንም በሦስት ልንከፍላቸው እንችላለን፡፡ ሀ) የግል ሕይወትን፤ ለ) የቤተ ሰብ ሕይወትንና ሐ) ማህበራዊ ሕይወትን የሚመለከቱ መመዘኛዎች በቃሉ ውስጥ ተቀምጠው እናገኛለን፡፡ ዛሬ ሽማግሌዎችን ለአገልግሎት ስንሾም፤ ተመራጮች በዓለም ካላቸው ዝናና ስኬት አንጻር ሳይሆን፣ ከዚህ በላይ ባየናቸው ሦስት መመዘኛዎች አንጻር ብንመርጥ፣ ከመልካም ባሕርያቸውና ፈሪሃ እግዚአብሔር ካለበት ሕይወታቸው አንጻር ቢሾሙ ቤተ ክርስቲያንን ፍሬአማ ሊያደርጓትና ቤተ ክርስቲያን በአካባቢዋ ላለው ኅብረተ-ሰብ መልካም ምሳሌ ሆና መገኘት ትችላለች፡፡
የምርጫ ዘመን፡- የሐዋርያት ሥራ ጸሐፊ ሉቃስም ሆነ፤ ሐዋርያው ጳውሎስ የሽማግሌዎችን መስፈርት ሲያስቀምጥ፤ ለምን ያህል ጊዜ ማገልገል እንዳለባቸው ያስቀመጠው ነገር የለም፡፡ በዘመናችን ያሉ ቤተ እምነቶች በሽማግሌዎች አገልግሎት የሚጠቀሙ በሙሉ ጊዜ ሳይሆን፣ ለተወሰነ ዓመት በተርም፣ በዙር እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ ስንመለከት፣ አስተዳደሩ ከሐዋርያት ወደ ሽማግሌዎች፣ ከሽማግሌዎች ወደ ኤጲስ ቆጶስ አስተዳደር መጥቶ፤ ለረጅም ጊዜ የተሠራበት አስተዳደር ዓይነት እንደ ነበረና ምርጫውም የዕድሜ ልክ እንደ ነበረ እንመለከታለን፡፡ ካልቪን መጥቶ የሽማግሌዎችና የዲያቆናትን አገልግሎት ክፍል በማደራጀት እንደገና ሥፍራ እንዲኖረው ያደረገው እርሱ ነው፤ ዛሬ ያሉትም አብያተ ክርስቲያናት የሚመቻቸውንና ይጠቅመናል ያሉትን የአስተዳደር፣ የአመራረጥና የጊዜ ርዝማኔ እንደሚመቻቸው በማድረግ እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡ አንድ ሰው ለሦስት ወይም ለአራት ዓመት፣ ለሁለት ጊዜ ተመርጦ ካገለገለ በኋላ፣ የቱንም ያህል ጠቃሚና አስፈላጊ ሰው ቢሆንም፣ ሳይመረጥና ለማረፍ፣ አዲስ ራዕይ ለመቀበልና በአዲስ ኃይል ለመሥራት፣ ለአንድ ዙር ማረፍ አለበት ብለው ብዙዎቹ ተስማምተው ይጠቀሙበታል፡፡
ሐ) ዲያቆናት፡- የዲያቆናት አገልግሎት እንደ ሽማግሌዎች አገልግሎት መቼ እንደ ተጀመረ ቃሉ አይነግረንም፤ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 6፡1-6 ባለው ክፍል ላይ በተለምዶ ዲያቆናት እያልን የምንጠራቸው ሰባት አገልጋዮች የተመረጡት በማዕድ እደላው ለተፈጠረው ችግር አገልግሎት እንዲሰጡ ብቻ ነበር እንጂ ዲያቆናት አልነበሩም፡፡ ምክንያቱም በዚህ ጊዜ የሽማግሌዎች ምርጫ በቤተ ክርስቲያን ሳይካሄድና ሳይኖር ዲያቆናት ነበሩ ብሎ ለመቀበል ያስቸግራል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ሽማግሌዎች ተጠቅሰው የምናገኘው በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 11፡30 ላይ ስለሆነ ነው፡፡ ሽማግሌዎች ሳይመረጡ ዲያቆናት ተመርጠው ነበር የሚለው ሐሳብ አካሄድ አያስኬድም፡፡ ሐዋርያው ጰውሎስም በሐዋርያት ሥራ 14፡23 ላይ ሽማግሌዎችን እያስመረጠ ቢዞርም፣ ዲያቆናትን ማስመረጡን ቃሉ አይነግረንም፤ ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ከተመረጡ ዲያቆናትም ተመርጠው ሊሆን ይችላል ብሎ ማሰብ ይቻላል፡፡ ጳውሎስም የሚመረጡበትን መለኪያ አስቀምጦልናል፡፡
ዲያቆን የሚለውን ቃል በግሪክ ዲያቆኖስ ይለዋል፣ ትርጉሙም ‹‹አገልጋይ›› ማለት ሲሆን፣ በዚህ መሠረት ለማዕድ አገልግሎት መመረጣቸውን ቃሉ በግልጽ ያሳየናል፤ ‹‹የእግዚአብሔርን ቃል ትተን ማዕድን እናገለግል ዘንድ የሚገባ ነገር አይደለም፡፡ ወንድሞች ሆይ፡- በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብም የሞላባቸውን ሰባት ሰዎች ከእናንተ ምረጡ፣ ለዚህም ጉዳይ እንሾማቸዋለን›› የሚለው የቃል መመሳሰልን ከማመልከት በስተቀር ዲያቆናት መመረጣቸውን አያመለክትም፤ ከዚያም በኋላ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ቃሉ ደግሞ ተጠቅሶ አናገኘውም፡፡ የዲያቆናትና ሽማግሌዎች ምርጫ መቼ እንደ ተጀመረ ቃሉ አይነገረንም፤ በአዲስ ኪዳን ያሉ አብዛኛዎቹ መልእክቶች ሁሉ ሲጻፉ የሚላኩት ለ‹‹ቅዱሳን›› ብሎው ሲሆን፤ ሐዋርያው ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች ሲጽፍ ግን ‹‹ለሽማግሌዎች (ኤጲስ ቆጶስ) እና ዲያቆናት ብሎ መጻፉን እናገኛለን (ፊልጵ. 1፡1)፡፡
ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈለት በመጀመሪያ መልእክቱ ስለ ዲያቆናት ምርጫ መለኪያዎችን አስቀምጦ እናገኛለን፤ መለኪያዎቹ በተቀመጡበት ሥፍራ ቢሆንም፤ ዲያቆናት ምን መሥራት እንዳለባቸው በግልጽ የሚጠቁም ነገር የለም፡፡ አንድ የምናውቀው ነገር ቢኖር ስማቸው ከሽማግሌዎች ጋር መጠቀሱንና ሲመረጡ መለኪያቸው ምን መሆን እንዳለበት ብቻ ገልጾ እናገኛለን፡፡
‹‹እንዲሁም ዲያቆናት ጭምቶች በሁለት ቃል የማይናገሩ ለብዙ ወይን ጠጅ የማይጎመጁ፣ ነውረኛ ረብ የማይወዱ፣ በንጹህ ሕሊና የሃይማኖትን ምስጢር የሚይዙ ሊሆኑ ይገባቸዋል፡፡ እነዚህም ደግሞ አስቀድመው ይፈተኑ፣ ከዚያም በኋላ ያለ ነቀፋ ቢሆኑ በዲቁና ሥራ ያገልግሉ፡፡ እንዲሁም ሴቶች ጭምቶች የማያሙ፣ ልከኞች፣ በነገር ሁሉ የታመኑ ሊሆኑ ይገባቸዋል፡፡ ዲያቆናት ልጆቻቸውንና የራሳቸውን ቤቶች በመልካም እየገዙ እያንዳንዳቸው የአንዲት ሴት ባሎች ይሁኑ፡፡ በዲቁና ሥራ በመልካም ያገለገሉ ለራሳቸው ትልቅ ማዕረግና በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው እምነት ብዙ ድፍረት ያገኛሉ›› (1ጢሞ. 3፡8-13)፡፡
በአዲስ ኪዳን ያለውን አሠራር ስንመለከት የብሉይ ኪዳኑን የካህናትን አገልግሎት በሽማግሌዎች፣ የሌዋውያንን አገልግሎት በዲያቆናት ገልብጠው ያመጡት ሳይሆን አይቀርም ብዬ በግሌ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም አይሁዶች የኖሩበት ሥርዓትና ልማድ ቶሎ አልተላቀቃቸውም፤ ቀደም ብዬ ስለ አጥቢያ ባጠናነው ጥናት ለጸሎት ቤተ መቅደስ ይሄዱ እንደ ነበረ አይተናል (የሐዋ. 2፡46፣ 3፡1)፡፡ በዚህ ሁኔታ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች የካህናትና የሌዋውያን አገልግሎት ለአይሁዶች የታወቀ በመሆኑ፤ ስለ ሽምግልናና ዲያቆናት አገልግሎት ብዙ ገለጻ ሲሰጡት አናይም፡፡
በዚህ በአንደኛ ጢሞቴዎስ ምዕራፍ ሦስት ውስጥ በምናገኘው መለኪያ ውስጥ ዲያቆናት በምን በምን ማገልገል እንዳለበቸው ባይናገርም፤ እንደየ ቤተ ክርስቲያኑ ራዕይ፣ እቅድና የአገልግሎት ስፋት መሠረት መድበው የአገልግሎት ዝርዝር ሊያወጡላቸው ይችላሉ፡፡ ለማንኛውም ነገር ከሽማግሌዎች ሥር ሆነው በረዳትነት በተሰጣቸው ጸጋና ኃላፊነት መሠረት ማገልገላቸው የሚያጠያይቅ አይደለም፤ አገልግሎቱ ቤተ ክርስቲያንን በማዕድ፣ ገንዘብ በመያዝ፣ በጽዳትና በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ ሊሆን እንደሚችልና ሽማግሌዎች እንዲያግዙአቸው በሚፈልጉበት ሥፍራ ሁሉ እንዲያገለግሉ ሊያደርጉ እንደሚችሉ መረዳት እንችላለን፡፡ በዚህ መሠረት የቤተ ክርስቲያን ቢሮዎች ሁለት ሲሆኑ ሌሎቹ የጸጋ ስጦታዎች ቢሮ ሳይኖራቸው አካሉን ለማነፅ የሚያገለግሉ መሆናቸውን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን መረዳት እንችላለን፡፡
0 Comments