3 . ዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን

ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ ባለው መሠረት፣ አንዲት የማትታይ ዓለም አቀፋዊ (UNIVERSAL) ቤተ ክርስቲያን አለችው፡፡ በግሪክኛው አጠራር ቀደም ብለን ‹‹ኤክሌሽያ›› (ተጠርተው የወጡ) ብለን የጠራናት ስትሆን፣  በወንጌል ጥሪ ደርሷቸው ከሰይጣን ወደ ክርስቶስ ግዛት፣ ከጨለማ ወደ  ብርሃን ተጠርተው የወጡ፤ በኢየሱስ ክርስቶስ አምነውና በደሙ ታጥበው፣ በአንድ ቦታ በአካል ተሰባስበው የማይገኙ፣ ከየቤተ እምነቱ የሆኑ፣ እውነተኛ አማኞች ሁሉ የዚህች ቤተ ክርስቲያን አባሎች ናቸው፡፡

አንዷ የማትታየዋ ዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን በተለያየ ሥፍራና አገር፣ ቋንቋና ባህል ውስጥ ተሰራጭታ ትገኛለች፡፡ ከበዓለ ኀምሳ እስከ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት ድረስ ያሉትን እውነተኛ አማኞችን ይዛ ትገኛለች፡፡ በቀለም፣ በቋንቋ፣ በባህልና በዕውቀት ሳትለያይ፣ ሁሉንም አቅፋ የምትገኝ የእውነት አምድና መሠረት ሆና፣ የዘላለም ሕይወትን ለሰው ሁሉ የምታበስር መሆኗን መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክርላታል (1ጢሞ. 3፡15)፡፡ በክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ ወንድምና እህት ሆነው በፍቅር አምላካቸውን ያመልካሉ፣ ያከብራሉ፣ ያገለግላሉ፡፡

ዓለም አቀፍዋ ቤተ ክርስቲያን፣ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በተለያዩ ምሳሌዎች ተገልጣ እናገኛታለን፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያኑ መካከል ያለውን ግንኙነት ለመግለጥ የተጠቀመባቸው ምሳሌዎች እጅጉን በጣም ግልጽና  እውነቱን በሚገባ ቁልጭ አድርገው የሚገልጹና የሚያስጨብጡ ናቸው፡፡

አካል፡- ቤተ ክርስቲያንን ከሚገልጡት ምሳሌዎች የመጀመሪያው አካል ሲሆን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በአንድ አካል ተመስላ የምናገኛት በተለያዩ የጳውሎስ መልእክቶች ውስጥ ነው፡፡ በዚህ አንድ አካል፣ ክርስቶስ ራስና መሠረት ሲሆን፣ አማኞች ደግሞ ሕያዋን የአካሉ ብልቶች ሆነው አካሉን ለማገልገል መቀመጣቸውን ያመለክቱናል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎሰም በአንደኛ ቆሮንቶስ መልእክቱ ቆሮ. 12፡12-31 ድረስ ስለ አካል ብዙ እውነቶችን ያሳያል፤ ‹‹አካልም አንድ እንደ ሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደሆኑ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናል›› ቤተ ክርስቲያን ከማንኛውም ቤተ እምነት (ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክና ፕሮቴስታቶችን) ዳግም ተወልደው እውነተኛ የሆኑትን አማኞች የያዘች አንድ አካል መሆኗን በማሳየት፤ የአካሉንና የብልቶቹን ተግባር በመግለጽ ያብራራል፡፡ አካል ብዙ ብልቶች ቢኖሩትም በመተባበርና በስምምነት ለአንድ ዓላማና ጥቅም እያንዳንዱ ብልት ሥራውን በሚገባ ይወጣል፡፡ እንደዚሁም ቤተ ክርስቲያን አንድ አካል ሆና የተለያዩ የጸጋ ስጦታ ያላቸው አባላት ሁሉ በተሰጣቸው ስጦታ አማካኝነት ለአካሉ ጥቅም፣ ለእግዚአብሔር ክብር የተሰጣትን አገልግሎት በትጋት እንድትወጣ የሚያደርግ የተሰጠ ምሳሌ ነው (ሮሜ. 12፡3-8፣ ቆላ. 1፡18፣ ኤፌ. 2፡20)፡፡

            ከዚህ በላይ ያሉትን ጥቅሶች ጠቅለል አድርገን ስንመለከታቸው የሚሰጡን ዋነኛው ትምህርታቸው በአካልና በብልቶች መካከል ያለው ግንኙነት፤ በክርስቶስና በምዕመናን መካከል ያለውን ግንኙነት ያመለክቱናል፡፡ ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን ራስ ስለሆነ ተገቢውንና ከፍተኛውን ሥፍራ መያዝ እንዳለበት፤ የሕይወት ምንጯና ሙላቷ እርሱ ስለሆነ፣ ቤተ ክርስቲያን ድምጹን ልትሰማውና ልትታዘዘው እንደሚገባትና የመሪነቱ ሥፍራ በፍጹም ሊነፈገው እንደማይገባ ያመለክቱናል፡፡ ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት በዚህ ምድር ላይ ብዙ ቤተ እምነቶች ቢኖሩም ክርስቶስ ያለችው አንዲት እውነተኛና ንፅህት ድንግል ቤተ ክርስቲያን ብቻ ናት፡፡ በአካል መመሰሏ የሚያሳየን ይህን እውነት ነው፡፡

ሕንጻ፡- ጳውሎስ በሁለተኛ ደረጃ ቤተ ክርስቲያንን በሕንጻ መስሏት እናገኛታለን፤ ‹‹በሐዋርያትና በነብያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፣ በእርሱም ሕንጻ ሁሉ እየተጋጠመ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል፣ በእርሱም እናንተ ደግሞ ለእግዚአብሔር መኖርያ ለመሆን በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ›› (ኤፌ. 2፡20-22) በሚለው መሠረት፤ ቤት በምንሠራበት ጊዜ በተለያዩ የሸክላና የብሎኬት ጡቦች ተጠቅመን ስንሠራ፣ እርስ በርሳቸው በሲሚንቶ ፍቅር ተጣብቀውና ተያይዘው አብረው አንድ ቤት ሆነው እንደሚሠሩት፤ አማኞችም ሁሉ እንዲሁ በፍቅር አንድ ሕንጻ ለመሆን መሠራት እንዳለብን ያመለክተናል፡፡

ጴጥሮስም በመልእክቱ 1ኛ ጴጥ. 2፡4-6 ላይ ‹‹… በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ወደ ተመረጠና ክቡር ወደ ሆነው ሕያው ድንጋይ ወደ እርሱ እየቀረባችሁ፣ እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ …መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ፡፡ በመጽሐፍ፡- እነሆ የተመረጠና የከበረን የማዕዘን ራስ ድንጋይ በጽዮን አኖራለሁ፤ በእርሱ የሚያምን አያፍርም ተብሎ ተጥፎአልና›› የሚለውን የኢሳይያስን ትንቢት በመጥቀስ፤ ትንቢቱ በክርስቶስ መፈጸሙን እያመለከተን፤ በፍቅር አብረን እርስ በርሳችን ተያይዘን አንድ ሕንጻ፣ አካል ወይም ሕብረት፣ ወይም ጉባኤ መሆናችንን በመግለጽ፤ እኛም ይህን እውነት በመረዳት መኖር እንዳለብን ያመለክተናል፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን የተመሰለችው በሕንጻ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በሕንጻ የተመሰለችበት ምክንያት የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና ማደሪያ ስለሆነች እንደሆነ፤ የሚከተሉት ጥቅሶች ውስጥ ማየት እንችላለን፡፡ ‹‹የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን?… የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፣ ያውም እናንተ ናችሁ›› (1ቆሮ. 3፡16-17፣ 6፡19-20)

ቤተ ክርስቲያን በሕንጻ መመሰሏ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከመሆኗ ባሻገር መጠለያ፣ ከለላና ዋስትና እንዳለን ታሳያለች፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቤተ መቅደሱ እኛው ስለሆንን በቅድስና መኖርና መመላለስ እንዳለብን ያሳስበናል፡፡ አለበለዚያ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር በነበረበት ጊዜ ቤተ መቅደሱን ከነጋዴዎችና ከወንበዴዎች እንዳጸዳው ሁሉ ዛሬም ቤተ መቅደሱን ከኃጢአት ሁሉ ያጸዳል (ሉቃ. 19፡45)፡፡

ሙሽራ፡- ቤተ ክርስቲያን በሦስተኛ ደረጃ ተመስላ የምናገኛት በሙሽራ ነው፤ ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክቱ ስለ ባልና ሚስት ግንኙነት በገለጸበት ጊዜ የክርስቶስንና የቤተ ክርስቲያንን ግንኙነት የሚገልጥ ታላቅ ሚስጥር እንደሆነ አስተምሮአል (ኤፌ. 5፡32)፡፡ መጥምቁ ዮሐንስም ‹‹ሙሽራይቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው፣ ቆሞ የሚሰማው ሚዜው ግን በሙሽራው ድምፅ እጅግ ደስ ይለዋል፡፡ እንግዲህ ይህ ደስታዬ ተፈጸመ›› በማለት ራሱን እንደ ሚዜ፤ ክርስቶስን ለቤተ ክርስቲያን ሙሽራዋ፣ እርሷን ደግሞ ሙሽሪቱ አድርጎ አቅርቦአል (ዮሐ. 3፡29)፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስም በራዕዩ ‹‹ሃሌሉያ ሁሉን የሚገዛ ጌታ አምላካችን ነግሦአልና፡፡ የበጉ ሠርግ ስለ ደረሰ ሚስቱም ራስዋን ስላዘጋጀች ደስ ይበለን ሐሤትም እናድርግ ክብርንም ለእርሱ እናቅርብ፡፡ ያጌጠና የተጣራ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ እንድትጐናጸፍ ተሰጥቶአታል›› በማለት ሙሽራው ክርስቶስ ሙሽሪት ቤተ ክርስቲያን መሆንዋን ያመለክታል (ራዕ.19፡7-8)፡፡ ስለዚህ ዛሬ ቤተ ክርስቲያን ሙሽሪት ሆና ራስዋን እያዘጋጀች ትገኛለች፤ አንድ ቀን ጌታ ወደ ምድር በሚመጣበት ጊዜ የሠርጉ ሥነ-ሥርዓት በአየር ላይ ይሆናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ማለት እኛ ስለሆንን፤ ጌታን በንጽህና ለመቀበል በቃሉ እንደሚገባ እየኖርን ራሳችንን በቅድስና በመጠበቅ ልንዘጋጅ ይገባናል፡፡

መንጋ፡- ቤተ ክርስቲያን በአካል፣ በሕንጻና በሙሽራ ብቻ ሳይሆን በመንጋም ተመስላ እናገኛታለን፤ ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ ስለ እረኝነቱ ሲያስተምር፣ ‹‹መልካም እረኛ እኔ ነኝ፡፡ መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል፡፡ …አብም እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል ነፍሴንም ስለ በጎች አኖራለሁ፡፡ ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ድምፄንም ይሰማሉ አንድም መንጋ ይሆናሉ፣ እረኛውም አንድ›› በማለት እረኛው እርሱ ሲሆን፤ ቤተ ክርስቲያን ከአይሁድና ከአሕዛብ የሆነች አንድ መንጋ (አካል) ብቻ እንዳለችው ገልጾአል (ዮሐ. 10፡1-18)፡፡ ስለ መልካም እረኛና በጎች በአዲስ ኪዳን ብቻ ሳይሆን፤ በብሉይ ኪዳንም እግዚአብሔር እረኛቸው ሲሆን፤ እስራኤልም መንጋ ተብላ ትጠራ ነበር (ኢሳ. 40፡11)፡፡ ዳዊትም ‹‹እግዚአብሔር እረኛዬ ነው የሚያሳጣኝ የለም›› በማለት በ(መዝ.23፡1) ላይ መንጋነቱን በመቀበል ዘምሮለታል፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስም በመልእክቱ ሽማግሌዎችን ለመምከር በሚጽፍበትም ጊዜ ‹‹በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሐርን መንጋ ጠብቁ … ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ›› በማለት መንጋው እንክብካቤ እንደ ሚያስፈልገውና ኃላፊነታቸውን በሚገባ መወጣት እንዳለባቸው ያሳስባቸዋል (1ጴጥ. 5፡2)፡፡ በአዲስ ኪዳንም ያንኑ ሥዕል በማምጣት ኢየሱስ እረኛ ሲሆን፣ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ መንጋ ተብላ ተጠርታለች፡፡

ወገንና በአንደኛ ጴጥሮስ 2፡9-10 ላይ ‹‹እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትነግሩ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤ እናንተ ቀድሞ ወገን አልነበራችሁም አሁን ግን የእግዚአብሔር ወገን ናችሁ፤ እናንተ ምሕረት ያገኛችሁ አልነበራችሁም አሁን ግን ምሕረትን አግኝታችኋል›› በማለት በትውልድ፣ በካህናት፣ በሕዝብና በወገን መስሏት እንገኛለን፡፡ በብሉይ ኪዳን የነበሩ ካህናት ሕዝቡን ይዘው ወደ እግዚአብሔር እንደሚቀርቡት፤ ቤተ ክርስቲያንም እንደ ካህናት ሕዝቡን ይዛ ትቀርባለች (ዘፀ. 19፡5-6)፡፡ ቤተ ክርስቲያን ወገን በሚል ምሳሌ አስቀምጦአታል፡፡ እያንዳንዱ ምዕመን የካህን ወገን እንደሆነ ቃሉ ይናገራል፡፡ ስለዚህ እያንዳንዳችን ለጠፉት ሰዎች የመጸለይ የመማለድ ትልቅ ኃላፊነት አለብን፡፡ በቤተ ክርስቲያን ምንም አገልግሎት አልተሰጠንም የምንል ብንኖር፤ ከጌታ የተሰጠን ትልቅ ኃላፊነት እንዳለን ማወቅና መረዳት ያስፈልገናል፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *