የጸጋ ስጦታዎችን ማደሉ፡- በድነታችን ሁሉም የሥላሴ አካላት ድርሻ እንደ ነበራቸው ሁሉ፣ የጸጋ ስጦታዎችንም በማደል በኩል ሁሉም የሥላሴ አካል እያንዳንዳቸው ድርሻ እንዳላቸው ከቃሉ ማየት እንችላለን፡፡     

የጸጋ ስጦታዎች ምንጫቸው፣ ያዕቆብ በመልእክቱ እንደሚናገረው እግዚአብሔር አብ እንደሆነ ያመለክተናል፤ ‹‹በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፣ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ›› (ያዕ. 1፡17) በማለት ይገልጠዋል፡፡ ጳውሎስም  ደግሞ በኤፌሶን መልእክቱ  ‹‹… እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን›› (ኤፌ. 4፡7) በማለት የአብ ስጦታዎች በክርስቶስ በኩል እንደሚሰጡ ያስተምረናል፡፡ በቆሮንቶስ መልእክቱም ‹‹ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል›› (1ቆሮ. 12፡11) በማለት ሲናገር የምናየው፤ መንፈስ ቅዱስ እነዚህን የጸጋ ስጦታዎች በሥላሴ በዕቅዳቸውና በሥራ ድርሻቸው መሠረት ማደሉን ያሳየናል፡፡ በአንደኛ ጴጥሮስም ምዕራፍ 4፡10 ላይም ‹‹… እያንዳንዳችሁ የጸጋን ስጦታ እንደ ተቀበላችሁ መጠን በዚያው ጸጋ እርስ በርሳችሁ አገልግሉ›› በማለት መንፈስ ቅዱስ በእኛ ሕይወት ውሰጥ የጸጋ ስጦታዎችን በማደል ድርሻውን እንደሚወጣ፤ እኛም በተቀበልነው ማገልገል እንደሚጠበቅብን ያመለክታል፡፡

መንፈስ ቅዱስ የሚሰጣቸው የጸጋ ስጦታዎች ስንት ናቸው? በመጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጸጋ ስጦታዎች ተጠቅሶና ተዘርዝሮ የምናገኘው በአራት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ብቻ ነው፡፡ ሁሉንም የጻፈው ጳውሎስ ሲሆን፤ በተለያየ ምክንያት ለተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ነው ልኮት የምናገኘው፡፡ በሮሜ ምዕ. 12፡4-7፣ በ1ቆሮ. 12፡4-11, 27-30፣    በኤፌ. 4፡11 ላይና ጠቅለል ባለ መልኩ በ 1ጴጥ. 4፡10-11 ላይ ሲሆን በቁጥር 18 ያህል ይሆናሉ፡፡ በተለያየ ቤተ እምነት የተለያየ አከፋፈል፣ አቀማመጥና አጠቃቀም አላቸው፡፡ የተለያየ አቀማመጥና አጠቃቀም ቢኖራቸውም፣ እነዚህ ስጦታዎች የተሰጡት ለአንድ ዓላማ አካሉን ለማነፅ፣ ምዕመናንን ለአገልግሎት ለማዘጋጀትና እግዚአብሔርን በነገር ሁሉ ለማክበር እንደ ሆነ ቃሉ ይናገራል፡፡

በመጀመሪያ ይህን ጥናት ስንጀምር፤ በመግቢያችን ላይ እንደ ተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በየጊዜው ለሚፈጠርና ለሚነሣ፤ ለአንድ ችግር መፍትሔ ለመስጠት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ጳውሎስም ስለ ጸጋ ስጦታዎች ልጻፍ ብሎ ሳይሆን የጻፈው፣ በተለያዩ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ ለመስጠት ብሎ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በዚህም ምክንያት ስጦታዎቹ በተነገሩበት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የነበረውን ችግር በቅድሚያ ማየቱ ጠቃሚ ይሆናል፡፡

መንፈስ ቅዱስ ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ስጦታዎችን እንደ ሰጣቸው የታወቀ ነው፤ ነገር ግን በተለያየ ችግር  ምክንያት በአገባቡ አልተጠቀሙበትም፡፡ በዚህ ምክንያት ሐዋርያው ጳውሎስ ችግራቸውን አስወግደው፤ በአገባቡ መጠቀም እንዲችሉ ሰፊ ትምህርት ሰጣቸው፡፡ ችግሮቹም የሚከተሉት ሲሆኑ፣ ለሁሉም ችግሮች መፍትሔ አስቀምጦአል፡፡ ችግሮቹም መከፋፈል ምዕራፍ 1፣ ቅንዓትና ክርክር ምዕ. 3፣ ዝሙት ምዕ. 5፣ እርስ በእርስ መካሰስ  ምዕ. 6፣ የጋብቻ ችግር ምዕ. 7፣ ለጣዖት የተሰዋ መብላት ምዕ. 8-10፣ ስለ ጸጉር መሸፈንና የጌታን ራት ማቃለል     ምዕ. 11፣ በጸጋ ስጦታዎች መበላለጥ በተለይም በልሳንና በትንቢት መካከል ምዕ. 12-14 ባሉት ክፍሎች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ 

በአጥቢያቱ ከነበሩት ዋና ችግሮች ከላይ እንዳየነው፣ አንዱ በልሳንና በትንቢት መካከል የተፈጠረው ችግር ከረር ያለ እንደ ነበር ማየት እንችላለን፤ በዚህ ምክንያት ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ችግር ለመፍታት/ለማቃለል ለሌሎች ስጦታዎች ያልሰጠውን ለሁለቱ ስጦታዎች ብቻ በሦስት ምዕራፍ ሠፊ የመፍትሔ ትምህርቶች ሰጥቶ እናገኛለን፡፡ የጸጋ ስጦታዎች ለቤተ ክርስቲያን የተሰጡት አካሉን ለማነፅ ሲሆን፤ በአጥቢያቱ ግን አካሉን ለማፍረስ የደረሱ ሆነው ነበር፡፡

በዚህም ምክንያት ጳውሎስ ስለ ልሳንና ትንቢት መፍትሔ ለመስጠት ፈልጎ ሳለ ሌሎችንም ዘጠኙን የጸጋ ስጦታዎች ጨምሮ በመዘርዘር ሁሉም ስጦታዎች አካሉን ለማነፅ እንደተሰጡ ያስተምራል፡፡ ‹‹የጸጋም ስጦታ ልዩ ልዩ ነው፣ መንፈስ ግን አንድ ነው፣ አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው፣ ጌታም አንድ ነው፣ አሠራርም ልዩ ልዩ ነው ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው›› (12፡4-6) በማለት ስጦታዎች ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት አካሉን ለማነፅ ለጥቅም እንደ ተሰጡ ያሳስባቸዋል፡፡

ስጦታዎቹም ከቁጥር 7-11 ባለው ክፍል ዘጠኙ ስጦታዎች ተዘርዝረው ይገኛሉ፤ ጥበብንና እውቀትን መናገር፣ እምነት፣ መፈወስ፣ ተአምራት ማድረግ፣ ትንቢት መናገር፣ መናፍስትን መለየት፣ ልሳን መናገርና መተርጐም ናቸው፡፡ በስጦታዎች መካከል መበላለጥም እንደሌለ በአካል መመሳሰል ከትንሹ ጀምሮ እስከ ትልቁ ድረስ ያሉትን በአካሉ ላይ ያሉት ብልቶች ሁሉ ለአካሉ ጥቅም እንደተሰጡ ያሳያል፡፡ እንዲሁ በመንፈስ ቅዱስ የተሰጡ የጸጋ ስጦታዎች ሁሉ ለአካሉ ጠቃሚዎች እንደሆኑ በሚገባቸው መንገድ በማሳየት፣ የአካሉ ብልቶች የሆኑ አማኞች ሁሉ ለአካሉ መታነፅ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክቱ ያስተምራቸዋል፡፡

በመጨረሻ ‹‹አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው›› (1ቆሮ. 12፡5) ባለው መሠረት ከቁጥር 27-30 ባለው ክፍል ላይ  ሐሳቡን ከሌሎች ስጦታዎች ጋር በመደባለቅና እንደገና በማንሳት፤ አማኝ ሁሉ አንድ ዓይነት ስጦታ እንዳልተሰጣቸውና ስጦታዎቹ ለአካሉ አስፈላጊዎች እንደሆኑ በማሳየት የላቀውን የጸጋ ስጦታ እንዲፈልጉ፣ ያሳስባቸዋል፡፡ ከሁሉ የሚበልጠውን ፍቅር አሳይቶአቸው፤ እንደገና ወደ ዋናው ችግራችው ወደ ልሳንና ትንቢት (ምዕ. 14) ላይ በመመለስ ሠፊ ትንተናና ገለፃ በመስጠት፤ እነዚህን ስጦታዎች በሥነ-ሥርዓትና አግባብ ባለው መንገድ መጠቀም እንዳለባቸው በማሳሰብ ትምህርቱን ይጨርሳል፡፡      

በሁለተኛ ደረጃ የምንመለከተው ጳውሎስ ለኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን የጻፈውን መልእክት ይሆናል፤ የኤፌሶን አጥቢያ እንደ ቆሮንቶስ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ችግር የበዛባት አልነበረችም፡፡ ጳውሎስ መልእክቱን ሲጽፍ ስለ እግዚአብሔር የማዳን ሥራ ከምዕራፍ 1-3 ያሳያቸውና በዚህ በእግዚአብሔር የማዳን ሥራ ውስጥ እንዴት እንደሚገባ መመላለስ እንዳለባቸው ከምዕራፍ 4-6 ባለው ክፍል እያስተማራቸው እያለ፤ በመሐል ስለ ጸጋ ስጦታዎች አንስቶ፤ ስለ ዓላማቸው፣ እንዴትና ለምን እንደ ተሰጡ በመግለጥ አስተምሮአቸዋል፡፡

በዚህ በኤፌሶን ምዕራፍ 4፡11 ላይ የተጠቀሱት የጸጋ ስጦታዎች ስንመለከት፤ ከሌሎች የጸጋ ስጦታዎች የሚበልጡ ሳይሆኑ፤ ከስጦታዎቹ ልዩ ባሕርያትና ተፈጥሮ የተነሳ፤ የሙሉ ጊዜ አገልጋይነትን የሚፈልጉና ቤተ ክርስቲያንን የመምራትና አቅጣጫ የማስያዝ ተፈጥሮ ያላቸው የጸጋ ስጦታዎች ናቸው፡፡ ስጦታዎች ሁሉ አካሉን ለማነፅ የተሰጡ እንደሆነ ይታወቃል፤ እነዚህ የጸጋ ስጦታዎች ግን አካሉን ለማነፅ/ለማሳደግ ስጦታ የተሰጣቸውን ቅዱሳንን ለአገልግሎት ማዘጋጀት እንዲችሉ የአገልግሎት ስጦታ የተሰጣቸው፤ ሐዋርያት፣ ነብያት፣ ወንጌል-ሰባኪዎች፣ እረኞችና አስተማሪዎች እንደ ሆኑ ያሳያቸዋል፡፡ 

ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት አካሉን ለማነፅ የተሰጡት የጸጋ ስጦታዎች አንዱ ከአንዱ ሳይበላለጡ፤ ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽና ለማሳደግ የተሰጡ እንጂ እንደ ልዩ የአገልግሎት ቢሮ የሚታዩ ስጦታዎች አይደሉም ብዬ አምናለሁ፡፡ እነዚህን  የጸጋ ስጦታዎች ከመንፈስ ቅዱስ የተቀበሉ፤ አገልጋዮች ምዕመናኑን በግልና በኅብረት ሕይወታቸው ወደ ክርስቶስ ሙላት እንዲያድጉ መርዳት ዋና ኃላፊነታቸው እንደሆነ ተገልጾአል፡፡

አብያተ ክርስቲያናት እንደየ ቤተ እምነቱ ሙሉ ጊዜአቸውን ሰጥተውና ሳይሰጡ የሚያገለግሉ ብላ በመክፈልና የተለያየ ማዕረግ ሰጥታ፤ እንደ አስፈላጊነቱ በማሰማራት እንዲያገለግሉ ያደርጋሉ፡፡ መቼም ቢሆን የጸጋ ስጦታ የተሰጣቸው ምዕመናን ሁሉ ሙሉ ጊዜአቸውን ሰጥተው ማገልገል አይጠበቅባቸውም፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳንን ለአገልግሎት ለማዘጋጀት እንዲችሉ ጸጋው ያላቸውን አገልጋዮች፣ እንዳስፈላጊነቱ ዕውቅና በመስጠትና በመሾም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ልታሰማራ ትችላለች፡፡

ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ 12፡3-8 ባለው ክፍል ውስጥ ስለ ጸጋ ስጦታዎች ያስተማረውን ስንመለከት፤ በአይሁድና በአህዛብ መካከል የነበረውን መናናቅ፣ ወይም አይሁድ አህዛብን የበታች አድርገው መመልከታቸውን እንዲያስተካክሉ፤ ‹‹እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፣ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ›› በማለት ያሳስባቸዋል፡፡ ባስተላለፈው ትምህርት ውስጥ፣ ስለ ጸጋ ስጦታዎች አንስቶ መናገር ሲጀምር እንዲህ ይላል ‹‹በአንድ አካል ብዙ ብልቶች እንዳሉን የብልቶቹም ሁሉ ሥራ አንድ እንዳይደለ፣ እንዲሁ ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፣ እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን›› ቁ.4-5 በማለት አይሁድና አህዛብ አንድ አካልና እርስ በርሳቸው  ብልቶች መሆናቸውን በማሳየት፣ አካሉን ለማነፅ የተለያየ የጸጋ ስጦታዎች ለሁሉም እንደተሰጣቸው ያሳያቸዋል፡፡ 

ዛሬም  ሁላችንም ለአካሉ አስፈላጊዎች ስለሆንን፣ ኢየሱስን ክርስቶስን ስንቀበልና የሕይወታችን ጌታ ስናደርገው፤ ቢያንስ አንድ የጸጋ ስጦታ ለእያንዳንዳችን አካሉን ለማነፅ ይሰጠናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን እነዚህን በመንፈስ ቅዱስ የጸጋ ስጦታዎች የተሰጣቸውን ሁሉ ሳታበላልጥ በእኩል ደረጃ ለአካሉ ጥቅም እንደሚሰጡ አምና መቀበል አለባት፡፡ በዚህ እውነት ተመሥርተን ሁላችንም በተሰጠን ጸጋ እንደሚገባ ብናገለግል ፍሬአማና ቤተ ክርስቲያናችንንም ማሳደግ እንችላለን ብዬ አምናለሁ፡፡

በአንዳንድ ቤተ እምነቶች እነዚህን የጸጋ ስጦታዎች ያላቸውን አማኞች ከፍተኛ ሥፍራ ቢሮ (office) ሰጥተዋቸው እናገኛለን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን የቢሮ አገልግሎት እንደሆኑ የሚያስተምረን የሽማግልናንና የድቁናን አገልግሎት ብቻ እንደሆነ በአዲስ ኪዳን በብዙ ቦታ ማስረጃ እናገኛለን፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ሲጽፍ እንዲህ ይላል ‹‹በፊልጵስዩስ ለሚኖሩ ከኤጲስ ቆጶሳት (ሽማግሌዎች) እና ከዲያቆናት ጋር በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት ቅዱሳን ሁሉ›› በማለት ሦስት አካላትን ጠቅሶ እናገኛለን (ፊል.1፡1)፡፡ እንዲሁም ለጢሞቴዎስ በላከው መልእክት በአንደኛ ጢሞቴዎስ 3፡1-13 ባለው ክፍል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሽማግሌዎችና ዲያቆናትን ጠቅሶ ለአገልግሎት ለመሾም የሚያበቃቸውን መለኪያ ያስቀምጣል፡፡

ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደምናገኘው የአስተዳደር ዓይነቶች ሦስት እንደሆኑ ወደፊት ቤተ ክርስቲያን በሚለው ርዕስ ሥር በስፋት እንመለከተዋለን፡፡ የግለ ሰብ የበላይነትን፣ የቡድን የበላይነትንና የምዕመናንን የበላይነት በማጉላት ሁሉም እንደሚያመቻቸው በማድረግ ሲጠቀሙበት እንመለከታለን፡፡ ይህም ጳውሎስና ጴጥሮስ በመልእክታቸው እንዳስተማሩትና በተሐድሶ ዘመን የነበረቸው ቤተ ክርስቲያን እንዳስተማረችው፤ ቤተ ክርስቲያን የሚኖራት ቢሮዎች ሁለት ሲሆኑ፤ ሌሎቹ የተለያየ የጸጋ ስጦታ ያላቸው የሙሉ ጊዜ (ተከፋይ) አገልጋዮችና ተከፋይ ያልሆኑ አገልጋዮች (ምዕመናን) ከእነርሱ ሥር ሆነው አብረው የሚያገለግሉ፣ አካሉን የሚያንፁና የሚያሳድጉ መሆን እንደሚገባቸው መጽሐፍ ቅዱስ በስፋት ያስተምረናል፡፡

በሮሜ ምዕራፍ 12፡7 ላይ ‹‹አገልግሎት ቢሆን በአገልግሎታችን እንትጋ›› እንዲሁም በ1ኛ. ጴጥሮስ ምዕራፍ 4፡10-11 ላይ ‹‹እያንዳንዳችሁ የጸጋን ስጦታ እንደ ተቀበላችሁ መጠን በዚያው ጸጋ እርስ በርሳችሁ አገልግሉ፤ ማንም ሰው የሚናገር ቢሆን፣ እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር የሚያገለግልም ቢሆን፣ እግዚአብሔር በሚሰጠኝ ኃይል ነው ብሎ ያገልግል…›› በማለት ምዕመናን ሁሉ ያላቸውን የጸጋ ስጦታ በመጠቀም አካሉን ማነፅ እንዳለባቸው ያሳያል፡፡

            በእነዚህ በሁለቱ ጥቅሶች ውስጥ ‹‹አገልግሎት›› በሚለው ቃል ውስጥ ብዙ በዝርዝር ያልተጠቀሱ ስጦታዎች በጥቅል ተቀምጠው ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ጥቂቶቹን ብጠቅስ የጸሎት፣ የዝማሬ፣ የሙዚቃ፣ የማስመለክ፣ የመጎብኘት፣ እንግዳ የመቀበል፣ የእስር ቤት፣ የሆስፒታል፣ ተጧሪዎችን መርዳት… የመሳሰሉትን አገልግሎቶች ሁሉ ሊይዝ ይችላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ለእነዚህ አገልግሎቶች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች አሏቸው፡፡ በእነዚህ ጥቅሶች መሠረት አቅሙ ያላት ቤተ ክርስቲያን ይህን ማድረጓ ችግር የለውም፡፡ ማንኛውም ነገር በቤተ ክርስቲያን ስምምነትና ዕውቅና ሲሆን ምንም ችግር አይፈጥርም፡፡

ቤተ ክርስቲያን ሳታውቅና ሹመት ሳትሰጠን በራሳችን ብቻ ብናደርገው ተገቢ አይሆንም፤ ምናልባትም ስለ መጨረሻው ጊዜ ጌታ በወንጌሉ ሲናገር፣ ‹‹በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፣ ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም፡፡ በዚያን ቀን ብዙዎች፣ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ፣ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፣ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፣ በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንምን? ይሉኛል፡፡ የዚያን ጊዜም፡- ከቶ አላወቅኋችሁም እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ›› (ማቴ. 7፡21-23) የሚለው ቃል የራሳችንን ፈቃድ እያደረግን በመመላለስ ስንገኝ፤ ቃሉ በእኛ ላይ እንዳይፈጸምብን መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡

የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ መስጠቱ፡- መንፈስ ቅዱስ የጸጋ ስጦታዎችን መስጠት ብቻ ሳይሆን፤ በገላትያ መጽሐፍ ላይ የምናገኛቸውን ‹‹ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት›› (ገላ. 5፡22) የተባሉትን የመንፈስ ፍሬ ይሰጣል፡፡ በጸጋ ስጦታዎችና በመንፈስ ፍሬ መካከል ልዩነቱ ምንድን ነው ብለን ብንጠይቅ፤ የምናገኘው መልስ፣ የጸጋ ስጦታዎች አካሉን ለማነፅና ለማገልገል እንድንችል ከእግዚአብሔር አብ፣ በክርስቶስ በኩል፣ በመንፈስ ቅዱስ አዳይነት (አካፋይነት) የሚሰጡ ሲሆኑ፤ የመንፈስ ፍሬ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ መለኮታዊ ባሕርይ እንድናፈራ/ እንዲኖረን የሚሰጡን ከባሕርያችን ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡

ጌታን ኢየሱስን ወደ ሕይወታችን አዳኛችን እንዲሆን ከጋበዝንበትና ከወሰንበት ቀንና ሰዓት ጀምሮ ዳግም ልደትን አግኝተን አዲስ ፍጥረት ከሆንበት ቀን አንስቶ፤ መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን የሚሠራው ከቅድስና ጋር ተያይዞ ባሕርያችንን መቅረጽ ነው፡፡ በመለኮታዊ ባሕርያችን የልጁን መልክ እየመሰልን እንድንመጣና (2ጴጥ. 1፡4፣         ሮሜ. 8፡29) በቅድስና ሕይወታችን እያደግን እንድንሄድ በማድረግ ፍሬያማዎች ያደርገናል፡፡ ስለዚህ በስጦታዎቹና በፍሬው መካከል ልዩነት ያለ ቢሆንም፣ የሚነጣጠሉ አይደሉም፡፡ ከእኛ ያለ መረዳት ካልሆነ በስተቀር ሁለቱንም የሚሠራው መንፈስ ቅዱስ ስለሆነ ልንነጣጥላቸው አንችልም፣ ተገቢም አይሆንም፡፡ 

መንፈስ ቅዱስ ከዚህ በላይ ከጠቀስናቸው ታላላቅ ሥራዎች በተጨማሪ ብዙ ሥራዎችን በሕይወታችን እንደሚሠራ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል፤ ኃይል ይሰጣል (የሐዋ. 1፡8)፣  ይመራል (ዮሐ. 16፡13)፣ ያስተምራል    (ዮሐ. 14፡26)፣ ያነጻል (የሐዋ. 15፡8-9)፣ ይማልዳል (ሮሜ. 8፡26-27)፣ ለአገልግሎት ይጠራል (የሐዋ. 13፡2)

ከዚህ በላይ ያየናቸው ሐሳቦች አማኞች የመንፈስ ቅዱስን ሙላት በመቀበል ራዕይ በማግኘት፣ ምሪት በማግኘት፣ በቅድስና በመኖር፣ ምዕመናን ጌታ የሚደሰትበትና የሚከብርበትን ሕይወት ሲኖሩ፤ የቤተ ክርስቲያን ሕይወት እያደገና ባላመኑ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት እያገኘት ስትመጣ፤ ለብዙ ነፍሳት ምሳሌ በመሆን ለመዳናቸው ምክንያት ትሆናለች፡፡ በዓለም ዘንድ ትከበራለች፣ በመንግሥት ዘንድ ሥፍራ ይኖራታል፣ እግዚአብሔርም ይከብርባታል፡፡ ስለዚህ የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ለአማኞችም ለቤተ ክርስቲያንም እጅግ አስፈላጊና ጠቃሚ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ የሥላሴ አካል ሆኖና ዕቅድ ፈጻሚ ሆኖ የሚሠራቸውን የሥራ ድርሻ፣ ከዚህ በላይ ባለው መልኩ ተመልክተናል፡፡ ስለ መንፈስ ቅዱስ ያልተመለሱ ጥያቄዎች ቢኖሩን፤ በተጨማሪ ሌሎች መጽሐፍትን ማንበብ ወይም በኢሜል አድራሻዬ ጥያቄአችሁን ብትልኩልኝ፤ ጌታ በረዳኝ መጠን መልስ ልሰጣችሁ እችላለሁ፡፡ ስለ መንፈስ ቅዱስ የምናጠናውን ጥናት ጨርሰን፤ በሚቀጥለው ጥናታችን ስለ ድነት/ደህንነት እንጀምራለን፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *