የመንፈስ ቅዱስ አሠራር ዳሰሳ፡- ከላይ  እንደ ተመለከትነው የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትና ሙላት ለሐዋርያት ለአገልግሎታቸው አስፈላጊዎች እንደ ነበሩ፤ ለእኛም እጅግ አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ የመንፈስ ቅዱስ አሠራር በተለያየ መልክና መንገድ ስለሚገለጥ አዳዲስ አማኞች በመንፈስ ቅዱስ በሚሞሉበት ጊዜ አንዳንድ ያልተለመዱ ነገሮች ሊያሳዩና ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ በአንድ ጊዜ ሲጠመቁና ሲሞሉ የተፈጸሙትን ድርጊቶች ስንመለከት፤ ድንገት እንደሚነጥቅ አውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መጣ፤ እንደ እሳት የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ መንፈስ ቅዱስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር ይላል፡፡ ድምፅ፣ ልሳንና ንግግሮች ተከስተዋል፡፡

ከላይ ከሰማይ የመጣው ድምፅ፣  ወደ ልሳኖች ሲለወጥ፣ ልሳኖቹ ወደ ንግግር ተለውጠዋል፡፡ ዓላማው የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ መግለጥ ነበር፤  በኢሳይያስ ትንቢት መሠረት ምዕራፍ 28፡9-12 ፍርድን፣ በሐዋርያት ሥራ 1፡5 ትንቢት መሠረት ተስፋን ያመለክታል፡፡ በመጀመሪያ የሐዋርያት በልሳኖች መናገር በኢሳይያስ ትንቢት መሠረት እግዚአብሔር ድንቅ ሥራውን ለሕዝቡ በልዩ ልሳን (ቋንቋ) የተናገረበት ዕለት ነበር፡፡ እግዚአብሔር በኢሳይያስ በኩል የተናገረውን፣ የእስራኤል ሕዝብ ባለመስማታቸው ወደ ባቢሎን ምርኮ ለ70 ዓመት እንደ ተወሰዱ፤ በበዓለ ኀምሳ ቀንም በልሳኖች የተላለፈውን ድንቅ የእግዚአብሔርን ሥራ ስላልተቀበሉ በ70 ዓ.ም ለሮማውያን ታልፈው በመሰጠታቸው ፍርዱ ተፈጸመባቸው (ተልዕኮው የት ደርሷል ከሚለው መጽሐፌ ከገጽ 34-40 ያለውን ያንብቡ)፡፡

በሁለተኛ ሐዋርያት በልሳኖች መናገራቸው የተስፋውን መፈጸም ሲያመለክት፤ እንዲሁም ለማያምኑት ሰዎች  ምልክት ነበር፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ፣ ‹‹እንግዲያስ በልሳኖች መናገር ለማያምኑ ምልክት ነው እንጂ ለሚያምኑ አይደለም›› በሚለው መሠረት የሐዋርያት ሥራ 2፡4 ልሳን ምልክትነቱ ለነጴጥሮስ ሳይሆን በዙሪያቸው ለተሰበሰቡት ለማያምኑት ሰዎች ነበር፡፡ ምክንያቱም ‹‹እኛም እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋችንን እንዴት እንሰማን? (የሐዋ. 2፡8) ብለው ከተናገሩት ምስክርነታቸውን እናገኛለን፡፡ በዚህ መሠረት 2፡4 ልሳን ለማያምኑ ምልክት እንዲሆን የተሰጠ ሲሆን፤ የቆሮንቶስ 12፡7-11 ላይ ያለው ለሚያምኑ የሚሰጥ ስጦታ ነው፤ ስጦታ ከሆነ ደግሞ ለሁሉም ሰው አይሰጥም፤ ምክንያቱም ቃሉ እንደሚናገረው ‹‹…መንፈስ ቅዱስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል›› ብሎ ስለሚናገር፡፡ ስለዚህ ስጦታ ሆኖ ያልተሰጣችሁ የሰውን ኮፒ በማድረግ አትጠቀሙ፡፡ የተሰጣችሁ ደግሞ ጌታን አመስግኑ፡፡

ከሐዋርያት በመቀጠል መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ የሰማርያ ሰዎች ናቸው፤ የሰማርያ አማኞች ወንጌል በተሰበከላቸው ጊዜ አምነው በውኃ እንደ ተጠመቁ ቃሉ ቢናገርም፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን አልተቀበሉም ነበር፡፡ ‹‹በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያት የሰማርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ተቀበሉ ሰምተው ጴጥሮስንና ዮሐንስን ሰደዱላቸው፡፡ እነርሱም በወረዱ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ይቀበሉ ዘንድ ጸለዩላቸው በጌታ በኢየሱስ ስም ብቻ ተጠምቀው ነበር እንጂ ከእነርሱ በአንዱ ላይ ስንኳ ገና አልወረደም ነበርና፡፡ በዚያን ጊዜ እጃቸውን ጫኑባቸው መንፈስ ቅዱስንም ተቀበሉ›› (የሐዋ. 8፤14-17)፡፡ የሰማርያ ሰዎች መንፈስ ቅዱስን ሲቀበሉ፣ በሐዋርያት ጊዜ ያልነበረ እጅ መጫን ታይቶአል (የሐዋርያት እጅ መጫን መስማማትንም ያመለክታል)፤ ከሰማይ ድምፅና ልሳንም አልነበረም፡፡ ነገር ግን በእጅ መጫኑ ጊዜ ጥምቀትም ሙላትም ተከናውኗል ብዬ እምናለሁ፡፡ በዚህ ጊዜ የአይሁድና የአሕዛብ ድብልቅ የሆኑት ሕዝቦች በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ማግኘታቸው የተረጋገጠበት አንድ ትልቅ ሂደት ተከናውኖአል፡፡

በሦስተኛ ወደ ቆርኔሌዎስ መለወጥ ስንመጣ እስከ አሁን ድረስ ካየናቸው ለየት ያለ ነው፤ ጴጥሮስ ቃሉን እየተናገረ እያለ ‹‹ቃሉን  በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ፡፡ ከጴጥሮስም ጋር የመጡት ሁሉ ከተገረዙት ወገን የሆኑ ምዕመናን በአሕዛብ ላይ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ስለ ፈሰሰ ተገረሙ በልሳኖች ሲናገሩ እግዚአብሔርንም ሲያከብሩ ሰምተዋቸዋልና፡፡ በመቀጠልም ‹‹በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ፡- እነዚህ እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እንዳይጠመቁ ውኃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማን ነው? አለ:: በኢየሱስ ክርስቶስ ስምም ይጠመቁ ዘንድ አዘዛቸው›› (የሐዋ. 10፡44-48) ይላል፡፡ በዚህ ሥፍራ ድምፅ የለም፣ እጅ መጫን የለም፣ ጸሎትም የለም፣ ትንቢትም የለም፤ ልሳን ብቻ ተገልጦ እናገኛለን፡፡ ሌላው ድንቅ ነገር አሕዛብ (ውሾች) የሚሏቸው መንፈስ ቅዱስ ሲወርድባቸው በማየታቸው የተገረዙት አይሁድ አማኞች እጅግ ተደንቀዋል፡፡ የሰማርያ ሰዎች መንፈስ ቅዱስን ከመቀበላቸው በፊት በውኃ ተጠመቁ፤ ቆርኔሌዎስ የውኃ ጥምቀትን የወሰደው ከመንፈስ ቅዱስ መውረድ በኋላ ነበር፡፡

 በአራተኛ የምንመለከተው የጳውሎስን ሕይወት መለወጥ ነው፤ የጳውሎስ መለወጥ ከቆርኔሌዎስ መለወጥ በኋላ የተከናወነ በመሆኑ ነው፡፡ በድርጊት የቆርኔሌዎስ ታሪክ ሲቀድም፣ በአጻጻፍ ደግሞ የጳውሎስ ታሪክ ይቀድማል፡፡ ስለዚህ እኔ ያስቀመጥኩት በቅደም ተከተሉ ነው፡፡ ወደ ጳወሎስ የመጣው ድምፅ ለምን ታሳድደኛለህ የሚል ሲሆን፤ ከሦስት ቀን በኋላ ‹‹ሐናንያም ሄዶ ወደ ቤቱ ገባ እጁንም ጭኖበት፡- ወንድሜ ሳውል ሆይ ፣ ጌታ እርሱም በመጣህበት መንገድ የታየህ ኢየሱስ ነው፣ ደግሞ ታይ ዘንድና መንፈስ ቅዱስ ይሞላብህ ዘንድ ላከኝ›› (የሐዋ. 9፡17) ብሎ በጸለየለት ጊዜ ከዓይኑ ላይ እንደ ቅርፊት ያለ ነገር ከወደቀለት በኋላ፤ ተነስቶም በውኃ እንደ ተጠመቀ ቃሉ ይናገራል፡፡  በዚህ ጊዜ እጅ መጫን ሲኖር፣ ትንቢትና ልሳን እንዳለ አናይም፤ ነገር ግን ሐዋርያው ጳውሎስ በአንደኛ ቆሮንቶስ መልእክቱ 14፡18 ላይ ‹‹ከሁላችሁ ይልቅ በልሳኖች እናገራለሁና›› በማለት የልሳን ስጦታ እንዳለው ያመለክታል፡፡

በመጨረሻ ወደ ኤፌሶን አማኞች የለውጥ ሁኔታ ስንመጣ፣ መጥምቁ ዮሐንስ ስለ ክርስቶስ የሰበከውን ስብከት ሰምተው፤ በዮሐንስ ጥምቀት የተጠመቁ እንደሆነ ከቃሉ መረዳት እንችላለን፡፡ ጳውሎስ መጥቶ ‹‹ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀበላችሁን?›› ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ የሰጡት መልስ ‹‹አልተቀበልንም መንፈስ ቅዱስ እንዳለ ስንኳ አልሰማንም›› የሚል ነበር፡፡ ‹‹እንኪያ በምን ተጠመቃችሁ? ብሎ እንደገና ሲጠይቃቸው፤ እነርሱም በዮሐንስ ጥምቀት ብለው መለሱለት፡፡ ጳወሎስም ‹‹ዮሐንስስ ከእርሱ በኋላ በሚመጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ያምኑ ዘንድ ለሕዝብ እየተናገረ በንስሐ ጥምቀት አጠመቀ አላቸው፡፡ ይህንም በሰሙ ጊዜ በጌታ በኢየሱስ ስም ተጠመቁ፤ ጳውሎስም እጁን በጫነባቸው ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው በልሳኖችም ተናገሩ፣ ትንቢትም ተናገሩ›› (የሐዋ. 19፡1-7) በማለት አስቀምጦልናል፡፡ በዚህ ጊዜ ከላይ የመጣ ድምፅ የለም፣ በእጅ መጫን፣ ልሳንና ትንቢት ተሰጥተዋቸዋል፤ መንፈስ ቅዱስን ከመቀበላቸው በፊትም የውኃ ጥምቀት መውሰዳቸው እንደቀደመ እንመለከታለን፡፡

በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ያየነው፣ መንፈስ ቅዱስ ለተለያዩ ሰዎች፣ በተለያየ ጊዜና በተለያየ ሁኔታ ከድነት ጋር፣ ከድነት በኋላ ሰዎች የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ እንዳገኙ ቃሉ ያሳየናል፡፡ ተጠቅሰው በምናገኛቸው በአምስቱም ሥፍራዎች ያሉ ጥቅሶች የቤተ ክርስቲያን ቋሚ መመሪያ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ በተለይም ጸሐፊው ሉቃስ የተጠቀመባቸውን ቃላትንም ልብ ማለት ይጠይቃል፤ ትጠመቃላችሁ 1፡5፣ ሞላባቸው 2፡4፣ 4፡31፣ 9፡17፣ 7፡55፣ አፈሰሰው 2፡33፣ 10፡45፣ ተቀበሉ 8፡17፣ 10፡47 ወረደ 10፡44፣ 11፡15 ብሎ የተጠቀመባቸው ቃላቶች ግራ ያጋባሉ፡፡ ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ በሰዎች ሕይወት ለሚሠራው ሥራ ፎርሙላ ወይም ቋሚ የሆነ መመሪያ ልናወጣለት በፍጹም አንችልም፡፡

እነዚህን ሁሉ ሂደቶች ጠቅለል አድርገን ስንመለከታቸው ዋናዎቹ ሁለት ነገሮች ናቸው፤ የመጀመሪያው በጌታ  ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎች ሲያምኑ፤ በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅን፣ ዳግም መወለድን፣ የእግዚአብሔር ልጅ፣ አዲስ ፍጥረትና የክርስቶስ አካል መሆንን ያገኛሉ፡፡ ሁለተኛው ዋና ነገር በአገልግሎታቸው ለጌታ ኢየሱስ ምስክሮች ለመሆን የመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንደሚያስፈልጋቸው ማወቅ ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን መዳን እንዴት እንደሚከናወን አንድ ላይ ጠቅለል አድርገን ስናስቀምጠው፤ ክርስቶስ ራሱ በዮሐንስ ወንጌል ላይ ‹‹የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፣ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን›› (ዮሐ. 14፡23) ብሎ በተናገረው መሠረት፤ እንዲሁም በመልእክቱ 1ዮሐ. 3፡24 እና 4፡13 ላይ የእግዚአብሔርን መኖር የምናውቀው እርሱ በሰጠን በመንፈሱ አማካኝነት እንደሆነ ይናገራል፡፡ ስለዚህ የአብ፣ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ በአንድ ጊዜ በሰው ውስጥ በመግባታቸው ድነት ይከናወናል፤ አለበለዚያ ድነት ተከናወነ ማለት በፍጹም አይቻልም፡፡

የሐዋርያትን ድነት ከእኛ ለየት የሚያደርጋቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ሐዋርያት በብሉይና በአዲስ ኪዳን መሸጋገሪያ ላይ ነበሩ፤ ደግሞም በዕብራውያን 9፡22 ላይ ቃሉ እንደሚናገረው ‹‹ደም ሳይፈስ ስርየት የለም›› ስለሚል፣ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ ሳይወርድ፣ ምንም እንኳን ጌታ ሐዋርያቱን ለአገልግሎት ቢመርጣቸውም ድነታቸው የተከናወነው በዮሐንስ ወንጌል 20፡22 ላይ እንደሆነ አምናለሁ፤ (ምንም እንኳን ለቅምሻ የተሰጣቸው ቢሆንም)፤ በበዓለ ኀምሳ ቀን በሙላት የክርስቶስ አካል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን በተመሠረተችበት ቀን በሙላት ተከናወነላቸው፡፡

ስለዚህ ይህን እውነተኛ የሆነውን የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትና ሙላት ምዕመናኖቻችን በትክክል ተረድተው፤ እንዲለማመዱት የአጥቢያ አገልጋዮች የማስተማርና የመጸለይ ኃላፊነት አለብን፡፡ እኛም ምዕመናን ዕለት በዕለት እንደ ቃሉ በመጠማትና በመሻት የመንፈስ ቅዱስን ልምምድ እንደ ቃሉ የመለማመድ ኃላፊነት ይኖርብናል፡፡ እንደ ስሞን የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ በገንዘብ የመግዛትና የመሸጥ፤ ወይም ሌላውን የመኰረጅ ጉዳይ በሌለበት ንጹሕ በሆነ ልብና መንገድ ራሳችንን ሆነን መለማመድ እንዲሆንልን ጌታ ይርዳን፡፡

የመንፈስ ቅዱስን ሙላት ለማግኘት ሰዎች ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ አንዳንድ እንደ ቃሉ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎች ሊያሳዩ ይችላሉ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ሙላት ጊዜ አማኞች እስኪገባቸው ድረስ የተለያዩ ከፍተኛ ድምጽ ማውጣት፣ መሬት መውደቅና መንከባለል፣ ወንበር መደብደብ፣ ግርግዳ መደብደብ የመሳሰሉት ሁኔታዎች ሊታዩና ሊከሰቱ፣ እንዲሁም ሰዎችን ኮፒ በማድረግ ስሕተቶችም ሊፈጸሙ  ይችላሉ፡፡ ስለዚህ እውነተኛ ቃሉን ማስተማር ዋጋ ቢያሰከፍልም፣ ቀስ በቀስ አላስፈላጊ የሆኑ ነገሮች እየተስተካከሉ እንዲመጡ ያደርጋል፡፡ 

በመንፈስ ቅዱስ ስም የሚሠሩ እንደ ቃሉ ባልሆኑ በውሸት መገለጥ አማካኝነት ትዳር ይፈርሳል፣ ትዳር ይመሠረታል፣ ከሥራ መውጣት፣ ወደ ዝሙት የሚያመራና እነዚህን የመሳሰሉ ስሕተቶችም እንዳሉ የታወቀ ነው፡፡ ስለዚህ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት እንዲኖር፣ መሪዎችና አስተማሪዎች ቃሉን የማስተማር ትልቅ ኃላፊነት አለብን፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይህ ችግር እንዳለ ካወቅን ምዕመኖቿችንን ማስተማርና ወደ ትክክለኛው ልምምድና አሠራር ምዕመናን እንዲመጡ የማድረግ  ኃላፊነታችን የበዛ ነው፡፡ ለዚህም ጌታ ይርዳን፣ ጸጋውንም ያብዛልን፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *