በባለፈው ጥናታችን መንፈስ ቅዱስ በብሉይ ኪዳንና በአዲስ ኪዳን በክርስቶስና በአማኝ ሕይወት የሠራውን እየተመለከትን መቆየታችን የሚታወስ ነው፡፡ ጥናታችንን ያቆምነው መንፈስ ቅዱስ በአማኝ ሕይወት ስለሚሠረው ሥራ ስንመለከት፤ ስለ ክርስቶስ ምስክርነት እንደሚሰጥ፣ ዳግም ልደት እንደሚሰጥ፣ የእግዚአብሔር ልጅና አዲስ ፍጥረት እንደሚያደርግ ተመልክተን ነበር፡፡ በመቀጠልም በጣም አስቸጋሪና አከራካሪ ወደ ሆነው፤ በመንፈስ ቅዱስ አማኙን እንደሚያጠምቅ፤ በብሉይ ኪዳን የተነገሩትን ትንቢቶች ተመልክተን ነበር፤ ጥናታችንን ያቆምነው፡፡ 

በመጨረሻም ለእናንተ የምትሠሩት የቤት ሥራ ጥያቄ መሰጠቱም የሚታወስ ነው፤ ጥያቄውም ትንቢቱ ተፈጽሞአል  ወይም አልተፈጸመም ካላችሁ ማስረጃችሁን ይዛችሁ ቅረቡ የሚል ነበር፡፡ አሁን ጥናታችንን ለመቀጠል ምን መልስ ይዛችሁ ቀርባችኋል፡፡ መቼም መልሳችሁ አልተፈጸመም እንደማትሉ እርግጠኛ ነኝ፤ ከስምንት መቶ ዓመት ጀምሮ እስከ  አምስት መቶ ዓመተ ዓለም ድረስ በተለያዩ ነቢያት በኢዩኤል፣ በኢሳይያስና በኤርምያስ  የተነገሩት ትንቢቶች በበዓለ ኀምሳ ቀን መፈጸሙን ጴጥሮስ በሐዋርያት ሥራ 2፡33 ላይ ‹‹በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን የተስፋ ቃል ከአብ ተቀብሎ ይህን እናንተ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው›› የሚለውን ሁላችንም የምንቀበለው ሀቅ ነው፡፡

በብሉይ ኪዳን ብቻ ሳይሆን፤ በአዲስ ኪዳንም የተነገሩትንም ትንቢቶች ስንመለከት፤ በአዲስ ኪዳን ስለ መንፈስ ቅዱስ መሰጠት የተናገረው ጌታ ራሱ ነው፡፡ በአገልግሎቱ መጀመሪያና ከትንሣኤው በኋላም እንደ ገና ተናግሮታል፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ በወንጌሉ እንደ ዘገበው፤ ‹‹ከበዓሉም በታላቁ በኋለኛው ቀን ኢየሱስ ቆሞ፡- ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ፡፡ በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፣ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል ብሎ ጮኸ፡፡ ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ፤ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ መንፈስ ገና አልወረደም ነበርና›› በማለት ትንቢቱን ዘግቦት እናገኛለን (ዮሐ. 7፡37-39)፡፡ ከትንሣኤው በኋላ በ20፡22 ላይ ‹‹መንፈስ ቅዱስ ተቀበሉ›› በሐዋ. 1፡5 ላይ ‹‹… ከእኔ የሰማችሁትን አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቁ፤ ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና፣ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ›› የሚለውን ከስምንት መቶ ዓመት በፊት ተነግሮ የነበረው ትንቢት በቅርብ ቀን (40 ቀን) እንደሚፈጸም፤ ትንቢቱን በመከለስ እንደ ተናገረው ሉቃስ ዘግቦታል፡፡

መንፈስ ቅዱስ በብሉይ ኪዳን ከሚሠራበት አሠራር ለየት ባለ መንገድ ሊሠራ እንደሚችል ከተነገሩት ትንቢቶች መካከል በተለይም ስለ ማጥመቁ የሩቅ ትንቢቶችን (ከ800-500 ዓመተ ዓለም) እና የቅርብ ከሆኑት (የ40 ቀን) ውስጥ ጥቂቶቹን ጠቅሰን ተመልክተናል፡፡ አሁን ደግሞ በመካከለኛ ርቀት ከተናገሩት ነቢያት አንዱ የሆነው መጥምቁ ዮሐንስ፣ ኢየሱስ አገልግሎት ከመጀመሩ በፊት፣ ከሦስት ዓመት በፊት ተልኮ የተናገረ አገልጋይ ነበር፡፡ ለክርስቶስ አገልግሎት መንገድ ጠራጊ ሆኖ ያገለገለና ስለ መንፈስ ቅዱስ መምጣት፤ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 3፡16 እንደምናገኘው ትንቢቱን እንዲህ በማለት አስቀምጦታል ‹‹እኔስ በውኃ አጠምቃችኋለሁ ነገር ግን የጫማውን ጠፍር መፍታት ከማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ ይመጣል እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል››፡፡ ይህ የመንፈስ ቅዱስ የማጥመቅ ትንቢት የተነገረላቸው ሕዝቡ  በመጥምቁ ዮሐንስ የንስሐ ጥምቀት ሊጠመቁ በተሰበሰቡበት ጊዜ ላይ ነበር፡፡

ቀደም ብዬ ይህ ትንቢት ስለ መፈጸሙ መልስ እንዲኖረን በጠየቅሁት መሠረት፤ ሁላችንም ተፈጽሟል ብለን  እንደምንመልስ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ይህን ጥያቄ ከመለስን በኋላ የሚቀጥለው ጥያቄ እንዲህ የሚል ነው፡፡ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2፡4 ላይ ያለው ድርጊት ጥምቀት ነው? ወይስ ሙላት? ወይስ ሁለቱንም? ሉቃስን ብትጠይቁት ምን መልስ ይሰጣችሁ ይሆን? ይህ ጥያቄ በየዘመናቱ አጠያያቂና አነጋጋሪ ቢሆንም ከአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ አንስቶ ይበልጥ ብዙዎችን ግራ የሚያጋባ ሆኖአል፡፡

እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በብሉይ ኪዳን ከሚሠራበት አሠራር፣ በአዲስ ኪዳን በተለየ መንገድ ለመሥራት እንደሚመጣ በተለያዩ ነቢያት ትንቢት መነገሩን ተመልክተናል፡፡ ትንቢቱም በተነገረው መሠረት በበዓለ ኀምሳ ቀን፤ በጸሎት ይተጉ በነበሩ አንድ መቶ ሃያ ሰዎች ላይ ወርዷል፡፡ ጴጥሮስ በሩቅ፣ በመካከለኛና በቅርብ የተነገሩትን የትንቢቶች ፍጻሜ የተናገረው እርሱ ነው፤ የተናገረውም በበዓለ ኀምሳ ቀን ለተሰበሰበው ሕዝብ ነበር እንዲህ በማለት ‹‹…የመንፈስ ቅዱስን የተስፋ ቃል ከአብ ተቀብሎ ይህን እናንተ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው››      (የሐዋ. 2፡33)፡፡ እንደገናም ጴጥሮስ የቆርኔሌዎስን ቤት አገልግሎ ወደ ኢየሩሳሌም በተመለስ ጊዜ፤ ለገጠመው ክርክር መልስ ሲሰጥ ‹‹ለመናገር በጀመርሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ለእኛ ደግሞ በመጀመሪያ እንደ ወረደ ለእነርሱ ወረደላቸው›› (11፡15) በማለት ስለ መንፈስ ቅዱስ መምጣት የተነገረው ትንቢት በእውነት መፈጸሙን ይናገራል፡፡

ስለዘህ በነቢዩ ኢዩኤል፣ በመጥምቁ ዮሐንስና በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በራሱ የተነገረው ‹‹ትጠመቃላችሁ›› የሚለው ትንቢት ተፈጽሞአል፤ በትንቢቱ መፈጸም ምንም ጥያቄ አይኖረንም፡፡ ጥያቄአችን የሐዋርያት ሥራ 2፤4 ጥምቀት ነው? ወይስ ሙላት? ወይስ ሁለቱንም? የሚለው ነው፡፡ ትንቢቱ ከተፈጸመ ጥምቀት ነው፤ ሉቃስ ግን የተጠቀመበት ቃል ሞላባቸው የሚለውን ነው፤ ጴጥሮስ ስለ ፍጻሜው ሲናገር ኢዩኤል የተጠቀመበትን ቃል በመጠቀም ‹‹አፈሰሰው›› ብሎ ነው የተጠቀመ፡፡    

የመንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ መፍሰስና መውረድ፤ በብሉይ ኪዳን ጊዜ እግዚአብሔር በሲና ተራራ ለሙሴና ለሕዝቡ በመገለጥ ግርማውን፣ ታላቅነቱን፣ ቅድስናውን ካሳየበት ታላቅ ድርጊት ጋር ይመሳሰላል፡፡ በአዲስ ኪዳንም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በመገለጥ ተራራ ላይ በታላቅ ክብርና ብርሃን በማንፀባረቅ ከሙሴና ከኤልያስ ጋር አብሮ ተገልጦ እንደነበረና የአባቱን ምስክርነት እንዳገኘ መጽሐፍ ቅዱስ በሉቃስ 9፡28-36 ያስረዳናል፡፡ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ በተነገረለት ትንቢት መሠረት በበዓለ ኀምሳ ቀን በታላቅ ክብር ተገለጠ፡፡ ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ እንደሚመጣ የተነገረለት መንፈስ ቅዱስ በበዓለ ኀምሳ ቀን በደቀ መዛሙርት ሕይወት ውስጥ አስደናቂ በሆነ ኃይል በማያውቁት ልሳን የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ እንዲናገሩ አድርጎአቸዋል፡፡

የመንፈስ ቅዱስ ክብር የተገለጠባቸውን መንገዶች ስንመለከት ከአብም ከወልድም በተለየ ሁኔታ ነበር፤

            1ኛ. እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መምጣቱ፤

2ኛ. እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች መታየታቸው፤

3ኛ. መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣችው በሌላ ልሳኖች መናገራቸውን፤

 ልዩ ያደርገዋል (የሐዋ. 2፡1-4)፡፡ መንፈስ ቅዱስ በተነገረለት ትንቢት መሠረት ሲመጣ የመለኮታዊነቱ ክብሩ (Gloryfication) የተገለጠበት መንገድ አስደናቂ ነበር፡፡ ነፋሱና እሳቱ ከውጭ የታዩ ምልክቶች ሲሆኑ፤ ልሳኑ ከውስጥ የወጣ ውስጣዊ ምልክት ነበር፡፡ በበዓለ ኀምሳ ቀን በማያውቁት ቋንቋ እንዲናገሩ ማድረጉ ለማያምኑት በበዓሉ ላይ ለተሰበሰቡት ሰዎች ምልክት ሲሆን፤ ቋንቋውን ላልተማሩት ሐዋርያት ደግሞ ተዓምር ነበር፡፡  በእርግጥ መንፈስ ቅዱስ በዚህ መልክ በመምጣቱ ትንቢቱ ተፈጽሞአል፡፡

ከበዓለ ኀምሳ ቀን በኋላ ያለውን የመንፈስ ቅዱስ አሠራር ስንመለከት፤ በተለያየ ቦታ ቢሰጥም ነፋሱና እሳቱ አልተደገሙም፡፡ በሰማርያ (ግማሽ አይሁድና አሕዛብ ለሆኑ) በቆርኔሌዎስ ቤት ለነበሩትና ፣ በኤፌሶንም ለነበሩት (አሕዛቦች) አውሎ ነፋሱና እሳቱ ሲቀሩ፤ የልሳኑ ልምምድ በሁሉም ዘንድ ባይሆንም ታይቷል፡፡ ይህ ድርጊት ለሳምራውያንና ለአሕዛቦች በመሰጠት ከአይሁዶች ጋር በክርስቶስ አንድ አካል መሆናቸውን እግዚአብሔር ራሱ ሳያዳላ መንፈሱን በማደል መስክሮአል፡፡

ጴጥሮስም በአሕዛቦች (በቆርኔሌዎስ ቤት) ላይ ስለ ወረደው መንፈስ ቅዱስ ሲናገር እንዲህ ይላል፣ ‹‹ለመናገርም በጀመርኩ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ለእኛ ደግሞ በመጀመሪያ እንደ ወረደ ለእነርሱ ወረደላቸው፡፡ ዮሐንስ በውኃ አጠመቀ እናንተ ግን በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ ያለውም የጌታ ቃል ትዝ አለኝ›› (የሐዋ. ሥራ 11፡15) በማለት ሲናገር የምንረዳው ሦስት ነገሮችን ነው፡፡ የመጀመሪያው ለአሥር ዓመት ያህል እንደ በዓለ ኀምሳው ዓይነት አወራረድ/አመጣጥ መጥቶም አያውቅም ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ከላይ አስቀድሜ እንዳልኩት ከነፋሱና ከእሳቱ በስተቀር፤ በልሳኑ ተመሳሳይ ነበር ማለት ነው፡፡ በምዕራፍ 10፡44 ላይ ‹‹ጴጥሮስ ይህን ነገር ገና ሲናገር ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ፡፡ ከጴጥሮስም ጋር የመጡት ሁሉ ከተገረዙት ወገን የሆኑ ምዕመናን በአሕዛብ ላይ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ስለ ፈሰሰ ተገረሙ በልሳኖችም ሲናገሩ እግዚአብሔርን ሲያከብሩ ሰምተዋቸዋልና›› በማለት ይናገራል፡፡

 ሦስተኛው ጴጥሮስ ለአሕዛቦች ስለ መሰጠቱ ሲናገር ‹‹እንግዲህ እግዚአብሔር በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላመነው ለእኛ ደግሞ እንደ ሰጠን ያን ስጦታ ለእነርሱ ከሰጠ እግዚአብሔርን ለመከልከል እችል ዘንድ እኔ ማን ነበርኩ?›› (የሐዋ. 11፡17) በማለት መከልከል አለመቻሉን፤ ከአይሁዶች ለደረሰበት ክስና ተቃውሞ መልስ በመስጠት፤ እግዚአብሔር ሳያዳላ ለአሕዛቦችም እንደ አይሁዶች የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ እንደ ሰጣቸው ያስረዳል፡፡

ሐዋርያትና በይሁዳም የነበሩት ወንድሞችም የጴጥሮስን ሪፖርት ከሰሙ በኋላ ስለ አሕዛብ መንፈስ ቅዱስን መቀበል እንዲህ ብለው ተቀበሉት፤ ‹‹ይህን በሰሙ ጊዜም ዝም አሉና፣ እንኪያስ እግዚአብሔር ለአሕዛብ ደግሞ ለሕይወት የሚሆን ንስሐን ሰጣቸው እያሉ እግዚአብሔርን አከበሩ›› (የሐዋ. 11፡18)፡፡ ከዚህ የምንረዳው እውነት ቢኖር፤ አሕዛብ ጳውሎስ እንደሚናገረው ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቁ ነበሩ፤ የሚለውን ሀሳባቸውን መለወጣቸውን ያመለክተናል፡፡ ጳውሎስም ስለ አሕዛብ መዳን እንዲህ ይላል፤ ‹‹ስለዚህ እናንተ አስቀድሞ በሥጋ አሕዛብ የነበራችሁ በሥጋ በእጅ የተገረዙ በተባሉት ያልተገረዙ የተባላችሁ ይህን አስቡ፤ በዚያ ዘመን  ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ሆናችሁ በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ፡፡ አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል›› (ኤፌ. 2፡12-13)፡፡

ስለዚህ እግዚአብሔር በነቢዩ ኤርምያስ፣ እነሆ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን  የምገባበት ወራት ይመጣል›› (ኤር. 31፡31)፤ እንዲሁም በነቢዩ ሕዝቅኤል ‹‹… መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ…›› ‹‹ሕዝ. 36፡26-27) ብለው በተናገሩት መሠረት ከእስራኤል ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የገባበት ቀን፣ መንፈሱንም በውስጣቸው ያስቀመጠበት ቀን በዓለ ኀምሳ ሲሆን፤ ከቃል ኪዳኑ ርቀው የነበሩትንም አሕዛቦች በዚህ መልክ መንፈስ ቅዱሱን በመስጠት የቃል ኪዳኑ አካል አደረጋቸው፡፡ በሐዋርያት ሥራ 10፡44 እና 11፡15 ላይ ስለ አሕዛብ መዳን ጴጥሮስ ‹‹ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ›› ‹‹ለመናገርም በጀመርሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ለእኛ ደግሞ በመጀመሪያ እንደ ወረደ ለእነርሱ ወረደላቸው›› በማለት ሲናገር፤ ጳውሎስም ስለ አሕዛብ መዳንና ቃል ኪዳን ውስጥ መግባት እንዲህ ይላል ‹‹ይህም አሕዛብ አብረው እንዲወርሱ፣ በአንድ አካልም አብረው እንዲሆኑ፣ በወንጌልም መሰበክ በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነ የተስፋ ቃል አብረው እንዲካፈሉ›› ነው በማለት የተገለጠለትን ምሥጢር ያስቀምጣል፡፡ (ኤፌ.3፡4-5) እግዚአብሔር ሳያዳላ የሕዝቦች አምላክ መሆኑን አረጋግጦአል፡፡

አሁን ቀደም ብለን ወደ ጠየቅነው ጥያቄ እንደገና እንመለስና ስለ መንፈስ ቅዱስ ጥምቀት የምናጠናውን  ጥናታችንን እንጨርሳለን፤ የሐዋርያት ሥራ 2፡4 ጥምቀት? ወይስ ሙላት? ወይስ ሁለቱንም? ለሚለው ጥያቄ የሰጣችሁትን ምላሽ ታስታውሳላችሁ? በብሉይ ኪዳን በተለያዩ ነቢያቶች የተነገረው ትንቢት በበዓለ ኀምሳ ቀን ፍጻሜ ማግኘቱን ማንም ሰው ቢሆን የሚክድ የለም፡፡ ችግሩ ያለው ትርጓሜና ቃላት አጠቃቀም ላይ ነው፡፡ ትንቢቱ ሲነገር የሚለው ‹‹ትጠመቃላችሁ›› ሲሆን፣ ፍጻሜው ግን ‹‹ሞላባቸው›› ይላል፤ ይህ ድርጊት የመጀመሪያ በመሆኑ የሐዋ. 2፡4 ጥምቀትም ሙላትም በመሆን ‹‹ሁለቱንም›› ያመለክታል፡፡

መልሱ ጥምቀትም ሙላትም ነው ካልን በጥምቀትና በሙላት መካከል ምንም ልዩነት የለም እንዴ? የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀሬ ነው፡፡ ጥምቀትን ሐዋርያው ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ መልእክቱ ምዕራፍ 12፡12 ላይ ‹‹… እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናል›› በሚለው መሠረት ወደ ክርስቶስ አካልነት የምንገባበት ድርጊት/ሁኔታ ነው፤ ሐዋርያው ዮሐንስ ደግሞ በወንጌሉ ምዕራፍ 3፡5 ላይ ‹‹… ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም›› በሚለው መሠረት ዳግም ልደት (ልጅነት) የምናገኝበት ሲሆን፣ ሐዋርያው ጳውሎስም ‹‹አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደ ገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና›› (ሮሜ. 8፡15) በማለት በመንፈሱ የምንመራ ሁሉ የልጅነትን መንፈስ እንደ ተቀበልን ሲገልጥ፤ በኤፌሶን መልእክቱ 1፡13 ላይ ደግሞ ‹‹… በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ›› እንዲሁም በቲቶ መልእክቱ ላይ ‹‹… በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን›› በሚለው መሠረት አዲስ ፍጥረት ለመሆናችንና ለደህንነታችን ዋስትና በመንፈስ ቅዱስ መታተማችንን ይገልጣል፡፡ በመንፈስ መጠመቅ፣ ዳግም ልደት ማገኘት፣ አንድ አካል መሆን፣ አዲስ ፍጥረት መሆን የአንድ ጊዜ ድርጊት እንደሆኑ የእግዚአብሔር ቃል ያስተምረናል፡፡

እነዚህን ትምህርቶች ወደ ድነት ትምህርት ስንመጣ እንደገና እንመለከታቸዋለን፤ ስለ መንፈስ ቅዱስ ሙላት በሚቀጥለው ጥናታችን እንመለከተዋለን፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትና ሙላት ምን አንድነትና ልዩነት አላቸው በእኔ ሕይወት ተፈጽመዋል ወይስ አልተፈጸሙም ብላችሁ ራሳችሁን እየጠየቃችሁና መልስ እየሰጣችሁ ቆዩ፡፡ ጌታ ሁላችንንም በሰላም ይጠብቀን፣ ያቆየን፣ ያገናኘን ተባረኩ፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *