ቀን  ሳለ ሩጥ

ከእንቅልፌ ስነቃ፣ ጠዋት ተነስቼ፣

ምን እንደምሠራ፣  ግራ ተጋብቼ፡፡

የሚያስፈልገኝን ላሳካ ብሞክር፣

ትርጉም አልሰጥ አለኝ የሕይወቴ ምሥጢር፡፡

ልብላ ልጠጣ፣ ወይስ ቤቴን ላፅዳ፣

ወይስ ልንጎራደድ፣ ከሳሎን ከጓዳ፣

ቲቪዬ ላይ ላፍጥጥ፣ ዓይኔ እስከሚጐዳ፣

ዞር ዞር ልበል፣ ልሂድ ልሰናዳ፡፡

ምን ላርግበት፣ ቀኔን በምን ላሳልፈው፣

ብቸኝነት ገባኝ፣ ውስጤን አስኮረፈው፡፡

እያልኩኝ በሀሳቤ፣ የማደርገውን ሳጣ፣

ቀን ሳለ ሩጥ፣ የሚል ድምፅ ወደ እኔ መጣ፡፡

የማሳልፈውን ቀኔን ዞር ብዬ ሳይ፣

በራሴ አፈርኩኝ፣ ቀና ስል ወደ ላይ፡፡

አንዱም አይረባኝም፣ የቀኔ ሁኔታ፣

ለዓለም ስዳክር፣ ለሌለበት ደስታ፣

የዘላለም ቤቴን ሳልፈልግ ላንዳፍታ፡፡

በማይረባ ነገር ቁጭ ብዬ ሙሉ ቀን፣

አንድ እንኳን ሳላነብ፣ የእግዚአብሔር ቃሉን፣

ቀን ቀንን ሲተካ፣ ዕድሜዬ እየሮጠ፣

ሙሽራው ሲመጣ፣ ሰዓቱ አመለጠ፡፡

መንገድ እውነት ሕይወት ነውና ኢየሱሴ፣

ከእርሱ ጋር ልጣበቅ፣ ልውጣና ከሱሴ፡፡

ስለዚህ ወገኖቼ፣ ዛሬ ነው ሰዓቱ፣

ቀን ሳለ ሩጡና ግቡ ወደ እውነቱ፡፡

ምክንያት መደርደር፣ ሰበብ ማብዛት ትተን፣

ወደ እሱ እንመለስ፣ በእግሩ ሥር አንሁን፡፡

በተሰበረ ልብ በእውነተኛ መንፈስ፣

በንስሓ ታጥበን፣ ቃሉንም በመልበስ፡፡

በጸሎት ስንተጋ፣ ከእርሱ ስንጠጋ፣

ጌታ ይሰማናል፣ መንፈሱ አለ እኛ ጋ፡፡

ሰላማችን በዝቶ፣ ሥጋት ይሸሽና፣

ከአፋችን ይወጣል፣ የበዛ ምስጋና፡፡

ጤናችን ተመልሶ፣ ምድራችን ተፈውሶ፣

ዕንባችን ታብሶልን፣ ሥጋታችን ቀንሶ፡፡

ሌሊቱም ይነጋል፣ እንደመሸ አይቀርም፣

እግዚአብሔር ይራራል፣ ፍቅሩ ሁሌ አይጐልም፡፡

ከሱ ለመታረቅ ከሱ ለመስማማት፣

ቀን ሳለ መሮጥ ነው፣ ከእቅፉ ለመግባት።

       ከየትም ወርቅ እጅጉ

       ከብስራተ ወንጌል ገነት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *