ውድ የተልዕኮ ኦን ላይን አገልግሎት ተከታታዮች ላለፉት ሦስት ዓመታት ተልዕኮ teleko.org በሚለው ድህረ ገጽ እና የሶሻል ሚዲያ ቴሌግራምና ፌስ ቡክ ተከታታይ የሆኑ ጽሑፎችንና ትምህርቶችን ስናጋራ ቆይተናል፡፡ በዚህ ሳምንት የክርስቶስን ትንሣኤ ልናከብር እየተዘጋጀን ባለንበት ጊዜ ከቅዱስ ቃሉ አንድ ታሪክ እንድንካፈል ወደድን፡፡

        የምንካፈለው ጽሑፍ ርዕሱ ‹‹ታላቁ ጠላት›› የሚል ሲሆን፣ ታሪኩ የተመሠረተው በዮሐንስ ወንገል ምዕራፍ  11፡1-44 ላይ ‹‹መልካም ትንሣኤ›› የሆነላቸውን ቤተሰብ ታሪክ ይሆናል፡፡ የዓለም ሕዝብ ሁሉ የተለያየ የሚከተለው እምነት ቢኖረውም፣ ሰው ሁሉ  ሞት የተባለ ‹‹ታላቅ ጠላት›› አለበት፤ ይህን ሞት እግዚአብሔር በኃጢአት ምክንያት የወሰነው ቢሆንም፣ ሰው ራሱ ይህን ሥጋዊ ሞት፣ በሌላው እምነት ተከታይ ላይና በራሱ እምነት ተከታይ ላይ ጭምር ሳይቀር ሲያደርስ እናስተውላለን፡፡ ለምን ይሆን?

       በመጽሐፍ ቅዱሳችን ስንመለከት፣ የአልዓዛር እህቶች ማርታና ማርያም ወንድማቸው በታመመ ጊዜ ወደ ኢየሱስ መጥቶ እንዲፈውስላቸው መልእክተኛ ላኩ፡፡ ይሁንና ኢየሱስ አልዓዛር ከመሞቱ በፊት ሊደርስላቸው የወደደ አይመስልም፡፡ እንዲያውም በአልዓዛር ሞት ኢየሱስ ደስ ተሰኝቶአል (ቁ. 15)፡፡ ስለ ጠላው ወይም እነማርታን ለማሳዘን ፈልጐ አልነበርም፤ ሆኖም ዓላማ ነበረው፡፡ ይኸውም የደቀ መዛሙርቱ እምነት ይፀና ዘንድ ነበር፡፡

       አንዳንዴ እግዚአብሔር የተመኘነውን ነገር በፈለግነው ጊዜ አያደርግልንም፤ ስለዚህም፣ እግዚአብሔር ጸሎታችንን ያልሰማ በሚመስለን ወቅት እንኳ፣ ለእኛ የተሻለ ነገር እንዳለው መገንዘብ አለብን፡፡ ኢየሱስ ማርታና ማርያም ወዳሉበት መንደር ቢታንያ በደረሰ ጊዜ፡- ‹‹ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፣ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል›› (ቁ. 25) ሲል ታላቅ ምስጢር ገለጸላቸው፡፡ እርሱ ከሞት እንደሚነሣና ሌሎችንም ለማስነሣት ኃይል እንዳለው መናገሩ ነው፡፡ ይህንን እውነት ለማስረዳት አልዓዛር እስከሚሞት መዘግየትና ከመቃብር በማስነሣት ኃይሉን ማሳየት ነበረበት፡፡ በመጨረሻም ጌታ ወደ መቃብሩ በመሄድ ‹‹አልዓዛር ሆይ ተነሥ›› ሲል ‹‹ከታላቁ ጠላት›› ሞት አላቀቀው፡፡ ሞትም የእግዚአብሔርን ልጅ ታዞ አልዓዛርን ፈታው፤ ለማርታ፣ ማርያምና ለቤተሰቡ ሁሉ ታላቅ ደስታ ሆነላቸው፡፡

       ዛሬ እኛ ወንድሞቻችንን በወንጌል ‹‹ከታላቁ ጠላት›› ከዘላለም ሞት ማዳን ሲገባን፤ በተለያየ ምክንያት በሥጋ ሞት እንዲለዩን ምክንያት ስንሆን እናያለን፤ በዚህም ድርጊታችን በእግዚአብሔር ፊት እንደ ቃየል ተጠያቂዎች ነን፡፡ እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝን ማለት አንችልም፡፡ ‹‹ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ›› ያለንና ታላቁን የሰውን ልጅ ጠላት ያሸነፈን ጌታ እየተከተልን ለምን ከማይመጥነን ተግባር ሥር ወደቅን? ሁላችንም የምናምነውና የምንከተለው እምነት ኖሮን ሳለ፣ በዓለም ዙሪያ ይህ ሁሉ ደም መፋሰስ የሚፈጸመው ለምን ይሆን? ትንሣኤ መብልና መጠጥ ብቻ ከመሆኑ አልፎ፣ ከታላቁ ጠላት እጅ የምናመልጥበትና የምናስመልጥበት ጊዜ ይሁንልን፡፡ ይህ ታሪክ ምን ያስተምረናል? የተማርነውን በተግባር እንድንኖር እግዚአብሔር ይርዳን፡፡   

*መልካም ትንሣኤ*

2013 EC   


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *