ሐ) አስተምህሮተ መንፈስ ቅዱስ     

1) መንፈስ ቅዱስ ማነው?

መንፈስ ቅዱስ ማነው? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ መጽሐፍ ቅዱስን በሙሉ መዳሰስን ይጠይቃል፤ ቀደም ብለን በአስተምህሮተ እግዚአብሔር እና ክርስቶስ እንደ ተመለከትነው፤ አሁን ደግሞ ስለ አስተምህሮተ መንፈስ ቅዱስ ዘርዘር አድርገን እናጠናለን፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከሥላሴ አካላት አንዱና ሦስተኛው አካል እንደሆነ ስለ ሥላሴ ባደረግነው ጥናት መጠነኛ ዳሰሳ አድርገን ማየታችን ይታወሳል፡፡ በዳሰሳችን ፈጣሪ መሆኑን፣ ሁሉን ማድረግ መቻሉን፣ ሁሉን ማወቁን፣ በሁሉ ሥፍራ መገኘቱን፣ በሁሉ ነገርም ላይ ሥልጣን እንዳለው፣ ለሰው ልጆች ድነት ወኪል (Agent) ሆኖ ለማገልገል ወደ ምድር መምጣቱን ተመልክተናል፡፡ በዚህ ጥናታችን በመቀጠል የምንመለከተው፣ መንፈስ ቅዱስ በብሉይና አዲስ ኪዳን ያከናወናቸውን  ዋና ዋና ተግባራት ማየት ይሆናል፡፡

ቄስ ማንሰል ትምህርተ መንፈስ ቅዱስ በሚለው መጽሐፋቸው፣ እንዲህ አስቀምጠውታል፤ ‹‹አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በህላዌ፣ በባሕርይ፣ በመለኮትና በፈቃድ አንድ ሲሆኑ፣ በግብር (በሥራ) አንድ ዓላማ አላቸው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ አንድነት እያለ በአካል፣ በስምና በግብር ሦስትነት አላቸውና አንድነታቸውን ሳንረሳ፣ የመንፈስ ቅዱስን ሥራና የሥራ አፈጻጸም ለየብቻቸው ማጥናት ይገባናል›› (በገጽ 23 ላይ) ብለው በጻፉት መሠረት እኔም መንገዳቸውን ተከትዬ ለማቅረብ ጥረት አድርጌአለሁ፡፡  

1፡1 በብሉይ ኪዳን፡-  

መንፈስ ቅዱስ በፍጥረት ሥራ መካፈሉን፣ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ያመለክታሉ፡፡ የዘፍጥረት መጽሐፍ ገና ከመጀመሪያው በፍጥረት ሥራ መካፈሉን ያመለክተናል፡፡ ፍጥረትን መፍጠር የመጀመሪያው ትልቁ የሥራ ድርሻው እንደ ነበረ፣ ቀደም ብለን በአስተምህሮተ እግዚአብሔር ላይ ስለ አየን አሁን በስፋት አናየውም፡፡ ከፍጥረት ሥራ ቀጥለንም ስናይ ሰዎችን በመምራት፣ በመንዳት፣ ጥበብና ኃይል በመስጠት እንዲያገለግሉ እንደረዳቸው በቃሉ በስፋት እናያለን፡፡ በአዲስ ኪዳንም በኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎትና በአማኞችም ሕይወት የተለያዩ ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝም በጥናታችን ዘርዘር አድርገን እንመለከታለን፡፡

አብን መግለጡ፡- በብሉይ ኪዳን ስለ መንፈስ ቅዱስ ስለ ማንነቱና ሥራው በስፋት ተገልጦ እንደማይገኝ የታወቀ ቢሆንም፣ አብ ራሱን ለሰው ልጆች በሚገልጥበት ጊዜ ያለ መንፈስ ቅዱስ መሆን እንደማይችል ከቃሉ መረዳት እንችላለን፡፡ ስለ መገለጥ ስንመለከት ሳለ እግዚአብሔር ራሱን ለሰው ልጆች በገለጠ ጊዜ፣ ይህ መገለጥ የተከናወነው በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት እንደሆነ፣ ጳውሎስ በአዲስ ኪዳን ካስቀመጠው እውነት መረዳት ይቻላል፡፡                   ‹‹… ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር ለእግዚአብሔር ያለውን ማንም አያውቅም›› (1ቆሮ.2፡11)፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስም በመልእክቱ በምዕራፍ 3፡24 ‹‹ትእዛዙንም የሚጠብቅ በእርሱ ይኖራል፣ እርሱም ይኖርበታል፣ በዚህም በእኛ እንዲኖር ከሰጠን ከመንፈሱ እናውቃለን›› እንዲሁም በ4፡13 ላይ ‹‹ከመንፈሱ ስለ ሰጠን በእርሱ እንድንኖር እርሱም በእኛ እንዲኖር በዚህ እናውቃለን›› በማለት የእግዚአብሔርን መገለጥና በውስጣችን እንኳን መኖሩን ማወቅ የምንችለው፣ በተሰጠን በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት እንደሆነ ያስረዳል፡፡   

            አብን በመግለጥ የመንፈስ ቅዱስ ድርሻ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ አብን እንደ ገለጠ ዮሐንስ በወንጌሉ ‹‹መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው›› (ዮሐ.1፡18) በማለት ይገልጻል፡፡  አብ ራሱን ሲገልጽ ያለ ወልድና ያለ መንፈስ ቅዱስ ሊከናውን አይችልም፤ ምክንያቱም ሥላሴ ተነጣጥለው የሚሠሩት ሥራ ቢኖርም፣ በአብዛኛው ሥራቸው በአንድ ላይ በመሆኑ ነው፡፡ ዮሐንስ ይህን ከላይ በተመለከትነው ጥቅስ ውስጥ ከአማኞች ጋር አያይዞ በሚናገርበት ጊዜ፣ በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን አብን የመግለጥና የማስረዳት ኃላፊነትና ተግባር ከወልድ ጋር፣ መንፈስ ቅዱስም ድርሻ እንዳለው መረዳት እንደሚያስፈልግ ይናገራል፡፡ ምንም እንኳን አሠራሩ የተለያየ ቢሆንም ግልጠተ-እግዚአብሔርን (አብን መግለጥ) ማካሄድ ዋና ተግባሩ ነበር፡፡ በብሉይ ኪዳን ጊዜ እንደ አዲስ ኪዳኑ በግልጽ ባይታወቅም፤ በፍጥረት ሥራ መካፈሉ፣ ለሰማያት ውበት መስጠትና የአብን መገለጥ እውን በማድረግ የመሳሰሉትን ሥራዎች አከናውኖአል፡፡

በብሉይ ኪዳን ጊዜ እግዚአብሔር ግልጠተ-መለኮት በሚያደርግበት ጊዜ፤ መንፈስ ቅዱስ እስትንፋሰ-መለኮት እንዲከናውን ያደርጋል፡፡ ሰዎች እግዚአብሔር በሚገለጥላቸው ጊዜ አንዳንዶቹ በመገለጥ ደረጃ ብቻ  የሚወሰኑ ሆነው ይቀራሉ፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? ሰዎች የእግዚአብሔርን ማንነት ያዩበታል፣ ኃይል ይቀበሉበታል፣ ምስጢር ይገልጡበታል፣ ተስፋና ፍርድ ያስተላልፉበታል፣ ይቀቡበታል፡፡ ከእግዚአብሔር ዘንድ መገለጥ ሲመጣ በሰዎች ሕይወት አንድ ትልቅ ሥራ ይሠራል፡፡ በተለይም መገለጥ የመጣላቸው ሰዎች፣ በጽሑፍ በሚያሰፍሩበት ጊዜ ምሪትን መስጠት የመንፈስ ቅዱስ ሥራና ኃላፊነት እንደሆነ ከሚከተለው ጥቅስ ማየት እንችላለን፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስ በሁለተኛ መልእክቱ በምዕራፍ 1፡21 ላይ ‹‹ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ›› በማለት ስለ ብሉይና አዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ያስረዳል፡፡ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በምናጠናበት ጊዜ በስፋት መመልከታችን የሚታወስ ነው፡፡

ከዚህ በመቀጠል መንፈስ ቅዱስ በእስራኤላውያን ሕይወት የሠራቸውን ሥራዎች ዘርዘር አድረገን እንመለከታለን፡፡ በመጀመሪያ እግዚአብሔር ታቦትን ሲሰጣቸው የሚሠራውን ሰው በመንፈስ ቅዱስ እንደ ሞላው ሲናገር፤ ‹‹…ባስልኤልን በስሙ ጠርቼዋለሁ፡፡ በሥራ ሁሉ ብልሃት በጥበብም በማስተዋልም በእውቀትም የእግዚአብሔርን መንፈስ ሞላሁበት የጥበብን ሥራ ያስተውል ዘንድ›› ይላል (ዘፀ. 31፡1-4፤ 35፡31)፡፡ ሙሴ የእስራኤልን ማህበር ሊመራ የሚችል ሰው፣ እግዚአብሔር እንዲሾምለት በጠየቀ ጊዜ፤ ‹‹እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፡- መንፈስ ያለበትን ሰው የነዌን ልጅ ኢያሱን ወስደህ እጅህን በላዩ ጫንበት›› ብሎ አዘዘው (ዘኍ. 27፡18)፡፡ ‹‹ሙሴም እጆቹን ስለ ጫነበት የነዌ ልጅ ኢያሱ የጥበብን መንፈስ ተሞላ፤ የእስራኤልም ልጅች ታዘዙለት›› (ዘዳ. 34፡9)፡፡ ከዚህ ጥቅስ የምንመለከተው፣ መሪነት ያለ መንፈስ ቅዱስ ሙላት፣ እገዛና ድጋፍ እንደማይሆን ይህ ክፍል ያስተምረናል፡፡

እሥራኤላውያን በምድረ በዳ ሲጓዙ ቀን በደመና ዓምድ ሌሊት በእሳት ዓምድ በመሆን ምሪትና ጥበብ በመስጠት መንፈስ ቅዱስ እንደ መራቸው፤ ነህምያ በመጽሐፉ እንዲህ ይላል፣ ‹‹አንተ በምህረትህ ብዛት በምድረ በዳ አልተውሃቸውም በመንገድም ይመራቸው ዘንድ የደመና ዓምድ በቀን፣ የሚሄዱበትንም መንገድ ያበራላቸው ዘንድ የእሳት ዓምድ በሌሊት ከእነርሱ አልራቀም፡፡ ያስተምራቸውም ዘንድ መልካሙን መንፈስህን ሰጠሃቸው፣ መናህንም ከአፋቸው አልከለከልህም፣ ለጥማታቸውም ውኃ ሰጠሃቸው፡፡ አርባ ዓመትም በምድረ በዳ መገብሃቸው፣ ምንም አላጡም ልብሳቸውም አላረጀም፣ እግራቸውም አላበጠም››፡፡ መንፈስ ቅዱስ ምሪትና ጥበብ መስጠት ብቻ ሳይሆን፣ እሥራኤላውያን ሲያምፁ ጠላት ሆኖ ቅጣትን ያከናውን እንደነበረ  ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ ‹‹እነርሱ ግን ዐመፁ ቅዱስ መንፈሱንም አስመረሩ፣ ስለዚህ ተመልሶ ጠላት ሆናቸው፣ እርሱም ተዋጋቸው›› (ኢሳ. 63፡10-11)፡፡

እግዚአብሔር በምድረ በዳ በደመናና በእሳት ዓምድ መምራት ብቻ ሳይሆን፤ ለሥራው የፈለጋቸውን ሰዎች ነቢያትን፣ ካህናትን፣ ነገሥታትንና ለተለያዩ ግለ ሰቦች፣ መንፈስ ቅዱስ በጊዜዓዊነት እየወረደ ኃይል ይሞላባቸው ነበር፡፡ ጎቶንያልን በእስራኤል ላይ ፈራጅ እንዲሆን የእግዚአብሔር መንፈስ ወረደበት (መሳ. 3፡10)፤ ጌዴዎን እስራኤላውያንን ከምድያማውያንና አማሌቃውያንን እጅ ለማዳን የእግዚአብሔርን ኃይል ተቀበለ (መሳ. 6፡34)፤ ዮፍታሔም የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ላይ በመጣ ጊዜ አሞናውያንን በታላቅ አመታት መታቸው (መሳ. 11፡29)፤ በሶምሶን ላይ ‹‹የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ላይ በኃይል ወረደ፤ ጠቦትን እንደሚቆራርጥ በእጁ ምንም ሳይኖር ቈራረጠው›› (መሳ. 13፡25፣ 14፡6፣19፣ 15፡14)፡፡ ከዚህ በኋላ ሶምሶን በእግዚአብሔር መንፈስ የሠራቸውን ሥራዎች ይበልጥ ለመረዳት፤ ጥቅሶቹን ብናነባቸው በጣም አስደናቂና አስገራሚ የሆኑ ነገሮችን ማየት እንችላለን፡፡ በሳዖል ላይ የእግዚአብሔር መንፈስ በወረደ ጊዜ አሞናውያንን መታቸው፤ ከዚያም ንጉሥ አድርገው አነገሡት (1ሳሙ. 11፡6)፡፡ ሳዖል የእግዚአብሔርን ቃል በናቀ ጊዜ፣ እግዚአብሔር መንፈሱን በዳዊት ላይ አፈሰሰ (1ሳሙ. 16፡13)፡፡ በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ ከሳዖል በራቀ ጊዜ፣ ክፉ መንፈስ ያሰቃየው ጀመር፡፡

ነቢያትና ከነቢያት ውጭ የሆኑትን ለሥራው የሚፈልጋቸውን ሰዎች እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ትንቢት እንዲናገሩ ያደርግ እንደ ነበር፤ ከቃሉ እንመለከታለን፡፡ የንጉሥ ሳዖል መልእክተኞቹ የእግዚአብሔር መንፈስ በወረደባችው ጊዜ፣ ትንቢት መናገር ሲጀምሩ፣ ንጉሡም ትንቢት መናገር ጀመረ (1ሳሙ. 19፡19-24፡፡ በብሉይ ኪዳን ያሉትን ታላላቅና ታናናሽ ነቢያቶች ሁሉ ስንመለከት፤ በእግዚአብሔር መንፈስ ትንቢት ከመናገር አልፈው፤ የትንቢት መልእክት የጻፉ በመሆናቸው፤ ቃሉ ለእኛም ደርሶን እየተጠቀምንበት እንገኛለን፡፡

እግዚአብሔር በመንፈሱ አማካኝነት ለነገሥታት የተሰወረውን ምስጢር እንዲገልጡ የተጠቀመባቸው እንደ ዳንኤል ያሉ አገልጋዮች ነበሩ (ዳን. 4፡8-9፣ 18፣ 5፡11፣ ሚክ. 3፡8፣)፡፡ ነቢዩ ዳንኤልን በሁለት ነገሥታት ዘመን እግዚአብሔር የሰወረውን ምስጢሩን ለንጉሦቹ በመግለጥ ተጠቅሞበታል፡፡ ዛሬም በዘመናችን ከሰዎች የውስጥ ዕቃ አልፈው የአገርንና የነገሥታትን እንቆቅልሽ የሚፈቱ፤ ምስጢርን በመግለጥ የሚሠራባቸው አገልጋዮች እግዚአብሔር እንዲያስነሳልን በጸሎት በጌታ ፊት መቅረብ ይጠበቅብናል፡፡

በብሉይ ኪዳን ከዚህ በላይ ባየናቸው መንገዶች መንፈስ ቅዱስ ይሠራ እንደ ነበር ተመልክተናል፡፡ አንዳንዶች የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ ዘመን ብለው ለመከፋፈል ቢሞክሩም፤ የሦስቱን የሥላሴ ሥራ መነጣጠል አስቸጋሪ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን አሠራሩ ለየት ያለ ይሁን እንጂ ወልድም መንፈስ ቅዱስም ያልሠሩበት ጊዜ የለም፡፡ በአዲስ ኪዳንም እንዲሁ ነው፣ በድነት ሥራ ላይ ልንነጣጥላቸው አንችልም፡፡ ያለ አብ፣ ያለ ወልድና ያለ መንፈስ ቅዱስ በተናጠል ድነት ሊኖር አይችልም፡፡ ወደፊት ወደ ድነት ስንደርስ በስፋት እናየዋለን፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *