የክርስቶስ አገልግሎት
ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን በአባቱ በወጣው ዕቅድ መሠረት በሦስት የአገልግሎት (ቢሮዎች) ክፍሎች እንደ ካህን፣ ነቢይና ንጉሥ ሆኖ እንደሚያገለግል አስቀድሞ በብሉይ ኪዳን የተነገሩ ትንቢቶች ነበሩ፡፡ በዚህም መሠረት የብሉይ ኪዳን ሰዎች፣ መሲህ ይመጣል ብለው ይጠብቁት እንደ ነበረ፣ የትንቢት መጻሕፍት ሁሉ ዘግበዋል፡፡ በተለይም በኢሳይያስ ምዕራፍ 53 ላይ በስፋት ተነግሮ እንደምናገኘው፣ አገልግሎቱን ለመወጣት ወደዚህ ምድር፣ ከድንግል ማርያም ሥጋ ነስቶ በመወለድ፣ አገልግሎቱን ሲጨርስ መከራ በመቀበል እንዳለፈ እንመለከታለን፡፡ በአዲስ ኪዳንም መሲህ ይመጣል ብለው መጠበቃቸውን ከካህኑ ዘካርያስ ጸሎትም መረዳት ይቻላል፤ ‹‹የእስራኤል ጌታ አምላክ ይባረክ … ማዳኑም ከወደረኞቻችንና ከሚጠሉን ሁሉ እጅ ነው … በእርሱም ከጠላቶቻችን እጅ ድነን በዘመናችን ሁሉ ያለ ፍርሃት በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ እንድናገለግለው ሰጠን›› ከሚለው (ሉቃ. 1፡68-75)፡፡ በተነገረው ትንቢት መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ በእነዚህ ቢሮዎች ለማገልገል በዮርዳኖስ ወንዝ በሚጠመቅበት ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ተቀብቶ አገልግሎቱን ጀምረ፤ በምድር በነበረበት ጊዜ በብሉይ ኪዳን ይፈጸሙ ነበሩትን የነብይነትና የካህንነት አገልግሎቱን ፈጽሞ የንጉሥነት አገልግሎቱን ወደፊት ለመስጠት በአባቱ ቀኝ ተቀምጦ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡
ነብይነት፡- ሙሴ በምድረ በዳ ሕዝቡን እየመራ ሳለ ለመጨረሻ ጊዜ በዘዳግም መጽሐፍ የተናገረውን ትንቢት እንመልከት፡፡ ‹‹አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ መካከል ከወንድሞችህ እንደ እኔ ያለ ነብይ ያስነሣልሃል›› (ዘዳ. 18፡15-18) ብሎ የተናገረው የቅርብ ትንቢቱ ተፈጻሚነት ያገኘው በነቢዩ ሳሙኤል ሲሆን፤ የሩቅ ፍጻሜው ደግሞ የሚያመለክተው የኢየሱስ ክርስቶስን በነብይነት ማገልገል ነው፡፡ ጴጥሮስም ‹ብርና ወርቅ የለኝም› ብሎ በተፈወሰው ሰው ምክንያት ለተሰበሰቡት ሰዎች በሚናገርበት ጊዜ ስለ ክርስቶስ ነብይነት ሙሴ የተናገረውን በመጥቀስ እንዲህ በማለት ተናገራቸው ‹‹ሙሴ ለአባቶች፡- ጌታ አምላክ እኔን እንዳስነሣኝ ነብይን ከወንድሞቻችሁ ያስነሣላችኋል በሚነግራችሁ ሁሉ እርሱን ስሙት፡፡ ያንም ነብይ የማትሰማው ነፍስ ሁሉ ከሕዝብ ተለይታ ትጠፋለች›› (የሐዋ. 3፡22-23) ተብሎ በብሉይ ኪዳን የተነገረው ትንቢት መፈጸሙን አበሰራቸው ፡፡
በሥላሴ ዕቅድ መሠረት ጌታ ኢየሱስ ሰው ሆኖ በምድር በነበረበት ጊዜ እንደ ነብይ ሆኖ አገልግሎአል፡፡ የብሉይ ኪዳን ነቢያት የእግዚአብሔር አፍ ሆነው መልእክት፣ ከእግዚአብሔር ወደ ሰዎች ያስተላልፉ እንደ ነበረ፤ ኢየሱስም ከአባቱ የሰማውንና የሚያውቀውን መልእክት ለሰዎች አስተላልፎአል፡፡ በተወለደበት አገር ወደ ምኩራብ ገብቶ በሚያስተምርበት ጊዜ ሰዎች ሁሉ በትምህርቱ ተገርመው አፋቸውን ከፍተው ሲሰሙት ሳለ፤ ብዙዎች የመንደራችን የጸራቢውና የማርያም ልጅ አይደለምን ብለው ተሰናከሉበት፡፡ በዚህ ጊዜ ጌታም ‹‹…ነብይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ቤቱ በቀር ሳይከበር አይቀርም›› በማለት ነብይነቱን ራሱ አረጋግጦ ተናግሮአል (ማቴ. 13፡57)፡፡
‹‹… አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፣ ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና፡፡ አብ ወልድን ይወዳልና የሚያደርገውንም ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ትደነቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራ ያሳየዋል›› (ዮሐ. 5፡19-20)፡፡ ‹‹… እንደ ሰማሁ…(5፡30) ‹‹… የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁ…(6፡38) ‹‹የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ነው… የላከኝም አብ ስለ እኔ ይመሰክራል›› (8፡16፣ 18)፡፡ በናይን ከተማ ለእናቱ አንድ ብቻ የነበረውን ልጅ ከሞት ባስነሳ ጊዜ ‹‹… ታላቅ ነብይ በእኛ መካከል ተነስቶአል…›› (ሉቃ. 7፡17) እያሉ እግዚአብሔርን እንዳመሰገኑ ቃሉ ይናገራል (ዮሐ. 4፡19፣ 9፡17)፡፡
የአብን መልእክት ለሰዎች በመናገር ብቻ ሳይወሰን በማንነቱና በሕይወቱ ጭምር አባቱን (አብን) ገልጾ አሳይቶአል፡፡ ከዚህ በላይ ባየናቸው ጥቅሶች ሁሉ ክርስቶስ ነብይ ሆኖ ያገለገለው በተነገረው ትንቢት መሠረት እንደሆነ መረዳት እንችላለን፡፡ ዛሬም እኛን በተጻፈው ቃሉ አማካኝነት፣ እውነተኛ ነቢያችን ሆኖ እያገለገለን ይገኛል፡፡
ካህንነት፡- ክርስቶስ በነብይነት ብቻ ሳይሆን በካህንነትም ማገልገሉን የዕብራውያን ጸሐፊ በሰፊው ዘግቦት እናገኛለን፡፡ በዕብራውያን ዘገባ መሠረት ክርስቶስ ያገለገለው እንደ መልከ ጼዴቅ ካህን ሆኖ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ ክርስቶስ ራሱ መልከ ጼዴቅ ሳይሆን፤ እንደ መልከ ጼዴቅ ካህን ሆኖአል ብሎ ያመሳስለዋል፡፡ ጸሐፊው ያመሳሰለው መልከ ጼዴቅ ማነው? መልከ ጼዴቅ የሳሌም (በዳዊት ኢየሩሳሌም ከመባሏ በፊት የነበራት ስም) አገር ካህንና ንጉሥ ነበር፡፡ በታሪክ መጽሐፍ ስለ መልከ ጼዴቅ ተጽፎ የተገኘ ማስረጃ የለም፤ ማለት አባቱና እናቱ ማን እንደሆኑ፣ መቼ ተወልዶ መቼ እንደ ሞተም አይታወቅም፡፡ በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ እንደምናገኘው አብርሃም አሥራትን ሲሰጠው፣ አብርሃምን ባረከው፡፡ የዕብራውያን መልእክት ሌዊ በአብርሃም ወገብ ውስጥ ሆኖ ገና ሳይወለድ ለመልከ ጼዴቅ አሥራት እንደ ሰጠው ይናገራል፡፡ በዚህ ምክንያት መልከ ጼዴቅ ከሌዊ እንደሚበልጥ ያሳየናል (ዕብ. 7፡4-10)፡፡ ክርስቶስ ደግሞ ከመልከ ጼዴቅ ይበልጣል፡፡
ክርስቶስ በዕብራውያን መጽሐፍ ላይ ካህን ሆኖ የተሾመበትን ሦስት ምክንያት በግልጽ አስቀምጦልናል፡፡ ‹‹እነርሱም ያለ መሐላ ካህናት ሆነዋልና እርሱ ግን፡- ጌታ፡- አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ ማለ አይጸጸትም ብሎ በተናገረለት ከመሐላ ጋር ካህን ሆኖአልና ያለ መሐላ ካህን እንዳልሆነ መጠን እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል›› (ዕብ. 7፡20-21፣ 5፡6) በማለት ካህንነቱት ያበስርልናል፡፡ በመጀመሪያ በካህንነቱ የተሾመው እንደ መልከ ጼደቅ፤ ሁለተኛው በካህንነቱ የተሾመው ለዘላለም፣ ሦስተኛ በካህንነቱ የተሾመው በመሐላ ተፈጽሞ እንደ ሆነ በግልጽ ያስቀምጠዋል፡፡ ክርስቶስ ካህንነቱ በአባቱ መሐላ የጸደቀለት ስለሆነ፣ በእርሱ የሚያምኑበትን ሁሉ ለማዳን ዋስ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ‹‹እነርሱ እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፣ እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለ ሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል›› (ዕብ. 7፡23-25) በማለት ካህንነቱ እውነተኛና በአባቱ ተቀባይነት ያገኘ መሆኑን ያመለክታል፡፡
ክርስቶስ፣ በአሮን ካህንነት ሲፈጸሙ የኖሩትን ለኃጢአት መስዋዕት የማቅረብ ተግባራትን ሁሉ፣ ለእርሱ ጥላ ሆነው ሲቀርቡ የነበሩት ሥርዓቶች ሁሉ ለመፈጸም፣ ራሱን ለኃጢአት መስዋዕት አድርጎ በማቅረብ፤ በእግዚአብሔር ፊት ሕዝብን ወክሎ፣ በሰማያዊ ሥፍራ ወደ ምትገኘው ቅድስተ ቅዱሳን ገባ፡፡ በእግዚአብሔር የተሾመ በመሆኑ ካህንነቱ ለዘላለም ስለሆነ ለእኛም ዛሬ የመማለድ ሥራ ይሠራል (7፡25፣ 5፡1-10)፡፡ ራሱ እግዚአብሔር የሆነ በሌላ በኩል ደግሞ ሰው የሆነ፤ የሁለቱም ባሕርይ ያለው በመሆኑ፣ (1ጢሞ. 2፡5) ሁለቱን ሊያስታርቅ የሚችል እውነተኛ ሊቀ ካህናችን እርሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ ሞቶ የቀረ ሳይሆን ሞትን ድል አድርጎ የተነሣ ካህን በሰማይ አለን፡፡ በዚህ ሁላችንም ደስ ሊለንና ልናመሰግነው ይገባናል፡፡
ንጉሥነት፡- ክርስቶስ ነብይና ካህን ብቻ ሳይሆን ንጉሥም እንደሆነ የእግዚአብሔር ቃል በስፋት ይናገራል፡፡ አብዛኛዎቹ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ስለ ክርስቶስ ንጉሥነት ወይም መሲህ ሆኖ መምጣት ስለ ተናገሩ፤ ሕዝቡም ይህን በታላቅ ጉጉት ይጠብቁት እንደ ነበረ፤ ቀደም ብለን ካህኑን ዘካሪያስን በመጥቀስ ተመልክተናል፡፡ በተለይ በኢሳይያስ የትንቢት መጽሐፍ ምዕራፍ 9፡6-7 ባለው ክፍል ውስጥ ‹‹… በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፣ ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም›› ተብሎ ንጉሥነቱ ቢነገርለትም፤ እንዲሁም በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 2፡2 ላይ ሰብአ ሰገል ‹‹የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? እያሉ ንጉሥነቱን እያወጁ፣ ንጉሥ ሄሮድስን ሊጠይቁት ቢመጡም፣ የእስራኤል ሕዝብ ግን በንጉሥነት አልተቀበለውም፡፡ የጠበቁበት ቤተሰብና ሥፍራ፣ እርሱ የመጣበት ቤተሰብና ሥፍራ አልተገናኘም፤ በዚህ ምክንያት አዳኝነቱንና ንጉሥነቱን ሳይቀበሉት ቀሩ፡፡ ሰብአ ሰገል ንጉሥነቱን የተረዱት በኮከብ አማካኝነት ተረድተው እንደሆነ ቃሉ ይናገራል፡፡ በአጠገቡ ያሉ የእስራኤል ሕዝብ ግን አስወግደው፣ ስቀለው በማለት ንጉሥነቱን ሳይቀበሉ ቀሩ፡፡
ክርስቶስ ራሱ ሲናገር መንግሥቱ በምድር ሳይሆን በሰማይ እንደ ሆነ፤ በስብከቶቹና በትምህርቱ በማስረገጥ አሳይቶአል፡፡ ‹‹አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም›› (ዮሐ. 18፡36) ‹‹… መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች… ›› ‹‹… የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ…›› (ማቴ. 4፡17-23) ‹‹የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ደርሳለች…›› (12፡28) የእስራኤል ሕዝብ በሙሉ ሳይሆን፣ ጥቂቶች ምግብ የመገባቸው ሰዎች እንደ ንጉሥ ሊያነግሡት ቢፈልጉም ጊዜው ገና ስለነበረ አልተቀበላቸውም (ዮሐ. 6፡15)፡፡ ሠፊው ሕዝብ ባለ መቀበሉ ምክንያት፣ ንጉሥ ሆኖ ሰማያዊ መንግሥቱን በዚህ በምድር ሊመሠርት አልቻለም፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም እየወጣ ሳለ፣ ደቀ መዛሙርቱ ‹‹በጌታ ስም የሚመጣ ንጉሥ የተባረከ ነው በሰማይ ሰላም በአርያምም ክብር አሉ›› ፈሪሳውያንም ይህን ሲሰሙ፣ ጌታን ሕዝቡን ዝም አሰኝ ሲሉት፣ እርሱም ‹‹እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ አላቸው›› (ሉቃ. 19፡28-40)፣ ይህ የሚያሳየን ንጉሥ እያሉ መጮኻቸውን መቀበሉን ነው፡፡
የፋሲካውን እንጀራ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ለመብላት ወደ ኢየሩሳሌም ቀርበው ቦታ እንዲያዘጋጁለት ሲልካቸው ሳለ፣ ጌታ ራሱ ስለ ዝግጅቱ ቢጠይቋችሁ ለጌታ ያስፈልገዋል በሉ፣ በመቀጠልም ‹‹ለጽዮን ልጅ፡- እነሆ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሉአት›› ብሎ የተናገራቸው በነቢዩ ዘካርያስ በተነገረው ትንቢት መሠረት፣ የሰጣቸው መመሪያ ንጉሥነቱን በማረጋገጥ እንደ ሆነ ወንጌላዊው ማቴዎስ ዘግቦ እናገኛለን (ማቴ. 21፡5)፡፡ ዮሐንስም በወንጌሉ በናትናኤልና በክርስቶስ መካከል ስለ ነበረው ክርክር አንስቶ ሲጽፍ በመጨረሻ ላይ ናትናኤል በመረታት ስለ ክርስቶስ ሲናገር እንዲህ አለ፣ ‹‹… አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ አለው›› (ዮሐ. 1፡50)፤ ስለዚህ የንጉሥነቱ ጊዜ ቢዘገይም ወደፊት ንጉሥ ሆኖ በዕቅዱ መሠረት መግዛቱ አይቀሬ ነው፡፡ ዮሐንስ በራዕዩ ለወደፊት ንጉሥ ሆኖ ስለ መምጣቱ ሲናገር ‹‹በልብሱና በጭኑ የተጻፈበት፡- የነገሥታት ንጉሥና የጌታዎች ጌታ የሚል ስም አለው›› (ራዕ. 19፡16) በማለት በንጉሥነቱ አንድ ቀን እንደሚነግስ ገልጾአል፡፡ ዛሬም ቢሆን በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በሰው ልብ ውስጥ ንጉሥ ሆኖ እየገዛ ይገኛል፣ ነብይነቱና ካህንነቱ ተፈጻሚነት ካገኙ ንጉሥነቱም የማይፈጸምበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡
0 Comments