ለ) አስተምህሮተ ክርስቶስ
- አስተምህሮተ ሰው
በክፍል አንድ አስተምህሮተ እግዚአብሔር በሚለው ሥር መጽሐፍ ቅዱስ፣ እግዚአብሔርና መላእክት የሚሉትን ሦስት ትምህርቶችን ተመለከትን፡፡ አሁን ደግሞ አስተምህሮተ ክርስቶስ የሚለውን ክፍል ሁለት ትምህርት ጀምረን፤ በሥሩ ያሉትን አስተምህሮተሰው፣ አስተምህሮተሰብዓዊነትና መለኮታዊነት የሚሉትን ሦስት ትምህርቶችን እናጠናለን፡፡ በፍልስፍናም ሆነ በእምነት የሰውን ማንነት ለማወቅ የተለያዩ ጥያቄዎች ሲጠየቁ ቆይተዋል፡፡ ጥያቄዎቹም ሰው ማነው? ከየት መጣ? በምድር የመኖሩ ዓላማ ምንድን ነው? ወዴት ነው የሚሄደው? መጨረሻው ምንድን ነው? የሚሉት መሠረታዊ ጥያቄዎች ሰውን ሁሉ ለዘመናት ያነጋገሩና ያወያዩ የከፋፈሉም ጥያቄዎች ናቸው፡፡ አንዳንዱ መልስ አግኝቶ፣ አንዳንዱ ደግሞ መልስ ሳያገኝ፣ ይህችን ዓለም ተሰናብተው የሄዱ በብዙ ሺህ ሚሊዮንየሚቆጠሩሰዎች ናቸው፡፡ እናንተም ለእነዚህጥያቄዎች መልስ አግኝታችኋል?
‹‹ሰው ምንድን ነው? ሰው መሆን ምን ማለት ነው? ሰው ምን ማድረግ ይገባዋል? ለሚሉትና ለመሳሰሉት ጥያቄዎች መልስ መስጠት በመጀመሪያ ሲታይ ከባድ አይመስልም፡፡ የዚህ መጽሐፍ ጸሓፊ እኔ ሰው ነኝ፤ ውድ አንባቢዬ ደግሞ ሰው ነዎ፡፡ ስለ ሰው የሚጻፉ መጻሐፍት ማለቂያ የላቸውም፤ ስለ ሰው የሚገኙ አሳቦችም እንደየጸሓፊው የተለያዩና ብዙ ናቸው›› ሲሉ ቄስ ማንሰል፣ ሰው ሁሉ የሚጠይቃቸውን ጥያቄዎች በመጽሐፋቸው አስፍረው እናገኛለን፡፡በመቀጠልም ‹‹ሰው ረቅቅ ባለመሆኑ ያለ አስተርእዮ (መገለጥ) በቀጥታ ሊጠና ይችላልና ሰው ሰውን ይመረምራል፤ የሚያገኘው አሳብ ግን ትክክለኛ ወይም የተዛባ ሊሆን ይችላል›› በማለት በቃሉና ከቃሉም ውጭ ሰውን በማጥናት መልስ ማግኘት ይገባናል ሲሉ አሳባቸውን አስቀምጠዋል(ቄስ ማንሰል፣ ትምህርተ ክርስቶስ፣ ገጽ 13)፡፡
ስለ ሰው ጅማሬ በጣም ብዙ መጻሕፍት ተጽፈው ይገኛሉ፤ ወደፊትም ገና ብዙ እንደሚጻፉ ይታወቃል፡፡ ስለ ሰውም የተጻፉት መጻሕፍት የተለያየ አመለካከት ቢኖራቸውም፤ሁሉም ታሪኮቹንበሚከተሉት መልክ በማስቀመጥ፣ ብዙዎቹ ይስማሙበታል፡፡ሰው ልብስ ሳይለብስ ዕራቁቱን ወደዚህ ዓለም የመጣ፣ ምንም የዘመኑ ዕውቀት የሌለው፣ ቀስ በቀስ በልምምድ ወደ ሥልጣኔ የመጣ፣ ከአውሬ፣ ከፀሐይና ከዝናብ ራሱን ለማዳን በጫካ ከመኖር በዋሻ ወደ መኖር የጀመረ፣ በዋሻ ከመኖር ቤት ሠርቶ ወደ መኖር፤ ከዕራቁትነት ወደ ልብስ መልበስ፤ በእንጨት ከመቆፈር በዶማ፣ በዶማ ከመቆፈር በበሬ ማረስ፣ በበሬ ከማረስ በትራክተር ማረስ ያደገ፤ በእግር ከመሄድ በእንሰሳ መሄድ፣ ከዚያም በመኪና፣ በአውሮፕላንና ወደ ህዋ በመንኮራኩር መሄድ የቻለ ሰው፣ አስደናቂ ፍጡር፣ ክቡር ፍጡር፣ እንደዚሁም አምላኩን በመታዘዝ መኖር ያልቻለ ደካማ፣ራሱን በራሱ ለማጥፋት (በሚሠራቸው የጦር መሣሪያ) የጀመረ አሳዛኝ፣ እንደሆነ የሚጻፉለት ታሪኮቹያስረዳሉ፡፡
ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ስንመጣ ሰው አስደናቂ የሆነ ጅማሬ ያለው፣ በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ የተፈጠረ፣ ከፍጥረታት ሁሉ የላቀ ክቡር ፍጥረት እንደሆነ እንረዳለን፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የሰው ልጅ ላለው ጥያቄ ሁሉ መልስ የሚሆን እንደያዘ እንመለከታለን፡፡ እግዚአብሔር ፍጥረትን ሁሉ በፈጠረበት መጽሐፍ ውስጥ በቃሉ እንዲህ በማለት የሚናገረውን በዘፍጥረት መጽሐፍ ምዕራፍ 1፡26-27 እንመልከት፡፡ ‹‹እግዚአብሔርም አለ፡- ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፣ … እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፣ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፣ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው›› ይላል፡፡መጽሐፍ ቅዱሳችን በዚህ መልኩ የሰው ጅማሬ በእግዚአብሔር እንደሆነ በግልጽ ያሳየናል፡፡ በመቀጠልም ስንመለከት ‹‹እግዚአብሔር አዳምን በፈጠረ ቀን በእግዚአብሔር ምሳሌ አደረገው ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው ባረካቸውም፡፡ ስማቸውንም በፈጠረበት ቀን አዳም ብሎ ጠራቸው›› (ዘፍ.5፡2) በማለት ሰው በእግዚአብሔር የተፈጠረ የእጁ ሥራ እንደሆነ ያረጋግጥልናል፡፡
ሰው በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ተፈጠረ ብሎ መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር እግዚአብሔር እንደ ሰው እጅ፣ እግር፣ ዓይን፣ ጆሮ… የመሳሰሉት ሁሉ አሉት ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ‹‹መልክና›› ‹‹ምሳሌ›› የሚለው አካልን የሚያመለክት ሳይሆን አስተሳሰብን፣ እውቀትን፣ ሞራላዊ ሁኔታንና የማስተዳደር ችሎታን የሚያመለክት ነው፡፡ እግዚአብሔር ብዙ ተባዙ ብሎ ከባረካቸው በኋላ ‹‹… ምድርንም ሙሉአት ‹ግዙአትም› …›› (ዘፍ.1፡28) በማለት የሚናገረው ሐሳብ ማስተዳደርን ያመለክታል፡፡ እግዚአብሔር በዘፍጥረት መጽሐፍ ምዕራፍ አንድ ላይ ፍጥረትን ከፈጠረ በኋላ፣ አዳምንና ሔዋንን የፍጥረት ገዥ አድርጎ ኃላፊነት ሲሰጣቸው፤ በምዕራፍ ሁለት ላይ የገነት ጠባቂ አድርጎ እንደ አስቀመጣቸው ቃሉ ያሳየናል፡፡ሐዋርያው ጳውሎስም በመልእክቶቹ ‹‹…እንደ እግዚአብሔር ምሳሌየተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ›› (ኤፌ.4፡21-24)፣ ‹‹…. የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል›› (ቆላ.3፡10) በማለት በኃጢአት ምክንያት ተበላሽቶ የነበረውን የእግዚአብሔር መልክ በክርስቶስ በኩል መልሰው መልበስ (ማግኘት) እንዳለባቸው ለሁለቱም ከተማ አማኞች ያሳስባቸዋል፡፡
መጽሐፍ ቅዱሳችን እግዚአብሔር የከበረ እንደሆነ ይነግረናል፤ ነብዩ ኢሳይያስ ሰውን የፈጠረበትን ምክንያት ሲናገርም እንዲህ ይላል፣ ‹‹ለክብሬ የፈጠርኳቸው›› (ኢሳ.43፡7)፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው ረዳት ፈልጎ ሳይሆን ለክብሩ እንደ ፈጠረን ያመለክታል፤ እርሱን እያመለክን በኅብረት እንድንኖር ተፈጥረናል፡፡ ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክቱ ምዕራፍ 1፡12 ላይ ‹‹…እኛ ለክብሩ ምሥጋና እንሆን ዘንድ ነው›› በማለት በክርስቶስ እንደገና ለእግዚአብሔር ክብር የመፈጠራችንን ዓላማ ያመለክተናል፡፡ ሰው ከከበረው እግዚአብሔር ጋር በኅብረት እንዲኖር ተፈጥሮአል፡፡
ደግሞም ወንድና ሴት አድርጎ እንደ ፈጠራቸው ይናገራል፤ይህም በአንድ ወንድና ሴት መካከል የጾታ መፈላለግ እንዳለ ያሳየናል፡፡ በመካከላቸው መፈላለግ ቢኖርም፣ ወንድና ሴት ሰው በመሆናቸው እኩል ናቸው፡፡ በወንድና በሴት መካከል ግን የጾታ ልዩነት፣ የአስተሳሰብና የጉልበት (የአቅም) ልዩነቶች እንዳሉ ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው በሚልበት ጊዜ በወንድና በሴት መካከል መፈላለግ፣ መዋደድ፣ አንዱ የሌላውን ጉድለት መሙላት እንዳለ ያስገነዝበናል፡፡ ጋብቻም በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የሚፈጸም ተግባር ስለሆነ፤ ከዚህ ውጭ ያለውን የዘመናችን የጋብቻ ሁኔታ (ወንድ ከወንድ፣ ሴት ከሴት) እግዚአብሔር ያዘጋጀው ስላልሆነ አይቀበለውም፡፡ ቤተ ክርስቲያንም አትቀበለውም፤በመጨረሻም ወደ ፍርድ ያስገባል፡፡ ሰው በእግዚአብሔር የመፈጠሩን እውነት፣ ቃሉ የሚናገረውን በእምነት መቀበል የእኛ የሰዎች ድርሻ ነው፡፡
የእግዚአብሔር ቃል እንደሚናገረው የሰው ጅማሬ በራሱ በእግዚአብሔር ሆኖ ስለ አስቀመጠበት ሥፍራ እንዲህ በማለት ይናገራል፡፡ ‹‹እግዚአብሔር አምላክም በምሥራቅ በዔደን ገነትን ተከለ የፈጠረውንም ሰው ከዚያ አኖረው›› (ዘፍ.2፡8-9)፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የሚያስፈልገውን ‹‹…ለማየት ደስ የሚያሰኘውን ለመብላትም መልካም የሆነውን…›› (2፡15) ከፈጠረና ካዘጋጀ በኋላ ሰውን በመልኩና በምሳሌው ፈጥሮ በዔደን ገነት አስቀምጦ ያበጃትምይጠብቃትም ዘንድ ኃላፊነት ሰጠው፡፡ ቃሉ እንደሚናገረው ‹‹ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት››(ዘፍ.2፡18) ይላል፡፡ እግዚአብሔር በዔደን ገነት ሁሉን ነገር ቢያዘጋጅለትም እንደ እርሱ ያለ ረዳት ስላላገኘ በብቸኝነት ሲጠቃ አይቶት በመረዳዳት ሕይወት እንዲኖሩ ሔዋንን ከጎን አጥንቱ ሴት አድርጎ አዘጋጀለት፡፡አዳምም እግዚአብሔር ለሰጠው ለሔዋንና ለፍጥረት ሁሉ ስም አወጣላቸው፡፡ ከሔዋን ጋርም የሰላምና የደስታ ሕይወት መኖር እንደ ጀመሩ ምንም ጥርጥር በሌለው ሁኔታ መኖራቸውን ያስረዳል፡፡ ስለዚህ የሰው ጅማሬ ትልና ዝንጀሮ ሳይሆን እግዚአብሔር ራሱ ነው፡፡ይህም በእግዚአብሔር መልክ መፈጠራችንን ማመን የክርስትናችን መሠረት ሆኖ ከዚህ ይጀምራል፡፡
የሰው ተፈጥሮ፡-የሰው ተፈጥሮ በዘመናት ሁሉሲያከራክር የኖረ ሲሆን፣ ዛሬም ክርክሩ ይቀጥላል፡፡ ክርክሩም ሰው ሁለት ወይም ሦስት ተፈጥሮ ነው በማለት ሲያከራክር የኖረ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የዳይኮቶሚስ አመለካከት ያላቸው ሥጋና መንፈስ ወይም ሥጋና ነፍስ ብለው በመክፈል የሰውን ተፈጥሮ በሁለት ይከፍሉታል፤ የትራይኮቶሚስ አመለካከት ያላቸው ደግሞ በሦስት በመክፈል ሰው ሥጋ፣ ነፍስና መንፈስ ነው በማለት ያስቀምጡታል፡፡እነዚህ ሁለት አመለካከቶች ሁለቱም የሚከራከሩበትና የሚያቀርቡት ማስረጃ በቃሉ መሠረት እንደ ሆነ እንመለከታለን፡፡ የሰውን ተፈጥሮ ቃሉእንዲህ አድረጎ ያቀርበዋል ‹‹እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው በአፍንጫውም የሕይወትን እስትንፋስን እፍ አለበት፣ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ›› (ዘፍ.2፡7)፡፡ በዚህ ሥፍራ ስንመለከት እውነት ነው፣ ሰው የተሠራው ከሁለት ነገር ከአፈርና ከእግዚአብሔር እስትንፋስ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡አንዱ ቁስ አካል ሲሆን፣ ሌላው መንፈሳዊ አካል ብለው በመክፈል፣ ሰው ሥጋና መንፈስ ነው ወይም ሥጋና ነፍስ ነው ብለው የሚቀበሉና የሚያምኑ ልክ ናቸው፡፡
በመቀጠልም ቃሉን ትኩረት ሰጥተነው ስናየው የሚታይ አፈርና የማይታየው የእግዚአብሔር እስትንፋስ ሁለቱ ሲገናኙ ሌላ የማይታይ ነገር እንደ ተፈጠረ ቃሉ እንዲህ በማለት አስቀምጦታል፡፡ ‹‹ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ›› በማለት ከሁለቱ የተገኘውን ውጤት ያሳያል፡፡ ስለዚህ ሰው ከሁለት ነገር ተፈጥሮ ሳለ፣ በውጤቱ ግን ሥጋ፣ መንፈስና ነፍስ ያለው ፍጥረት ሆኖአል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም ለተሰሎንቄ ሰዎች በጻፈው መልአክቱ በዕድገት (progressive revelation) ወደ እርሱ የመጣውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት፣ እንዲህ አድርጎ ያቀርበዋል ‹‹የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ መንፈሳችሁም፣ ነፍሳችሁምሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ›› (1ተሰ.5፡23) በማለት ሦስቱንም ጠቅሶአቸው እናገኛለን፡፡ ስለዚህ ሰው ሦስት ነው የሚል አመለካከት ያላቸውም ልክ ናቸው፡፡
ስለዚህ ሥጋ የሚታይ ሲሆን ነፍስና መንፈስ የማይታዩ ናቸው፤ ሥጋ የነፍስና የመንፈስ መያዣ ሲሆን መብላትና መጠጣት፣ መንቀሳቀስና መሥራት የሥጋ ተግባሮች ናቸው፡፡ እንዲሁም መንፈስ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ሕብረት የሚያደርግበትና የማወቅ ኃይል እንደሆነ ቃሉ ከሚናገረው መረዳት ይቻላል ‹‹… ኢየሱስ በልባቸው እንዲህ እንዳሰቡ በመንፈሱ አውቆ…›› (ማር.2፡8)፣ ነፍስ ደግሞ የስሜት ሁሉ ማረፊያ እንደሆነች ከሚቀጥለው ጥቅስ ይመልከቱ ‹‹ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች›› (ማቴ.26፡38)፣ ጌታ ነፍሱ የስሜቱ ሁሉ ማረፊያ እንደሆነች እናስተውል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ መንፈስና ነፍስ የሚሉትን እየለዋወጠ እንደሚጠቀም ወይም እንደሚወራረሱ ማየት እንችላለን፤ ቢሆንም ግን ሁለቱም ለማይታየው አካል የሚያገለግሉ ናቸው (ትምህርተክርስቶስ በቄስ ማንሰል ገጽ 37)፡፡
ሰው ከሁለት ከሚታይ (አፈር) እና ከማይታይ (ከእግዚአብሔር እስትንፋስ) ነገር በመሠራቱ በግልጽ ሁለት ተፈጥሮ እንዳለው መረዳት እንችላለን፡፡ ሰው ከሁለት ነገሮች ተፈጥሮ ሦስት የተለያዩ ነገሮች እንዳሉት በግልጽ ቃሉ ያሳየናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የማይታየውን ተፈጥሮ መንፈስንና ነፍስን እየለዋወጠ ቢጠቀምም፤ ሁለቱም ከሰማይ የሆነውን አካል ሲያመለክቱ፤ በተግባራቸው ደግሞ የተለያዩ መሆናቸውን መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡ መንፈስከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝበትና የማወቅ ኃይላችን ሲሆን፤ ነፍስ ደግሞ የስሜታችን ሁሉ ማረፊያ ናት፡፡ ስለ እነዚህ ሁሉ ነገሮች መጽሐፍ ቅዱስ በስፋት ባይነግረንም በሳይንሳዊ መንገድ ማስረጃ ማግኘት ስለምንችለው ነገሮች ጥቂት ለማለት እወዳለሁ፡፡ ይህን ሐሳብ በተመለከተ ወይም ነፍስ የስሜት ሁሉ ማረፊያ ነች ስንል በሚከተለው መንገድ ተከፋፍለው፣ ሰውከዕለት ተግባሩ ጀምሮ እስከሚሞትበት ቀን ድረስ እያሰበና እያቀደ የሚኖረው በአእምሮው እንደ ሆነ መረዳት እንችላለን፡፡የሰው ህሊና-የዕውቀት ቦታ፣ ፈቃዱ-የውሳኔ መስጫ ቦታ፣ እንዲሁም ስሜቱ-የመልካምና የክፉ ድርጊት ቦታ መሆኑን ሰዎች በደረሱበት ጥናትና ምርምር ያቀርቡልናል፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስም ለመንፈሳዊ ልጁ በጻፈለት መልእክት መልሶ መላልሶ፣ ‹‹ከንጹሕ ልብና ከበጎ ሕሊና… ›› (1ጢሞ 1፡5)፣ ‹‹እምነትና በጎ ሕሊና ይኑርህ… ›› (1፡19) በማለት እንደ ሌሎች አማኞች ሕሊናውን እንዳይጥል ይመክረዋል፡፡ ለሮሜ አማኞችም ‹‹እንግዲህ ወንድሞችሆይ፡-ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፣ እርሱም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ›› (ሮሜ 12፡1-2) በማለት ሲመክራቸው፤ ለተሰሎንቄ አማኞች ደግሞ በሥጋቸው፣ በመንፈሳቸውና በነፍሳቸው ሁሉ ተቀድሰው ጌታን እያገለገሉ ምፅዓቱን መጠበቅ እንዳለባቸው ይመክራቸዋል (1ተሰ.5፡23)፡፡ ስለዚህ ሰው ከሁለት ነገሮች ተገኝቶ፣ ሳለ በሦስት ዋና ዋና ነገሮች አማካኝነት፣ በዚህ ምድር ላይ ሲኖር እየተጠቀመ ያለውበሕሊናው፣ ፈቃዱና በስሜቱ እንደሆነ መረዳት እንችላለን፡፡ሥጋ ከሌለ መንፈስና ነፍስ ለብቻቸው ሊኖሩ አይችሉም፡፡ ስለ ሰው ተፈጥሮ በሚገባ ባይገባንም በተረዳነውና በተሰጠን ማንነት እየኖርን፤ወደ እርሱ እስከምንሄድ ድረስ በትዕግስት እየተመላለስን፣ እግዚአብሔርን እየባረክን፣ እያመሰገንንና እያገለገልን ልንኖር ይገባናል፡፡
0 Comments