ያልወደቁ መላእክት
በቀደመው ጥናታችን የተመለከትነው አስተምህሮተ እግዚአብሔር የሚል ነበር፤ በመቀጠል የምንመለከተው አስተምህሮተ መላእክት የሚለውን ሦስተኛውን ርዕሳችንን ይሆናል፡፡ ስለ መላእክት መፈጠር ስናጠና መቼ እንደ ተፈጠሩ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን ምንም ሥፍራ የለውም፡፡ መላእክት እግዚአብሔር ከፈጠራቸው ፍጥረታት መካከል አንዱ መሆናቸው ቃሉ ስለሚነግረን መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ ሰዎች የመላእክትን መኖር ቢያምኑም ባያምኑም እርግጠኛ የሆነ ማረጋገጫ ማቅረብ የሚችል ሰው የለም፤ ምክንያቱም ስለማይታዩና ማስረጃ ማቅረብ ስለማይቻል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን መኖራቸውን በቃሉ አረጋግጧል፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን እውነት ከተቀበልን ስለ መላእክት መኖር ማመን ይኖርብናል፡፡ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መላእክት ብሉይ ኪዳን አንድ መቶ ጊዜ፣ አዲስ ኪዳን ሁለት መቶ ጊዜ ያህል ስለ መላእክት መኖር የሚናገር ትምህርት አላቸው፡፡ ከስልሳ ስድስቱ መጽሐፍ ሠላሳ አራቱ ስለ መላእክት ጽፈው እናገኛለን፡፡
1.1 ትርጉም፡- መላእክት በእንግሊዝኛው አጠራር ‹‹ኤንጅል››፣ በግሪክኛው ደግሞ ‹‹አንጅሎስ›› ማለት ሲሆን፣ ትርጉሙም ‹‹መልእክተኛ›› ማለት ነው፡፡ ስማቸው ከሥራቸው ጋር እንደሚሄድ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወደ ተለያዩ ሰዎች ተልከው መሄዳቸውን ይነግረናል፡፡ በብሉይና በአዲስ ኪዳን ወደ ሰዎች ተልከው መሄዳቸውን የሚከተሉት ጥቅሶች ያሳዩናል፡፡ በዘፍጥረት መጽሐፍ እንደምናነበው የሶዶም ሕዝብ ኃጢአት እጅግ በበዛበት ጊዜ፣ እግዚአብሔር መላእክቱን ልኮ ከተማይቱን ሊያጠፋ ባሰበበት ሰዓት ላይ፣ ‹‹እነዚያ ሰዎች የእርሱን (የሎጥን) እጅ የሚስቱንም እጅ የሁለቱን የሴቶች ልጆቹንም ይዘው አወጡትና በከተማይቱ ውጭ አስቀመጡት›› በማለት ከጥፋት እንዳዳኑት ቃሉ ይናገራል (ዘፍ.19፡1-22)፡፡ መላእክት ለማጥፋት የሚላኩ ብቻ ሳይሆኑ የሰላም መልእክተኛ እንደሆኑም ወደ ዳንኤል፣ ዘካርያስና የጌታ እናት ማርያም ተልከው መልእክት እንዳደረሱ ከቃሉ እናነባለን (ዳን.9፡20-23፣ ሉቃ.1፡8-38)፡፡
1.2 የመላእክት ማንነት፡- መላእክት በእግዚአብሔር ዙሪያ በመገኘት እንዲያመልኩት ሆነው የተፈጠሩና የማይታይ አካል ያላቸው ናቸው፡፡ መላእክት መቼ እንደተፈጠሩ ቃሉ ምንም ፍንጭ ባይሰጠንም፤ ብዙ ሊቃውንት በመጀመሪያው ቀን እንደ ተፈጠሩ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ እግዚአብሔር ሁሉን ከፈጠረ በኋላ በሰባተኛው ቀን ስላረፈ፣ መላእክት ከዚህ ቀን በፊት እንደ ተፈጠሩ ግልጥ ነው ብለው ቄስ ማንሰል ይናገራሉ፡፡ አስቀድመን ከርዕሳችን እንዳየነው፤ መላእክት በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት በመሥራታቸው ምክንያት ከነበሩበት ክብር ስለተጣሉ፣ በክብር ያሉ ያልወደቁና የወደቁ መላእክት ተብለው በሁለት ተከፍለው እናገኛለን፡፡ በመጀመሪያ ያልወደቁትን መላእክት በስፋት ተመልክተን በመቀጠልም የወደቁትን መላእክት እንመለከታለን፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ በቈላስይስ መልእክቱ ‹‹የሚታዩትና የማይታዩትም ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ (በክርስቶስ) ተፈጥረዋልና›› በማለት የሥላሴ ሁለተኛው አክል የሆነው ክርስቶስ በመላእክት መፈጠር ላይ ተሳትፎ እንዳለው ይናገራል (ቈላ.1፡15-16)፡፡ መላእክት ምንም እንኳን የሚታይ፣ የሚጨበጥና የሚዳሰስ አካል ባይኖራቸውም፤ ዕውቀት (1ጴጥ.1፡12)፣ ስሜትና (ሉቃ.2፡13)፣ ፈቃድ (ይሁዳ ቁ 9) ስለ አላቸው፣ ግብረ ገባዊ ባሕርይና ከፍ ያለ የማሰብ ችሎታ እንዳላቸው መረዳት እንችላለን፡፡ መላእክት ወደ ሰዎች በሚላኩበት ጊዜ፣ ሰዎች በሚገባቸው ቋንቋ መልእክቱን መናገር፣ የሰዎችን ጥያቄ መቀበል ይችሉ ነበር፡፡ መላእክት መንፈሳውያን ፍጡራን በመሆናቸው ሥጋና አጥንት የላቸውም፤ (ሉቃ.24፡39) ቢሆንም ግን ወደ ሰዎች በሚላኩበት ጊዜ በሥጋ አካልና በመላእክት መልክ እንደተገለጡ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል (መሳ.2፡1-5፣ ማቴ.28፡5)፡፡ መላእክት ባላቸው ችሎታ ተጠቅመው ኃጢአት እንደ ሠሩ፤ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ወደፊት በስፋት እንመለከታለን፡፡
ስለ መላእክት ማንነት ዘርዘር አድርገን የሚከተሉትን ጥቀሶች እንመለከታለን፤ የዕብራውያን ጸሐፊ መላእክት መናፍስት (ሥጋና አጥንት የላቸውም ማለት ነው) እንደ ሆኑ ሲነግረን ሳለ ሰዎችንም ለማገልገል የተላኩ እንደሆኑም እግረ መንገዱን ይገልጻል (ዕብ.1፡13-14)፡፡ መንፈስ የሚለውን ቃል አጠቃቀም ስንመለከት የሰውን መንፈስ፣ መላእክትንና መንፈስ ቅዱስን ለመግለጥ መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቀምበታል፡፡ ኢየሱስ ለሰዱቃውያን ጥያቄ በሰጠው መልስ ላይ እንደ ሰው ‹‹አያገቡም፣ አይጋቡም›› በማለት መላእክት እንደማይዋለዱ ያመለክታል (ማር.12፡25)፡፡ ስለዚህ በቁጥር ብዙ ሆነው እንደ ተፈጠሩ ከቃሉ ማየት እንችላለን፤ (ዘዳ.33፡2፣ ማቴ. 26፡53፣ ዕብ.12፡22፣ ራዕይ 5፡11)፡፡ መላእክት ባለመሞታቸው ምከንያት የቁጥር መቀነስ አይታይባቸውም (ሉቃ. 20፡36)፤ ነቢዩ ዳንኤል መላእክት በተገለጠለት ጊዜ ስለ ነበረው ሁናቴ ሲናገር፤ ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ የሆነው ሚካኤል የተባለው አለቃ ሊረዳው እንደ መጣ ይናገራል፤ ከዚህ መረዳት የምንችለው መላእክት በአለቆች መከፋፈላቸውን መረዳት እንችላለን (ዳን.10፡13)፡፡ ቀደም ብለን እንዳየነው መላእክት ተልከው ወደ ሰዎች እንደሚመጡ ተመልክተናል፤ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ሐዋርያው ጴጥሮስ በእስር ቤት በነበረበት ጊዜ፣ በቤተ ክርስቲያን አጥብቀው ይጸልዩ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ጸሎታቸውን ሰምቶ፣ መልአኩን ልኮ ከእስር ቤት እንዲ ወጣ አደረገው፤ ከዚህ የምንረዳው የጸሎትን መልስ ወደ ሰዎች ይዘው እንደሚመጡ ነው (የሐዋ.12፡7-11)፤ በሉቃስ ወንጌልም እንደምንመለከተው ካህኑ ዘካርያስ በአገልግሎት ላይ እያለ፣ ‹‹ዘካርያስ ሆይ ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፣ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ›› በማለት የጸሎቱን መልስ ይዞለት እንደ መጣ እንመለከታለን (ሉቃ.1፡8-23)፡፡
1፡3 የመላእክት ስሞች፡- መጽሐፍ ቅዱስ መላእክትን በተለያየ የጋራ በሆነ ስም ይጠራቸዋል፡፡ በኢዮብ መጽሐፍ እንደምናገኘው ‹‹ከዕለታት አንድ ቀን እንዲህ ሆነ የአምላክ ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም የእግዚአብሔር ልጆች መጡ›› በማለት የሚናገረውና የሚያመለክተው መላእክትን እንደሆነ መረዳት አያስቸግርም፤ ምክንያቱም ‹‹ሰይጣንም ደግሞ በመካከላቸው መጣ›› በማለት የመናፍስት ስብሰባ በእግዚአብሔር ፊት እንደ ተደረገ ያመለክታል (ኢዮ.1፡6፣ 2፡1)፡፡ መዝሙረኛው በመዝሙሩ ‹‹እውነትህንም ደግሞ በቅዱሳን ማኅበር ያመሰግናሉ፣ … ከአማልክትስ ልጆች እግዚአብሔርን ማን ይመስለዋል በቅዱሳን ምክር እግዚአብሔር ክቡር ነው፣ በዙሪያው ባሉት ሁሉ ላይ ታላቅና ግሩም ነው›› (መዝ.89፡5-7) በማለት መላእክት የእግዚአብሔር ልጆች እንደሆኑና ቅዱሳን ተብለው በዙሪያው ሆነው እንደሚያመልኩት ይናገራል፡፡
መላእክት በተለያየ ስም እንደሚጠሩ ቀደም ብለን አይተናል፤ ናቡከደነፆር ከምድር አራዊት ጋር እንደ በሬ ሣር እንደሚበላ ባየው ሕልም ውስጥ፣ ስለ ተላከው መልእክተኛ ስም እንዲህ ይላል (ዳን 4፡13) ‹‹ቅዱስ ጠባቂ›› ቁ.17 ‹‹የጠባቂዎች ትእዛዝ›› ቁ.23 ‹‹ቅዱሱን ጠባቂ›› (ጉበኛ) በእነዚህ አጠራር ስማቸው ከተግባራቸው ጋር ተመሳስሎ እናገኘዋለን፡፡ አዳምና ሔዋን ኃጢአትን ሠርተው ከገነት በተባረሩ ጊዜ፣ ወደ ገነት ተመልሰው እንዳይገቡ ‹‹ኪሩቤል›› የተባለውን መልአክ የምትገለባበጥ የነበልባል ስይፍ አሲዞ በኤደን ገነት አስቀመጠው፡፡ የመልአኩ ተግባር የእግዚአብሔርን ቅድስናውን መጠበቅ እንደሆነ ያመለክተናል (ዘፍ.3፡22-24)፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶንና በቈላስይስ መልእክቶቹ ጠቅለል ባለ መልኩ ‹‹ዙፋናት፣ ጌትነት፣ አለቅነትና ሥልጣናት›› እያለ የሚጠራቸው መላእክትን እንደሆነ ብዙ ሊቃውንት የሚስማሙና የማይስማሙ አሉ፤ እኔ ከሚስማሙት ወገን ነኝ (ቆላ.1፡16፤ ኤፌ.1፡21)፡፡ መናፍስት፣ የእግዚአብሔር ልጆች፣ ቅዱሳን፣ ጉበኛ፣ ዙፋናትና ሥልጣናት የሚሉት ስሞች የብዛት መጠሪያ እንደ ሆነ ተመልክተናል፡፡ በመቀጠል በስም የተጠቀሱትን መላእክት ከሥራቸው ጭምር እንመለከታለን፡፡
ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ ‹‹ … እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፣ የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞልቶት ነበር፡፡ ሱራፌልም ከእርሱ በላይ ቆመው ነበር፣ ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው በሁለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር፣ በሁለቱም ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበር፣ በሁለቱም ክንፍ ይበር ነበር›› (ኢሳ.6፡1- 3) በማለት ሱራፌል የተባሉት መላእክት ተግባራቸው እግዚአብሔርን ማምለክ እንደ ሆነ ያመለክታል፡፡ በዚህ ሥፍራ ሱራፌል ክንፍ እንዳላቸው ቃሉ ይናገራል፤ ሁሉም መላእክት ክንፍ ይኑራቸው አይኑራቸው፣ ቃሉ ምንም አይናገርም፤ ሁሉም መብረር እንደሚችሉ ብዙ ማስረጃ እናገኛለን፡፡
በስም ተጠቅሰው ከምናገኛቸው መላእክት አንዱ ሚካኤል ነው፤ በዚህ በትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ 10 ላይ ዳንኤል ስለ ታላቅ ጦርነት በተገለጠለት ጊዜ ‹‹እነሆም፣ በፍታ የለበሰውን ጥሩም የአፌዝን ወርቅ በወገቡ ላይ የታጠቀውን ሰው አየሁ›› በማለት ይህ ሰው በእጁ እየዳሰሰውና የጸሎቱን መልስ እየነገረው እንዲህ አለው፣ ‹‹እኔም ስለ ቃልህ መጥቻለሁ፡፡ የፋርስ መንግሥት አለቃ ግን ሀያ አንድ ቀን ተቋቋመኝ፣ እነሆም፣ ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ፣ እኔም ከፋርስ ነገሥታት ጋር በዚያ ተውሁት›› (ዳን.10፡13፣21) በማለት ሚካኤል ከአለቆቹ መላእክት መካከል አንዱ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ይሁዳም በመልእክቱ በቁ.9 ላይ፣ ‹‹የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር … ›› ብሎ በሚናገርበት ክፍል ውሰጥ ሚካኤል የተባለው መልአክ አለቃ መሆኑን ያሳያል፡፡ በራዕይ መጽሐፍ ወደፊት ከዘንዶው (ሰይጣን፣ ዲያብሎስ) ጋር እንደሚዋጋ ይናገራል (ራዕ.12፡7-8)፡፡
ነቢዩ ዳንኤል ስለ ተዋጊው መላእክ ሚካኤል ብቻ ሳይሆን፣ ስለ መልእክተኛው ገብርኤልም ጽፎልን እናገኛለን፡፡ ዳንኤል ስለ ተገለጠለት ራዕይ ትኩረት ለመስጠት እያሰበ እያለ፣ ‹‹ እነሆም፣ የሰው ምስያ በፊቴ ቆሞ ነበር፡፡ በኡባኤልም ወንዝ መካከል፡- ገብርኤል ሆይ፣ ራዕዩን ለዚህ ሰው አስታውቀው ብሎ የሚጮኸውን የሰውን ድምፅ ሰማሁ›› በማለት የገብርኤልን መልእክተኛነት ያበስራል (ዳን.8፡16)፡፡ በምዕራፍ 9፡21 ላይም ማቅ ለብሶ በአመድም ላይ ሆኖ፣ ሲጾምና ሲጸልይ እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ ተገልጦለት፣ ለሚጸልይላት ከተማ ‹‹ሰባ ሱባኤ›› መቀጠሩን እንደ ነገረው ይናገራል፡፡ በአዲስ ኪዳንም መልአኩ ገብርኤል ወደ ዘካርያስና ወደ ማርያም መጥቶ ወንድ ልጅ እንደሚወልዱ በየተራ መጥቶ መልእክት እንዳመጣላቸው፣ ሉቃስ በወንጌሉ ምዕራፍ አንድና ሁለት ላይ አስፍሮልን እናገኛለን፡፡
ሐዋርያው ዮሐንስ በራዕዩ ላይ ‹‹ከዚያም ተመለከትሁ፣ የብዙ መላእክትን ድምፅ ሰማሁ፣ ቁጥራቸውም ሺህ ጊዜ ሺህና እልፍ ጊዜ እልፍ ነበር፣ እነርሱም በዙፋኑና በሕያዋን ፍጡራኑ፣ በሽማግሌዎቹም ዙሪያ ከበው ነበር፤ በታላቅ ድምጽም እንዲህ ብለው ዘመሩ፣ ‹የታረደው በግ ኃይልና ባለጠግነት፣ ጥበብና ብርታት፣ ክብርና ሞገስ፣ ምስጋናም፣ ሊቀበል ይገባዋል›› ብለው ለሰው ልጆች ሁሉ አዳኝ ለሆነው ጌታ በአንድነት ሲያመልኩና ሲያመሰግኑ ያሳየናል (ራዕ. 5፡11-12 ዐ.መ.ት)፡፡ መላእክት ስለ ተግባራቸው መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን በስፋት ሲሆን፣ በስም የሚጠቅሳቸው ግን ሁለት ብቻ ሲሆኑ፤ መላእክት ምንም እንኳን ኃይላችው ውሱን ቢሆንም፤ ባላቸው ኃይል እግዚአብሔርን ለማገልገል ራሳቸውን እንደ ሰጡ ሁሉ፣ እኛም ሁላችን ራሳችንን ለጌታ ልንሰጠውና ልናገለግለው ይገባናል፡፡
1፡4 የእግዚአብሔር መልአክ፡- የብሉይ ኪዳን መጻሕፍቶች አብዛኛውን ጊዜ ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ›› ብለው የሚናገሩት ሁለት ትርጉም ይኖረዋል፡፡ አንደኛው መላእክትን በቀጥታ ሲያመለክት፣ ሁለተኛው ደግሞ ‹‹እግዚአብሔር›› ወልድን ያመለክታል፡፡ በመጀመሪያ ለመላእክት የሚያመለክተው ቃል ቀደም ብለን እንደ ተመለከትነው፣ አማርኛችን የ‹‹እግዚአብሔር መልአክ›› ብሎ የሚጠቀመው፣ የዕብራይስጡም ለክርስቶስ የሚጠቀመውን ሲሆን፣ ቃሉም ‹‹ቲኦፈኒ›› ተብሎ ይጠራል፡፡ በዚህም መሠረት በብሉይ ኪዳን ክርስቶስ ለአጭር ጊዜ የመላእክትን ወይም የሰውን ሥጋ ለብሶ ይገለጥ እንደ ነበር መረዳት እንችላለን፡፡ የሚከተሉት ጥቅሶች የ‹‹እግዚአብሔር መልአክ›› እያሉ ክርስቶስን የሚያመለክቱ ሲሆኑ፣ (ዘፍ.16፡10-13፣ 22፡12፣ 31፡11-13፤ ዘፀ.3፡2-3)፤ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኙት ጥቅሶች ደግሞ በግልጽ መላእክትን ያመለክታሉ (2ሳሙ.24፡16፤ መዝ.34፡7፤ ዘካ.1፡11-13፤ ሉቃ.1፡11)፡፡
0 Comments