ወልድ፡- ‹‹እግዚአብሔር ወልድ›› ከሥላሴ አካል አንዱ ሲሆን፤ የሰው ልጆችን ለማዳን ወደዚህ ምድር ከድንግል ማርያም ሥጋ ነስቶ በመምጣትና ለኃጢአታችን በመስቀል ላይ በመሞት ከአባቱ ጋር ያስታረቀን ወልድ ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በቲቶ መልእክቱ ምዕራፍ 1፡1-4 ባለው ክፍል ላይ ‹‹… የማይዋሽ እግዚአብሔር(አብ) ከዘላለም ዘመናት በፊት ተስፋ ሰጠ፣ በዘመኑም ጊዜ፣ መድኃኒታችን እግዚአብሔር (ወልድ) እንዳዘዘ፣ ለእኔ አደራ በተሰጠኝ ስብከት ቃሉን ገለጠ›› በማለት አብንና ወልድን በህላዌ ያላቸውን ግንኙነት በግልጽ በማሳየት፤ ሁለቱን አብሮ በማስቀመጥ ወልድ እግዚአብሔር ተብሎ መጠራቱንና መሆኑን ያሳየናል፡፡ እንዲሁም ቀደም ብለን ባየናቸው ጥቅሶች በማቴ.28፡18፣ በ2ቆሮ.13፡14 ላይ በታላቁ ትእዛዝና በጳውሎስ ሰላምታ ላይ ከሥላሴ ጋር እኩል አብሮ በመጠቀሱ መለኮታዊነቱን በግልጽ ማየት እንችላለን፡፡
ሀ) ይፈጥራል፡- የእግዚአብሔር ወልድ ፈጣሪነትን፣ ስለ እግዚአብሔር አብ ፈጣሪነት ስንመለከት አብረን ያየነው ቢሆንም፣ የሥላሴ አንዱ አካል በመሆኑ በፍጥረት ሥራ አብሮ መካፈሉን፣ አንዳንድ ተጨማሪ ክፍሎችን እንመለከታለን፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በቲቶ መልአክቱ ‹‹እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው፣ የሚታዩትና የማይታዩትም ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ (ወልድ) ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር ነው ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል እርሱም ከሁሉ በፊት ነው›› (ቆላ.1፡15-17) በማለት ፈጣሪነቱን ያረጋግጣል፡፡ ዮሐንስም በወንጌሉ ምዕራፍ 1፡3 ላይ ስንመለከት ‹‹ሁሉ በእርሱ ሆነ…›› በማለት እግዚአብሔር ወልድ በፍጥረት ሥራ ከአብ ጋር ተካፋይ እንደነበረ ያመለክተናል፡፡ ስለ ፈጣሪነቱ አንስተን ስንነጋገር ስለ መለኮታዊነቱም ጭምር እያየን እንደሆነ መረዳት አለብን፡፡ ፈጣሪ ካልሆነ መለኮታዊ፣ መለኮታዊ ካልሆነ ፈጣሪ ሊሆን አይችልም፤ ሁለቱ ነገሮች የተያያዙ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ወልድ (ቃል) በሥጋ በመገለጡ፣ ሊታይ፣ ሊጨበጥና ሊዳሰስ የማይችለውን አብን መግለጥ ችሎአል፡፡
ለ) ያቅዳል፡- ፈጣሪነትና መለኮታዊነት እንደማይነጣጠሉ ሁሉ፣ ፈጣሪነትና አቃጅነትም አይነጣጠሉም፤ ወልድ በፈጣሪነቱ እንደ ተካፈለ፣ እንዲሁ በአቃጅነቱም ከአብ ጋር እንደ ነበረ መረዳት የሚያስቸግር አይደለም፡፡ ማቀድ ብቻ ሳይሆን የታቀደውን በተግባር የመፈጸም ኃላፊነትም የወልድ እንደ ነበረ ከቃሉ እንረዳለን፡፡ የሥላሴ አካላት አብረው ያቀዱትን ወልድ ሰው ሆኖ በመምጣት፣ የታቀደውን ዕቅድ የሰው ልጆችን ድነት ለመፈጸም፣ በመስቀል ላይ ደሙን በማፍሰስ የኃጢአታችንን ዋጋ በመክፈል ፈጸመው፡፡ በዮሐንስ ወንጌል እንደምናገኘው፣ ዕቅዳቸውን ለመፈጸም በተቃረበ ጊዜ፣ ‹‹…አንተን የላክኸውን … እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርኩህ›› (ዮሐ.17፡3-4) በማለት ተልዕኮውን እንደ ፈጸመ አድርጎ ለአባቱ በጸሎት ሪፖርት አቀረበ፡፡ በዚህ ጥቅስ ላይ በአብ መላኩንና በተላከበት ዕቅድ መሠረት ተልዕኮውን መፈጸሙን በግልጽ ይናገራል፡፡ በሌላ ሥፍራም ‹‹የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና›› (5፡30) ‹‹የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ነው እንጂ ብቻዬን አይደለሁም›› (8፡16) በማለት ዕቅድ ፈጻሚነቱን ‹‹ተፈጸመ›› (19፡30) በማለት ተልዕኮውን እንደ ጨረሰ ዮሐንስ በወንጌሉ ላይ አስፍሮ እናገኛለን፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሐሳቦች ከአብ ጋር ስለ ድነት ማቀዱና ዕቅዱን መፈጸሙ፣ ከሥላሴ አካል አንዱ መሆኑን ያረጋግጥልናል፡፡
ሐ) ይወለዳል፡- በእግዚአብሔር አብና ወልድ መካከል የአባትነትና የልጅነት ግንኙነት እንዳላቸው፣ አብም ኢየሱስ በሚጠመቅበት ጊዜ ‹‹የምወደው ልጄ›› (ማቴ.3፡17) ሲል፣ ኢየሱስም ‹‹አባቴ›› (ዮሐ.14፡2፣ 17፡5፣21) እያለ መለኮታዊ ግንኙነታቸውን ሲገላለጹ በቃሉ ውስጥ እንመለከታለን፡፡ ስለ እግዚአብሔር አብ በምናጠናበት ጊዜ አብ ለእስራኤል፣ ለዓለም ሕዝብ ሁሉና ለወልድም አባት እንደሆነ ተመልክተን ነበር፡፡ አሁን ደግሞ እያየን ያለነው የእግዚአብሔር ወልድ ልጅነትን ነው፡፡ ወልድ ከሥላሴ አካል ለመሆኑ ከሚታወቅበት መንገድ አንዱ በልጅነቱ ነው፡፡ ልጅነቱ በመለኮታዊነቱና በሰብዓዊነቱ የሚገልጽ ሲሆን፣ ‹የእግዚአብሔር ልጅና› ‹የሰው ልጅ› በመባል የሚጠራባቸው ስሞች እንደሆኑ በመቀጠል እንመለከታለን፡፡
1) የእግዚአብሔር ልጅ፡- የአብና የወልድ የአባትነትና የልጅነት ግንኙነት እንደ ምድራዊ አባትነትና ልጅነት ሳይሆን፣ ወልድ የአብ የባሕርዩ ልጅ ነው፡፡ ከአንድ ወንድና ሴት የተገኘ ሳይሆን በዕቅዳቸው መሠረት አባትነትና ልጅነትን ይዘው በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት በመታዘዝና በመቀባበል ምሳሌ ሊሆኑን የወሰዱት የሥልጣን ስም ነው፡፡ የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ በምዕራፍ 1፡1-3 ባለው ክፍል ውስጥ የጻፈልንን ስንመለከት ‹‹… ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፣ እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ ሁሉን በሥልጣኑ ቃል እየደገፈ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ…›› በማለት ወልድ ልጅ መሆኑንና በሥልጣን እኩል መሆናቸውን ያመለክታል፡፡
አብ የወልድን ልጅነት ማወጁ፡- ወልድ በሚጠመቅበትና በክብር በተራራው ላይ በተገለጠ ጊዜ የአባቱን ምሥክርነት አግኝቷል (ማቴ.3፡17፣ 17፡5፣ ማር.1፡11)፤ በወልድ በራሱ አንደበት ልጅነቱን መቀበሉን በሚቀጥሉት ጥቅሶች ማየት እንችላለን፡፡ ‹‹የእግዚአብሔር ልጅ›› (ዮሐ.5፡25)፣ ‹‹የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ›› (10፡36)፣ ‹‹የእግዚአብሔር ልጅ›› (11፡4)፣ ‹‹አባቴ›› (5፡17-18)፣ ‹‹የእግዚአብሔር ልጅ ነህን? …እኔ እንደ ሆንሁ እናንተ ትላላችሁ›› (ሉቃ.22፡70)፡፡ መላእክትም የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አውጀዋል (ሉቃ.135)፤ ሰዎች ልጅነቱን መቀበላቸውን መስክረዋል፣ ጴጥሮስ ‹‹አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ›› (ማቴ.16፡16፣ ደቀ መዛሙርት ‹‹በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነህ›› (14፡33)፣ መቶ አለቃውና ጠባቆቹ ‹‹በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ›› (27፡54)፣ መጥምቁ ዮሐንስ ‹‹እኔም አይቻለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ መስክሬአለሁ›› (ዮሐ.1፡34)፣ ናትናኤል ‹‹አንተ የአግዚአብሔር ልጅ ነህ›› (1፡50)፣ አጋንንትም ልጅነቱን ተቀብለው መስክረውለታል፤ ‹‹ኢየሱስ ሆይ፣ የእግዚአብሔር ልጅ ከአንተ ጋር ምን አለን? (ማቴ.8፡29፣ ማር.3፡11፣ ሉቃ.4፡41):: በዚህ ሥፍራ ጠላቶቹ አጋንንት እንኳን ጌታን መዋሸት ስለማይችሉ እውነቱን ተናግረዋል እንጂ፤ አባታቸው ዲያቢሎስ የውሸት አባት በመሆኑ የሚናገሩትን ሁሉ እውነት ነው ብሎ መቀበሉ አደገኛነት አለው፡፡ ስለዚህ አጋንንትን ስናስወጣ የሚናገሩትን ሁሉ እውነት ነው ብሎ ከመቀበል ጥንቃቄ ማድረግ አለብን (ዮሐ.8፡44)::
2) የሰው ልጅ፡- ወልድ የእግዚአብሔር ልጅ መባሉ ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ ተብሎ እንደ ተጠራ መጽሐፍ ቅዱስ በስፋት ያስተምረናል፤ በመለኮታዊነቱ የእግዚአብሔር ልጅ ተብሎ እንደ ተጠራ ሁሉ፣ በሰብዓዊነቱም ‹‹የሰው ልጅ›› ተብሎ ተጠርቷል፡፡ የሰው ልጅ ተብሎ መጠራቱ በአዲስ ኪዳን የጀመረ ሳይሆን በብሉይ ኪዳንም፣ በማርያም ማህፀን ሳያድር በፊት ‹‹የሰው ልጅ›› ተብሎ ተጠርቶአል፡፡ ዳንኤል በትንቢቱ በምዕራፍ 7፡13-14 ላይ ‹‹… እነሆም፡- የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ››፤ ‹‹በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ›› የሚለው ሐሳብ ከዘላለም በፊት የተሰጠው ስም እንደሆነ ያመለክተናል፡፡ ጌታ ራሱ የዳንኤልን ሀሳብ ወስዶ በአዲስ ኪዳን ወደ 84 ለሚሆን ጊዜ ‹‹የሰው ልጅ›› የሚለውን ስም ለራሱ ተጠቅሞበታል፡፡ ‹‹የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል›› (ማቴ.24፡30፣ 26፡64)፣ ‹‹የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአልና›› (ሉቃ.19፡10፣)፡፡ በዚህ ልጅነት በሚለው ርዕስ ሥር መለኮታዊና ሰብዓዊ ስሞቹን ተመልክተናል፡፡ እግዚአብሔር ወልድ በድነት ዕቅዳቸው መሠረት እንደ ልጅ በመሆን የድነትን ሥራ ከፈጸመ በኋላ ‹‹እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርኩህ፤ አሁንም አባት ሆይ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ›› (ዮሐ.17፡5) በማለት የተላከበትን የልጅነቱን ተግባር እንዳከናወነ በጸሎት ለአባቱ አቅርቦአል፡፡
5.4 መንፈስ ቅዱስ፡- ‹‹እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ›› እግዚአብሔር በህላዌው አንድ ነው፤ መንፈስ ቅዱስ የሥላሴ አንዱ አካል ሆኖ ህላዌ ሲኖረው፣ በመለኮት፣ በክብርና በባሕርይ፣ ከአብና ከወልድ እኩል የሆነና በህልውናው ግን ከአብና ከወልድ የሚለይ ነው፡፡ ስለ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ያለን ግንዛቤ ብዙ ጊዜ አናሳና የተለያየ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ኃይል ወይም ንፋስ ብቻ የሚመስለንም አንጠፋም፡፡ ቀጥለን መንፈስ ቅዱስ በሥላሴ ውስጥ እኩል የሚያደርገውን ተግባር እናያለን፡፡
ሀ) ይፈጥራል፡- አብና ወልድ ፈጣሪ እንደሆኑ ሁሉ መንፈስ ቅዱስም ፈጣሪ ነው፤ ቀደም ብለን ስለ ሥላሴ ስንመለከት አንድ አምላክ በሦስት አካል ተገልጦ እንደሚኖር ተመልክተናል፡፡ የሥላሴ ሁለተኛው አካል፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በውኃ በሚጠመቅበት ጊዜ ከሰማይ ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው›› የሚለው ድምጽ ሲመጣ፣ ምስክርነቱን ለማጽናት፣ መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ላይ በርግብ አምሳል ወረደበት (ማቴ.3፡16)፡፡ በዚህ የጥምቀት ሥርዓት ጊዜ ሥላሴን በግልጽ ማየት ብቻ ሳይሆን የሥራ ድርሻቸውንም ማየት እንችላለን፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታላቁን ተልዕኮ ለደቀ መዛሙርቱ በሚሰጥበት ጊዜና ጳውሎስ በጻፈው ደብዳቤ መጨረሻ ላይ ቡራኬ ሲሰጥ መጠቀሱ፣ መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ጋር በመለኮት እኩል መሆኑን ያመለክቱናል (ማቴ.28፡18-20፣ 2ቆሮ.13፡14)፤ መለኮት ከሆነ ደግሞ ፈጣሪነቱን መረዳት አያስቸግረንም፡፡
በዘፍጥረት መጽሐፍ ምዕራፍ 1፡2 ላይ የሚናገረው ሐሳብ በዕቅዳቸው መሠረት አብ ዓለምን ሲፈጥር፣ ወልድ ደግሞ ድረሻውን መወጣቱን ‹‹ሁሉ በእርሱ ሆነ›› (ዮሐ.1፡3) ከሚለው ጥቅስ በፍጥረት ሥራ ተሳታፊ መሆኑን ሲያሳይ፣ ‹‹…የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር›› የሚለውን ሐሳብ፣ ኢዮብ ‹‹የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጠረኝ›› ብሎ ከሚናገረው ጋር፣ (ኢዮ.33፡4) ‹‹በመንፈሱ ሰማያት ውበትን አገኙ›› (26፡13) ከሚለው ጋር፣ የመዝሙረኛው ዳዊትን ‹‹መንፈስህን ትልካለህ ይፈጠራሉም፣ የምድርንም ፊት ታድሳለህ›› (መዝ.104፡30) ከሚለው ጋር ስናገናኘው፤ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ውበት በመስጠት ብቻ ሳይሆን የፈጣሪነት ድርሻውንም ያሳዩናል፡፡
መንፈስ ቅዱስ ከሥላሴ አካል አንዱና መለኮታዊ እንደሆነ ከቃሉ አረጋገጥን፤ መለኮታዊ ከሆነ ደግሞ ለአብና ለወልድ ያየናቸውን ባሕርያት ለመንፈስ ቅዱስም መስጠት ይቻላል፡፡ ከዚህ በፊት ለአብ ካየናቸው ባሕርያት ውስጥ ጥቂቶቹን ብቻ በመውሰድ የመንፈስ ቅዱስን መለኮታዊነቱን የሚያሳዩትን ዋና ዋናዎቹን ባሕርያት ብቻ እንመለከታለን፡፡ መንፈስ ቅዱስ በሚከተሉት ጥቅሶች መሠረት ‹‹ሁሉን ያደርጋል›› (ኢዮ.33፡4፣ ሮሜ.8፤11)፣ ሁሉን ያውቃል (የሐዋ.5፡3፣ 1ቆሮ.2፡10-12)፣ በሁሉ ሥፍራ ይገኛል (መዝ.139፡7)፣ በሁሉ ነገር ላይ ሥልጣን አለው (የሐዋ.13፡2)
መንፈስ ቅዱስ የራሱ አካል ያለውና በራሱ ዕውቀት፣ ስሜትና ፈቃድ የሚኖር፣ በዕቅዳቸው መሠረት የሚወስን፣ የሚያደርግ፣ የሚሾምና ስጦታዎችን የሚሰጥ መለኮታዊ ከሥላሴ አካል አንዱ ሆኖ በፍጥረት ሥራ የተካፈለ መሆኑን መመልከታችን፣ ስለ መንፈስ ቅዱስ ያለንን አመለካከት ያሰፋልናል፡፡ ዛሬም በእያንዳንዳችን ሕይወት ትልቅ ሥራ እንዳለው ወደፊት መንፈስ ቅዱስ በአማኝ ሕይወት በሚለው ጥናታችን በስፋት እንመለከተዋለን፡፡
ለ) ዕቅድ ይፈጥማል፡- መንፈስ ቅዱስ ከሥላሴ አካላት አንዱ እንደ ሆነና በፍጥረት ሥራ እንደ ተካፈለ ተመልክተናል፡፡ በፍጥረት ሥራ ተካፋይ ከሆነ ባቀዱትም ዕቅድ ተካፋይ ለመሆኑ ምንም ጥያቄ ሊኖር አይችልም፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ዕቅድ ፈጻሚነትን በፍጥረት ሥራ ውበት በመስጠትና በክርስቶስ ሕይወት ከመፀነስ ጀመሮ ከሞት እስከ ማስነሳት ድረስ የሠራውን ሥራውን ማየቱ በቂ ነው፡፡ ዕቅድ ፈጻሚነቱን በብሉይና በአዲስ ኪዳን መሠረት፣ ምን ያህል ኃላፊነትና ተግባር እንዳለውና እንዳከናወነ ወደፊት ጊዜ ወስደን፣ የመንፈስ ቅዱስ ሥራዎች በሚለው ርዕስ ሥር የሠራቸውን ሥራዎች በስፋት እንመለከታለን፡፡ ሐ) ይሠርፃል፡- ስለ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና ከአብና ከወልድ ሠርፆ (ወጥቶ) እንደ መጣ እንመለከታለን፡፡ ይህም በህላዌ አንድ መሆናቸውን የበለጠ ያሳያል፡፡ ወልድም ከአብ ወጥቶ እንደመጣ የዮሐንስ ወንጌል ጸሐፊ ‹‹ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለሁ›› በማለት ስለ ራሱ የተናገረውን አስፍሮ እናገኛለን (ዮሐ.16፡28)፡፡ ኢየሱስ ስለ መንፈስ ቅዱስ ‹‹እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ›› (ዮሐ. 15፡26) ‹‹… እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ›› (ዮሐ. 16፡7) የሚለው በዚህ ሥፍራ የሚገኘው አባባሉ አስደናቂ የሆነ የሥላሴን አንድነት፣ በዕቅዳቸውም መሠረት የሥራ ክፍፍላቸውንና አንዱ ለአንዱ ያላቸውን መታዘዝ ማየት ያስችላል፡፡ እነዚህ ሁለት ሐሳቦች የምዕራቡንና የምሥራቁን አብያተ ክርስቲያናት የከፋፈለ ቢሆንም፤ አብ ወልድንና መንፈስ ቅዱስን ሲልክ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ተልከው የድነት ሥራ ለመሥራት ወደዚህ ዓለም ሲመጡ፣ በመላኩ ተግባር ወልድም መንፈስን ከአብ ጋር ሆኖ እንደሚልክ ያለውን እውነታ ያመለክተናል፡፡ በሥላሴ አካል አብ እንደ አባት፣ ወልድ እንደ ልጅ፣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ሠራፂ ሆነው እንደ ተገለጡ ቃሉ ያስተምረናል፡፡ በአማኞች ውስጥ ወልድም መንፈስ ቅዱስም እንደሚኖሩ የሚከተሉት ጥቅሶች ያመለክቱናል (ሮሜ.8፡9-10፣ ገላ.2፡20፣ 1ቆሮ.3፡16፣ 6፡19)፡፡ ከዚህ በላይ ያየነው ጥናት የሚያመለክተን፣ አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ሥላሴ በሚለው መጠሪያ ሥር ያላቸውን ግንኙነትና ልዩነት ለማየት ሲሆን፤ ቀደም ብዬ እንዳልኩት፣ መንፈስ ቅዱስ በሚለውን ርዕስ ሥር ወደ ፊት በስፋት በማጥናት እንመለከተዋለን፡፡ ከአስተምህሮተ እግዚአብሔር ከሚለው ዋና ጥናታችን የሚቀጥለው ስለ አስተምህሮተ መላእክት ይሆናል፡፡
0 Comments