2.4 የእግዚአብሔር መጠሪያ
ስለ አስተምህሮተ እግዚአብሔር ስንጀምር፣ የእግዚአብሔር መኖር በሚለው ርዕስ ሥር እንደተመለከትነው፣ ቃሉ ከሁለት ጥምር ከሆኑ የግዕዝ ቃሎች የመጣና ትርጉሙም ‹‹የሕዝቦች ጌታ›› ማለት እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ ይህ በአማርኛችን ሲሆን፣ በመቀጠል እግዚአብሔር የሚለውን መጠሪያ ስም በመሠረታዊ ቋንቋው እንመለከተዋለን፡፡ ብሉይ ኪዳን በተጻፈበት በዕብራይስጥ ቋንቋ ስናጠና ስም መለያ፣ መጠሪያና የማንነት መገለጫ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በተለይ በዕብራውያን ዘንድ አንድ ስም የባለስሙን ማንነት እንዲያመለክት ብለው ያወጣሉ፡፡ ስለዚህ በዕብራይስጥ ቋንቋ እግዚአብሔር የሚሉት መጠሪያ ስሞች ማንነቱን በሚገልጹ በተለያዩ ስሞች ተጠርቶ እናገኛለን፡፡
እነዚህም ስሞች በሁለት ተከፍለው ሲገኙ፤ የመጀመሪያው እግዚአብሔር ራሱን ለሰው ልጆች በገለጠበትና ባስተዋወቀበት ጊዜ የተጠቀመባቸውና ሰዎች ከተደረገላቸው ነገር የተነሳ ለእርሱ የሰጡት ስሞች ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ እግዚአብሔር ለሙሴ በተገለጠ ጊዜ፣ ‹‹እነሆ እኔ ወደ እስራኤል ልጆች በመጣሁ ጊዜ የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ላከኝ ባልሁም ጊዜ፣ ስሙስ ማን ነው? ባሉኝ ጊዜ ምን እላቸዋለሁ? ብሎ ሲጠይቀው እግዚአብሔርም ሙሴን፡- ‹‹ያለና የሚኖር፣ እኔ ነኝ አለው›› በመቀጠልም ‹‹… ይህ ለዘላለሙ ስሜ ነው›› በማለት ራሱን ‹‹ያህዌ›› በሚለው ስም አስተዋወቀው (ዘፀ.3፡13-15)፡፡ አጋርም ከአብርሃም ቤት ተባርራ በምድረ በዳ በችግር ውስጥ በነበረችበት ጊዜ፣ እግዚአብሔር በመልአክ መልክ በተገለጠላት ጊዜ፣ ከተደረገላት ነገር ተነስታ ‹‹የሚያዬኝን አየሁት›› ስትል እግዚአብሔርን ‹‹ኤልሮኢ›› ብላ ጠራችው፡፡ (ዘፍ. 16፡7-14) ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናያቸው የእግዚአብሔር ስሞች ሁሉ እግዚአብሔር የራሱን ማንነት ለመግለጥ ለራሱ የሰጣቸውና ሰዎች ለእርሱ የሰጡት ስሞች መሆናቸውን ከቃሉ መረዳት እንችላለን፡፡ አስቀድመን ለራሱ የሰጣቸውን መጠሪያ ስሞች እንመለከታለን፡፡
4.1 ራሱን የገለጠበት ስሞች፡- እግዚአብሔር ለሰው ልጆች በተገለጠ ጊዜ መጠሪያ እንዲሆን ራሱን ያስተዋወቀበትና እንዲጠራበት የሰጣቸው ስሞች ሦስት ሲሆኑ፤ እነርሱም ሀ. ኤሎሄም ለ. ያህዌና ሐ. አዶናይ ናቸው፡፡ በተለይም በአዲሱ መደበኛ ትርጉም እያንዳንዳቸው ስሞቹ የት የት እንደተጠቀሱና የትኛውን ትርጉም እንደ ያዙ በደንብ ተለይተው በመቀመጣቸው ለማስተማርም አመቺ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ እነዚህ ስሞች የእግዚአብሔርን ማንነት፣ ባሕርያቱን፣ ኃይሉንና አምላክነቱን ጭምር በስፋት ያሳዩናል፡፡
ሀ) ኤሎሄም፡- በዘፍጥረት 1፡1 ላይ ኤሎሄም የሚለውን ስም የዕብራይስጡ ትርጉም ተጠቅሞበት እናገኛለን፡፡ ትርጉሙም አምላክ፣ ገዢ፣ ፈጣሪ … መሪ ማለት ነው፡፡ ጌታም በመስቀል ላይ ሆኖ ‹‹ኤሎሄ ኤሎሄ ላማሰበቅታኒ›› ብሎ ወደ አባቱ በታላቅ ድምጽ በመጮህ የደረሰበትን መከራ አስታውቋል፡፡ ጌታ በአዲስ ኪዳን የተጠቀመበት ቃል ነጠላ ሲሆን ኤሎሄም የብዙ ቁጥር ነው፣ ቢሆንም ግን ብዛቱ ስንት እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ቃሉ የብዙ ቁጥር ቢሆንም፣ ብዙ አምላኮችን እንዳሉን አያመለክትም፡፡ ምክንያቱም ሙሴ በዘዳግም 6፡4 ላይ እንደምናነበው ‹‹እስራኤል ሆይ ስማ አምላካችን እግዚአብሔር፣ አንድ እግዚአብሔር ነው›› በማለት አረጋግጦልናል፤ ኤሎሄም ከሌሎቹ ስሞቹ ይበልጥ ፈጣሪነቱን፣ ገዥነቱንና ኃያልነቱን ያመለክተናል፡፡
ለ) ያህዌ፡- እግዚአብሔር በሁለተኛ ደረጃ ራሱን ለሙሴ እንዳስተዋወቀውና እስራኤሎች የሚያውቁትና የሚፈሩት ስም ‹‹ያህዌ›› የሚለው ስም ሲሆን፣ እንደ ኤሎሄም የዕብራይስጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙም ‹‹ያለና የሚኖር፣ ዘላለማዊ፣ አዳኝ፣ ራሱን በራሱ ያኖረ፣ ነፃ ሆኖ የሚኖር፣ ሌላ ኃይል ወይም መደገፊያ የማያስፈልገው ማለት ነው፡፡ በእንግለዝኛ (Jehovah) የሚለውን ይጠቀማል፤ አይሁዶች ይህን ያህዌ የሚለውን ስም ከማክበራቸውና ከመፍራታቸው የተነሳ በፍጹም አይጠሩትም፣ ቃሉንም ሲያነቡና ሲያጠኑ፣ በያህዌ ፈንታ አዶናይ ብለው ነው የሚያነቡት (ዘጸ. 3፡13-14፣ 6፡6)፡፡ እግዚአብሔር በዚህ ስም ይበልጥ የሚታወቀው፣ ሕዝቡን ከባርነት በማውጣት ቃል ኪዳኑን በመጠበቁ፣ ቅዱስ በመሆኑና በቅድስና መምራቱንና በሕዝቡ መካከል በመገኘት አምላክነቱን እንደ ገለጸላቸው መጽሐፍ ቅዱስ ሲያስተምረን፤ ስሙም በብሉይ ኪዳን ከ7000 ጊዜ በላይ ተጽፎ እናገኘዋለን፡፡ በአዲስ ኪዳንም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹እኔ ነኝ›› (ያህዌ) በማለት ለራሱ ተጠቅሞበታል (ዮሐ.8፡58፣ 18፡5፡-8)፡፡ እግዚአብሔር የእስራኤል አዳኝ እንደሆነ ሁሉ፣ የእኛም አዳኝ ስለሆነ እንድንድንበት በሰጠን በልጁ በመታመን የዘላለም ሕይወት ወራሾች እንሁን፡፡
ሐ) አዶናይ፡- ሦስተኛው መጠሪያ ስሙ አዶናይ ሲሆን፣ ትርጉሙም ‹‹ጌታ›› ማለት ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን ነቢያቶች ሁሉ ‹‹የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር›› እንዲህ ይላል እያሉ የተናገሩትና የተጠቀሙት በዚህ ስም ነው፡፡ ከላይ እንደተመለከትነው አይሁዶች ዕለት በዕለት ለአምልኮና ለጸሎት በመጥራት የሚጠቀሙበት ስም ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ስም የእኔነትን ትርጉም በመያዝ፣ የእኔ ጌታ አለቃ፣ ገዢ፣ ማለትን ያሳያል፡፡ ኢያሱ በፊቱ የቆመውን ሰው በጠየቀ ጊዜ ያገኘው መልስ ‹‹እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ አሁን መጥቻለሁ አለ›› (ኢያ.5፡14)፤ ኢሳይያስም ‹‹የጌታንም ድምፅ›› ሰማሁ ይላል (ኢሳ.6፡8)፤ ዘካርያስም በመልእክቱ ‹‹የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ›› በማለት ይጠቀማል (ዘካ.8፡1)፤ ከዚህ በላይ ያየናቸው አገልጋዮች ሁሉም አዶናይ የሚለውን ስም ሲጠቀሙበት ቃሉ ያሳየናል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ለእኛ ጌታ ስለሆነ የእኔ ‹‹ጌታ›› እያልን ልንጠራው፣ ልናከብረውና ልንታዘዘው እንደሚገባን ጥናታችን ያመለክተናል፡፡
4.2 በሰዎች የተጠራባቸው ስሞች፡- ከዚህ በላይ ያየናቸው ስሞች እግዚአብሔር ራሱን ለሰው ልጆች ሲገልጥ የተጠቀመባቸው ስሞች ሲሆኑ፤ ቀጥለን የምናጠናቸው ስሞች ሰዎች ከተደረገላቸው ነገር ተነስተው ለእግዚአብሔር የሰጡት ስሞች ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ራሱን ለተለያዩ ሰዎች ሲገልጥ፣ የተጠቀመባቸው ስሞች ጥቂት ሲሆኑ፤ ሰዎች ከተደረገላቸውና ከተሠራላቸው ድርጊት በመነሳት ለእርሱ የሰጡትን ስሞች ከብዙዎች መካከል ጥቂቶቹን ከዚህ በታች በመቀጠል እንመለከታለን፡፡ ሁሉንም ዘርዝሮ ማስቀመጥ ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ ሌሎቹን ለእናንተ ጥናት እንዲሆን በማሰብ ጥቂቶቹን ብቻ አስቀምጫለሁ፡፡
ኤልሮኢ፡- አጋር ከአብርሃም ቤት ኮብልላ በምድረ በዳ በውኃው ምንጭ አጠገብ በነበረች ጊዜ እግዚአብሔር ተገልጦላት፣ ለልጇ ስም በማውጣትና ወደፊት ስለሚገጥመው የሕይወት ጉዞ ሁሉ ስለ ተነገራት፤ ‹‹እርስዋም ይናገራት የነበረውን የእግዚአብሔርን ስም ‹‹ኤልሮኢ›› ብላ ጠራች የሚያየኝን በውኑ እዚህ ደግሞ አየሁትን?›› (ዘፍ.16፡7-13) በማለት እግዚአብሔር ያያል ስትል እንደ ጠራችው ቃሉ ያሳየናል፡፡ ዛሬም በተለያየ ችግር ውስጥ ያለን ብንኖር፣ እግዚአብሔር ችግራችንን ያያል፣ ከችግራችንም ስለሚያወጣን በትዕግስትና በእምነት እንጠብቀው፡፡
ኤልሻዳይ፡- አብርሃም ልጅ በማጣት በሚቸገርበት ጊዜ፣ እግዚአብሔር ራሱ ተገልጦለት፣ ‹‹እኔ ኤልሻዳይ ነኝ በፊቴ ተመላለስ፣ ፍጹምም ሁን›› በማለት እግዚዘብሔር ሁሉን ቻይነቱን ልጅ በመስጠት አስመሰከረ:: (ዘፍ.17፡1) እግዚአብሔር በየዘመናቱ መካን ለሆኑ ቤተ ሰቦች ልጅ ሲሰጥ፣ በቃሉም ደግሞም ብዙዎቻችን የዓይን ምስክሮች ነን፡፡ ይህ ሲባል መካኖች ሁሉ ይወልወዳሉ ማለት አይደለም፤ ምክንያቱም የመካንነቱ ምክንያት ብዙ ስለሆነ፡፡ ከእግዚአብሔር የሆነ፣ (1ኛ ሳሙ.1፡5) በእርጅና (ሉቃ. 1፡18) ከበሽታና ከዘር የሚመጡ መካንነቶች ስለ አሉ፣ ችግራችን የትኛው እንደሆነ ማወቁ ጠቃሚ ነው፡፡ ጌታ ፈቃዱ ከሆነ እነዚህን ሁሉ ችግሮች አስወግዶ መስጠት ይችላልና እንታመነው፡፡
ያህዌ ይርኢ፡- በመቀጠልም የአብርሃምን ታሪክ ስንመለከት፣ እግዚአብሔር ለሃያ አምስት ዓመት ጠብቆ ያገኘውን ልጁን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብለት እንደ ጠየቀው እናያለን፡፡ እርሱም አምላኩን በመታዘዝ ልጁን ለመሠዋት ወደ ሞሪያም ተራራ ይዞ በመሄድ የመሠዊያ ሥፍራ አዘጋጅቶ፣ ልጁን በመሠዊያው ላይ አጋድሞ መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ተዘጋጀ፡፡ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር መታዘዙን ተመልክቶ የሚሠዋውን በግ ራሱ አዘጋጀለትና አብርሃም በጉን መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፡፡ ከዚያ በኋላ አብርሃም የቦታውን ስም ‹‹ያህዌ ይርኢ›› ብሎ ጠራው፤ ትርጓሜውም ‹‹እግዚአብሔር ያዘጋጃል›› ማለት ነው (ዘፍ.22፡1-19)፡፡ አንድ ጓደኛዬ እግዚአብሔር ያላሰበውን ነገር ስላደረገለት የእኔ ‹‹ዶልዷሌ›› ያላሰብኩት ሰጠኝ ብሎ አመሰገነ፡፡ በግላችሁ ለእግዚአብሔር የሰጣችሁት ስም ይኖራችሁ ይሆን?
ያህዌ ሻሎም፡- ቀጣዩ እግዚአብሔር የተገለጠለትና ለእግዚአብሔር ስም የሰጠው ጌዴዎን ነው፤ እርሱም ከጠላቶቹ ተደብቆ በወይን መጥመቂያው ውስጥ ስንዴ እየወቃ ሳለ እግዚአብሔር በመልአክ መልክ ተገልጦለት ‹‹ሰላም ላንተ ይሁን አትፍራ አትሞትም›› አለው፡፡ ጌዴዎንም በዚህ ጊዜ የሥፍራውን ስም ‹‹ያህዌ ሻሎም›› ብሎ ጠራው፣ ትርጉሙም ‹‹እግዚአብሔር ሰላም ነው›› ማለት ነው (መሳ.6፡11-24)፡፡ እግዚአብሔር ለእናንተ ሰላማችሁ ነውን ?
ያህዌ ሮይ፡- መዝሙረኛው ዳዊት ከበግ እረኝነት ለንጉሥነት የታጨ ሰው ነበር፤ ለንጉሥነት ቢታጭም ንጉሥ ከመሆኑ በፊት በብዙ መከራ ውስጥ አልፏል፡፡ ንጉሡ ሳኦል ዳዊት ለንጉሥነት እንደ ተቀባ ባወቀ ጊዜ ሊገድለው ብዙ ጊዜ ከሥፍራ ወደ ሥፍራ አሳዶታል፡፡ በዚህ ጊዜ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹ያህዌ ሮይ›› በማለት ዘመረለት፤ ትርጓሜውም ‹‹እግዚአብሔር እረኛዬ ነው›› ማለት ነው (መዝ.23፡1)፡፡ በዚህ ጊዜ ዓለም በኮቢድ 19፣ ኮሮና ቫይረስ እየተጨነቀች ባለችበት ጊዜ፣ አንድ ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ የሄደ ወንድም በአንድ ፋብሪካ ውስጥ ይሠራ በነበረበት ጊዜ፣ ይህ በሽታ ተከስቶ ሁሉም በየቤቱ ሲቀመጥ፣ እርሱ የሚሠራበት ፋብሪካ ምግብ አምራች ስለነበረ፣ ሥራውን ቀጥሎ ነበረ፡፡ ይህ ኢትዮጵያዊ የሚሠራው ከአርባ ሁለት የአገሬው ተወላጆች ጋር ነበር፡፡ ሁሉም እየሠሩ ሳለ አርባ ሁለቱም ሰዎች በበሽታው ተይዘው፣ ሥራ ሲያቋርጡ፤ እርሱ ግን ሌሎች ሰዎች በምትካቸው ተተክተውለት ሥራውን እየሠራ ይገኛል፡፡ ይህ ወንድም ለእግዚአብሔር ‹‹እግዚአብሔር እረኛዬ ነው›› ከማለት ውጭ ለእግዚአብሔር ምን ስም ይሰጠው ይሆን?
ያህዌ ሻማህ፡- ይህን ስም የምናገኘው በነቢዩ ሕዝቅኤል መጽሐፍ ነው፤ ሕዝቅኤል የእስራኤል ሕዝብ በዓመጹ ምክንያት ወደ ባቢሎን ተማርኮ ሄዶ ሳለ፣ ለነቢይነት አገልግሎት የተጠራ ሰው ነው፡፡ እርሱም በጥሪው መሠረት ምርኮኛውን ሕዝብ ሲያገለግል እያለ፣ ከዕለታት አንድ ቀን እግዚአብሔር በሰው መልክ ተገልጦለት፤ ሕዝቡ ከምርኮ ሲመለስ ምን ዓይነት ቤት እንደሚሠሩና እያንዳንዱ ነገድ በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ሠፍረው እንዴት ማገልገል እንዳለባቸው መመሪያ ሰጠው፡፡ መመሪያ ሰጭውም በምዕራፉ መጨረሻ 48፡35 ላይ ‹‹ከዚያም ቀን ጅምሮ የከተማይቱ ስም፡- እግዚአብሔር በዚያ አለ ተብሎ ይጠራል›› በማለት ‹‹ያህዌ ሻማህ›› የሚለውን ስም እንደተጠቀመ መረዳት እንችላለን (ሕዝ. ምዕ. 47፣ 48 ሁለቱንም ምዕራፍ ተመልከቱ)፡፡
ከዚህ በላይ የተመለከትናቸው መጠሪያ ስሞች ሰዎች እግዚአብሔር ካደረገላቸውና ከሠራው ሥራ በመነሳት የሰጡት ስሞች ናቸው፡፡ ዛሬም በሚገባን ቋንቋችን ለእግዚአብሔር እንደ ጓደኛዬ ‹‹ዶልዷሌ›› ብላችሁ ብትጠሩት አይከፋም፡፡ ከልብ በሆነና በእውነተኛ እምነት ምስጋናችንንና አምልኮአችንን ለእግዚአብሔር እናቅርብለት፡፡ በሚቀጥለው ጥናታችን የመንመለከተው የእግዚአብሔርን አንድነትና ሦስትነት ስለሚገልጠው ሥላሴ ይሆናል፡፡
0 Comments