3.13 ፈራጅ ነው፡- በዚህ በመጨረሻው የእግዚአብሔር ባሕርያት ጥናታችን የምንመለከተው የእግዚአብሔርን ፈራጅነት፣ በሁሉ ሥፍራ መገኘትና አለመለወጡን እንመለከታለን፡፡ መዝሙረኛው ዳዊት ስለ እግዚአብሔር ፈራጅነት ሲናገር ‹‹የእግዚአብሔር ፍርድ እውነትና ቅንነት በአንድነት ነው›› በማለት ሚዛናዊ አምላክ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ፍርዱ የተመሠረተው በቅንነቱ፣ በእውነቱና በጻድቅነቱ ላይ ነው (መዝ. 19፡9)፤ መዝሙረኛው በሌላም ሥፍራ ‹‹እግዚአብሔር መሓሪና ጻድቅ ነው›› (መዝ.116፡5) በማለት ፈራጅነቱ በጽድቅ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ እግዚአብሔር በፈጠረው ፍጥረቱ ላይ የፈራጅነት ሥልጣን እንዳለው ቃሉ ያመለክተናል፡፡ እግዚአብሔር ጻድቁን ሊያመሰግን ኃጢአተኛውን ሊቀጣ የሚችልበት የባሕርይ ብቃት እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ ያሳየናል፡፡
አንዳንድ ጊዜ የእግዚአብሔር ፍርድ የዘገየ ሊመስለን ይችላል፤ ነገር ግን ስለ ፍቅሩና ምሕረቱ ይታገሣል እንጂ፣ ፍርዱ አይቀሬ ነው፡፡ ሲፈርድም በዘመድ፣ በጓደኛ፣ በትውውቅና በገንዘብ ምክንያት ብሎ በትክክል ከመፍረድ ወደ ኋላ አይልም፡፡ በእርሱ ዘንድ አድልዎ የለም፣ ምክንያቱም እርሱ የሰውን ፊት አይቶ አያዳላምና፡፡ እግዚአብሔር ድሆችን፣ ሀብታሞችን፣ የተማረውን፣ ያልተማረውንም በእኩል ዓይን ይመለከታል (መዝ.146፡6-10)፡፡
ጌታም በምድር በነበረበት ጊዜ በደረሰበት መከራና ሥቃይ ምላሽ ሳይሰጥ ‹‹…በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ›› በማለት ጴጥሮስ በመልእክቱ ያመለክተናል (1ጴጥ.2፡23)፡፡ ሥልጣን ያለው ጌታ በሰው ካልፈረደና ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ከሰጠ፣ እኛም በሰዎች በምንገፋበትና በምንጠላበት ጊዜ እግዚአብሔር እውነተኛና ቅን ፈራጅ መሆኑን አውቀን፤ እኛም ጌታ እንዳደረገው አሳልፈን በመስጠት፣ ይህን እውነት ልንቀበለውና ልናምነው ይገባናል፡፡ ከዚህ በላይ ያየነው የእግዚአብሔር ፈራጅነት በዕለታዊ ሕይወታችን በምንሠራው ኃጢአት ላይ የሚፈርድብንን ፍርድ ብቻ ሳይሆን፤ ጌታ በዮሐንስ ወንጌል ራሱ ሲናገር፣ በዘመን ፍጻሜም የመጨረሻውን ወሳኝ ፍርድ እንደሚፈርድም ከአባቱ ሥልጣን ስለ መሰጠቱ ሲናገር ‹‹የሰው ልጅም ስለሆነ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን ሰጠው›› ይላል (ዮሐ. 5፡27)፡፡
3.14 በሁሉ ሥፍራ አለ፡- እግዚአብሔር ፈራጅ ብቻ ሳይሆን፣ በሁሉ ሥፍራ ይገኛል፤ እግዚአብሔር ስለ ራሱ በቃሉ እንዲህ ይላል ‹‹ሰማይ ዙፋኔ ነው፣ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፣ የምትሠሩልኝ ቤት ምን ዓይነት ነው? የማርፍበትስ ስፍራ ምንድን ነው? እነዚህን ሁሉ እጄ ሠርታለችና፣ እነዚህ ሁሉ የእኔ ናቸው›› (ኢሳ.66፡1-2) እያለ ፈጣሪነቱን እያረጋገጠ፣ የተፈጠረ አለመሆኑን እያስረዳና በሁሉ ሥፍራ መገኘቱንም ያረጋግጣል፡፡
እግዚአብሔር በሁሉ ሥፍራ ስለ መገኘቱ፣ መዝሙረኛው በመዝሙሩ እንዲህ ይላል፣
‹‹ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ
ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ
ወደ ሰማይ ብወጣ አንተ በዚያ ነህ፣
ወደ ሲኦልም ብወርድ በዚያ አለህ፣
እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ፣
እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር፣
በዚያ እጅህ ትመራኛለች፣
ቀኝህም ትይዘኛለች›› (መዝ.139፡7-10)፡፡
ስለ ነብዩ ዮናስ በቃሉ እንደምናነበው፣ ወደ ነኔዌ በተላከ ጊዜ ለመሄድ ፈቃደኛ ባለመሆኑ፣ ከእግዚአብሔር ለመኮብለልና ለማምለጥ ሞክሮ አለመቻሉን ይነግረናል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር በሁሉ ሥፍራ እንደሚገኝ ያወቀ አይመስልም፤ እግዚአብሔር ግን በሁሉ ሥፍራ መገኘቱን ተከታትሎ በመያዙ አረጋገጠለት፡፡
እግዚአብሔር በሁሉ ሥፍራ አለ ስንል የጥንት የግሪክ የሥነ ፍጥረት ትምህርት፣ የፓንቴይዝም ትምህርትና የአዲሱ ዘመን እንቅስቃሴ ሁሉ ነገር እግዚአብሔር ነው፣ እግዚአብሔር ሁሉ ነገር ነው፣ ስለዚህ ተፈጥሮ ሁሉ እግዚአብሔር ነው፣ አንተም ራስህ እግዚአብሔር ነህ በማለት እንደሚያስተምሩት ሁሉ ነገር እግዚአብሔር ነው ማለታችን አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በመለኮታዊነቱ በሁሉ ሥፍራ መገኘት ይችላል ማለታችን ነው፡፡
እኛም ጸሎታችንን በየትኛውም ሥፍራ ሆነን ስንጸልይ የሚሰማን በሁሉ ሥፍራ በመገኘቱ ነው፡፡ በቤት፣ በቤተ ክርስቲያን፣ በሜዳ፣ በጫካ፣ በአየር ላይ የትም እንሁን ጸሎታችንን ይሰማል (1ኛ.ነገ.8፡30)፡፡ እግዚአብሔር ምንም ቦታ አይወስነውም፤ ይህ ማለት ግን አንዳንዶች እንደሚሉት በሁሉ ነገር ውስጥ ይገኛል ማለት አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በሁሉ ሥፍራ ይገኛል ስንል እግዚአብሔርን ምንም እንኳን በዓይናችን ማየት ባንችልም፣ እግዚአብሔር ዓይኖቹ በሥፍራ ሁሉ ስለሆኑ እርሱ ሁላችንንም ማየት ይችላል፤ ኃጢአት ስንሠራም ያየናል፣ ከእርሱ መደበቅ አንችልም፡፡ ‹‹እኔ የቅርብ አምላክ ነኝ እንጂ የሩቅ አምላክ አይደለሁም፡፡ ሰው በስውር ቢሸሸግ እኔ አላየውምን ሰማይንና ምድርንስ የሞላሁ እኔ አይደለሁምን ይላል እግዚአብሔር›› (ኤር.23፡23-24)፡፡ ስለዚህ ሁልጊዜ በእግዚአብሔር እንደምንታይ አውቀን በደስታችንም ሆነ በመከራችን ጊዜ በእውነትና በቅድስና ሕይወት እንመላለስ ፡፡
3.15 አይለወጥም፡- የመጨረሻው የእግዚአብሔር ባሕርይ አለመለወጥ ነው፤ መዝሙረኛው በመዝሙሩ ‹‹አንተ ግን ያው አንተ ነህ›› በማለት እግዚአብሔር በፍጹም የማይለወጥ መሆኑን ይናገራል (መዝ.102፡25-27)፡፡ እግዚአብሔር የሰጠንን አየር፣ ውሃ፣ ፀሐይን … ቢወስዳቸውና ያዘጋጀውን ተፈጥሮአዊ ሥርዓት፣ ሥርዓት አልባ እንዲሆን ቢያደርገው ኖሮ ምን ይውጠን ነበር? ሰው ይለዋወጣል፣ እግዚአብሔርን ስናገኝ፣ ጤና ሳንሆን፣ የሚቀርበን ስናጣ፣ ስንታመም የሚተወን አምላክ አይደለም፡፡ እርሱ በማንነቱ፣ በዕቅዱ፣ በተስፋውና በፍጹምነቱ ከቶ ለዘላለም የሚለወጥ አምላክ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በማንነቱ ስለማይለወጥ፣ የሚያቅዳቸውም ዕቅዶቹም አይለወጡም፣ የገባውም ተስፋ አይለወጥም፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ባለመለወጡ ምክንያት በሕይወታችን ባለው ዕቅድና በሰጠን ተስፋ አይለወጥብንም፡፡ በጸጋው በምሕረቱና በስጦታው ባለጠጋ በመሆኑ የሰጠንን ነገሮች እስከ አሁን ድረስ እየተጠቀምንባቸው እንገኛለን፤ ወደ ፊትም ጌታ እስኪመጣ ድረስ እንጠቀምባቸዋለን፡፡ እግዚአብሔር አይለወጥም፣ የሠራቸውም ነገሮች ያለ ፈቃዱ አይለወጡም፣ ስለዚህ እግዚአብሔርን ስላለመለወጡ፣ እንዲሁም የሰጠንን ንፁሕ አየር (Oxgen) ስላልወሰደብን ልናመሰግነውና በእውነትና በመንፈስ ልናመልከው ይገባናል (ያዕ.1፡17፣ ኢሳ.46፡9-10፣ ሚል.3፡6)፡፡ በሚቀጥለው ጥናታችን የእግዚአብሔርን መጠሪያ ስሞች እናጠናለን፡፡
0 Comments