3.10 ሁሉን አዋቂ ነው፡- ባለፈው ጥናታችን እግዚአብሔር ዘላለማዊ፣ ፍቅርና ነፃ መሆኑን ተመልክተን ነበር፤ ዛሬ ደግሞ እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂ፣ ሁሉን ቻይና ከሁሉ በላይ መሆኑን በጥናታችን እንመለከታለን፡፡ እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂ ነው፣ ስንል ዓለም ከመፈጠሩ በፊት የነበረውን፣ ዛሬም ያለውን፣ ወደ ፊትም የሚመጣውን ሁሉ ያውቃል፡፡ ዛሬ ብዙ ሳይንቲስቶችና ጠበብት ባሉበት አገር ዓለም በኮቢድ 19 ምክንያት ግራ እየተጋባች ትገኛለች፡፡ በመጀመሪያ ምን እንደሚመጣ አስቀድሞ የተናገረ አዋቂ ሰው አልነበረም፡፡ አሁንም ክትባትና መድኃኒት ለማግኘት ላይ ታች እያሉ ይገኛሉ እንጂ፣ ከመቅጽፈት መፍትሔውን ያወቀ ማንም የለም፡፡ ነቢዩ ኤርምያስ ከመወለዱ በፊት በማህፀን እያለ በእግዚአብሔር መታወቁን እንዲህ በማለት ይናገራል፤ ‹‹በሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፣ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ›› (ኤር.1፡4)፡፡ በትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ 2፡19-23 ላይ እግዚአብሔር ለንጉሡ ምስጢር በሕልም ገልጦለት፣ በኋላ ላይ የጠፋበትን የሕልሙን እንቆቅልሽ እግዚአብሔር እንደ ገለጠለት ዳንኤል ሲናገር ‹‹ጥበብንና ኃይል ለእርሱ ነውና የእግዚአብሔር ስም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይባረክ፤ ጊዜያትንና ዘመናትን ይለውጣል፣ ነገሥታትን ያፈልሳል፣ ነገሥታትንም ያስነሣል፣ ጥበብን ለጠቢባን እውቀትንም ለአስተዋዮች ይሰጣል፡፡ የጠለቀውንና የተሠወረውን ይገልጣል፣ በጨለማ ያለውን ያውቃል፣ ብርሃንም ከእርሱ ጋር ነው፡፡ ጥበብንና ኃይልን የሰጠኸኝ፣ እኛም የለመንንህን ነገር አሁን ያስታወቅኸኝ፣… የንጉሡን ነገር አስታውቀኸኛልና እገዛልሃለሁ አመሰግንህማለሁ››፡፡ መዝሙረኛውም በመዝሙሩ ደግሞ እግዚአብሔር የከክብትን ብዛት እንደሚቆጥርና በየስማቸው እንደሚጠራቸውም ይናገራል (መዝ.147፡4)፡፡ ቃሉ የእኛም ጠጉርም የተቆጠረ እንደሆነ ይናገራል፡፡

ከእነዚህ ጥቅሶች እንደምንረዳው እግዚአብሔር ዕውቀትን ሁሉ ጠቅልሎ መያዙን ነው፡፡ ዛሬም በሕይወታችን ሆኖ ያለፈውን፣ እየሆነ ያለውንና ወደፊትም የሚሆነውን ሁሉ ያውቃል፡፡ ስለዚህ ወደፊት ምን ይሆናል እያልን ከመጨነቅ፤ ጴጥሮስ በመልእክቱ ‹‹የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ (በእግዚአብሔር) ላይ ጣሉት›› (1ጴጥ.5፡7) እንዳለው ነገን በሚያውቀው በእርሱ ልንታመን፣ በእምነት ልንወጣ ልንገባ ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂ በመሆኑና እኛም በእርሱ በመታወቃችን ደሰ ሊለን ይገባል፡፡

3.11 ሁሉን ቻይ፡- ሁሉን አዋቂነቱ ቀጥለን የምንመለከተው ሁሉን ቻይነቱን ነው፤ መጽሐፍ ቅዱሳችን ገና ከመጀመሪያው እግዚአብሔር ፍጥረትን ከምንም ነገር ሲፈጥርና በቃሉ ብቻ ይሁን እያለ በመፍጠሩ ሁሉን ቻይነቱን ያሳየናል (ዘፍ.1፡1)፡፡ መላውን ዩኒቨርስን ሰማይን፣ ምድርን፣ እንስሳውን፣ አራዊቱን፣ እፅዋቱን፣ የሚታዩትንና የማይታዩትን ሁሉ መፍጠሩ እግጅ የላቀ ችሎታውን ያሳያል፡፡ የሰውን አካላዊ አፈጣጠር፣ ውስጣዊ አሠራርና አገጣጠም እንኳን ብንመለከተው እጅግ የሚገርም ነው፡፡ እስቲ አስቡ ስትሄዱ ሳለ እግራችሁ ጉልበታችሁ ላይ ወደ ፊትና ወደ ኋላ የሚታጠፍ ቢሆን፤  እንዴት መሄድ እንደምንችሉ፣ ሞክሩትና እዩት፤ እጃችሁ ክርናችሁ ላይ በሁለቱም አቅጣጫ የሚታጠፍ ቢሆን ዕቃ ከመሬት እንዴት ታነሱ ነበር? ጅዋጅዌ የምንጫወት ፍጥረት ያደርገን ነበር፤ ሰው መሆን እጅግ በጣም  አስቸጋሪ ይሆን ነበር፡፡ 

በዚህ ምክንያት ይመስለኛል፣ መዝሙረኛው ግሩምና ድንቅ ተደርጌ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ እንዲል ያስገደደው፡፡ የሰው አካሉ እንዴት እንደተሠራ ስንመለከት በጣም አስደናቂና የሚገርም ነው፡፡ የውስጥ ሰውነታችንን አሠራርም ስንመለከት እጅግ አስደናቂ ነው፡፡ አእምሮን፣ ልብን፣ ኩላሊትን፣… እንዲሁም በዓይን የማይታዩት ሴሎችና ነርቮች የመሳሰሉትን ሁሉ ስንመለከት ሰው ምን ያህል የረቀቀ ፍጡር መሆኑን መረዳትና መገንዘብ ምንም የሚያስቸግር አይመስለኝም፡፡ ይህን ሁሉ ድንቅ ሥራ የሠራው እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ ነው፡፡ ስለዚህ አንተም አንቺም የእርሱ ድንቅ እጅ ሥራዎች ናችሁ፤ እግዚአብሔር በፍጥረት ላይ ሁሉን ማድረግ እንደ ቻለ ሁሉ በእኛም ሕይወት ላይ ሁሉን ማድረግ እንደሚችል ሁሉ ቻይነቱን አምነን መቀበል ይኖርብናል፡፡

3.12 ከሁሉ በላይ ነው፡- ከባሕርያቱ ጥናታችን እግዚአብሔር ከሁሉ በላይ ነው የሚል ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን እግዚአብሔር ተፈጣሪ ሳይሆን ፈጣሪ በመሆኑ በሥልጣንም፣ በኃይልም፣ በዕውቀትና በጥበብ ከፍጥረታት፣ ከመላእክትና ከሰዎችም ሁሉ በላይ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለሁሉ ነገር መጀመር ምክንያት ሲሆን ለእርሱ ጅማሬ ምክንያት የሚሆን የለውም፡፡ ስለዚህ እኛ ሰዎች ፍጥረታትን ከፈጣሪ ጋር ማወዳደር በፍጹም አይገባንም፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክቱ ምዕራፍ 1፡11 ላይ ስለ እግዚአብሔር የድነት ዓላማና ዕቅድ ሲናገር፣ ‹‹…እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራ እንደ እርሱ አሳብ፣ አስቀድመን የተወሰንን በክርስቶስ ደግሞ ርስትን ተቀበልን›› በማለት ዓለም ከመፈጠሩ በፊት የዘላለሙን የረጅም ጊዜ ዕቅድ በማቀድ እንደ ዘረጋና በመፈጸም የታወቀ መሆኑን ያስቀምጣል፡፡

ነቢዩ ኢሳይያስ እንደሚነግረን ከፍጥረት ሁሉ በላይ በመሆኑ መላእክት ራሳቸው ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ እንደሚሰግዱለት ይነግረናል (ኢሳ.6፡1-5)፡፡ በፍቅሩም፣ በምሕረቱም፣ በቅድስናውም፣ በርኅራኄውና በቸርነቱም ከሁሉ በላይ ነው፡፡ እምነታችን የተመሠረተው ከሁሉ በላይ በሆነው በእግዚአብሔር ላይ ስለሆነ ምንም የሚያስፈራን ነገር ሊኖር አይገባም፡፡ እርሱ ከተፈጥሮ፣ ከበሽታ፣ ከአጋንንት… ሁሉ በላይ ነው፡፡ እግዚአብሔርን አግኝቶ የተዋጋው፣ የታገለው፣ ያሸነፈውና ድል ያደረገው ምንም ኃይል የለም፤ ባለፈውም፣ አሁንም፣ ወደፊትም አይኖርም፡፡ ምክንያቱም እርሱ የማይታይ፣ የማይጨበጥና የማይዳሰስ አምላክ ነው፡፡ ከሁሉ በላይ ያደረጉትም እነዚህ ባሕርያቶቹ ስለሆኑ እኛም በሁሉ በላይነቱ ላይ ልንደገፍበት ይገባናል፡፡

ጳውሎስ በመልእክቱ ‹የልጁን መልክ እንድንመስል መወሰናችንን›፣ (ሮሜ 8፡29-30) ጴጥሮስ ደግሞ ‹የመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች› መሆናችንን ከመንፈስ ቅዱስ ባገኙት የቃሉ መገለጥ አስረግጠው ጽፈውልናል (2ኛ ጴጥ. 1፡4)፡፡ ስለዚህ እንደ የመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች፣ ከሁሉ በላይ መሆኑን ብቻ ሳይሆን፣ ከዚህ በፊት ያየናቸውን  ባሕርያቱን ሁሉ ተቀብለንና አምነን በቅድስና፣ በምስጋናና በስግደት ለእርሱ ክብር ልንኖርለት ይገባናል፡፡

በዮሐንስ 14፡26 ላይ ‹‹አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል›› በሚለው በቃሉ መሠረት፤ እስከ አሁን ድረስ ካየናቸው የእግዚአብሔር ባሕርያት ብዙ ነገር እንደ ተማራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፤ በመጨረሻ በክፍል አምስት ጥናታችን ስለ ፈራጅነቱ፣ በሁሉ ሥፍራ ስለ መገኘቱና ስለ አለመለወጡ ተመልክተን፤ የእግዚአብሔር መጠሪያ የሚል አዲስ ርዕስ እንጀምራለን፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *