3.7 ዘላለማዊ ነው፡- መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ዘላለማዊነት ሲገልጽ፤ የዘፍጥረት መጽሐፍ 1፡1 ላይ ሲጀምር ‹‹በመጀመርያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ›› ይላል፡፡ በመጀመሪያ በሚልበት ጊዜ መጀመሪያውና መጨረሻው መቼ እንደሆነ በፍጹም ባይታወቅም፤ አብርሃምም በቤርሳቤህ የዘላለሙን አምላክ የእግዚአብሔርን ስም እንደ ጠራ ይነግረናል (ዘፍ.21፡33)፡??፡ ሙሴም በመዝሙሩ ‹‹ተራሮች ሳይወለዱ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ አንተ ነህ›› (መዝ.90፡2) በማለት ዘላለማዊነቱን ያበስራል፡፡ ይህንን እውነት የሚክድ ሰው ያለ ቢሆንም፣ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ በቢሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ወደዚህ ዓለም መጥተው ሁሉም ተመልሰው ሄደዋል፡፡ ዛሬም በዓለም ላይ ያሉ ሰዎች ሁሉ በየተራቸው ወደ አፈርነት ይመለሳሉ፡፡ እግዚአብሔር ሕመም፣ በሽታ፣ ድካምና እርጅና የማያውቀው ከዘላለም እስከ ዘላለም የሚኖር አምላክ እርሱ ብቻ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ በላይ የጠቀስናቸው ነገሮች በእግዚአብሔር ማንነት ውስጥ እንደማይታዩ ያስተምረናል፡፡ ፍጥረት ሁሉ ሲለወጥ፣ በተለይም ቃሉ ስለ ሰው ሲናገር ‹‹ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሣር ነው፣ ክብሩም ሁሉ እንደ ምድረ በዳ አበባ ነው›› በማለት ይናገራል (ኢሳ.40፡6)፡፡ ከሰው ጀምሮ ሁሉ ነገር አላፊና ጠፊ መሆኑን ሲገልጽ፤ እግዚአብሔር ግን ዘላለማዊ የማይለወጥ ጸንቶ የሚኖር መሆኑን ያስተምረናል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ከምንም ነገር ጋር ሊወዳደር አይችልም፡፡ እርሱ በዘፍጥረት መጽሐፍ ምዕራፍ 1፡1 ላይ እንዳየነው ፈጣሪ እንጂ ፍጡር አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ዘላለማዊ ስለሆነ ነበረ፣ አሁን አለ፣ ወደፊትም ይኖራል፡፡ ይህን አምላክ በእውነትና በቅንነት ልናመልከው ይገባል፡፡
3.8 ፍቅር ነው፡- እግዚአብሔር ዘላለማዊ ብቻ ሳይሆን ፍቅርም ነው፤ ሐዋርያው ዮሐንስ በ1ኛ ዮሐንስ መልእክቱ 4፡8-10 ላይ ‹‹እግዚአብሔር ፍቅር ነው›› በማለት ይገልጸዋል፡፡ እግዚአብሔር ፍቅር መሆኑን መረዳት የምንችለው አንድያ ልጁን ለእኛ ኃጢአተኞች አሳልፎ በመስጠቱ ነው፡፡ ይህንንም እውነት ሐዋርያው ዮሐንስ በመቀጠል ‹‹በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና፡፡ ፍቅርም እንደዚህ ነው፣ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም›› በማለት እኛን የወደደበትን የመጨረሻ የፍቅሩን ደረጃ ይገልጻል፡፡ የምንወደድ ሆነን ሳይሆን እግዚአብሔር ፍቅር ስለሆነ ወደደን፣ ጠራን አዳነንም፡፡ የዚህን ፍቅር ውለታ እንመልስ ብንል የምንችለው አይደለም፡፡ ስለዚህ ስለ ወደደን መውደድ ብቻ ይጠበቅብናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለሰው ልጆች የሚያስፈልጉትን ዝናብን፣ ፀሐይን፣ አየርን … በመስጠት ፍቅሩን ገልጾአል፡፡ ታዲያ ስንቶች እንሆን ለዚህ ፍቅሩ፣ እርሱን በመውደድ ምላሽ የሰጠን? ለወደደን ጌታ ምላሽ የሰጠን፣ ለዚህ ለተሰጠን ነፃ ስጦታ እግዚአብሔርን ልናመሰግነውና ልናገለግለው ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር በሁሉ ነገር ፍቅሩን ገልጾልናል ስሙ የተባረከ ይሁን፡፡ ለእኛ ያለው ፍቅሩ አይለወጥም፣ እኛም እንዳንለወጥበት በፍቅራችን እንጽና፡፡
3.9 ነጻ ነው፡- ቀደም ብለን እንዳየነው እግዚአብሔር ዘላለማዊ፣ ፍቅር እንደሆነ አይተናል፤ አሁን ደግሞ ነጻ መሆኑን እንመለከታለን፡፡ እግዚአብሔር በባሕርዩ ነጻ መሆኑን ሐዋርያው ጳውሎስ የነቢዩ ኢሳይያስን መጽሐፍ በመጥቀስ በሚከተለው መንገድ ያስቀምጠዋል፡፡ ‹‹የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፣ ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፣ ለመንገዱም ፍለጋ የለውም፡፡ የጌታን ልብ ያወቀው ማን ነው? ወይስ አማካሪው ማን ነበር? ወይስ ብድራቱን ይመልስ ዘንድ ለእርሱ አስቀድሞ የሰጠው ማን ነው? ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም ነውና፣ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን አሜን›› (ሮሜ.11፡33-36) በማለት እግዚአብሔር በባሕርዩ ነጻ መሆኑንና እርሱ በማንም አለመፈጠሩንና የማንንም እርዳታ አለመፈለጉን ያመለክታል፡፡ እርሱ ለሁሉ ነገር መፈጠርና መኖር ምክንያት ነው፡፡ የእርሱ መኖር ግን በማንም ምክንያትነት የመጣ አይደለም፡፡ ከተፈጥሮ ሕግ፣ ከቦታ ውስንነት፣ ከኃጢአት እንዲሁም ከድካም፣ ከእንቅልፍ፣ ከበሽታ… ሁሉ ነጻ ሆኖ ይኖራል፡፡ እርሱ ሁላችንንም ይረዳል እንጂ፣ የማንንም እርዳታ አይሻም፡፡
ባለፈው ጥናታችን ለሕይወታችሁ የሚቀርላችሁ፣ ምን አዲስ ትምህርት አገኛችሁበት? በሚቀጥለው ክፍል አራት የእግዚአብሔር ባሕርያት ጥናታችን ሁሉን አዋቂነቱን፣ ሁሉን ቻይነቱንና ከሁሉ በላይ መሆኑን እንመለከታለን፤ እስከዚያው እናንተም በሕይወታችሁ ከእነዚህ ባሕርያቱ ምን መማር እንዳለባችሁ፤ እየጸለያችሁ ቆዩ፡፡ ጌታ ካሰብነው በላይ ያስተምረናል፤ ጌታ በሰላም ያቆየን፣ ያገናኘን፡፡ መልካም የጥናት ጊዜ ይሁንልን፡፡
0 Comments