3.4 አይወሰንም፡- ከዚህ ቀደም ብለን ባለፈው ጥናታችን እንደ ተመለከትነው፤ እግዚአብሔር ኃያል በመሆኑና ሰው ባለመሆኑ በምንም ነገር አይወሰንም፡፡ ዳዊትም በመዝሙሩ ‹‹እግዚአብሔር ታላቅ ነው፣ … ለታላቅነቱም ፍጻሜ የለውም፡፡ ትውልደ ትውልድ ሥራህን ያመሰግናሉ፣ ኃይልህንም ያወራሉ›› (መዝ. 145፡3-4) በማለት ሲገልጸው፤ ሐዋርያው ጳውሎስም ‹‹ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም›› (የሐዋ. 17፡24) በማለት ኃያልነቱንና የማይወሰን መሆኑን ይገልጻል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር በኃያልነቱ ምክንያት በቦታ፣ በጊዜ፣ በአካል የሚወሰን አምላክ አይደለም፡፡ እግዚአብሔርን ማየት፣ መዳሰስና መጨበጥ ባንችልም ታላቁን ጌታ እንደ እኛ ልንወስነው አይገባም፡፡ እግዚአብሔር ባለ መወሰኑ ምክንያት ዓለምን ስለሚሞላ በዓለም ዙሪያ ያሉ የሰው ልጆችን ጸሎት ሁሉ በአንድ ጊዜ መስማትና መመለስ ይችላል፡፡
3.5 እውነት ነው፡- መጽሐፍ ቅዱስ በሮሜ 3፡4 ላይ ‹‹… ሰው ሁሉ ውሸተኛ ከሆነ እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን›› በማለት የእግዚአብሔርን ባሕርይ ይገልጻል፡፡ እግዚአብሔር በባሕርዩ እውነተኛ በመሆኑ የሰው ልጆች የሚገባቸውን ነገር ሁሉ እንዲያውቁ አድርጓል፡፡ የሰው ልጅ ግን በኃጢአቱ ምክንያት ይህን እውነት ሊያውቅ አልወደደም፡፡ ሰው ግን እውነትን በዓመፃ ለወጠ፤ በዚህም ምክንያት በሰው ላይ ስለ መጣበት ነገር ሲናገር፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ምዕራፍ ሮሜ.1፡18 ላይ እንዲህ ይላል፣ ‹‹እውነትን በዓመፃ በሚከለክሉ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በዓመፃቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ ከሰማይ ይገለጣልና››፡፡ የጌታ ቁጣ ከመገለጡ በፊት የሰው ልጆች ይህን እውነት እንዲያውቁ፣ እግዚአብሔር ልጁን እንደ ላከው ቃሉ ይናገራል፡፡
በቲቶም መልእክቱ ምዕራፍ 1፡2 ላይ ‹‹…እንደ አምልኮት ያለውን እውነት እንዲያውቁ የተላከ ስለዚህም ሕይወት የማይዋሽ እግዚአብሔር ከዘላለም ዘመናት በፊት ተስፋ ሰጠ›› ይላል፡፡ በዚህም ተስፋ መሠረት በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 14፡6 ላይ እንደምናገኘው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ ለብሶ በመምጣት ‹‹እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ›› በማለት ተናገረ፡፡ መናገር ብቻ አይደለም ለእውነት ኖረ፣ ሞተ፡፡ በአባቱ የተገባውን ቃል ኪዳን በመፈጸም፤ እግዚአብሔር ውሸት እንደማይናገር አረጋገጠ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ውሸት በፍጹም አይናገርም፣ አይሠራም የተናገረውንም በጊዜው ይፈጽማል፡፡ ሰዎች ኃጢአት ይሠራሉ፣ በእግዚአብሔር ስም ይዋሻሉ፣ ያታልላሉ፣ እውነተኛ ለመምሰል ይሞክራሉ፡፡ ኃጢአት ምንም ጊዜ ቢሆን በእርሱ ፊት መጋለጡ ስለማይቀር ከቅጣት ማምለጥ የሚችል የለም፡፡ እኛም ወደ ቅጣት እንዳንመጣ በንግግራችን፣ በሥራችንና በተግባራችን የእውነት ልጆች መሆናችንን ማረጋገጥና ማስመስከር አለብን፡፡
3.6 ቀናተኛ ነው፡- እግዚአብሔር እውነተኛ ብቻ ሳይሆን ቀናተኛም አምላክ ነው፤ ለእስራኤላውያን በሰጣቸው ከአሥርቱ ትእዛዛት አንዱ፣ በዘፀዓት መጽሐፍ ምዕራፍ 20፡6 ላይ ‹‹…እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና›› ይላል፡፡ ቀናተኛ የሚለውን ቃል ስንሰማ ወይም ስናነብ የሚሰማን ደስ የማይል፣ አሉታዊ (nagative) ሊሆን ይችላል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን የሚያቀርበው ጠቃሚ በሆነ በአዎንታዊ (positive) ጎኑ ነው፡፡ ሙሴ በመጻሕፍቱ እንዲህ ይላል ‹‹ስሙ ቀናተኛ የሆነ እግዚአብሔር ቅንዓት ያለው አምላክ ነውና ለሌላ አምላክ አትስገድ›› (ዘፀ.34፡14፣ ዘዳ.4፡24፣ 5፡10)፤ ኢሳይያሳም በመልእክቱ ምዕራፍ 48፡11 ላይ በይበልጥ እንዲህ በማለት ይገልጠዋል፣ ‹‹…ክብሬንም ለሌላ አልሰጥም›› የሚሉት ቃሎች ሁሉ የእግዚአብሔርን ቀናተኛነት የሚያመለክቱ ሲሆኑ፣ ለፈጠራቸው ሰዎች ያለውን ፍቅሩን ያሳያሉ፡፡ የእርሱ ፍጥረት የሆኑ ሁሉ ከእርሱ ውጭ ማንንም እንዳያመልኩ፣ እነርሱም ሌላ አምላክ አምልከው ክብራቸውን እንዳይጥሉና እንዳያጡ ይፈልጋል፡፡
በዚህ ምክንያት በራዕይ መጽሐፍ ምዕራፍ 4፡11 ላይ ‹‹ጌታችንና አምላካችን ሆይ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር፣ ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል›› ባሉት መሠረት እኛ ለእርሱ እነዚህን ነገሮች ማድረግ እንደሚገባን ይናገራል፡፡ ይህ የእውነተኛ አምልኮ የጤናማነት መሠረት ነው፡፡ ጴጥሮስ በሁለተኛ መልእክቱ 1፡4 ላይ ‹‹…ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል እንድትሆኑ፣ በእነዚያ ክብርና በጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋ ሰጠን››፡፡ በማለት በጌታ አማካኝነት ያገኘነውን ታላቅ በረከትና ኃላፊነት ያመለክተናል፡፡ ስለዚህ ከእግዚአብሔር ሌላ ማንንም እንዳናመልክ ቃሉ ይከለክለናል፤ አምልከን ብንገኝ እግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ በመሆኑ እንደ እስራኤላውያን በምርኮ ባይሆንም፤ በግል በተለያዩ ቅጣቶች ውስጥ ሊያሳልፈን ይችላል፡፡ በዛሬው ጥናታችን እግዚአብሔር በምንም ነገር አለመወሰኑ፣ እውነተኛና ቀናተኛ አምላክ በመሆኑ ምን ትምህርት አገኛችሁበት? በሚቀጥለው ጊዜ ጌታ በሰላም ያድርሰንና ዘላለማዊ፣ ፍቅርና ነጻ የማንንም እርዳታ የማይፈልግ አምላክ መሆኑን ጌታ በረዳን መጠን እንመለከታለን፡፡
0 Comments