6.5 የቃሉ ኃይል

ቀደም ባለው ጥናታችን ቃሉን አስፈላጊነት ተመልክተናል፤ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ አስፈላጊ የነፍሳችን ምግብ መሆኑንም አይተናል፡፡ ቃሉ ምግብ ብቻ ሳይሆን ኃይልም እንዳለው ቀጥለን እንመለከታለን፤ ሰው የእግዚአብሔርን ቃል ሲሰማ ሕይወቱ ይለውጣል፤ ምክንያቱም  ቃሉ ኃይል ስለ አለው ነው፡፡ ኢሳይያስ የቃሉን ኃያልነት ሲገልጽ በትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ 55፡11 ላይ እንዲህ ይላል፣ ‹‹ቃሌ የምሻውን ያደርጋል እንጂ በከንቱ ወደ እኔ አይመለስም›› ይላል፡፡ በየዘመናቱ ኃይለኛ የሆኑ ሰዎችን ቃሉ ሲነካቸው፣ ሲሰብራቸው፣ ሲፈርድባቸውና ሲያንጻቸው በተለያዩ ሰዎች ሕይወት ማየት እንችላለን፡፡

በብሉይ ኪዳን ታላቁን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር እንደ አውሬ ሣር ለሰባት ዓመት መብላቱ፣ (ዳንኤል 4፡15-16)፤ እንዲሁም ልጁ ብልጣሶር ማኔ፣ ቴቄል፣ ፋሬስ (እግዚአብሔር መንግሥትህን ቆርጦ ለሜዶናና ፋርስ ሰጠው) በሚለው ቃል ከሥልጣኑ መውረዱን እንመለከታለን (ዳን. 5፡25-28)፡፡ በአዲስ ኪዳን ደግሞ እንደ ሳውል ያለውን ‹‹ሳውል ሳውል፡- ስለ ምን ታሳድደኛለህ የሚለው ቃል ትጥቁን እንዳስፈታው እንመለከታለን (የሐዋ. 9፡4)፡፡ በመቀጠል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የቃሉን ኃያልነት የሚያሳዩትንና በተለያዩ ምሳሌዎች የተመሰለባቸውን ነገሮች እንመለከታለን፡፡ እነርሱም ዘር፣ እሳት፣ መዶሻና ሰይፍ ናቸው፡፡

በዘር፡- ማንኛውም ዘር ጤናማ ከሆነ ራሱን የመተካት ኃይል አለው፡፡  ስንዴ ቢዘራ ስንዴን፣ ማሽላ ቢዘራ ማሽላን እንደሚያፈራ ሁሉ፣ ማንኛውም ሕይወት ያለው ነገር ሁሉ ራሱን የመተካት ኃይል እንዳለው ሁሉ፤ እንዲሁም ቃሉ በሰው ሕይወት በሚዘራበት ጊዜ ሕይወት ይበቅላል፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስ በስደት ለነበሩት አማኞች መልእክት በጻፈበት ጊዜ እንዲህ ይላል፤ ‹‹ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፣ በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ … የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ይኖራል›› (1ኛ ጴጥ. 1.23-24) በማለት ቃሉ በሰው ልጆች  ውስጥ ሕይወትን  ሲዘራ ኃይል ስለ አለው ይበቅላል፡፡

በእሳት፡- የእግዚአብሔር ቃል እሳት ወርቅን እንደሚያነጥር ሁሉ ቃሉም የሰዎችን ልብ  በማንጠር የተለወጠ ሕይወት እንዲኖራቸው የማድረግ ኃይል አለው፡፡ መዝሙረኛው በመዝሙሩ ‹‹ጎልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል፣ ቃልህን በመጠበቅ ነው›› በማለት ቃሉ የማያስፈልገውን ነገር ሁሉ ከሕይወታችን አስወግዶ እንደሚያነጻን ይናገራል፡፡ (መዝ.    119፡9) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር በነበረበት ጊዜ ወደ አባቱ ሲጸልይ ሳለ ‹‹በእውነትህ ቀድሳቸው፣ ቃልህ እውነት ነው›› በማለት ቃሉ ሕይወት መስጠት ብቻ ሳይሆን የመቀደስ ኃይል እንዳለው ያረጋግጥልናል (ዮሐ.17፡17-19)፡፡ ቃሉ ዕለት በዕለት እንዲቀድሰን፣ በጌታ ፊት ሁልጊዜ በጸሎት እንቅረብ፡፡

በመዶሻ፡- ነቢዩ ኤርምያስ የእግዚአብሔር ቃል መዶሻ ድንጋይን እንደሚያደቅቅ እንዲሁ እንደ ተራራ ከፍ ያለውን የሰውን ልብ በመስበርና በማድቀቅ ወደ ፍርድ ሊያመጣ እንደሚችል ይናገራል፡፡ ቃሉ ወደ ሰዎች ሲመጣ አንዳንዱን ለሕይወት ሲተክል፣ ሌላውን ለጥፋት ሊነቅል፣ ሊያጠፋና ሊገለብጥ የሚችል ኃይል ያለው መሆኑን ይገልጻል፡፡ (ኤር. 1፡10፣23፡29) በአማኝም ሕይወት እንዲሁ የሚያስወግደው፣ የሚያፈርሰውና የሚያስተካክለው ነገር እንዳለው መረዳት እንችላለን፡፡ እግዚአብሔር ድንጋይ ልባችንን ይስበርልን እንጂ፤ እኛ ለፍርድ አንሰበርበት፤ ጌታ ይርዳን አሜን!በሰይፍ፡- ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክቱ መጽሐፍ ቅዱስን (ቃሉን) በሰይፍ መስሎት እናገኘዋለን፡፡ ‹‹… የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው›› በማለት ቃሉ የጠላታችንን ዲያብሎስን ሽንገላ የምንቃወምበት፣ የምናጠቃበትና ድል የምናደርግበት መሣሪያችን እንደ ሆነ ይናገራል (ኤፌ. 6፡11፣ 17)፡፡ ቃሉ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ንዴትን፣ ቁጣን፣ መራርነትን፣ ጩኸትንም፣ መሳደብንም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከሕይወታችን የማያስፈልጉትን ነገሮች በመቁረጥ ሊቀርፀንና ሊሠራን ይችላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ በብርሃን ተመስሎ እናገኛለን፤ መዝሙረኛው በመዝሙሩ ‹‹ሕግህ (ቃልህ) ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴ ብርሃን ነው›› ይላል፡፡ (መዝ.119፤105)፣ በመቀጠልም መዝሙረኛው ዳዊት ‹‹ከወርቅና ከክቡር ዕንቁ ይልቅ ይወደዳል፣ ከማርና ከማር ወለላም ይጣፍጣል›› በማለት ሲገልጽ፣ ሐዋርያው ዮሐንስም ‹‹ከመልአኩም እጅ ታናሽቱን መጽሐፍ ወስጄ በላኋት በአፌም እንደ ማር ጣፋጭ ሆነች›› በማለት የቃሉን አስፈላጊነት ይገልጻል፡፡ (መዝ.19፡7፣10፤ ራዕ.10፡10)፣ ሐዋርያው ያዕቆብ ደግሞ ፊት በሚታይበት መስተዋት፣ (ያዕ.1፡23)፤ ሐዋርያው ጴጥሮስም ሕፃን ልጅ በሚጠጣው በወተት ይመስለዋል፡፡ (1ጴጥ.2፡2)፣ ስለዚህ  ከዚህ በላይ እንዳየነው ቃሉ ለሕይወታችን እጅግ አስፈላጊ፣ ኃይል፣ ምግብና ሥልጣን ያለው ስለሆነ፤ ዘወትር በየቀኑ ማንበብ፣ ማጥናትና ማሰላሰል ይገባናል፡፡ ዕለት በዕለት የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ እንድንችል የሚረዳንና ለድል ሕይወታችን ሁልጊዜ ልንለብሰው የሚገባን የጦር ዕቃችን ነው፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *