የፍቅር መልእክትነቱ
በቀደመው ጥናታችን የመጽሐፍ ቅዱስን አስፈላጊነት ተመልክተናል፤ አሁንም በዚህ ጥናታችን ጨምረን የቃሉን አስፈላጊነት እናጠናለን፡፡ እግዚአብሔር ለሰዎች በየዘመናቱ፣ ከዘፍጥረት ጀምሮ እስከ ራዕይ ድረስ ያለውን ስንመለከት አጠቃላይ መልእክቱ የፍቅር ደብዳቤ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እግዚአብሔር ጤናማ ግንኙነት ለመፍጠር በየጊዜው ለሰው ልጆች የላከው መልእክት እጅግ አስገራሚ ነው፡፡ ሰው ባለመታዘዙ ምክንያት ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ጤናማ ግንኙነት ቢበላሽም፣ እግዚአብሔር ለሰው ካለው ፍቅር የተነሣ፣ ገና ከጥዋቱ ሰውን መፈለግ ጀመረ፡፡ እግዚአብሔር ፍቅር በመሆኑ፣ አዳም ኃጢአት ሠርቶ በተሸሸገበት ቦታ ድረስ ሄዶ ሲፈልገውና ሕብረት ሲመሠርት እንመለከታለን፡፡ አዳምን ከተደበቀበት ቦታ በመፈለግ ፍቅሩን ቆዳ በማልበስ ገለጸለት፤ በመቀጠልም አንድን ቤተ ሰብ (አብርሃምን) በመምረጥ የራሱን መንግሥት እንዲያውጅለት አደረገው፡፡ በመቀጠልም በየዘመናቱ ነቢያትን አስነስቶ ፍቅሩን፣ ምክሩንና ቁጣውን በደብዳቤ ወደ ሰው ልጆች ሲልክ ቆየ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር አዳምና ሔዋን የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ባለ መጠበቅ ከእግዚአብሔር ጋር ሕብረት ከሚያደርጉበት ከኤደን ገነት እንዴት እንደተለዩ፣ ከዚያም እግዚአብሔር በሙሴ አማካኝነት ሕግ በመስጠት እንደገና ሕብረት ለመመሥረት ማቀዱን ያመለክታል፡፡ ሕብረቱ የሚፈጸምበት ቤተ መቅደስ እንዲሠራለትና በዚያ ሕብረት ለማድረግ ማቀዱን፤ በመቀጠልም በነቢያት መልእክቶችን በማስተላለፍ ወደፊት በክርስቶስ በኩል ሊሠራው ያሰበውን ዕቅዱን መያዙን ያሳያል፡፡ አዲስ ኪዳንም እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለሰው ልጆች በመስቀል ላይ የሠራውን የደህንነት (ድነት) ሥራና ወደ ፊት የዋጃቸውን ልጆቹን ለመውሰድ እንደሚመጣ ያለውን የዘላለም ዕቅዱን ያመለክተናል፡፡
በዘፍጥረት መጽሐፍ ስንመለከት የፍጥረትን አጀማመርና አመጣጥ እንዲሁም የሰውን ያለመታዘዝና በኃጢአት መውደቅ፣ የእግዚአብሔርና የሰው ሕብረት መቋረጡን ማመልከት ብቻ ሳይሆን፣ ይህን የተቋረጠውን ሕብረት እንደገና ለመቀጠልና ለማደስ በሙሴ በኩል የሕግና የአምልኮ ሥነ ሥርዓት መሰጠቱንም ጭምር ያመለክተናል፡፡ በመቀጠልም በተለያዩ ነብያት አማካነኝነት የተበላሸውን ሕብረት ለማደስ እግዚአብሔር እርምጃ ወስዷል፡፡ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የመጨረሻውን የማደስ ሥራ ሠርቶ ወደ ሕብረቱ መለሰን (1ቆሮ.1፡9)፡፡ በራዕይ መጽሐፍ እንደምንመለከተው በዚህ ሕብረት በአዲስ ሰማይና ምድር አብረን እንደምንኖር ያመለክታል፡፡
ከወዳጃችን ከእግዚአብሔር የተላከውን የፍቅር ደብዳቤ የሆነውን የእግዚአብሔር ቃል ዘወትር በደስታና በናፍቆት፣ ከምንወደው ሰው እንደ ተጻፈልን ደብዳቤ ሁልጊዜ ማንበብ ደስ እንደሚለን ሁሉ፣ የእርሱንም ደስ እያለን ልናነበው ይገባናል፡፡ ምክንያቱም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እግዚአብሔር ሊነግረን የሚሻው አንድ ትልቅ ነገር ቢኖር በክርስቶስ በኩል አዲስ ሕይወት ልናገኝ መቻላችንን ነው፡፡ ‹‹በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና›› (ዮሐ. 3፡16) ይህ ጥቅስ የእግዚአብሔር ፍቅር የተገለጠበትና በልጁ የሚያምን ሁሉ የማይጠፋ ዘላለማዊ ሕይወት እንደሚያገኝ ይገልጣል፡፡
በአዲስ ኪዳንም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የአባቱንና የራሱን ፍቅር ይዞ በመምጣት፣ ይህን ፍቅር ሲገልጸው እንዲህ ይላል ‹‹ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም›› (ዮሐንስ 15፡13) በማለት አስቀምጦታል፡፡ ከኃጢአት የተነሳ ሙታን የሆኑት ሰዎች ሁሉ ወደ ኢየሱስ ካልመጡ በስተቀር ሕይወት ሊያገኙ አይችሉም፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የሚያስተላልፉት መልእክት ቢኖር ይህንኑ ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ጌታ ሊመጡ የሚወዱ ሁሉ ይህን ፍቅሩንና አዲስ ሕይወት ያገኛሉ፤ ከእግዚአብሔር ጋርም በመታረቅ፣ ሰላምና ደስታ ይሆንላቸዋል (ዮሐ. 5፡39)
በዚህ በፍቅር ደብዳቤ አማካኝነት ‹‹ኢየሱስ›› ክርስቶስና የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን የሚያምን ሁሉ በስሙ ሕይወት እንደሚሆንለት ቃሉ ይናገራል (ዮሐ. 20፡31)፤ በመጨረሻም ዮሐንስ በመልእክቱ እንዲህ ይላል፣ ‹‹የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ›› (1ኛ.ዮሐ. 5፡13)፡፡ የፍቅር መልእክቱ አስፈላጊያችን ነው፤ ታዲያ ይህ የፍቅር ደብዳቤ ደርሷችኋል? አንብባችሁታል? በፍቅር ደብዳቤው አማካኝነት አዲሱን ሕይወት ማግኘታችሁን ማረጋገጥ ትችላላችሁ? ያረጋገጥንም ጌታን እናመስግን፡፡
6.4 አስፈላጊነቱ
የመጽሐፍ ቅዱስን አንድነት፣ ሥልጣንና የፍቅር መልእክትነቱን በተመለከትነው መሠረት ለእያንዳንዳችን አስፈላጊያችን እንደ ሆነ መረዳት ይኖርብናል፡፡ ሥጋችን ህልውናው ተጠብቆና ኃይል አግኝቶ እንዲኖር ምግብ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ነፍሳችንም መንፈሳዊ ምግብ ያስፈልጋታል፡፡ በ1ኛ ጴጥሮስ መልእክት ምዕራፍ 2፡2 ላይ ‹‹ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደ ሆነ፣ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኮል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ›› በማለት የእግዚአብሔር ቃል መንፈሳዊ ምግባችን እንደሆነ ይናገራል፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር በነበረበት ጊዜ በሰይጣን ሲፈተን፣ ከመለሰለት መልስ እንደምናገኘው፣ ሰውም ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ እንደማይኖርም ጌታ በቃሉ ተናግሮአል (ዘዳ.8፡3፣ ማቴ. 4፡4.)፡፡ ይህ ማለት ሰው ለመኖር እንጀራ መብላት የለበትም ማለቱ አይደለም፡፡ ለሥጋው የሚበላ ነገር እንደሚያስፈልገው ሁሉ ለነፍሱም መንፈሳዊ ምግብ፣ የእግዚአብሔር ቃል ያስፈልገዋል ማለቱ ነው፡፡
መዝሙረኛውም በመዝሙር 119፡103 ላይ ስለ ቃሉ ምግብነት ሲናገር፣ ‹‹ቃልህ ለጉሮሮዬ ጣፋጭ ነው›› በማለት የፍራፍሬ ምግብ ዓይነት ጣፋጭ መሆኑን ያሳያል፡፡ ምዕራፉን በሙሉ ብንመለከት የቃሉን አስፈላጊነት በግልጽ የሚያሳዩ ብዙ ሐሳቦች አሉት፤ መንገዶቼ ይቀኑ ዘንድ፣ ሕያው እንድሆን፣ እንደ ቃልህ አስተዋይ አድርገኝ በማለት የቃሉን አስፈላጊነት በስፋት ይዘረዝራል፡፡ በተጨማሪ ነቢዩ ኤርምያስም በትንቢተ ኤርምያስ 15፡16 ላይ ‹‹ቃልህ ተገኝቶአል እኔም በልቼዋለሁ›› ሲል የቃሉን አስፈላጊነት አጉልቶ አሳይቶአል፡፡ እኛም እንደ ዳዊትና ኤርምያስ ቃሉ አስፈላጊያችን ስለ ሆነ ልንናፍቀውና ዘወትር በየቀኑ ልንመገበው (ልናነበው፣ ልናጠናው) ይገባናል፡፡
0 Comments