1.5 እውነተኛ ቃል

የእግዚአብሔር ቃል ከሰዎች ቃል ሁሉ የበለጠና የላቀ እውነተኛና ታማኝ ቃል ነው፡፡ እግዚአብሔር በየዘመናቱ  ለሰዎች የተናገረውን ሲፈጽም የኖረ፤ አሁንም እየፈጸመ የሚገኝ፤ ወደ ፊትም እየፈጸመ የሚኖር አምላክ ነው፡፡ እኛ ፍጥረቶቹ የሆንን ሰዎች እንኳን በምንነጋገራቸው እውነተኛና ታማኝ ቃሎች አማካይነት እርስ በርሳችን በመተማመን መልእክት እንለዋወጣለን፣ ሀሳብ ለሀሳብ እንግባባለን፤ ገንዘብ እንኳን ሳይቀር ያለ ምንም ማስረጃ በቃላችን ብቻ ተማምነን እንበዳደራለን፡፡ ምንም እንኳን ሁልጊዜ ባይሆንም በመካከላችን በእውነተኛ ቃል በመጠቀም በማህበራዊ ኑሮአችን እንመላለሳለን፡፡

የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በብራናና በፓፒረስ ላይ እየተጻፉ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፉ፤ የእግዚአብሔር ቃሎች ሆነው ምንም ሳይጨመርባቸውና ሳይቀነስባቸው ወደ ዘመናችን ለመድረስ ችለዋል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል እውነተኛ መሆኑን ከምንረዳበት መንገድ አንዱ፣ ከዕብራይስጡ ወደ ልዩ ልዩ ቋንቋ እየተተረጐመ፣ ከዘመን ወደ ዘመን ሳይለወጥ መቆየቱና ረጅም ዕድሜ በማስቆጠሩ ነው፡፡

በብሉይ ኪዳን የነበሩ ነብያት መልእክታቸውን ሲያስተላልፉ ‹‹እግዚአብሔር እንዲህ ይላል›› በማለት  መናገራቸው የቃሉን እውነተኛነት ለማሳየት ከተጠቀሙበት መንገድ አንዱ ነበር፡፡ እንዲህ ብለው ተናግረው የተናገሩት ቃል ባይፈጸም፣ በድንጊያ ተወግረው ስለሚሞቱ መልእክት የሚያስተላልፉት ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ ነበር፡፡ ነብያት የማይፈጸም ቃል ቢናገሩ በድንጋይ ስለሚያስወግራቸው እግዚአብሔር የሰጣቸውን ብቻ እንደ ተናገሩ መረዳት እንችላለን፡፡ ከእግዚአብሔር ዘንድ እውነተኛ ትንቢት ስላመጡና ውሸተኛ ትንቢት ስላመጡ አገልጋዮች በእግዚአብሔር ዘንድ ምን ምላሽ እንደሚያገኙ ቃሉ የሚለውን እንመልከት፡፡ ለዚህም ማስረጃ እንዲሆን የሚከተሉትን ጥቅሶች ማንበብ ተገቢ ይሆናል፡፡ (ዘኊ. 22፡38፣ 23፡12፤ ዘዳ.18፡18-23፤ 1ኛ.ነገ. 14፡18፤ 2ነገ. 9፡36፣ 14፡25፤ ኤር. 1፡9፤ ሕዝ.13፡1-7፤ ዘካ. 7፡7፣12፤)  

በዚህም ምክንያት አይሁድ በታማኝነት ከትውልድ ወደ ትውልድ እውነተኛ የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል ማስተላለፋቸውን በየዘመናቱ የተነሡ ሊቃውንት የዕብራይስጡንና የግሪኩን ቅጂዎች በማመሳከር አረጋግጠዋል፡፡ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትም የብሉይ ኪዳንን መጻሕፍት እውነተኛ የእግዚአብሔር ቃል መሆናቸውንና ታማኝነታቸውን ቅዱሳት መጻሕፍት በማለት መስክረውላቸዋል፡፡ (2ጢሞ. 3፡16 ተመልከቱ) ስለዚህ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ ልናምነውና የሚለውን ተቀብለን ልናነበው፣ ልናጠናውና ልንመራበት ይገባናል፡፡

አዲስ ኪዳን ስለ ብሉይ ኪዳን ብቻ ሳይሆን ስለ ራሱም የእግዚአብሐር ቃልነትና ታማኝነት ይመሰክራል፡፡ ሐዋርያው  ጴጥሮስ በመልእክቱ የጳውሎስ መልእክቶች ሁሉ ቅዱሳት መጻሕፍት መሆናቸውን፤ ‹‹የጌታችንም ትዕግሥት መዳናችሁ እንደ ሆነ ቁጠሩ፡፡ እንዲህም የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ ደግሞ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ›› በማለት መስክሯል (2ጴጥ.3፡15-16)፡፡ እንዲሁም ሐዋርያው ጳውሎስም ክርስቶስ በምድር በነበረበት ጊዜ የተናገረውን ቃል ሁሉ መጽሐፍ በማለት ጠርቶአቸዋል (ሉቃ.10፡7፤ 1ጢሞ.5፡18. ሁለቱን ጥቅሶች አመሳክሩ)፡፡

በ1947 ዓ.ም በሙት ባሕር አጠገብ የተገኙት የጥንት ጥቅልል መጻሕፍት የብሉይና የአዲስ ኪዳንን እውነተኛነትና ታማኝነት ይበልጥ ማረጋገጥ ችለዋል፡፡ እነዚህ በተለያየ ጊዜ በእጅ ተጽፈው የተገኙት ቅጂዎች፣ በአስራ ሁለተኛው ክፍለ ዘመን በእጅ ተጽፈው ከሚገኙት 5000 መጻሕፍት በላይ ከሚሆኑት፤ የአዲስ ኪዳን ጽሑፎች ጋር ሲተያዩ ምንም ስሕተት አልተገኘባቸውም፡፡ ስለዚህ የእነዚህ የጥንታዊ ቅጂዎች ማስረጃነታቸው እጅግ ጠንክሮና ከብሮ ይገኛል፡፡

ስለዚህ ከዚህ የምንረዳው ነገር ቢኖር ቃሉ የእግዚአብሔር ስለሆነ፤ እውነተኛነትና ታማኝነት እንዳለው መረዳት እንችላለን፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም በ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 14፡37 ላይ ‹‹የጌታ ትእዛዝ መሆኑን ይወቅ›› በማለት ቃሉ እውነተኛነትና ታማኝነት እንዳለው ተቀብሎ ሌሎችም እንዲቀበሉት ማድረጉን ገልጾአል፡፡ ጌታም በምድር በነበረ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ የብሉይ ኪዳንን መጻሕፍት ያለማመናቸውን ነቅፎአቸዋል፡፡ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 24፡25 ላይ ‹‹እናንተ የማታስተውሉ ነቢያትም የተናገሩትን ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ›› ብሎ የእስራኤልን ሕዝብ ሲወቅስ እንመለከታለን፡፡ ስለዚህ በነቢያትና በሐዋርያት የተጻፈው ቃሉን፣ ሰዎች ሁላችንም ይህን እውነተኛና ታማኝ የሆነውን ቃል ልናነበው፣ ልንታዘዘውና ልንጠብቀው እንደሚገባን መረዳት ይኖርብናል፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስም ‹‹በቅዱሳን ነቢያትም ቀድሞ የተባለውን ቃል በሐዋርያቶቻችሁም ያገኛችሁትን የጌታንና የመድኃኒትን ትእዛዝ እንድታስቡ በሁለቱ እያሳሰብኋችሁ ቅን ልቡናችሁን አነቃቃለሁ›› (2ጴጥ. 3፡2) በማለት እውነተኛውን ቃል እንዲታመኑበት ማሳሰቡ፤ ለእነርሱ ብቻ ሳይሆን፣ እኛንም በዚህ ዘመን ያለን ሰዎችን ሁሉ ይመለከታል፡፡

በመጨረሻም የቃሉን እውነተኛነትና ታማኝነት የምናየው በየዘመናቱ የሰዎችን ሕይወት መለወጥ በመቻሉ ነው፡፡  ከአሳዳጁ ሐዋርያው ጳውሎስ ጀምሮ የነፍሰ ገዳዮችን፣ ሌቦችን፣ አመንዝራዎችን፣ ሱሰኞችንና ሰካራሞችን ሕይወት ሁሉ  ለውጦአል፡፡ ቃሉ ሰላማዊ፣ ጨዋ፣ ራሱን የሚገዛና ሰውን ወዳድ አድርጎ በመለወጥ ለሚሠራው ሥራና አዲስ ሰው ለማድረጉም በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ምሥክር ሆነው አልፈዋል፤ ዛሬም ብዙዎች ምሥክሮች አሉ፡፡ ስለዚህ እኛም በዚህ ዘመን የምንገኝ አማኞችም ሆንን ያልሆንም የእግዚአብሔርን የቃሉን (መጽሐፍ ቅዱስ) እውነተኛነትና ታማኝነት እውነት መሆኑን ተቀብለን ልናነበው፣ ልናጠናው፣ ልንለወጥበትና ልናድግበት ይገባል፡፡ እግዚአብሔርም ቃሉን ለሕይወታችን መዳኛ፣ ማደጊያ፣ መጽናኛና ፈቃዱን ማወቂያ አድርጎ ስለ ሰጠን፣ ልናመሰግነው ይገባናል፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል የሚጠራጠር ልብ ይኖርህ ይሆን? አትጠራጠር እመነው፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *