እኔ የዛሬ ሠላሳ አምስት ዓመት የመጽሐፍ ቅዱስ አጠናን ዘዴ በኢቲሲ ስማር፣ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አጠናን ዘዴ/ ትምህርት የሚረዱ የአማርኛ መጽሐፍት አልነበሩም፤ ትምህርት ካቆምኩኝ ጥቂት ዓመታት አልፈው ስለነበረ፣ እንግሊዝኛው ለእኔ ላቲን ሆኖብኝ ነበር፡፡ በተቻለ መጠን በመፍጨርጨርና ጊዜ በመስጠት፣ በአስተማሪዎችም ዕርዳታ ትምህርቱን መከታተል ቻልኩኝ፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን በዚያው ዓመት የማታ መጽሐፍ ቅዱስ ትምሀርት ቤት ከፍታ ማስተማር ጀመረች፤ በዚህ ጊዜ በኢቲሲ መማሬ ስለሚታወቅ፣ ይህን ኮርስ እንዳስተምር በትምህርት ቤቱ ኃላፊ ተጠየኩኝ፡፡ እኔም ለማስተማር ስዘጋጅ፣ ለሁለት ወር ያህል ስለ (የክረምት ኮርስ) ነበር የተማርኩት፣ ብዙ ያወቅሁ መስሎኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ማስተማር ስጀምር ዓይኔ ፍጥ ብሎ ግራ ገባኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ኢቲሲ ለትምህርት ስሄድ በዚያው፣ ይህን ኮርስ ያስተማረኝና አሁንም በበጋው ይህን ኮርስ በድጋሚ እየሰጠ የሚገኘው ሚስተር (መጋቢ) እስቲቭ ስትራውስ ነበር፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን የማታ መጽሐፍ ቅዱስ ት/ቤት እንደ ከፈትን ነገርኩትና እርሱም በጣም ደስ አለው፤ እኔም ከአንድ ወር በፊት ከአንተ የወሰድኩት ትምህረት በጣም ከብዶኛልና እባክህን የምፈልገው ርዕስ ላይ ገብቼ እንድማር ፍቀድልኝ፣ አልኩትና ፈቀደልኝ፡፡ ትምሀርቱ የሚሰጠው ለአራት ወር ሲሆን እኔ የምፈልገው ትምህርት ላይ ብቻ እየገባሁ ለሁለት ወር ሳልከፍል እየተማርኩኝ፣ በቤተ ክርስቲያኔም ደግሞ ያንኑ ትምህርት እያስተማርኩ ቆየሁ፡፡ በዚህ አላበቃም እንደገና ይህ ኮርስ በሌላ ጊዜ ሲሰጥ፣ የምፈለገው ርዕስ ላይ ገብቼ ለአንድ ወር ተማርኩኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ይህን ትምህርት መጽሐፍ ባልጽፍበትም በብዙ ሥፍራ አስተምሬአለሁ፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላ በዚያው በኢቲሲ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ አስተማሪ ሆኜ ለአራት ዓመት ካስተማርኩ በኋላ፣ በተለያየ ችግር ምክንያት አቋርጬ ከአራት ዓመት በኋላ እንደገና የድግሪ ትምህርቴን መማር ጀመርኩ፡፡ ይህን ምስክርነት ላካፍላችሁ የቻልኩት፣ ይህን ትምህርት ወደ ትምህርት ቤት ገብታችሁ ለመማር ዕድል ላላገኛችሁ፣ ተስፋ ሳትቆርጡ እኔ ምንም አልጠቅምም ሳትሉ፣ ከሰውም በመማር፣ ከመጽሐፍም በማንበብ ትምህርት ቤትም ገብቶ በመማር ለራሳችሁና ለሌሎችም ጠቃሚ ሰዎች እንደትሆኑ ይጠቅማችኋል ብዬ ስለ አሰብኩኝ ነው፡፡ በእኔ ማስተማር ተጽዕኖ አድሮባቸው መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ገብተው፣ ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ከእኔ የበለጠ ተወዳጅ አስተማሪ የሆኑ ወንድሞች አሉ፡፡ እኔም ከማስተማር ያለፈ፣ የመጻፍ ልምድ ባይኖረኝም፣ ያለኝን የቃሉን መረዳት ላካፍላችሁ ብዬ የጀመርኩት፣ ጌታ አዘጋጅቶ በከፈተልኝ ‹‹ዌብ ሳይት›› አማካኝነት ነው፡፡ ስለዚህ በርቱና ቃሉን ባገኛችሁት መንገድ ሁሉ ቃርሙ፣ ጌታም ይረዳችኋል፤ አንዳንዶቻችሁንም ለአገልግሎቱ የሚፈልጋችሁ ትኖራላችሁ ብዬም አምናለሁ፡፡
አሁን ከምስክርነቱ ወደ ትምህርታችን እንመለስ፤ ዛሬ ለመጨረሻ ጊዜ በእኛና እግዚአብሔር መካከል ባለ ግንኙነት ስለ ማህበረ-ሰባችን/ኅብረተ-ሰባችን ምን የሚናገረን መልእክት እንዳለው ከትንቢተ ዮናስ መጽሐፍ ያጠናነውን ክፍል አብረን እንመለከታለን፡፡ ሙሉን ምዕራፍ 1-4 ያለውን እንዳጠናችሁት፣ የበለጠ የክፍሉን ሐሳብ መረዳትና ማስተዋል ችላችኋል ብዬ አስባለሁ፡፡ መጽሐፉን በሙሉ በዝርዝር ባናየውም ሐሳቡን ጠቅለል አድርጎ የሚያሳየውን ጥቅስ እንመልከት፡፡

‹‹እግዚአብሔርም ዮናስን፡- በውኑ ስለዚች ቅል ትቈጣ ዘንድ ይገባሃልን? አለው፡፡ እርሱም ፡- እስከ ሞት ድረስ እቈጣ ዘንድ ይገባኛል አለ፡፡ እግዚአብሔርም ፡- አንተ ትበቅል ዘንድ ላልደከምህባት ላላሳደግሃትም በአንድ ሌሊት ለበቀለች፣ በአንድ ሌሊትም ለደረቀችው ቅል አዝነሃል፡፡ እኔስ ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ ከመቶ ሀያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሶች ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ አላዝንምን? አለው፡፡›› (ቁ. 9-11) ይህ ክፍል የመጽሐፉን ጠቅላላና ዋና ሐሳብ ያሳየናል፡፡ ክፍሉን ስንመለከተው ዮናስ ቃሉን በኃጢአቷ ምክንያት ልትጠፋ ላለችው ለነነዌ (ለአሶራውያን) ከተማ ሕዝብ መልእክት እንዲያደርስ ሲላክ ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ምክንያቱም አሶራውያን የእስራኤል ጠላቶች ስለሆኑ እንዲድኑ ሳይሆን እንዲጠፉ ነው የሚፈልገው፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ ሕዝቦቼ ናቸውና ሄደህ ቃሌን ንገራቸውና ከማጥፋቴ በፊት በንስሐ እንዲመለሱ አድርግ ሲባል እንቢ ብሎ ኮበለለ፡፡ በኰበለለበት ሥፍራ በዓሳ ይዋጥና እግዚአብሔር ከዚያ ያወጣውና እንደገና ወደ ነነዌ ልኮት፣ ቃሉን ተናገሮ ሕዝቡ በንስሐ ተመለሰ፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን ይቅር አለ፡፡ በዚህ ጊዜ ነው ከላይ እንዳየነው፣ ዮናስ ከእግዚአብሔር ጋር ክርክር የገጠመው፡፡ ከዚህ መጽሐፍ በሕይወታችን የምንተገብረው ምን ያስተምረናል፡፡ ሁላችንም ከዚህ ክፍል ብዙ ልንማርበት እንችላለን ብዬ አስባለሁ፡፡ እኔ ከዚህ ክፍል የተማርኩትና በሕይወቴ መተግበር ያለብኝ፣ ከእኔ ዘር ውጭ ያሉትን ሰዎች ሁሉ እኩል መውደድና ማገልገል እንዳለብኝ አስተምሮኛል፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን ቤተ ክርስቲያኔም በማህበረ-ሰብ ውስጥ ያሉትን ከአማኞች ውጭ ያሉት ሰዎች ሁሉ መውደድና ማገልገል እንዳለባቸው አሳይቶኛል፤ ይህን ሁልጊዜ በሕይወታችን መተግበር እንዳለብን በሚገባ ተምሬአለሁ፡፡ በዚህ በሦስተኛው ክፍል የመጽሐፍ ቅዱስ አጠናን ዘዴ ወደ ማዛመድ ከመጣን ጊዜ ጀምሮ፣ የተመለከትነውንና የተረጐምነውን ከሕይወታችን ጋር እንዴት ማዛመድና በተግባር ማዋል እንዳለብን ከመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ክፍሎችን ወስደን ተመልክተናል፡፡ ‹‹አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ የእግዚአብሔርን ቃል ለመፍታት ይቻለው ዘንድ፣ ለመማር፣ ለማወቅና ለማደግ የሚያስፈልጉትን ብዙ ፍሬ አሳቦች ተመለክተናል፡፡ በአጠቃላይ ግን የመጀመሪያውና መሠረታዊው መስፈርት፣ የእግዚአብሔርን ቃል መራብ ነው … በሚያነቡበት ጊዜ፣ ጥናትዎ ሕይወትዎን በብዙ አቅጣጫዎች የሚለውጠው መሆኑን ይወቁ፡፡ ይህ ድርጊትዎ የአንድ መጽሐፍ ጥናታዊ ትንታኔ ብቻ ሳይሆን፣ ከሕያው እግዚአብሔር ጋር መገጣጠም (መገናኘት) ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር እርሱንና ቃሉን በመታዘዝ እንዲሁም በመታመንና በማፍቀር እንዲያድጉ የሚፈልግብዎ ሲሆን፣ በየደረጃውም ይረዳዎታል፡፡›› (መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ ለመረዳት በቲ.ኖርተን ስቴሬት፣ ትርጉም በተክሉ መንገሻ ገጽ 156) ቀደም ባለው ጊዜ እንዳየነው ወደ ማዛመድ ስንመጣ ልንረሳቸው የማይገቡ ነገሮች እንዳሉ ተመልክተናል፡፡

ይህም በእግዚአብሔርና በእኔ፣ በቤተሰቤ፣ በቤተ ክርስቲያኔና በማህበረ-ሰቤ መካከል ስላለው ግንኙነት ምን ይናገረኛል ብሎ መጠየቅና በሕይወት ተግባራዊ ማድረግ ትልቅ ጥበብና ዕውቀት፣ እንዲሁም እግዚአብሔር የሚደሰትበትና የሚባርከው ሕይወት ይሆናል፡፡ ስለዚህ ያነበብነውንና የተረጐምነውን እውነት ወደ ተግባራዊ ሕይወት ለማዛመድ ከልባችን ጥረት በማድረግ፣ እርምጃ እንውሰድ እንጂ ሰሚዎች ብቻ አንሁን፡፡ እግዚአብሔር ሁልጊዜ በቃሉ ሲናገረን እንስማ፣ በተግባር ለማድረግ እንታዘዘው፣ እርሱም ጸጋውንም ያበዛልናል፡፡ ሕይወታችንን ይባርካል፡ በአገልግሎታችንም ፍሬአማዎች ያደርገናል፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስ አጠናን ዘዴ እዚህ ላይ ጨርሻለሁ፤ በሌላ ርዕስ እስከምንገኛኝ ጌታ ከሁላችንም ጋር ይሁን፤ ጠቃሚ ሆኖ ካገኛችሁት በመጽሐፍ እንዲወጣ በጸሎታችሁ አስቡኝ፡፡ በርቱ ቃሉን የተመገበ ወድቆ አይወድቅም፣ በቃሉ ራሳችንን ስለምንገዛና ኃጢአትን ስለምናሸንፍ ከአሸናፊዎች ሁሉ እንበልጣለን፡፡ የጌታ ስም የተባረከ ይሁን፡፡

1 Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *