በዛሬው ጥናታችን የምንመለከተው ክፍል የኤፌሶን መልእክት ምዕራፍ 5፡21-33 ይሆናል፤ ከዚያ በፊት አስቀድመን በባለፈው የተሰጠውን የጥናት ክፍል ምን እንደ ተማርንበትና በተግባር ልናውለው የሚገባንን አብረን እንይ፡፡ የጥናት ክፍላችን የነበረው የሉቃስ ወንጌል 2፡41-52 ነበር፣ በተግባር የምታውሉት ምን ትምህርት አገኛችሁበት?
በዚህ ክፍል ወላጆችም ልጆችም የምንማረውና በተግባር ልናውላቸው የሚገቡ ብዙ ቁም ነገሮች አሉ፡፡ በቁጥር 41 ላይ ወላጆቹ ኢየሱስን ወደ ፋሲካ በዓል ይዘው መውጣታቸው፣ እኔ ለልጆቼ መንፈሳዊ ሕይወት መንገዱን የማሳየት ኃላፊነት እንዳለብኝ ተምሬአለሁ፡፡ ኢየሱስም ወላጆቹን ታዞ መውጣቱም፣ ልጆቻችን ለቤተ ሰባቸው መታዘዝ እንዳለባቸው ሊማሩበት ይገባል ብዬ አስባለሁ፣ ከማሰብም በላይ እጸልያለሁ፡፡
በመቀጠል ቁጥር 44 ላይ ወላጆቹ ልጃቸው የት እንዳለ ሳያውቁ የአንድ ቀን መንገድ ከሄዱ በኋላ፣ በአጠገባቸው ሲፈልጉት አጡት፣ ከዚያ ሦስት ቀን ሙሉ ፈለጉት፡፡ ባገኙት ጊዜ ‹‹እናቱም ፡- ልጄ ሆይ ለምን እንዲህ አደረግህብን እነሆ አባትህና እኔ እየተጨነቅን ስንፈልግህ ነበርን አለችው››፣ የራሳቸውን ጥፋት በልጃቸው ላይ አድርገው ቁጭ አሉ፡፡ በ(ቁጥር 49) ላይ የሰጣቸው መለስ የበለጠ ሳያበሳጫቸውና ይህ ልጅ ጉርምስና ከአሁኑ ጀምሮታል (እኛ እንደምንለው) ብለው ሳያስቡ አልቀሩም ብዬ አስባለሁ፡፡
እርሱም ‹‹ስለ ምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን?›› ብሎ የመለሰላቸው መልስ፣ ከዮሴፍ ሌላ (የእንጀራ አባት) አባት አለው እንዴ የሚል፣ የበለጠ ሌላ ጥያቄ የሚያጭር ቢሆንም፤ ይህ አነጋገሩ ለሁለቱም ምንም ባይገባቸውም፣ እናቱ ግን በልቧ ትጠብቀው እንደ ነበረ ቃሉ ይናገራል፡፡ ከዚህ የተማርኩት ነገር ቢኖር የራሴን ጥፋት መቀበል ሲኖርብኝ፣ ወደ ልጆቼ መውሰድ እንደሌለብኝ ነው፡፡ በመጨረሻ በ(ቁጥር 51) ላይ ‹‹…ይታዘዝላቸውም ነበር›› ከሚለው የተማርኩት ነገር ቢኖር በኢየሱስና በወላጆቹ መካከል የተፈጠረውን የአስተሳሰብ ልዩነት (generation gap) የምንለውን በማጥበብ ከወላጆቹ ጋር ወደ ትውልድ አገሩ አብሯቸው ተመልሶ በመታዘዝ አገለገላቸው፡፡ የማርቆስ ወንጌል ጸሐፊ ኢየሱስ ለሠላሳ ዓመት ቤተ ሰቦቹን ማገልገሉን የአናጺው ልጅ በማለት ዘግቦት እናገኛለን፡፡ ልጆቻችን ለወላጆቻቸው መታዘዝን ከዚህ መማር አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡
ኢየሱስ ለወላጆቹ በመታዘዙ ምክንያት እግዚአብሔር ያሳድገው እንደ ነበረ የሚቀጥለው ጥቅስ ያሳየናል፤ ‹‹ኢየሱስም ደግሞ በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ያድግ ነበር›› (ቁጥር 52) ከዚህ ክፍል በሕይወታችን ልንተገብረው የምንችለው ብዙ ትምህርት ማግኘት እንችላለን፡፡
አሁን ወደ ዛሬው ጥናታችን እንሄዳለን፤ በሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክቱ በመጀመሪያዎቹ ሦስት ምዕራፎች ስለ ዶክተሪን (ትምህርተ-መለኮት) ከጻፈ በኋላ በሚቀጥሉት ሦስት ምዕራፎች የጻፈው የተማሩትን ትምህርት እንዴት መኖር እንዳለባቸው በማዘዝ ነው፡፡ በዚህ በተሰጠን ምዕራፍ 5 ከቁጥር አንድ ጀምሮ እስከ ሃያ ድረስ አማኝ ክርስቲያኖች ሁሉ እንዴት መኖር እንደሚገባቸው ካመለከተ በኋላ፣ ከቁጥር 21 ጅምሮ እስከ ሠላሳ ሦስት ድረስ ባልና ሚስት እርስ በእርሳቸው በመታዘዝና በመከባበር እንዲኖሩ ያዛቸዋል፡፡
ይህን ክፍል በመመልከትና በመተርጐም ካየን በኋላ ከሕይወታችን ጋር የምናዛምዳቸውን በመንቀስ እንመለከታለን፡፡ ቀደም ብለን የመልእክት ጽሑፎችን ስናጠና እንዳየነው፣ ከጽሑፎች ሁሉ ቀላሉ እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ ያሉትን ሊጠየቁ የሚገባቸውን መጠየቅ፣ ቃላትን መተርጐም የመሳሰሉትን ሁሉ አድርገን ወደ ማዛማድ እንመጣለን፡፡ ወደ ማዛመድ ስንመጣ በእኛና በእግዚአብሔር፣ በእኛና ቤተሰባችን፣ በእኛና በቤተክርስቲያን እና በእኛና በሕብረተ-ሰባችን መካከል ስላው ግንኙነት፣ ጌታ በመንፈሱ ምን የሚናገረን ነገር ይኖር ይሆን? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ በመተርጐም የምናገኘው እውነት አንድ ሲሆን፣ ማዛመዳችን ግን በዛ ያለ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ጥናታችን በእኛና ቤተሰባችን መካከል ባለው ግንኙነት እግዚአብሔር የተናገረንን እውነት ከሕይወታችን ጋር እናዛምድ፡፡
እኔ ይህን ክፍል ሳጠና በመጀመሪያ ያገኘሁት በቁጥር 21 ‹‹ለእያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ›› በሚለው ጥቅስ ላይ ‹‹ የተገዛችሁ እና ፍርሃት›› የሚሉትን ለመተርጐም ሙከራ አድርጌአለሁ፡፡ መገዛት የሚለው ቃል መጽሐፍ ቅዱስን ከኀምሳ ዓመት በፊት ለተረጐሙ ሰዎችና ለእኛ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ለምንኖር ሰዎች የሚሰጠን ትርጉም በጣም የተለያየ ክብደት አለው፡፡ በመሠረታዊ ቋንቋም ሆነ፣ በእንግሊዝኛውም ‹‹መገዛት›› (submission) ማለት መታዘዝ ማለት ነው፡፡ ከዚህ ለግሌ የተማርኩትና በሕይወቴ መተግበር ያለብኝ፣ ለጌታ ራሴን በማክበር መስጠት (መገዛት) እንዳለብኝና ቤተሰቤም እንዲሁም ለጌታ መሰጠት እንዳለበት ተረድቻለሁ፡፡
በዚህ መሠረት ሁላችንም ለጌታ በፍቅር መገዛት ከቻልን፣ ‹‹ሚስቶች ሆይ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ››፣ ‹‹ባሎች ሆይ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ›› የሚለውን ትእዛዝ ለመፈጸምና እርስ በእርሳችን ለመገዛት (መታዘዝ) በጣም ቀላል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
በመቀጠል በዚህ ክፍል የተማርኩትና በተግባር ልገልጸው የሚገባኝና እንዲሁም ባለቤቴ ልታደርገው የሚገባትን ትልቅ ትምህርት ያገኘሁበት ክፍል ቁጥር 25-26 ላይ ‹‹በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ›› በሚለው ውስጥ እነዚህ ሁለት ቃላት ‹‹በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ›› የሚሉት ቃላት ትርጉም የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም፣ አንድን ድርጊት በተለያየ ሁኔታ መንጻትንና መቀደስን ሲገልጹት እንመለከታለን፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የኃጢአታችን ዋጋ ለመክፈል ደሙን ባፈሰሰ ጊዜ መንጻትን አግኝተናል፡፡ በዮሐንስ 17፡17 ላይ እንደምናገኘው ራሱን ስለ እኛ ቀድሶአል፣ በሰማነው ቃልም ተቀድሰናል፣ በቲቶ 3፡5 ላይ እንደምናገኘውም በመንፈስ ቅዱስም ተቀድሰናል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሁለት ቃላት አጉልተው የሚያሳዩን እነዚህን እውነቶች ነው፡፡ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን ለራሱ ያዘጋጃት በዚህ መልኩ ነው፡፡ እኔም ባለቤቴን ከነድካምዋ ተቀብዬ ከዚያ እንድትወጣና በቅድስና ሕይወት እንድትመላለስ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለብኝ ተረድቻለሁ፡፡ ኑሮአችን ሁሉ የተሳካና ፍሬአማ እንዲሆን የማድረጉ ድርሻ በተግባር መግለጽ እንዳለብኝ ተምሬአለሁ፡፡
እናንተ በጥናታችሁ ጊዜ ብዙ ማዛመድ ልታደርጉ ትችላላችሁ፤ እኔ ለመጨረሻ የተማርኩትን ላካፍላችሁና ልጨርስ፡፡ በቁጥር 32 ላይ ‹‹ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፣ እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እላለሁ›› በሚለው ውስጥ ‹የባልና ሚስት አንድ ሥጋ ናቸው› የሚለው ሐሳብ በሁለቱ በባልና ሚስት መካከል ያለው ጥምረት በክርስቶስና ቤተ ክርስቲያን መካከል ስላለው አንድነት፣ ታላቅ ምስጢር የሚገለጥበት በመሆኑ ጋብቻዬን በታላቅ አክብሮት መጠበቅ እንዳለብኝ ተምሬአለሁ፣ ደግሞም በተግባር ማሳየት እንዳለብኝ ተረድቻለሁ፡፡
የሚቀጥለው ጥናታችን በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 15፡36-41 ባለው ክፍል የተመሠረተ ሲሆን የተማርነውንና በተግባር ልንገልጸው የምንችለውን እውነቶች በየግላችን ካየን በኋላ፣ እንደገና አብረን እንመለከታለን፡፡
0 Comments