በመጀመሪያ ለጥናት የተሰጠው ክፍል የሚገኘው ማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 28፡19-20 ላይ ነበር፡፡ በዚህ ክፍል ጌታ ስለ ጥምቀት የሰጠውን ትእዛዝ፣ ጴጥሮስ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2፡38 ላይ ‹‹…በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ›› ብሎ ማስተማሩ በጌታ የተሰጠውን ትእዛዝ መለወጡ አይደለም፡፡ ‹‹ንስሐ ግቡ፣ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ›› ብሎ ያስተማረውን ትምህርት ጳውሎስ በኤፌሶን 1፡13 ላይ ‹‹እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፣ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል ሰምታችሁ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ፣ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ…›› ብሎ ካስተማረው ትምህርት ጋር አብረን እንየው፡፡
ጳውሎስ ዶክትሪኑን (መሠረታዊ የክርስትና) ሲመሠርት ያስተማራቸውን ዋና ዋና ነገሮች በቅድሚያ እናውጣቸው፤ አንደኛ መስማት (ቃሉን፣ ወንጌሉን)፣ ሁለተኛ ማመን (በክርስቶስ) ሦስተኛው መታተም (በመንፈስ ቅዱስ) ይህን ሐሳብ የራሱን ምሥክርነት በሰጠበት በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 22፡12-16 እና 26፡12-18 ላይ እነዚህን እውነቶች እናገኛለን፡፡ በተለይም ቁ. 17 ላይ ‹‹የኃጢአትንም ስርየት በእኔም በማመን…›› በማለት ድነት የሚገኘው በክርስቶስ በማመን ብቻ እንደሆነ ያሳያል፡፡
ቀደም ባሉት ትምህርቶች ላይ ወንጌሎች በታሪክ ላይ የተመሠረቱ ግለ ታሪኮች እንደሆኑ አይተናል፡፡ ስለዚህ ዶክትሪን (ትምህርተ-መለኮት) በታሪክ ላይ አይመሰረትም፡፡ ጴጥሮስ ያስተማረውን፣ ጳውሎስ ካስተማረው ትምህርት ጋር አብረን እያነፃፀርን እንመልከተው፡፡
የሐዋርያት ሥራ ኤፌሶን
-ይህንም በሰሙ ጊዜ ቁ. 37 – መስማት ቁ. 13)
-ንስሓ ግቡ -ማመን ቁ.13)
-በኢ. ክርስቶስ ስም ተጠመቁ ቁ. 38 -ማመን ቁ.13)
-የመ. ቅዱስ ስጦታ መቀበል ቁ. 38፣ -መታተም ቁ.13
ከሚለው ጋር ማነፃፀር አስፈላጊ ነው፡፡
ጴጥሮስ እንዲህ ማለቱ ጌታ ያስተማረውን ትምህርት መለወጡ ሳይሆን የጥምቀቱ ትእዛዝ ሰጭና ባለቤቱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ለማሳየት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ‹‹በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ›› ማለት በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እመኑ ማለት ነው፡፡ ጌታን ለማመናቸው አንዱ መመስከሪያ መንገድም በስሙ መጠመቃቸው ነበር እንጂ፤ ያጠመቃቸው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ብሎ እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ፡፡ አለበለዚያ ጴጥሮስ የሐሰት አስተማሪ ሊሆን ነው፤ ትምህርቱ ሐሰት ከሆነ ደግሞ ሌሎች ሐዋርያት ለምን አላወገዙትም?፣ ሐሰተኛ አስተማሪ ከሆነ እኛም አንቀበለውም፡፡ ስለዚህ እንዲህ ብሎ ለምን አስተማረ ብለን መጠየቅና መረዳት ይኖርብናል፡፡
ሁለተኛው የጥናት ክፍላችን በማርቆስ 11፡17 ላይ ጌታ ቤቱን ሲያጸዳ ‹‹ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ትባላለች›› በሚለው ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡ በብሉይ ኪዳን በመገናኛውም ሆነ ሰሎሞን ባሠራው ቤተ መቅደስ ሊቀ ካህኑ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ታቦቱ በሚገኝበት የሚገባበት ቅድስተ ቅዱሳን፣ ካህናት በየቀኑ የሚገቡበት ቅድስት፣ የአይሁድ ወንዶች የሚገቡበት አደባባይ፣ እና የሚቀጥለው አደባባይ የሴቶች ሲሆን፣ በመጨረሻ የሚገኘው አደባባይ ወደ ይሁዲነት የገቡ (የተቀበሉ) አሕዛብ የሚያመልኩበት ሥፍራ ነበር፡፡
በቤተ መቅደስ ነጋዴዎቹ ገብተው የነገዱት ሊቀ ካህኑ፣ ካህናት፣ ወንዶችና ሴቶች በሚገቡበት አደባባይ ሳይሆን በአሕዛብ አደባባይ ነበር፡፡ እነዚህ የተጠቀሱት ሥፍራዎች እጅግ የተከበሩና የሚፈሩ ነበሩ፡፡ በተለይም ታቦቱ ባለበት ቅድስተ ቅዱሳን ከሊቀ ካህኑ ውጭ ማንም ቢገባ ይቀሰፍ ስለ ነበር፣ ማንም ያለ ቦታው መግባት ፈጽሞ የተከለከለ ነበር፡፡ የአሕዛብን አደባባይ እንዲነገድበት የፈቀዱት ጥቅም ለማግኘት (በሙስና) ነበር፡፡ ስለዚህ ነው ጌታ ይህ እንዲነገድበት የፈቀዳችሁበት ሥፍራ የቤቴ አካል ነው፣ እንዲሁም ሰዎቹም እናንተ ያገለላችኋቸው ሕዝቦቼ ናቸው ማለቱ ነበር፡፡ የቃላት ጥናት ስናደርግ እንዳየነው ‹‹አሕዛብ›› (በግዕዝ) ሕዝቦች ማለት ነው፡፡
ሦስተኛው የጥናታችን ክፍል የተመሠረተው በ1ኛተሰሎንቄ 1፡2-3 ‹‹ … የፍቅራችሁን ድካም… እያሰብን እግዚአብሔርን ሁልጊዜ በሁላችሁ ምክንያት እናመሰግናለን›› በሚለው ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡ ጳውሎስ ስለ ተሰሎንቄ ሰዎች በሚጽፍበት ጊዜ በእምነታችሁ ደካሞች ናችሁ ለማለት ሳይሆን ብርቱዎች፣ ጠንካሮችና የተግባር ሰዎች ናችሁ ማለቱ ነው፡፡ ክፍሉን ስናነብ እነዚህን የሚጠቁሙ ሐሳቦች እናገኛለን፤ ‹‹የእምነታችሁን ሥራ፣ የተስፋችሁን መጽናት፣ ቃሉን በብዙ መከራ…ተቀበላችሁ፣ እኛንና ጌታን የምትመስሉ ናችሁ፣ ምሳሌ ሆናችሁላቸው፣ …እምነታችሁ በሁሉ ስፍራ ተወርቶአል፣ ኢየሱስን…ከሰማይ ትጠብቁ ዘንድ…›› የሚሉት ሐሳቡች በእምነታቸው ብርቱዎች እንደሆኑ እንጂ ደካሞች እንደ ሆኑ አያመለክቱም፡፡ ‹‹የእምነታችሁንም ድካም›› የሚለው እምነታቸውን በተግባር በማሳየት ብዙ ደክመዋል፣ ዋጋ በመክፈል ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል ማለቱ ነው፡፡
ሐ. ማዛመድ/ሥራ ላይ ማዋል
ዛሬ ማጥናት የምንጀምረው የጥናት ክፍላችን፣ ሦስተኛው ክፍል ወደ ሆነው ማዛመድ ወደምንለው የመጽሐፍ ቅዱስ አጠናን ዘዴ ያመጣናል፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል ስናነብና ስናጠና ሳለ፣ ተመልክተን ተመልክተን፣ ተርጉመን ተርጉመን፣ ከሕይወታችን ጋር ካላዛመድነው ወይም በሥራ ላይ ካላዋልነው፣ ልክ እንደ ውርጃ ይቆጠራል፡፡ አንድ ሴት ስምንት ወር ሙሉ ፅንሱን በማኅፀንዋ ተሸክማ ዘጠነኛው ወር ላይ ብታስወርድ ምን ይጠቅማታል? እኛም እንደ ሴትየዋ፣ በመመልከትና በመተርጐም ብዙ ጊዜ አጥፍተን ወደ ማዛመድ አምጥተን በሕይወታችን ተግባራዊ ሳናደርገው ብንቀር፣ እዚሁ ላይ ብናቆመው ምን ይጠቅመናል? ስለዚህ የተመለከትናቸውንና የተረጐምናቸውን እግዚአብሔር ቃል እውነቶች በሕይወታችን ልንተገብራቸውና ልንኖራቸው ይገባናል፡፡
መጽሐፍ ቅዱሳችንን የመረዳታችን የመጨረሻ ግብ ለእግዚአብሔር ክብር መኖር ነው፡፡ ቃሉን ለመታዘዝ ፈቃደኞች በመሆን ለእግዚአብሔር ቃል ትክክለኛ ትርጓሜ በመስጠት ቃሉን እንደሚገባ መኖር ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር አንድ ትእዛዝ የሚሰጠን እንድናውቀው መሆኑን ስንረዳ፣ የእኛ መልስ በደስታና በፍጹም ልብ መታዘዝ መሆን አለበት፡፡ አለበለዚያ በማዛመድ ያልተደገፈ ንባብና ጥናት እንደ ውርጃው ስለሚቆጠር፣ በመመልከትና በመተርጐም ያጠፋነው ጊዜ ምንም አይጠቅመንም፣ ማለት ነው፡፡
ማዛመዳችን ትክክለኛ እንዲሆንና ወደ እግዚአብሔር የበለጠ እንዲያቀርበንና ጌታ በሕይወታችን እንዲደሰት፣ በመረጥነው የምንባብ ክፍል፣ ምልከታና ትርጉም ላይ ጊዜ ወስደን በጥንቃቄ ከሠራን ሕይወታችንን የሚዳስስና የሚነካ ስለሚሆን ውጤታማ እንሆናለን፡፡ በሕይወታችን ዕለት በዕለት ቅድስናን የምንለማመድ ስንሆን ጌታ ይደሰትብናል፡፡
የብሉይ ኪዳን ሕግጋት ስናጠና የትኞቹ ለዚያ ዘመን ብቻ፣ የትኞቹ ደግሞ የጊዜ ገደብ የሌለባቸው እንደሆኑ ለይተን ማወቅ እንዳለብን ተመክተናል፡፡ በአዲስ ኪዳንም ቢሆን የአንደኛው ክፍለ ዘመን ችግር የነበሩትንና የዘመናችን ችግር የሆኑትን ለይተን ልናውቅ ይገባል፡፡ ምክንያቱም የእነርሱ ችግሮች የእኛ ችግሮች ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን ሁሉንም በቀጥታ ተግባራዊ ልናደርጋቸው የማይገቡትን ለይተን ልናውቃቸው ይገባል፡፡
ሁላችንም መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ለማወቅና ለራሳችን ለዕለታዊ ምልልሳችንና ኑሮአችን እንዲናገረን እንፈልጋለን፡፡ በዚህ ምክንያት አንድ ደስ የሚለንን ጥቅስ/ሀሳብ በመያዝ፣ ቃሉን ከዐውዱ አውጥተን/ለይተን፣ ቃሉ እንዲደግፈን ለማድረግ ጥረት ስናደርግ፣ ላለንበት ሁኔታ ለእኛ እንዲናገረን ስናደርገው፣ በፍጹም እንዳሰብነው አይሆንም፡፡ ፡፡ በዚህ መንገድ ጥቅሱ እኛን እንዲናገረን ስናደርግና መልካም ውጤት ስንጠብቅ፣ የጠበቅነው ባለመሆኑ በጌታ ላይ ያለን መታመን እየተሸረሸረ ይመጣል፡፡ በዚህ ጊዜ በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ላይ ወደ መጠራጠር እንመጣለን፣ ወይም እግዚአብሔር ረስቶኛል፣ ትቶኛል፣ አይሰማኝም፣ ዓይኑን ከእኔ ሰውሮአል እንላለን፡፡
መጽሐፍ ቅዱስን በመመልከትና በመተርጎም ስናነብና ስናጠና ባደረግናቸው ጉዟችን ሁሉ፣ የመጀመሪያውን ፍች ማግኘትና ከሁኔታችን ጋር ለማዛመድ እንድንችል መንፈስ ቅዱስ እንዲረዳንና ከጐናችን እንዲሆን፣ በታማኝነት በጸሎት በመደገፍ መጠየቅ ይገባናል፡፡ መመልከትና መተርጐም በራሱ በቂ እንዳልሆነ ቀደም ብለን ተመልክተናል፡፡ ስለዚህ በሕይወታችን ቃሉን እንደሚገባ ማዛመድ እንድንችልና ትርጉም ያለው ሕይወት እየኖርን ለሌሎች መልካም ምሳሌ እንድንሆን የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ያስፈልገናል፡፡
ቃሉን የምናነብና የምናጠና አማኞች ሁሉ አንድ ዓይነት መረዳትና አተረጓጐም ላይኖረን ይችላል፡፡ ነገር ግን ከመጀመሪያ ጀምሮ ያየናቸውንና የሄድንባቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጐምን ዘዴ ከተማርንና ካወቅን ወደ አንድ ሐሳብ መምጣት ባንችልም፣ ወደሚያስማማን ደረጃ መምጣት እንችላለን፡፡ በዚህም ለእኛ የሚተላለፈው እውነተኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ ፍች እግዚአብሔር መጀመሪያ በተናገረበት ጊዜ እንዲተላለፍ የፈለገው እውነት ለዘመናት ሁሉ መልእክት እንዲሆን (Timeless truth or princples) ያስቀመጠው እንደሆነ፣ ሁላችንም ይህ መረዳት ሊኖረን ይገባናል፡፡
መጽሐፍ ቅዱሳችንን ከተመለከትንና ከተረጐምን በኋላ ከሕይወታችን ጋር ማዛመድ/ሥራ ላይ ማዋል እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ መላልሰን አይተናል፡፡ በግል፣ በቤተ ሰብ፣ በቤተ ክርስቲያንና በማኅበረ ሰባችን ሕይወት ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ግንኙነት ምን እንደ ተናገረንና ምን እንድናደርግለት የፈለገው ነገር እንዳለ ማወቅና በተግባር ማዋል ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ጤንነትና ዕድገት ወሳኝነት አለው፡፡ የአብርሃምን ልጅ ለመሠዋት በእግዚአብሔር መታዘዝ ከሕይወታችሁ ጋር አዛምዱት? በተግባርም ግለጡት? (ዘፍ. 22፡2)
0 Comments