የዛሬውን ትምህርት ስለ ትምህርተ-መለኮት ችግር ከማየታችን በፊት፣ ባለፈው ለተጠየቁት ጥያቄዎች የሰጣችሁትን መልስ፣ ዛሬ አብረን እያስተያየን ራሳችሁን እያረማችሁና ማርክ እየሰጣችሁ ተከታተሉ፡፡ 

በመጀመሪያ ለጥናታችን የተሰጠን ክፍል ዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 4፡4 ላይ የሚገኘው ‹‹በሰማርያም ሊያልፍ ግድ ሆነበት›› የሚለው ነበር፡፡ በእነዚህ አራት ቃላት የተገለጸውን ታሪክ ለመተንተን ብዙ ሰዓት ይወስዳል፡፡ የታሪኩን ጅማሬ የምናገኘው በብሉይ ኪዳን በሁለተኛ ነገሥት ምዕራፍ 17 ላይ ነው፡፡ እስራኤል (አሥሩ ነገዶች) በሠሩት ኃጢአት እግዚአብሔር በአሦራውያን እጅ ለቅጣት አሳልፎ በሰጣቸው ጊዜ የተፈጸመ የታሪክ ጅማሬ ነው፡፡

 አሦራውያን እስራኤልን በማረኩ ጊዜ ግማሽ የሚሆነውን ሕዝብ ወደ አሦርና ሌሎች ከተማዎች ወስዶ አሰፈራቸው፡፡ ከባቢሎንና ከሌሎችም ከተማዎች ሕዝቦችን አምጥቶ በሰማርያ (የእስራኤል ዋና ከተማ) አስቀመጣቸው፡፡ በዚህ ጊዜ የእስራኤል ሰዎች (ሳምራያውያን) ከቁጥር 27-41 ባለው ክፍል ውስጥ ስንመለከት የሰማርያ ሰዎች እግዚአብሔርንም ጣዖትንም በአንድ ጊዜ ያመልኩ እንደ ነበረ ይናገራል፡፡

 በዚህ ምክንያት በሰሜኑ መንግሥት (እስራኤል፣ አሥሩ ነገዶች፣ ሰማርያ) እና በደቡብ መንግሥት (ይሁዳና ብንያም) መካከል ልዩነቶች ተፈጠሩ፡፡ የሰማርያ ሰዎች ጣዖት ከማምለካቸውም በተጨማሪ አሕዛብ በማግባታቸው ምክንያት፣ ከይሁዳ ሰዎች ጋር መለያየት ተጀመረ፡፡ ምርኮው በ722 ዓ.ዓ ከተካሄደ ጊዜ ጀምሮ በሳምራውያንና በአይሁዳውያን መካከል ልዩነቱ እያደገ መጥቶ እንደ እርኩስ መተያየት ጀመሩ፡፡ ሳምራውያን በሃይማኖትና በእምነት ከአሕዛብ ጋር ስለ ተደባለቁ አይሁዶች እንደ ውሻ አድርገው መቁጠር ጀመሩ፡፡

 አንድ ነገር ተደጋግሞ ሲደረግ ከልማድነት አልፎ ባሕል ይሆናል፤ በአይሁዳውያንና በሳምራውያን መካከል ያለው ጥላቻ አድጎ፣ ማንኛውም አይሁዳዊ  ከኢየሩሳሌም ተነስቶ ወደ ናዝሬት መሄድ ሲፈልግ በሰማርያ ከተማ አያልፍም፡፡ እንዲሁም አንድ አይሁዳዊ ከናዝሬት ተነስቶ ወደ ኢየሩሳሌም ለአምልኮ መምጣት ቢያስብ በሰማርያ አልፎ አይመጣም፡፡ ከዚያ ይልቅ ምንም ረጅምና አድካሚ ቢሆንም የዮርዳኖስን ወንዝ ሁለት ጊዜ ተሻግሮ መምጣት ይቀላቸው ነበር፡፡

 ኢየሱስም ከአሥራ ሁለት ዓመቱ ጀምሮ ከወላጆቹ ጋር ለአምልኮ ከናዝሬት ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጡ፣ በሰማርያ አልፎም አያውቅም፤ አሁን ግን በዚህ ወንጌል እንደምናነበው ‹‹በሰማርያ ሊያልፍ ግድ ሆነበት›› ይለናል፡፡ ለምን? ብለን ስጠይቅ  ለ700 መቶ ዓመት ተጠብቆ የነበረውን ባሕል ሊያፈርስ ግድ ሆነበት፤ ምክንያቱም በሰማርያ አንዲት ድነት የሚያስፈልጋት ሴትና በእርሷ ምስክርነት አማካኝነት ወደ ጌታ የሚመጡ የብዙ ሰዎችን መዳን አስቀድሞ አይቶ ነበርና ነው፡፡ ጌታ የጥልን ግርግዳ በዚህ መልኩ ሲያፈርስ፣ ዛሬ ስንቶች እንሆን የጥልን ግርግዳ እያቆምን ያለን?        

ሁለተኛው የጥናት ክፍላችን በኤፌሶን 2፡17 ላይ ‹‹መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን … የምሥራች ብሎ ሰበከ›› የሚለው ነበር፡፡ በዚህ ጥቅስ ውስጥ የባሕል ችግር እንዳለ መረዳት ያስቸግር ይሆናል፤ ቢሆንም ‹‹ርቃችሁ›› የሚለው ቃል በቁጥር 12፣ 13፣ እና 17 ላይ ሦስት ጊዜ ተደጋግሞ ይገኛል፡፡ ይህ ቃል ላይ ትኩረት ስናደርግ የሚጠቁመን ነገር አለው፡፡ አብርሃም በዘፍጥረት ምዕራፍ 12 ላይ የተጠራው የምድር ነገዶች ሁሉ በእርሱ እንዲባረኩ ነበር፤ ነገር ግን ትውልድ እየቀጠለ ሲሄድ እስራኤል አሕዛብን ማግለል  ጀመሩ፡፡ አይሁዶች በሠሩት ቤተ መቅደስ ውስጥ ይሁዲነትን የተቀበሉ አሕዛብ፣ ወንዶች አይሁዳውያን በሚያመልኩበት አደባባይ ገብተው ሊያመልኩ ቀርቶ፤ በሴቶች አደባባይ እንኳን አይፈቀድላቸውም ነበር፡፡ እግዚአብሔርን እየወደዱት አብረው ማምለክ እንኳን በፍጹም አይችሉም ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት አይሁድና አሕዛብ በብዙ ነገር ተራርቀው ኖረዋል፡፡ አሁን ክርስቶስ ሲመጣ ተራርቀው የነበሩትን አንድ አካል አድርጎ አቀራረባቸው፡፡

 ስለዚህ በዚህ ክፍል ስንመለከት በአምልኮ ባሕላችው ተራርቀው የሚኖሩ ነበሩ፡፡ ጌታ የምሥራች ብሎ በመስበኩ፣ እኛም አሕዛብ የነበርነው የምሥራቹን በመቀበላችን፣ ክርስቶስን ከሚያምን ሁሉ ጋር አንድ አካል መሆን ችለናል፡፡ ስለዚህ በደማችን፣ በዘራችን፣ በዕውቀታችን፣ በትምህርታችንና በባሕላችን ምክንያት ይህን መራራቅ እንዳንመልሰው እንጠንቀቅ፡፡

የመጨረሻው ለጥናት የተሰጠው ማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 16፡3 ላይ ‹‹ድንጋዩን ከመቃብር ደጃፍ ማን ያንከባልልናል?››    የሚለው ነበር፡፡ በዚህ ጥቅስ መሠረት በአገራችን ከምናውቀው የመቃብር ይዘቱን ስንመለከት የባሕል የአቀባበር ልዩነት እንዳለ መመልከት እንችላለን፡፡ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 27፡60 ላይ የአርማትያስ ዮሴፍ ባለጠጋ ስለ ነበረ፣ በዘመናችን ያሉ ሀብታዎች ሳይሞቱ የሚቀበሩበትን የቀብር ሥፍራ እንደሚያዘጋጁት፤ እርሱም ገና ሳይሞት ለራሱ መቀበሪያ የሚሆን ወቅሮ ያዘጋጀው የመቃብር ሥፍራ ነበር፡፡ የመቃበሩን ሁኔታ ስንመለከት ወደ መሬት የተቆፈረ ሳይሆን ዓለቱን ወደ ጐን ፈልፍሎ፣ ክዳኑን የሚንከባለል ድንጋይ አድርጎ አዘጋጅቶት እንደ ነበር እናያለን፡፡ ሴቶቹ በሦስተኛው ቀን ሽቶ ለመቀባት ሲሄዱ፣ የአቀባበሩን ሁኔታ ስለሚያውቁ ‹‹ድንጋዩን ከመቃብር ደጃፍ ማን ያንከባልልናል?›› ተባብለው የተናገሩት በዚህ ምክንያት ነበር፡፡ የምናጠናው ክፍል ሊተረጎም የሚገባው ከነበራቸው ባሕል አኳያ መሆን አለበት፤ ወይም የባሕል ልዩነት የሌለው ከመሰለን ትኩረት ሰጥተን በሚገባ እንመልከተው፡፡  

  • የትምህርተ-መለኮት ችግር፡

 የዛሬው ዕለት የጥናት ርዕሳችን የትምህርተ-መለኮትን ችግር በተመለከተ ይሆናል፡፡ ስለ ትምህርተ-መለኮት ትምህርት (ቲኦሎጂ) ስናነሣ ብዙ ሰዎች የማይስማማቸው አሉ፤ ምክንያቱም ቲኦሎጂ እንደማይበቅል የተቆላ ገብስ ስለሆነ ምንም ጥቅም የለውም ብለው ስለሚናገሩ፡፡ አንድ ጊዜ ከአንድ ወንድም ጋር ቢሮ መጥተው ሌሎች ወንድሞችም ባሉበት ስንወያይ፣ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መነጋገር ጀመርንና ስለ ሰማርያይቱ ሴት ታሪክ ተነስቶ ስንነጋገር ሳለ ሰውዬው ‹‹የሰማርያይቱ ሴት የያዕቆብ ሚስት ነበረች›› አሉ፡፡

 እኔም ‹‹በያዕቆብና በሰማርያይቱ ሴት መካከል የብዙ ሺህ ዓመት ርቀት አለ፣ ያዕቆብ የአብርሃም የልጅ ልጅ ሲሆን፣ የሰማርያይቱ ሴት የኖረችው በክርስቶስ ዘመን ነው፣›› ብላቸውም ሊሰሙኝ አልቻሉም፡፡ እንዲያውም እንዲህ አሉኝ፣ ‹‹አንተ አልደረስክበትም፣ አልተገለጠልህም›› አሉኝ፡፡ እንግዲህ ይህ ሐሳብ ትክክል ቢሆንም ባይሆንም ለራሳቸው ቲኦሎጂ ነው፡፡ ማንም ሰው የራሱ የሆነ ሐሳብና መረዳት እስካለው ድረስ፣ ከቲኦሎጂ መራቅና መሸሽ አይቻልም፡፡

 ትምህርተ-መለኮት፣ መሠረታዊ የክርስትና ትምህርት ወይም ቲኦሎጂ ስለ እግዚአብሔር የሚያስተምር ትምህርት ማለት ነው፡፡ የእንግሊዝኛውን ቃል ብንመለከትው፣ ቲኦ ማለት እግዚአብሔር ማለት ሲሆን፣ ሎጂ ማለት ደግሞ ጥናት ማለት ነው፣ ስለዚህ ቲኦሎጂ ማለት ስለ እግዚአብሔር የሚያስተምር ትምህርት ማለት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔርና ስለ ተናገራቸው እውነቶ የሚያስተምር መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ ይህን እውነት ለመረዳትና ለመኖር (በሕይወታችን ተግባራዊ ለማድረግ) እንድንችል መተርጐም ያስፈልጋል የምንለው ለዚህ ነው፡፡

 ከዚህ ቀደም ብለን በመመልከት ጊዜ በሰባት የመጠየቂያ ቃላት የጠየቅነው፣ የተለያዩ ምልከታዎችና በሐሳቡ መዋቅር ሥር ሰዋስውና የሥነ-ጽሑፉን ቅርጽ ያየነውና ያጠናነው በቀላሉ መተርጐም እንድንችል ነው፡፡ በአጠቃላይ ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳንን የተመለከትነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በእርሱ ሳይቃረን አንድ ወጥ የሆነ ትምህርተ-መለኮት ማስተማሩን ነው፡፡ የትምህርቱም መሠረት ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክ የሆነው ክርስቶስ ራሱ ነው፡፡

 ትምህርተ-መለኮትን ስንተረጉም በዘይቤአዊ ንግግሮች ላይ መመሥረት አደገኛ ነው፡፡ ለምሳሌ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 15 ቁጥር 2 ላይ ስለ ወይኑ ግንድ ላይ ወደ ተሳሳተ መረዳት መጥተን ትርጉም የምንሰጥበት ጊዜ አለ፡፡ ‹‹ፍሬ የማያፈራውን በእኔ ያለውን ቅርንጫፍ ሁሉ ያስወግድዋል፣ ፍሬ የሚያፈራውንም ሁሉ አብዝቶ እንዲያፈራ ያጠራዋል››፡፡ አንዱን ከደህንነት ማስወገድ ሌላውን ከማቆየት ጋር እናገናኘዋለን፣ ክፍሉን በሚገባ ስንመለከተው የማያፈራውም የሚያፈራውም ሁለቱም ዘንድ መቆረጥ አለ፡፡ ያስወግድዋል የሚለውን ‹ይቆርጠዋል› ሲል፣ ያጠራዋል የሚለውን ‹ይገርዘዋል› በማለት አዲሱ መደበኛው ትርጉም ተጠቅሞበታል፡፡ የሚወገድውም ቅርንጫፍ ተቆርጦ ሲሆን የሚጠራውም ቅርንጫፍ ተቆርጦ ነው፣ ሁለቱም ዘንድ የሚቀርና የሚጣል ቅርንጫፍ አለ፡፡ ስለዚህ በሁለቱ መካከል ምንም ልዩነት የለም፡፡ ክፍሉ የሚያስተላልፈው ቅርንጫፉ ከግንዱ ጋር ስለ አለው ግንኙነት ነው፡፡ ከግንዱ ጋር ግንኙነት ያለው ቅርንጫፍ ሁሉ ምግብ ያገኛል፣ ምግብ ካገኘ ሕይወት አለው፣ ሕይወት ካለው ደግሞ ፍሬ ያፈራል፣ የሚለውን መልእክት ነው የሚያስተላልፈው፡፡

 ትምህርተ-መለኮት በአንድ ጥቅስ ብቻ አይመሠረትም፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የተለያዩ ጥቅሶች ተወስደው፣ አንድ ልብስ ሠፊ የተለያዩ መጠን ያላቸውን ጨርቆች ከአንድ ቦንዳ ላይ ቀድዶ በማወጣት በጣም የሚያምርና ደስ የሚል ኮት ወይም ሱሪ አድርጎ እንደሚያወጣው፣ እንዲሁም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ/አስተማሪ ጥቅሶችን በአንድ ላይ በመስፋት/በማገጣጠም ነው ትምህርተ-መለኮትን የሚሠራው፡፡

 በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2፡1-4 ያለውን ክፍል ወስደን እንመልከት፡፡ ይህ ክፍል በያዝነው በሃያኛውና በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የተለያየ ትምህርተ-መለኮት የሚመሠረትበት ክፍል እንደ ሆነ ይታወቃል፡፡ ይህንን ክፍል ለቃላት ጥናትና ለትምህርተ-መለኮት ጥናትም ልንወስደው እንችላለን፡፡ በመጀመሪያ የቃላት ጥናት ማድረግ አስፈልጊ ነው፡፡ ሞላባቸው  (ተሞሉ አ.መ.ት) የሚለውን ቃል ለመረዳት የንባቡን ዐውዱንና በብሉይ ኪዳን የተነገረውን ትንቢት በሚገባ ማየት ያስፈልጋል፡፡

 ስለዚህ ክፍል በቅርብ፣ በመካከለኛና በሩቅ የተነገሩትን ትንቢቶች እንመልከት፡፡ የመጀመሪያው ከብዙ ዘመናት በፊት ትንቢት ከተናገሩት ከብዙዎች ነብያት መካከል፣ ከስምንት መቶ ዓመት በፊት በምዕራፍ 2፡28 ላይ እንደምናገኘው ነብዩ ኢዩኤል ነው፡፡ ‹‹…መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈሳለሁ…›› ሲል፣ ሁለተኛው ተናጋሪ መጥምቁ ዮሐንስ ከበዓለ ኀምሳ በዓል፣ ከሦስት ዓመት በፊት፣ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 3፡16 ላይ ‹‹… በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል…›› ሲል፣ የመጨረሻው ተናጋሪ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 1፡5 ላይ  ‹‹… ከእኔ የሰማችሀትን አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቁ፤ ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና፣ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ›› አለ፡፡ ብሎ ከዘገበውና እንደ መግቢያ አድረጎ  ከተጠቀመበት ክፍል፣ የጌታን የራሱን ትንቢት ነው የምናገኘው፡፡    

  በተለያዩ ነቢያት የተነገረውን የትንቢት ፍጻሜ የጻፈው ሉቃስ ሲሆን፣ ፍጻሜውን በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2፡4 ላይ ዘግቦልን እናገኛለን፡፡ ኢዩኤል ‹አፈሳለሁ›፣ ሉቃስ ‹ያጠምቃችኋል›፣ እና ‹ትጠመቃላችሁ› (ተናጋሪው ጌታ ሲሆን ጸሐፊው ሉቃስ) የሚለውን ተጠቅመዋል፡፡ የትንቢቱን ፍጻሜ የተናገረው ጴጥሮስ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2፡33 ላይ ‹‹… የመንፈስን ቅዱስን የተስፋ ቃል ከአብ ተቀብሎ ይህን እናንተ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው›› ይላል፡፡ ሉቃስም በምዕራፍ 2፡4 ላይ እንደ ተመለከትነው ፍጻሜውን ለመግለጥ የተጠቀመበት ቃል ሞላባቸው/ተሞሉ (አመት) የሚለውን ቃል ነው፡፡

ከብሉይ ኪዳን ተነስተን ዐውዱን ከፊትና ከኋላ ያለውን ተመልክተናል፡፡ አሁን አንድ መሠረታዊ ጥያቄ እንጠይቅ፣ በእነዚህ ነቢያት የተነገረው ትንቢት ተፈጽሞአል? ወይስ አልተፈጸመም? ሁለተኛው ጥያቄ የሐዋርያት ሥራ 2፡4 ጥምቀት ነው ? ወይስ ሙላት? የሚል ነው፡፡ ምንም እንኳን ቃላቶቹ የተለያዩ ቢሆኑም ትንቢቱ ተፈጽሞአል፣ አልተፈጸመም የሚል ሰው  ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡ ሁላችንም ትንቢቱ እንደ ተፈጸመ እናምናለን፡፡ ታዲያ ትንቢቱ ተፈጽሞአል የምንል ከሆነ የሐዋርያት ሥራ 2፡4 ጥምቀት ነው? ወይስ  ሙላት ነው? ለሚለው ጥያቄ መልሳችን ምን ይሆን?

 በሦስቱም ነብያት የተነገረው ትንቢት ተፈጽሞአል፣ ስለዚህ 2፡4 ጥምቀትም ሙላትም ነው፡፡ በጥምቀትና በሙላት መካከል  ልዩነት የለም እንዴ? ብለን ለምንጠይቀው ጥያቄ መልሱ አላቸው የሚል ነው፡፡ ጥምቀት የአንድ ጊዜ ድርጊት ሲሆን ሙላት የሚደጋገም ድርጊት ነው፡፡ በ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 12፡13 ላይ ‹‹… እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናል›› ብሎ እንደሚናገረው የክርስቶስ የአካሉ ብልት ለመሆን መንፈስ ቅዱስ ያጠምቀናል፡፡ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የምንመለከተውም ጥምቀት የአንድ ጊዜ ድርጊት መሆኑንና ሙላት መደጋገሙን ነው፡፡ (4፡7፣31፤ 7፡55፤ 8፡17) ሉቃስ በወንጌሉና በሐዋርያት ሥራ ስለ መንፈስ ቅዱስ ጥምቀትና ሙላት የተጠቀመባቸውን ቃላት ወደ 12 የሚደርሱትን በማጥናት ግልጽ ወደ ሆነ መረዳት መምጣት ይቻላል፡፡ (የኢትዮጵያ ገነት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ገጽ 71 ይመልከቱ)፡፡

የዚህን ትምህርተ-መለኮት ችግር ለመፍታት አስቀድመን ከቃላት ጥናት ተነስተን የቃላቱን ችግር ካስወገድን በኋላ፣ የትምህርተ-መለኮቱን ችግር ለማቃለል እንጀምራለን፡፡ በዚህም መንገድ ችግሩን ለመፍታት ቀላል ባይሆንም፣ ጊዜ ሰጥተነው ከሠራን ችግሩን መፍታት እንችላለን፡፡ ቃል ወይም ሐረግ ለትምህርተ-መለኮት እጅግ አስፈላጊ ስለሆነ የቃላት ጥናት ማድረጉና መጠቀሙ አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ለችግሩ የሚስማማ ሀሳብ ወይም ትርጉም ማግኘት ይቻላል፡፡ ጸሐፊው በተጨማሪ ስለዚህ ሐሳብ/ቃል የሰጠው ተጨማሪ ሐሳብ በክፍል/በመጽሐፉ ውስጥ ካለ መመልከት መልካም ነው፡፡ ሉቃስ ለተጠቀመበት ‹ሙላት› ለሚለው ቃሉ የሚስማማው ሀሳብ/ትርጉም የትኛው ነው ብሎ ለመወሰን የእኛ ውሳኔ ያስፈልጋል፡፡ በውሳኔአችን ከምንባቡ ጋር የሚሄደውን መምረጥ ይኖርብናል፡፡ እንደ ተለመደው የሚከተሉትን ጥያቄዎች በግላችን ሠርተን በሚቀጥለው ጥናታችን በሰላም እንገናኝ፡፡

1. በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 28፡19-20 ላይ ጌታ ስለ ጥምቀት የሰጠውን ትእዛዝ ለውጦ፣ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2፡38  ላይ ‹‹ … በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ›› ብሎ በሰጠው ትእዛዝ ያለውን የትምህርተ-መለኮት ችግር መፍትሔ ስጠው?

2. በማርቆስ 11፡17 ላይ ጌታ ቤቱን ሲያጸዳ ‹‹ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ትባላለች›› ለምን አለ? 3. በ1ኛተሰሎንቄ 1፡2-3 ላይ ‹‹ … የፍቅራችሁን ድካም… እያሰብን እግዚአብሔርን ሁልጊዜ በሁላችሁ ምክንያት እናመሰግናለን  ይላቸዋል፤ ድካም እያለባቸው ለምን ያመሰግናቸዋል?     


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *