የዛሬውን ትምህርት ስለ ባህልና ታሪካዊ መሠረት ችግር ከማየታችን በፊት፣ ባለፈው ለተጠየቁት ጥያቄዎች የሰጣችሁትን መልስ፣ ዛሬ አብረን እያስተያየን ራሳችሁን እያረማችሁና እያስተካከላችሁ ተከታተሉ፡፡
በመጀመሪያ የተሰጠው ጥናት በ1ኛ ዮሐ 4፡8 ላይ ‹እግዚአብሔር ፍቅር ነው› በሚለውና ‹ፍቅር እግዚአብሔር ነው› በሚለው መካከል ያለውን የሰዋስው ልዩነት ለመረዳት ነው፡፡ ‹‹ፍቅር እግዚአብሔር ነው›› ብንል ‹‹እግዚአብሔር ፍቅር ነው›› ከሚለው ጋር አንድ ዓይነት ቃላትን ነው የተጠቀመው፤ ትርጉሙ ግን ተለውጧል፡፡ ቃሉ አሁን ስለ ‹‹ፍቅር›› ነው አንድ ነገር የሚነግረን፡፡ እግዚአብሔር ከፍቅር ጋር አንድ አይደለም፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስን ዓረፍተ ነገሮች ስንመለከት የቃላቱ ቅደም ተከተል መቼና እንዴት ትርጉማቸውን እንደሚለውጡ እያስተዋልን መሆን አለበት፡፡›› (መልሱ መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ መረዳት በቲ. ኖርተን ስቴሬት፣ ተርጓሚ ተክሉ መንገሻ ገጽ.52 ላይ ይገኛልና ይመልከቱት፡፡)
ሁለተኛው ጥናታችን የተመሠረተው በሉቃስ 11፡37 ‹‹ይህንንም ሲናገር አንድ ፈሪሳዊ ከእርሱ ጋር ምሳ ይበላ ዘንድ ለመነው ገብቶም ተቀመጠ›› ማነው (እርሱ) የገባው? ‹እርሱ› የሚለውን ተውላጠ ስም ተርጉሙት? ወይም ማንን ነው የሚያመለክተው? በሚለው ዐረፍተ ነገር ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡ (በዓረፍተ ነገሩ ውስጥ ለተጠቀሰው ተውላጠ ስም ቅርብ የሆነው ስም ‹‹ፈሪሳዊ›› የሚለው ቢሆንም፣ በግልጥ እንደሚታየው ወደ ውስጥ ኢየሱስ ነው፡፡ በአገባቡ መሠረት ትርጉሙ ግልጥ ነው፡፡ ዝኒ ከማሁ 56/ በዚሁ መጽሐፍ ተመልከቱ) እነዚህን ጥያቄዎች በዚህ መጽሐፍ ላይ የመሠረትኩት መጻሕፍት ምን ያህል ጠቃሚ እንደ ሆኑ ለማሳየት ነው፣ ስለዚህ እንጠቀምባቸው፡፡
ሦስተኛው ጥናታችን የሚገኘው በዮሐንስ ራዕይ 12፡9 ላይ ሲሆን፣ ‹‹ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ›› ይላል፡፡ መቼ ነው የተጣለው? የግሡን ጊዜያት ግለጽ? የሚል ነበር፡፡ ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት አጠቃላይ የመጽሐፉን ዐውድና ይዘት ማየት ይጠይቃል፡፡
የዮሐንስ ራዕይ መጽሐፍን ስንመለከት በቅርጹ ትንቢታዊ ነው፤ በይዘቱ ደግሞ አልፎ አልፎ ግጥም የሆኑ ክፍሎች አሉት፣ ከቁጥር 10-12 ያለው ግጥምም አንዱ ክፍል ነው፡፡ መጽሐፉ በምዕራፍ 1፡19 መሠረት በሦስት ይከፈላል፤ አንደኛ ‹‹ያየኸውን›› የሚለው በምዕራፍ አንድ ላይ ዮሐንስ ጌታን ማየቱን ሲይዝ፤ ሁለተኛው ‹‹አሁንም ያለውን›› የሚሉት ቃላት የሚያመለክቱት በምዕራፍ ሁለትና ሦስት ላይ ያሉትን ሰባቱን አብያተ ክርስቲያናትን ነው፡፡ በመጨረሻም ‹‹ከዚህም በኋላ ይሆን ዘንድ ያለውን›› የሚለው ከምዕራፍ 4 ጀምሮ እስከ 22 ያለውን የሚይዝ ሲሆን፣ አፈፃጸሙ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በቅርብ በመካከለኛና በሩቅ ወደፊት የሚሆኑትን (የሚፈጸሙትን) ነገሮች ያመለክታል፡፡
በዚህ መሠረት ‹‹ ተጣለ›› የሚለውን የግሥ ጊዜያት ስንመለከተው ኃላፊ ነው፣ ነገር ግን ዮሐንስ የወደፊቱን ክንዋኔ በራዕዩ ሲመለከት ሰይጣን ተሸንፎ ወደ ምድር እንደ ተጣለ ተመልክቶአል፡፡ የተመለከተውን የወደፊቱን እንደ ኃላፊ አድረጎ አቅርቦታል፡፡ ይህ ክፍል ወደ ፊት የሚፈጸም እንደ ሆነ ከአውዱ እንመልከት፡፡ በቁጥር 12 ላይ ‹‹… ዲያቢሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወረዶአልና››፡፡ የሚለውን ሐሳብ ስንመለከት የመጀመሪያ ውድቀቱን ሳይሆን ወደፊት የሚፈጸመውን ነው የሚያመለክተው፡፡ በኤፌሶን ምዕራፍ 2፡2 ላይ ሰይጣን የሚኖረው በአየር ላይ ሆኖ በጭፍሮቹ አማካኝነት ዓለምን እንደሚገዛና የዚህ ዓለም አምላክ እንደ ተባለ ቃሉ ያመለክተናል፡፡ (ዮሐንስ 12፡31፣ 2ቆሮንቶስ 4፡4)
በኢሳይያስ ላይ 53 ነቢዩ ወደፊት በክርስቶስ ሕይወት የሚፈጸመውን፣ ‹‹በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፣ (ቁ.4) እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፣ (ቁ.5) ተጨነቀ፣ (ቁ.7) ስለ ዓመፀኞች ማለደ፣ (ቁ.12) ላይ ወደፊት የሚፈጸመውን እንደ ተፈጸመ አድረጎ በኃላፊ ጊዜያት እንዳቀረበው፣ እንዲሁም ዮሐንስም ራዕዩን ያቀረበው በተመሳሳይ መንገድ ነው፡፡ ስለዚህ የግሥ ጊዜያቱ ኃላፊ ሲሆን፣ በተፈጻሚነቱ ወደፊት የሚፈጸም ትንቢታዊ ነው፡፡
3) የባሕል/የታሪካዊ መሠረት ችግር፡-
በመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችንና ጥናታችን ጊዜ ሌላው የሚገጥመን የትርጉም ችግር የባሕል/የታሪካዊ መሠረት ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ዘመን የነበረው የአይሁድ ሕዝብ እንዲሁም፣ አዲስ ኪዳን ሲጻፍ የነበረው የግሪክ ሕዝብ ታሪክና ባሕል ካልተረዳን፣ መጽሐፍ ቅዱስን በራሳችን ባሕል መሠረት ከተረጐምነው ለመረዳት በምናደርገው ጥረት ላይ ችግር ይፈጠርብናል፡፡ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንዳንረዳ ችግር የሚፈጥርብን የአንድ ሕዝብ የአኗኗር፣ የአመጋገብ፣ የአለባበስ፣ የአነጋገር ዘይቤና የድርጊት አፈጻጸማቸውን መሠረታዊ ታሪኩንና ባሕሉን አለማወቃችን ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በአጠቃላይ በአንድ ጊዜ ሳይሆን በተለያየ ጊዜ ስለሆነ፣ እያንዳንዱ መጽሐፍ በተጻፈበት ጊዜ መልእክት ተቀባዮች እነማን እንደ ነበሩ፣ የተጻፈበት ዐውድና የወቅቱ ሁኔታ ምን ይመስል እንደ ነበርና ዓላማውን ማወቁ አስፈላጊ ነው፡፡ ‹‹በመጽሐፍ ቅዱስ ስለ ተጠቀሱት ሕዝቦች የታሪክ የመልክዓ ምድር (ጂኦግራፊ) እና የባሕል መሠረታዊ ዕውቀት መኖር የእግዚአብሔርን ቃል ለማጥናትና ለመረዳት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው የታወቀ ነው፡፡ የታሪክ ቅደም ተከተልን በየዘመናቱ ስለሚለዋወጡ የሕዝቦች ባሕል በቂ ግንዛቤ ሲኖር የእግዚአብሔርን ቃል በተሻለ መልኩ ለመረዳት ያግዛል›› (የመጽሐፍ ቅዱስ አጠናንና አተረጓጐም World Vision-East Africa Sub-R/O,Kenya ገጽ 23)፡፡
የታሪክ ምልከታ በምናደርግበት ጊዜ እንዳየነው፣ በብሉይ ኪዳን የምናገኘው ታሪክ የአይሁዶች ሲሆን፣ በአዲስ ኪዳንም ደግሞ የክርስቶስና የደቀ መዛሙርቱ ቢሆንም ዋናው የታሪኩ ባለቤት እግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔርም የሠራው በሰዎች ታሪክና ባሕል ውስጥ ስለሆነ፣ ታሪክንና ባሕልን ለያይተን ማየት አንችልም፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱሳችንን ስናነብና ስናጠና ታሪኮችንና ባሕሎችን በተገቢው መንገድ መረዳት ስንችል ቃሉን በተሻለ ሁኔታ ልንረዳ እንችላለን፡፡
ታሪክንና ባሕልን በምናጠናበት ጊዜ በብሉይ ኪዳን፣ በአዲስ ኪዳንና በእኛ ዘመን ያለውን የታሪክና የባሕል ልዩነቶች በሚገባ ማስተዋልና መረዳት ይኖርብናል፡፡ ከመመልከትና ከመተርጐም አልፈን ወደ ማዛመድ (ተግባራዊ ወደ ማድረግ) ስንመጣ ችግር እንዳይገጥመን አስቀድመን ባሕሉን/ታሪካዊ መሠረቱን በሚገባ መሥራት(መረዳት) ይኖርብናል፡፡ የዕብራውያን (አይሁዶች) የግሪኮች፣ የሮማውያን፣ የግብፃውያንና የሌሎችም አገሮች ታሪክና ባሕል በቃሉ ውሰጥ ተንፀባርቆ ስለሚገኝ፣ በእኛ ላይ ላለመጫን ጥንቃቄ ማድረግ አለብን፡፡
በመቀጠል ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ወስደን እንተርጉም፡፡ የመጀመሪያው በዘዳግም ምዕራፍ 22፣ ቁጥር 5 ላይ ‹‹ሴት የወንድ ልብስ አትልበስ፣ ወንድም የሴት ልብስ አይልበስ፣ ይህን የሚያደርግ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነው›› ይላል፡፡ በመጀመሪያ ዐውዱን ስንመለከተው ከፊትና ከኋላ ካለው ሐሳብ ጋር አብሮ አይሄድም፡፡ ይህን ክፍል መተርጐም የምንችለው ከታሪካቸውና ከባሕላቸው ተነስተን ነው፡፡
ይህን ክፍል በሚገባ ሳንተረጉም ወደ ማዛመድ ከሄድን ትልቅ ችግር ውስጥ እንገባለን፡፡ ከአንድ አርባ ዓመት በፊት፣ ከአንድ ሦስት ወንድሞች ጋር የሚስት ጉዳይ ተነስቶ ስንጫወት ሳለ፣ አንዱ ‹‹ እኔ ሚስቴ ሱሪ ብትለብስ በዓይኗ ሚጥሚጣ ነው የምጨምርባት ብሎ›› ተናገረ፡፡ እኛም የነበረንን የመጽሐፍ ቅዱስ መረዳት አካፍለነው ተለያየን፡፡ ደግነቱ እርሱም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሳያገባ ወደ ጌታ ተጠቃለለ፡፡ ስለዚህ በዚያን ጊዜ የነበረው የወንድና የሴት ልብስ ምን ዓይነት ነበር? ከዛሬው የወንድና የሴት ልብስ ጋር የነበረው መመሳሰል ምን ዓይነት ነበረ? ወይስ ምንም ዓይነት መመሳሰል አልነበረውም ነበር? ብለን መጠየቅና መልስ ማግኘት አለብን፡፡
በብሉይ ኪዳን ስንመለከት የወንዶችም የሴቶችም በአሰፋፉ ልዩነት ኖሮት የሁለቱም ልብስ ቀሚስ ነበር፡፡ የመካከለኛው ምሥራቅ አለባበስ እንደ ነበራቸው ከባሕላቸው መረዳት እንችላለን፡፡ መዝሙረኛውም በትንቢታዊ መዝሙሩ እንዲህ ይላል፣ ‹‹ልብሶቼን ለራሳቸው ተከፋፈሉ፣ በቀሚሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ›› በማለት በመዝሙር 22፡18 ላይ ይናገራል፡፡ የትንቢቱን ፍጻሜ ጸሐፊም ሐዋርያው ዮሐንስ በወንጌሉ 19፡23-24 ላይ እንዲህ ይላል ‹‹… እጀ ጠባቡን ወሰዱ፡፡ እጀ ጠባቡም ከላይ ጀምሮ ወጥ ሆኖ የተሠራ ነበረ እንጂ የተሰፋ አልነበረም፡፡ ስለዚህ እርስ በርሳቸው፣ ለማን እንዲሆን በእርሱ ዕጣ እንጣጣልበት እንጂ አንቅደደው ተባባሉ፡፡ … ›› በማለት ዘግቦታል፡፡
ከዚህ የምንረዳው የወንዶቹ እንደ እጀ ጠባብ ወይም እንደ ቀሚስ ያለ (የዐረቦቹን ጀለቢያ የመሰለ) ሲሆን፣ የሴቶቹ ደግሞ ፊትን መሸፋፈን ያለበት ከወንዶቹ የተለየ ቀሚስ ነበር፡፡ ስለዚህ ባሕሉን ሳንረዳ ለማዛመድ ብንነሣ፣ ‹‹ሴት የወንድ ልብስ አትልበስ፣ ወንድም የሴት ልብስ አይልበስ›› የሚለውን እንዳለ ብንወስደው፣ ዛሬ ወንዶችም ሴቶችም ቀሚስ ይልበሱ ማለታችን ነው፡፡ ይህ በጣም አስቸጋሪ ይሆናል፣ አንድ ጊዜ ሁለት ወንድሞች ሥራቸው መርካቶ ስለ ነበረ፣ በየዕለቱ በምሳ ሰዓት ከቤት ምሳ እየመጣላቸው ይበሉ ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ምሳ ያመጡላቸው ልጆች ሳይመቻቸው ስለ ቀረ፣ ማታ ተመልሰው መጥተው የምሳ ሳህኑን ሳይወስዱላቸው ቀሩባቸው፡፡
በዚህ ጊዜ አንደኛው የምሳ ሳህኑን ሥራ ቦታ ቀልፎበት ሊወጣ ሲል ጓደኛው እኔ አወስድልሃለሁ ብሎ ያዘለትና ትንሽ እርምጃ እንደ ሄዱ መንገድ ላይ አስቀምጦለት ቀደሞት ሄደ፡፡ ጓደኛውም እረ እባከህን ይዘህልኝ ሂድ እያለ እየጮኸ ቢለምነውም ጥሎት ሄደ፡፡ ችግሩ ምን እንደ ሆነ ገባችሁ?፡፡ ለአንደኛው በባሕሉ የምሳውን ዕቃ ይዞ መሄድ ስለ አሳፈረው፣ የምሳ ሣህኑን ቆልፎበት ወደ ቤቱ ለመሄድ ያሰበው ለዚህ ነው፡፡ ለዚያኛው ጓደኛው ደግሞ የምሳ ሣህን ይዞ መሄድ አይደለም፣ በመሥራቱም ስለሚያምንበት ቤቱ ምግብ መሥራት ይችላል፡፡ ስለዚህ ነው የበላበትን ሣህን ይዞ መሄድ የቀለለው፡፡ ጓደኛውም ሳይወድ እየከበደውና እየተሸማቀቀ፣ የበላበትን ሣህን ይዞ ወደ ቤቱ ሄደ፡፡
ስለዚህ አንድ የምንባብ ክፍል አልገባ ካለን ከመጽሐፉ ውስጥ መግለጫዎች/ኢንፎርሜሽን መሰብሰብ ያስፈልገናል፡፡ ተጨማሪ ርዳታ ከፈለግን የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላትና ኢንሳይክሎፒዲያ ብንመለከት ብዙ ሀሳብ ሊሰጡን ይችላሉ፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያ በተጨማሪ ማየት ብንችል በእጅጉ ተጠቃሚዎች እንሆናለን፡፡ እንደተለመደው የሚከተሉትን ጥያቄዎች ሠርተን በሚቀጥለው ጥናታችን በሰላም እንገናኝ፡፡
1. በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 4፡4 ላይ ‹‹በሰማርያም ሊያልፍ ግድ ሆነበት›› ጌታ በዚያ ለማለፍ ለምን ችግር ሆነበት?
2. በኤፌሶን 2፡17 ላይ ‹‹መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን … የምሥራች ብሎ ሰበከ›› በዚህ ጥቅስ ውስጥ የባሕል ችግር እንዳለ ይታያችኋል? ካለ እንዴት ተፈጠረ?
3. በማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 16፡3 ላይ ‹‹ድንጋዩን ከመቃብር ደጃፍ ማን ያንከባልልናል? እንደተባባሉ እናገኛለን፡፡ በዚህ ጥቅስ መሠረት በአገራችን ከምናውቀው የመቃብር ይዘት ምን የባሕል ልዩነት ታያላችሁ(አገኛችሁ)? በኔት ወርክ ምክንያት በመቋረጡ ይቅርታ እጠይቃለሁ።
0 Comments