የዛሬውን ትምህርት ስለ ትርጉም ምንጭ ከማየታችን በፊት፣ ባለፈው ለተጠየቁት ጥያቄዎች የሰጣችሁትን መልስ፣ ዛሬ ከሚሰጡት መልሶች ጋር በማመሳከር ምን ያህል ተቀራራቢ መልሶች እንደ ነበሩ ተመልከቱ፡፡
በመጀመሪያ የአረማይክ ቋንቋ የማን ሀገር ቋንቋ ነበር? እና በአረማይክ የተጻፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ማስረጃ ስጥ? የሚል ነበር፡፡ በብሉይ ኪዳን በየዘመናቱ ገናና የነበሩ ሀገሮችን መጽሐፍ ቅዱሳችንም የዓለም ታሪክም ያወሱልናል፡፡ የዛሬን አያድርገውና ግብፅ፣ ሶሪያ፣ አሦር፣ ባቢሎን (የዛሬው ኢራቅ)፣ ሜዶፋርስ (ኢራን)፣ ግሪክና ሮም፣ በየዘመናቱ የተነሱና ከመቶ ሃያ የማያንሱ ሀገሮችን የገዙና ያስተዳደሩ ገናና መንግሥታት ነበሩ፡፡ ነብዩ ዳንኤልም በትንቢቱ በምዕራፍ ሁለት፣ ሰባትና ስምንት ላይ ከባቢሎን ጀምሮ እስከ ሮም ድረስ ባየው ሕልምና ራዕይ ውስጥ በተገለጠለት መሠረት፣ በጊዜው ዓለም ተብሎ የሚታወቀውን ግዛት ገናና በመሆን ተራ በተራ መግዛታቸው በታሪክም የታወቀ ነው፡፡
ግብፅ ከገናናነቷ ወድቃ ሶሪያ ገናና መሆን ስትጀምር የአረማይክ ቋንቋዋን አስፋፍታ የሶሪያ የንግድ ቋንቋ (እንደ ዘመኑ እንግሊዝኛ የመግባቢያ ቋንቋ) እንዲሆንና እንዲታወቅ አደረገች፡፡ አሦር ሶሪያን አሸንፋ በተራዋ ገናና ስትሆን የራስዋን ቋንቋ በመንግሥታዊ አስተዳደር በሆነው ጉዳይ ላይ ብቻ ስትጠቀም፣ አረማይክን የንግድ ቋንቋ ሆኖ እንዲቀጥል አደረገች፡፡ በመቀጠልም ባቢሎን አሦርን አሸንፋ ገናና መሆን ስትጀምር፣ አሦር እንዳደረገችው እርሷም ስላደረገች፣ አረማይክ በብዙ ሀገሮች ስለተስፋፋ በንግድ ቋንቋነቱ ተፈላጊ ሆኖ ቀጠለ፡፡ ባቢሎንም ወድቃ ሜዶፋርስ ገናና ስትሆንም፣ ገናናው አረማይክ የንግድ ቋንቋነቱን ቀጠለበት፡፡
ሜዶፋርስ በግሪክ ተሸንፋ ስትወድቅ አረማይክ ተቀናቃኝ መጣበት፡፡ የግሪክ ንጉሥ የነበረው ታላቁ እስክንድር በግሪክ ቋንቋ ላይ ሠፊ ሥራ በመሥራቱ ቋንቋው አረማይክን ተክቶ የንግድ ቋንቋ እንዲሆን አደረገ፡፡ እንዲህ ቢሆንም ግን አረማይክ የሠፊው ሕዝብ ቋንቋነቱን በመቀጠል ብዙዎች በግሪክና በሮም ዘመንም ይጠቀሙበት ነበር፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም በዚህ ቋንቋ በመናገር እንደ ተጠቀመበት ይታወቃል፤ በዚህ ቋንቋ ትንቢተ ዳንኤል ከምዕራፍ 7-12 ያለው ክፍል ተጽፎበታል፡፡
በሁለተኛ የተሰጠው ጥናት በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 16፡ 13 ‹‹ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፡- ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል?›› ብሎ በጠየቃቸው ጥያቄ ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡ ኢየሱስ የሄደባት ይህች ከተማ በሁለት መሪዎች ስም የተሰየመች ከተማ ነበረች፤ በመጀመሪያ ታላቁ እስክንድር በሚገዛበት ጊዜ በአባቱ ስም ‹‹ፊልጶስ›› ተብላ እንድትጠራ አድርጎ ነበር፡፡ በመቀጠልም ሮም ገናና ሆና ዓለምን ስትገዛ በንጉሡ መጠሪያ ቄሣር በሚለው ስም ላይ በመመሥረት ቂሣርያ ተብላ መጠራት ጀመረች፡፡ የወንጌሉ ጸሐፊ ግን ሁለቱንም ስሞች በመጠቀም ‹‹ፊልጶስ ቂሣርያ›› በማለት ሲጠቀምበት እንመለከታለን፡፡ ይህ ሥፍራ በሁለቱም ነገሥታት ዘመን ከፍተኛ አምልኮ የሚካሄድበት ሥፍራ ነበር፡፡ ሰዎች በከፍተኛ ደረጃ የአጋንንትን ጥልቅ ሥራ የሚሠሩበትና ከጥልቁ ሠራዊት ጋር ግንኙነት የሚያደርጉበት ሥፍራ ሲሆን፣ ሰዎችም ወደዚያ ሥፍራ መሄድ በጣም ይፈሩ ነበር፡፡ ጌታ ግን ደቀ መዛሙርቱን ወደዚያ ሥፍራ ይዟቸው በመሄድ ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል? ብሎ ጥያቄ ጠየቃቸው፡፡ የእነርሱን የተለያዩ መልሶች ከሰማ በኋላ፣ እናንተስ ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ቀደም ብሎ ‹‹አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ›› ብሎ መለሰለት፡፡ በመቀጠልም ጌታ ‹‹በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፣ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም›› በማለት ተናገረው ይበልጥ የሚገባን ታሪኩን ስናውቅ ሲሆን፣ በጥልቁ ሠራዊት ላይ ሥልጣን እንዳለውና ለእነርሱም ሥልጣን መስጠቱን ማወጁ እንደሆነ ይገባናል፡፡
በመጨረሻም ለጥናት የቀረበው በ1ኛ ጴጥሮስ ምዕራፍ 1፡13 ላይ ‹‹ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና በመጠን ኖራችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ›› በሚለው ጥቅስ ውስጥ የባሕል ልዩነቶችን ማየት እንድንችል የሚያደርግ ነበር፡፡ ይህ ክፍል ለቃላትና ለባሕልም ጥናት ይሆናል፤ ‹‹ልቡናችሁን›› የሚለው ቃል ልብን ነው ወይስ አእምሮን ነው የሚያመለክተው፣ ብለን ቃሉን አስቀድመን መተርጐም አለብን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ዘመን ስለ ሰው የነበራቸው መረዳት፣ ሰው የሚያስበውና የሰውነቱ ሁሉ ዋና ተቆጣጣሪና አዛዥ ልቡ እንደሆነ ይረዱ ነበር፡፡ የእኛም የመጽሐፍ ቅዱስ (1954 ትርጉም) ተርጓሚዎች ‹‹ልቦናችሁን›› የሚለውን ቃል በዘመኑ በነበረው አረዳድ እነርሱ አእምሮ ማለታቸው ነበር፡፡
በአሁኑ ዘመን ሳይንስ እያደገ በመምጣቱ የሰው ዋና የሰውነቱ ተቆጣጣሪ አእምሮው እንደ ሆነ በማስረጃ አረጋግጠዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙ ትርጉሞች ልቡና የሚለውን ቃል ‹አእምሮ› ብለው ተርጉመውታል፡፡ (አዲሱ መደበኛ ትርጉም ‹‹ልባችሁን አዘጋጁ›› ብሎ ተርጉሞታል)፡፡ ጌታ ሲመጣ ጸጋውን ለመቀበል ልባችንን (አእምሮአችንን) ማዘጋጀት እንዳለብን ያስተምረናል፡፡ በባሕል በኩል ያለውን ልዩነት ስንመለከት ቀደም ያሉት ሰዎች ‹የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁ› የሚለው ሐሳብ በቀላሉ ይገባቸው ነበር፣ ምክንያቱም የሚታጠቁት ወገባቸው ላይ ስለ ነበረ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሰው ቀበቶውን የሚታጠቀው በወገቡ ላይ ሳይሆን በመቀመጫው ስለ ሆነ፣ ለዚህ ዘመን ትውልድ በቀላሉ ይገባዋል ብዬ አላስብም፡፡ ምክንያቱም የልቦናን ወገብ መታጠቅ ለወጣቱ በቀላሉ ስለማይገባው ነው፤ ሰው በአእምሮው ያስባል እንጂ በመቀመጫው ሊያስብ በፍጹም አይችልም፡፡(ዶክተር ምሕረት ደበበም በቲቪ ፕሮግራሙ ‹‹አእምሮን ማዘጋጀት››(mindset) በማለት ያካሂዳል፡፡ (በEBS tv ተከታተሉት ጠቃሚ ትምህርት ታገኙበታላችሁ)፡፡
3 . ሦስት የትርጉም ምንጮች፡-
በዛሬ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን የምንመለከተው የትርጉም ምንጮችን ይሆናል፤ መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጐም የምንነሣበት የራሱ የሆነ ምንጭ ያለው ቢሆንም፣ ሌሎች ምንጮችም እንዳሉትም መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡ ብዙዎች የመጽሐፍ ቅዱስ አዋቂዎች እንደሚስማሙበት ሦስት የትርጉም ምንጮች አሉ፡፡ ሦስቱ የትርጉም ምንጭ የምንላቸው ተርጓሚው፣ ቃሉና ጸሐፊው ናቸው፣ ስለ እንዳንዳቸው ቀጥለን እንመለከታለን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጐም በምንነሣበት ጊዜ መጠንቀቅ ያለብን የጸሐፊውን ሐሳብ ስተን፣ የራሳችንን መረዳትና ስሜት እንዳናጸባርቅ ነው፡፡
ሀ. ተርጓሚው፡- የመጀመሪያው እውነተኛ የትርጉም ምንጭ ያለው በተርጓሚው ዘንድ እንደሆነ ብዙዎች የመጽሐፍ ቅዱስ አዋቂዎች ይስማሙበታል፡፡ ተርጓሚው ማለት እኔ ነኝ፣ አንተ ነህ፣ አንቺ ነሽ፣ እኛ አንባቢዎች ሁላችን ነን፡፡ ተርጓሚዎች ከዚህ ቀደም ብለን ያየናቸውን የመመልከት ሂደቶች በትክክል እየተመለከትን ከሄድን ትርጉሙ ትክክል ሊሆን ይችላል፡፡ ልንመለከት የሚገባውን በትክክል ካልተመለከትን ግን ትርጉሙን ልንስት እንችላለን፡፡ ስለዚህ ጥሩ ተመልካቾች ከሆንን፣ ጥሩ ተርጓሚዎች እንሆናለን፡፡
ለ. ቃሉ፡- ሁለተኛው እውነተኛ የትርጉም ምንጭ ያለው በቃሉ በራሱ ውስጥ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ላለፉት ሃያ ዓመታት ጊዜ ውስጥ የተነሱት የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች፣ ቃሉ በራሱ ትርጉም አልባ ነው ብለው ቢናገሩም፣ የማንክደው ሐቅ ቢኖር ግን የቃሉን የትርጉም ምንጭነት ነው፡፡ የጸሐፊውን ሐሳብ በትክክል ሊያስተላልፍ የሚችለው ቃሉ ራሱ ነው፡፡ ቢሆንም ግን ሰዎች ቃሉን ካልተረዱት በተሳሳተ መንገድ ሊተረጉሙት ይችላሉ፡፡ በተለይ በአማርኛ ቋንቋ፣ አንድ ቃል በማጥበቅና በማላላት ሁለት ትርጉም ሊኖረው ይችላል፡፡ በማጥበቅና በማላላት ብቻ ሳይሆን፣ አንድ ቃል ሁለት፣ ሦስት ትርጉም ሊኖረው ይችላል፡፡ እንደዚያ ቢሆንም አሁንም ቃሉ ውስጥ ትርጉም አለ ማለት እንችላለን፡፡ ትርጉሙ የሚወሰነው ግን በጸሐፊውና በተርጓሚው አጠቃቀም መሠረት ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ከበደ የሚለውን ቃል በዐ/ነገር ውስጥ ስናገኘው ባለቤት ሲሆን ስም ይሆናል፣ ግሥ ሲሆን ትርጉሙ ተለውጦ መዘነ ማለት ይሆናል፡፡ ወደፊት ቃላትን ወደ መተርጐም ስንመጣ ብዙ ምሳሌዎችን ጨምረን እንመለከታለን፡፡
ሐ. ጸሐፊው፡- ተርጓሚውና ቃሉ የትርጉም ምንጭ ቢሆኑም፣ እውነተኛው የትርጉም ምንጭ ጸሐፊው ራሱ ነው፡፡ ምክንያቱም ተናጋሪው ራሱ ስለሆነ ሊለውና ሊያስተላልፍ የፈለገውን ሐሳብ በሚገባ ያውቃል፤ ከዚህ የተነሣ ከተርጓሚውም፣ ከቃሉም ይልቅ ትክክለኛ የትርጉም ምንጭ ጸሐፊው(ደራሲው) ነው፡፡ ስለዚህ እኛም እንተረጉማለን ስንል፣ ጸሐፊው ሊል ወደ ፈለገው ሐሳብ ለመድረስ ጥረት እናደርጋለን ማለታችን ነው፤ ወይም ወደ ጸሐፊው ትርጉም እንደርሳለን ማለታችን ነው፡፡ ጥሩ ተመልካች ከሆንንና በመንፈስ ቅዱስ ርዳታ ከተደገፍን፣ በቀጥታ ጸሐፊው ወዳለው መድረስ ባይሆንልንም፣ በምናደርገው የጥናት ጥረታችንና መረዳታችን ወደ ጸሐፊው ሐሳብ እንጠጋለን ማለት ነው፡፡
ስለዚህ የጸሐፊውን ሐሳብ/ዕቅድ ማወቅና መረዳት የመተርጐማችን ዓላማው ነው፡፡ በቃሉ ውስጥ ያለውን መልእክት ለማውጣትና ቃሉ በማይናገረው በሌላ ነገር እንዳንታመን ጥንቃቄ ማድረግ ዓላማችን መሆን አለበት፡፡ እግዚአብሔር በቃሉ ምን ብሎ እንደ ተናገረ ማወቅ የምንችለው ትክክለኛና አስተማማኝ በሆነ መንገድ ቃሉን ስንተረጉም ነው፡፡ መተርጐም ስንል ጸሐፊው እንዲጽፍ ያነሳሳውን ዓላማ ማወቅና መልእክቱ የተነገረበትን ዓላማ በሚገባ መረዳት አስፈላጊያችን በመሆኑ ነው፡፡
- ትርጉማዊ መጠይቆችን መጠየቅ
በመጀመሪያ ላይ በመመልከት ጊዜ በሰባት የመጠይቂያ ቃላት ተጠቅመን የጠየቅነው፣ ቀጥሎም የተለያዩ ምልከታዎች ያደረግነው፣ ከዚያም ሰዋስውንና የሥነ-ጽሑፉን ቅርጽ ስናይ የቆየነው፣ ወደ ትክክለኛ ትርጉም ለመምጣት ነበር፡፡ ቀደም ብለን በምልከታ ጊዜ እንጠይቅ እንደ ነበረው፣ አሁንም በሦስቱ ትርጉማዊ መጠይቆች በመጠቀም ብንጠይቅ ለማንኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል/ምንባብ ትርጉም ሊያስገኙልን ይችላሉ፡፡ ይህን ሁሉ ሥራ የምንሠራው የምንባቡን መልእክት/ሀሳብ ለመረዳት ነው፡፡ ጥያቄዎቹም የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. ጸሐፊው ስለ ምንድን ነው የሚናገረው? ብለን በምንጠይቅበት ጊዜ የድርጊቱን ባለቤት ያስገኝልናል፡፡
2. ጸሐፊው ስለ ድርጊቱ ባለቤት ምን አለ? የሚለውን ስንጠይቅ ማሟያ ሀሳቡን ይሰጠናል፡፡
3. ጸሐፊው ለምን ጻፈው? የሚለውን ጥያቄ ስንጠይቅ የተጻፈበትን ዓላማ እንድናገኝ ይረዳናል፡፡
- ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የምናገኘው ከተመለከትነው ውስጥ ሲሆን፣ በተሻለ መንገድ ስንመለከት በተሻለ መንገድ እንተረጉማለን፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች በአእምሮአችን ይዘን እየተመለከትን ሳለ መተርጐም መጀመር ይኖርብናል፡፡ የበለጠ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ የሐሳቡን መዋቅር/ስትራክቸሩን በደንብ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ምንባቡን ለመረዳትና ጥያቄዎቹን ለመመለስ የሰዋስው/ቨርቲካል ቻርት ሁልጊዜ መሥራት ጠቃሚ ነው፡፡(ለአስተማሪዎች)
- አንዳንድ ጊዜ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ የቃላት ጥናት ማድረግም አስፈላጊ ነው፡፡ ምከንያቱም ቃላት ትርጉምን ስለሚያጣምሙ የቃላት ጥናት በማድረግ ችግሩን ማቃለል ያስፈልጋል፡፡ የቃላት ጥናት እንዴት እንደምናደርግ በሚቀጥለው ጥናታችን ጊዜ እንማራለን፡፡ በሁሉ ላይ ሳይሆን በተወሰኑ በምንባቡ ውስጥ በሚገኙ ዋና ዋና ቃላት ላይ ብቻ ጥናት ማድረግ በቂ ነው፡፡
- እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ዝርዝሮችን በሚገባ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ምንባቡን በዝርዝር ማየት ከቻልን የበለጠ ልንረዳውና ዋና ሐሳቡን ለማግኘት የምንችልበት ደረጃ ላይ ለመድረስ እንችላለን፡፡
- ለእነዚህ ጥያቄዎች ያለህ መልስ፣ ጥናት በጀመርክበት ጊዜና ጥናትህን በጨረስክበት ጊዜ ያለው መረዳትህ የተለያየ ይሆናል፤ ምክንያቱም በምልከታችን ላይ በደንብ ከሠራን መረዳታችን እየጨመረ ስለሚመጣ ይሠፋል፣ ያድጋል፡፡
- ባለቤትና አንቀጹን (ማሟያ ሀሳቡን) በአንድ ላይ አድርገን ሙሉ ሀሳብ እንዲሰጡን ለማድረግ መቻል አለብን፡፡ ዋናውን ሀሳብ ማን? ለምን? ምን? መቼ? የት? እንዴት? ብለን በመጠየቅ ማግኘት እንችላለን፡፡
- ዓላማን የሚያስገኘውን ጥያቄ ጥናታቸንን ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ በአእምሮአችን ውስጥ ይዘን ማጥናት ይኖርብናል፡፡
ከዚህ በላይ የተመለከትናቸውን ሐሳቦች የበለጠ መረዳት የምንችለው አንድ ክፍል ወስደን ስንሠራና ስንለማመድ ነው፡፡ የአብዛኛዎቹ መልእክቶች ዓላማቸው ለማስተማር፣ ለማዘዝ፣ ለማጽናናት፣ ለማስጠንቀቅ ለመምከር የተጻፉ ስለ ሆኑ በዓላማቸው ግልጽ ናቸው፡፡ እንደ ሕግ፣ ታሪክ፣ ግጥምና ትንቢት ያሉት ጽሑፎች ግን ዓላማቸው በግልጽ ስላልተቀመጠ በቀላሉ ማግኘት ያስቸግረናል፡፡ (ይህን ሐሳብ ቀደም ብለን ተመልክተናል) ቢሆንም ግን ጸሐፊው በዓላማ ነውና የጻፈው ለመረዳት ሙከራና ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡
በዛሬው ቀን ከዚህ በላይ የተመለከትነው ሦስት የትርጉም ምንጮች መኖራቸውን ቢሆንም፣ ትርጉም አንድ ብቻ ነው፡፡ ሦስቱም የሚያደርሱን ወደ አንዱ ትርጉም ነው፡፡ ይህ ማለት ሁላችንም በፈለግነው መንገድ በምንወደውና ደስ በሚለን መንገድ ቃሉን መተርጐም የለብንም፣ ወይም የራሳችንን ትርጉም ይዘን ቃሉን ወደ መተርጐምና ያሰብነውን እንዲናገርልን ለማድረግ መሞከር አይኖርብንም፡፡ ከዚያ ይልቅ ጸሐፊው ሊል ወደ ፈለገው ሐሳብ/እውነተኛ ምንጭ ለመድረስ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል፡፡
ከዚህ በላይ የተመለከትነው ስለ ትርጉም ምንጮችና የተለያዩ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ወደ ዋናው ሐሳብ መድረስን ነበር፡፡ በተለይም ዓላማን ሊያስገኝ የሚችለውን ጥያቄ በመጠየቅ ዋናውን ሐሳብ ማግኘትን ይመለከታል፡፡ በዚህም መሠረት ዓላማን ስለ መረዳት፣ በቤታችሁ ሆናችሁ የምትሠሩዋቸው ሦስት ጥያቄዎች ተዘጋጅተው ቀርበዋል፡፡
- በማቴዎስ ምዕራፍ 5፡21-48 ባለው ክፍል ውስጥ ስለ መግደል፣ ማመንዘር፣ መፋታት፣ መሐላ፣ መበቀልና መውደድ ጸሐፊው በአንድነት ሲገልጽ፣ ዓላማው ስለ ምንድን ለማስተማር ፈልጐ ነው?
- በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 10፡38-42 ላይ ያለውን ሉቃስ ሲጽፍ ዓላማው ምን ነበር?
- በጌታ አምኖ የተለወጠና የዳነ ክርስቲያን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ኃጢአት እንደሚሠራ የታወቀ ነው፤ ሐዋርያው ዮሐንስ በመጀመሪያ መልእክቱ ምዕራፍ 3፡8 ላይ ‹‹ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው›› ብሎ ሲጽፍ ዓላማው ምን ለማስተማር ፈልጐ ነው?
0 Comments