የዛሬውን ትምህርት ስለ መተርጐም ከማየታችን በፊት ባለፈው ለተጠየቁት ጥያቄዎች የተሰጡትን መልሶች እንመልከት፡፡  በመጀመሪያ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 2፡27 ላይ ‹‹በእውነት ታሞ ለሞት እንኳ ቀርቦ ነበርና፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ማረው ኀዘን በኀዘን ላይ እንዳይጨመርብኝ … ›› በማለት በሚናገረው ውስጥ ከሁለቱ ኀዘኖቹ አንዱ በግልጽ እንደ ምንመለከተው የአፍሮዲጡ መታመም ሲሆን፣ ሁለተኛው ኀዘኑ በባለፈው ባጠናነው ትምህርት እንዳየነው የሁለቱ ሴቶች በአገልግሎታቸው አለመስማማታቸው ነበር፡፡  

በሁለተኛ የተሰጠው ጥናት በገላትያ ምዕራፍ 1፡16 ላይ ‹‹… ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ … ›› የሚለው ወደ መተረጐም ያዘነበለ ጥያቄ ነው፡፡ ከዚህ ሐረግ ውስጥ የምናገኘው ትምህርት ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጆች ለማዳን ሰብዓዊ አካል ይዞ መምጣቱን ያመለክታል፡፡ በዕብራውያን መልእክት ምዕራፍ 2፡14-18 ባለው ክፍል ውስጥ ‹‹… የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም›› በሚለው መሠረት ኢየሱስ እንደ ጳውሎስ ያለ የሚራብ፣ የሚጠማ፣ የሚያንቀላፋ፣ የሚደክም፣ የሚያዝን፣ የሚደሰትና የሚሞት አካል(ሥጋ) ይዞ መገኘቱን ያመለክታል፡፡ ጳውሎስ ‹ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ› የሚለው እርሱን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን ሁላችንንም የሚመለከት ነው፡፡ ጌታ ሁላችንም ባለፍንበት መንገድ ያለፈ በመሆኑ የችግራችን ተካፋይ መሆን የቻለው በዚህ ምክንያት ነው፤ ስሙ የተባረከ ይሁን፡፡       

በሦስተኛ ተሰጥቶ የነበረው ጥናት የተመሠረተው በዕብራውያን ምዕረፍ 2፡6-8 ላይ ባለው ክፍል ላይ ሲሆን፣ መልሱም በምርጫ የሚመለስ ነው፡፡ መልሱ ምርጫ ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ በምናጠናበት መንገድ መጠናት አለበት፡፡ በመዝሙረ ዳዊት ላይ ስንመለከተው በቅርጹ ግጥም፣ በይዘቱ ትንቢት ሲሆን፣ በዕብራውያን ጸሐፊ መልእክት ሆኖ እናገኘዋለን፤ በዚህ መሠረት መልሱ መ . ሁሉም መልስ ነው የሚለው ነው፡፡

ለ. መተርጐም

 እግዚአብሔር እስከ አሁን ድረስ ረድቶን፣ የመጀመሪያውን የመጽሐፍ ቅዱስ አጠናን ዘዴ የመመልከት ክፍል ጨርሰን ሁለተኛውን የመተርጐም ክፍል በመጀመር ላይ ነን፡፡ በመመልከት ዙሪያ ምን ያህል እንደ ተጠቀማችሁ ባላውቅም፣ ትንሽ ነገር እንዳገኛችሁበት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ አሁን የመተርጐምን ጥናት(ሥራ) እንጀምራለን፡፡

 ሁላችንም መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ፣ ለምናነበው ነገር ትርጉም መስጠታችን አይቀርም፣ ዋናው አጠያያቂው ጉዳይ ግን የምንሰጠው ትርጉም ምን ያህል ትክክለኛ ነው የሚለው ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ጥናት የምናደርገው ሁላችንም እንደፈለግን እንዳንተረጉምና ወደ ተሳሳተ ትርጉም እንዳንደርስ እንዲረዳን ነው፤ ስለዚህ ወደ ትክክለኛው ትርጉም ሊያደርሱን የሚችሉትን ዘዴዎች በመቀጠል ለመጠቆም እንጀምራለን፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ሐሳብ፣ ዓላማና ዕቅድ የያዘ ስለሆነ፣ ስናነበው፣ ስናጠናውና ስንተረጉመው ጥንቃቄ ማድረግ አለብን፡፡ ‹‹የእግዚአብሔር ሐሳብ የተጠበቀው በዚህ መጽሐፍ ከሆነ ባንጻሩም የእግዚአብሔር ሐሳብ በአግባቡ መተላለፍ ካለበት መጽሐፉን በዘፈቀደ ልናነበውም ሆነ ልንተረጉመው አንችልም ማለት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በመጽሐፍ ቅዱስ መተረጐም ካለበት መነበብም ያለበት ከፊት ወደኋላ እንዲሁም ከኋላ ወደፊት በማየት ነው፡፡ ይኸውም ብሉይ ኪዳን በአዲስ ኪዳን መነጽርነት ሊነበብ፣ አዲስ ኪዳንም በብሉይ ኪዳን መነጽርነት ሊነበብ ይገባል›› (ምኒልክ አስፋው የመጽሐፍ ቅዱስና የትርጓሜ ስልቱ ገጽ 12)፡፡

መጽሐፍ ቅዱስን መተርጐም ከመመልከት ቀጥሎ የሚመጣ ሂደት ነው፣ ጥሩ ተመልካች ከሆንን ጥሩ ተርጓሚ መሆን እንችላለን፡፡ ጥሩ ተርጓሚ ከሆንን ጥሩ በተግባር የምንገልጸው (የምንኖረው) እንሆናለን፡፡ በዚህም ምክንያት ቃሉን ስናጠናና ስንተረጉም ዘዴውን ማወቅ  ለራሳችንም ሆነ ሌሎችን ለማገልገል እጅግ አስፈላጊና ጠቃሚ ነው፡፡ በሕይወታችንና በአገልግሎታችን ቃሉ የመጨረሻው  ባለ ሥልጣን  መሆኑን ማወቅ ለመንፈሳዊ ዕድገታችን እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ ነው፡፡

  1. የመተርጐም ዓላማው ምንድን ነው?፡-

የመተርጐም ዓላማው ከእግዚአብሔር ለሰዎች የተላከውንና የተላለፈውን መልእክት ሳናዛባና ሳንለውጥ በትክክል መተርጐምና መረዳት መቻል ማለት ነው፡፡ በብሉይ ኪዳንና በመጀመሪያው ምዕተ ዓመት ባሉ ሰዎችና በእኛ መካከል ክፍተቶች በመኖራቸው ምክንያት መተርጐም አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቶአል፡፡ መመልከት ያለውን ሐሳብ በምንባቡ ውስጥ ምን እንዳለ ለማወቅ አጥንቶ መድረስ ሲሆን፣ መተርጎም ግን በቃሉ ውሰጥ የተቀመጠውን ምን ማለት እንደሆነ ትርጉም ለመስጠት መወሰን ነው፡፡ ቃሉን በሕይወታችን ተግባራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ የሆኑትን ነገሮች ማስተካከል ማለት ነው፡፡

2.    መተርጐም ያስፈለገበት ምክንያት፡-  

  • የጊዜ ክፍተት፡- በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን የተጻፉት ነገሮችና የተፈጸሙበት ሁነቶች ካለንበት ዘመን ጋር የብዙ ሺ ዓመታት ርቀት አላቸው፡፡ ከዚህ የተነሣ በሐሳብ፣ በዕውቀትና በአስተሳሰብ፣ በአመጋገብ፣ በአለባበስና በአነጋገር  መለያየትና መራራቅ ስለ አለ፣ የተጻፉት ነገሮች እንዳይገቡን እንቅፋት ይሆኑብናል፡፡ ስለዚህ የተራራቅንበት የጊዜ ክፍተቶች መረዳት ዋና አስፈላጊ ችግር ፈቺ መንገድ ነው፡፡
  • የቋንቋ ክፍተት፡- የጊዜ ክፍተት ከሚፈጥሩት መካከል አንዱ ቋንቋ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በሦስት የተለያዩ ቋንቋዎች ተጽፏል፤ ብሉይ ኪዳን በዕብራይስጥና በአረማይክ ቋንቋ የተጻፈ ሲሆን፣ አዲስ ኪዳን ደግሞ በግሪክ ቋንቋ ተጽፏል፡፡ እያንዳንዱ ቋንቋም የራሱ የሆነ ሰዋስው፣ የቃላት ፍቺ፣ የሀሳብ አገላለጽ፣ የምንባብ አወቃቀር፣ ምሳሌአዊና ዘይቤአዊ አጠቃቀም… ወዘተ አለው፡፡ ይህን ችግር ማቃለል የሚቻለው የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያዎችንና መዝገበ ቃላትን በመጠቀም ይሆናል፡፡

መሠረታዊ ቋንቋዎች የሚያስተላልፉትን እውነቶች(ሐሳብ) ሌሎች ቋንቋዎች ማስተላለፍ አለመቻላቸውን ጥናታችንን ስንጀምር ተመልክተናል፡፡ በዚያን ጊዜ ስለ ተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አመጣጥ፣ በመተርጐም ጊዜ እናነሣለን ባልኩት መሠረት አሁን እንመልከት፡፡ አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ሲተረጐም ምንም እንኳን ተርጓሚዎች የዕብራይስጡን፣ የግሪኩን፣ የላቲኑንና የግዕዙን ትርጉም፣ ቢመለከቱም ዋና መሠረት አድርገው የሚተረጉሙት አንድን ትርጉም ነው፡፡ ስለዚህ ያ ትርጉም (ልጅ እናትና አባቱን እንደሚመስል) መሠረቱን ይመስላል፡፡

  • ክፍተትባሕላዊ፡- በእኛና መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ዓለም (ሕዝብ) መካከል ከፍተኛ የባሕል ክፍተት አለ፤ ባሕል አጠቃላይ የሰውን የሕይወት ገጽታ የሚያሳይ የተለያዩ እሴቶች ጥንቅር ውጤት የሆነ ሥርዓት ነው፡፡ ባሕል የሰው ሁለንተናዊ የአኗኗር መንገድ (ዘይቤ) ነው፡፡ ቀደም ብዬ እንደ ገለጥኩት በሐሳብ፣ በዕውቀትና በአስተሳሰብ፣ በአመጋገብ፣ በአለባበስና በአነጋገር መለያየትና መራራቅ አለ፣ በተጨማሪም በፖለቲካ፣ በመጓጓዣ፣ በእርሻ፣ በንግድና በሃይማኖት ልዩነት አለ፡፡ ከዚህ የተነሣ መጽሐፍ ቅዱስን እንደሚገባ እንዳንረዳ እንቅፋት ይሆኑብናል፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን ችግሩን ማስወገድ ይኖርብናል፡፡ 
  • ታሪካዊ ክፍተት፡- በእኛና በቅዱሳት መጻሕፍት መካከል ከፍተኛ የሆነ የጊዜ ርቀት አለ፤ ታሪክ ባለፉት ጊዜ ውስጥ ስለተፈጸሙ የተለያዩ ሁነቶች ወይም ክንዋኔዎች የሚደረግ ጥናት ነው፡፡ ታሪክ ባለፉት ጊዜያት ስለተፈጸሙት ሁነቶች የተለያዩ ሥነ-ጽሑፋዊ ቅርጾችን በመጠቀም በጽሑፍ የሠፈረ ዘገባ ነው፡፡ ታሪክ ጸሐፊዎች ሰዎች ያሰቡትን፣ የተናገሩትንና ያደረጉትን ነገሮች በማጥናት መረጃዎችን በመሰብሰብና ትርጉም በመስጠት አቀናጅተው በሰው ቋንቋ በጽሑፍ ያሰፍሩታል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም የታሪክ መጽሐፍ ነው፣ ከሌሎች የታሪክ መጻሕፍት ልዩ የሚያደርገው፣ በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን የታሪኩ ባለቤት እግዚአብሔር በመሆኑ ነው ፡፡
  • ሥነ-ጽሑፋዊ ክፍተት፡- ሥነ-ጽሑፍ በቋንቋ የተቀናጀ የሐሳብ ውጤት ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትን የጻፉልን ሰዎች የጻፉበት ቋንቋ፣ የተጠቀሙባቸው የአጻጻፍ ስልቶች፣ ፈሊጣዊና ምሳሌያዊ አነጋገሮች፣ የታሪክ አዘጋገባቸው … ከእኛ ዘመን ጋር ስናነጻጽረው ሠፊ ክፍተት አለው፡፡ በተለይም የጥበብ መጻሕፍትን ስንመለከት እንዳየነው የእነርሱ የግጥም አጻጻፍና የእኛ የግጥም አጻጻፍ በእጅጉ የተለያዩ ናቸው፡፡ ከዚህ የተነሣ የምናነበው የግጥም ጽሑፍ ሁሉ አይገባን ይሆናል፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ስንተረጉም እንደ ሥነ-ጽሑፉ ቅርጽ መሆን እንዳለበት መረዳት ይኖርብናል፡፡  
  • መልክዓ ምድራዊ ክፍተት፡- በእኛና መጽሐፍ ቅዱስ  በተጻፈበት ዘመን ከፍተኛ የሆነ የመልክዓ ምድር ለውጦች በተለያዩ ሥፍራዎች፣ ከተሞች፣ መንደሮችና አገሮች ላይ ተካሂደዋል፡፡ ለውጦቹም የአየር ጠባይ፣ የከተሞች መፍረስና መገንባት፣ በሰዎች ኑሮ ሁሉ ላይ ትልቅ ለውጥ ታይቶአል፡፡ እነዚህም ለውጦች በአተረጓጐማችን ላይ የማይናቅ ትርጉም የማዛባት ሚና አላቸው፡፡ ከዚህም የተነሣ በቃሉ ውስጥ የተጻፉትን እውነቶች ለመረዳት ለዘመኑ አማኝ በጣም አስቸጋሪ ስለ ሆነ መልክዓ ምድራዊ  ለውጦችን ማጥናት ይጠበቅብናል፡፡

 ከዚህ በላይ በመተረጐም ሥር ያየነው የመተረጐምን ዓላማና መተርጐም ያስፈለገበትን ምክንያቶች ነበር፡፡ እንደ ተለመደው የሚከተሉትን ጥያቄዎች በየግላችን ሠርተን በሚቀጥለው ጥናታችን እንገናኝ፤ ሰላም ከእናንተ ጋር ይሁን፡፡

  1. የአረማይክ ቋንቋ የማን ሀገር ቋንቋ ነበር? በአረማይክ የተጻፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ማስረጃ ስጥ?
  2. በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 16፡ 13 ላይ ‹‹ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፡- ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል?›› ብሎ በጠየቃቸው ጥያቄ  ውስጥ ስለ ከተማይቱ የምታውቀውን ግለጽ?

3.  በ1ኛ ጴጥሮስ ምዕራፍ 1፡13 ላይ ‹‹ስለዚህ       የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና በመጠን ኖራችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ›› በሚለው ጥቅስ ውስጥ የምታየውን የባሕል ክፍተት ግለጽ? 


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *