የዛሬውን ትምህርት ስለ ትንቢት ከማየታችን በፊት በባለፈው በጥበብ መጻሕፍት (ግጥም፣ ቅኔ) ዙሪያ ለተጠየቁት ጥያቄዎች የተሰጡትን መልሶች በአካል ክፍል ውስጥ እንደሆንን በማሰብ አብረን እንመልከት፡፡

 የመጀመሪያው የተሰጠው መዝሙር 5፡1 ላይ ሲሆን፣ መልሱም ከተሰጡት ምርጫዎች፣ ሀ.ተመሳሳይ ተጓዳኝ የሚለው መልሳችሁ ከሆነ፣ መልሳችሁ ትክክል ነው፡፡ ‹‹አቤቱ ቃሌን አድምጥ፣ ጩኸቴንም አስተውል››፣ የሚለውን ግጥም ተመሳሳይ ተጓዳኝ የሚያደርገው፣ በመጀመሪያው መስመር ላይ ‹ቃሌን› የሚለውን ቃል ሲጠቀም፣ በሁለተኛው መስመር ላይ ‹ጩኸቴንም› የሚለውን ከራሱ አልፎ በስፋት፣ ለሌሎች ሁሉ የሚሰማ ድምጽ አድርጎ አቅርቦታል፡፡ በመጀመሪያው መስመር ላይ ‹አድምጥ› የሚለውን በሁለተኛው መስመር ላይ ‹አስተውል› በማለት የበለጠ ትኩረት እንዲሰጠው መፈለጉን ያመለክታል፡፡ በዚህ ግጥም ጸሐፊው በመጀመሪያው መስመር ላይ የገለጸውን ሐሳብ፣ በሁለተኛው መስመር ላይ በሌላ ቃል ተጠቅሞ ያንኑ ሐሳብ ሲገልጽ እንጂ አዲስ ሐሳብ ሲገልጽ አንመለከትም፡፡ አይሁዶች ሐሳባቸውን በጽሑፍ ከሚገልጡበት መንገድ አንዱ፣  በማጥበብ ወይም በማስፋት የሚጠቀሙበት መንገድ ‹ተመሳሳይ ተጓዳኝ› ግጥም ይባላል፡፡ 

ሁለተኛው ተሰጥቶ የነበረው መዝሙር 34፡10 ሲሆን፣ መልሱም ‹ለ› ‹‹ተቃራኒ ተጓዳኝ›› የሚለው ስለሆነ፣ የእናንተም መልስ ይህ ከሆነ መልሳችሁ ትክክል ነው፡፡ በመቀጠል ግጥሙን ስንመለከት በመጀመሪያው መስመር ላይ ‹‹ ‹ባለጠጎች› ሲል፣ በሁለተኛው መስመር የመጀመሪያውን ሐሳብ በመቃረን ‹እግዚአብሔርን የሚፈልጉ (ድሆች)› ብሎ ያስቀምጠዋል፡፡ እንደገና በመጀመሪያው መስመር ላይ ‹ተራቡ› ሲል በሁለተኛው መስመር ላይ ‹ከመልካም ነገር ሁሉ አይጎድሉም (ይጠግባሉ) በማለት የመጀመሪያውን ሐሳብ ተቃርኖት እናገኛለን፡፡ የግጥምን ጽሑፎች ስናነብና ስናጠና የምናገኘው፣ ሁለተኛው የጽሑፋቸው ዓይነት ‹ተቃራኒ ተጓዳኝ› ግጥም ይህን ይመስላል፡፡

በመጨረሻ ተሰጥቶ የነበረው በመዝሙር 29፡1-2 ላይ ሲሆን፣ መልሱም ሐ. ‹ዕድገታዊ ተጓዳኝ› የሚለው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህንንም ሁላችሁም አግኝታችሁት ከሆነ መልካም ነው፣ ወደፊትም በርቱና ሥሩ፣ የበለጠ ታድጉበታላችሁ፡፡
በመቀጠል የዕድገቱን ሁኔታ ስንመለከት፣ በመጀመሪያው መስመር ‹ለእግዚአብሔር አምጡ›፣ ሲል ምን ማምጣት እንዳለብን በግልጽ አይታወቅም፣ በሁለተኛ መስመር ላይ ይመጣና ‹የስሙን ክብር› በማለት ግልጽ ያደርገዋል፣ በሦስተኛው መስመር በመቀጠል፣ በቅድስናው ስፍራ በማለት ሐሳቡን ያሳድገዋል፡፡ በመቀጠልም የመዝሙሩን ቁጥሮች ብትመለከቱት ሐሳቡን እያሳደገው እንደ ሄደ ማየት ይቻላል፡፡ ይህ ሦስተኛው የግጥም ዓይነት ሌላኛው ሐሳባቸውን የሚገልጹበት የአጻጻፍ ስልታቸው ነው፡፡ በዚህ መንገድ የግጥም ጥናታችሁን ቀጥሉበት፡፡  

መ. ትንቢት፡- በዛሬ ጥናታችን የምንመለከተው አራተኛውን የሥነ-ጽሑፍ ቅርጽ የትንቢት መጻሕፍትን ይሆናል፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበረውን አገልግሎት ስንመለከት በሦስት የተከፈለ ነበር፡፡ የመጀመሪያው አገልግሎት የካህናት ሲሆን፣ በእነርሱም አገለግሎት፣ ሕግ በሙሴ አማካኝነት ለእስራኤል ሕዝብ ተሰጠ፡፡ በዚህም ሕግ አማካኝነት በተሰጣቸው የመቅደስ ሥርዓት መሠረት፣ ሕዝቡን ወደ እግዚአብሔር በመሥዋዕት አማካኝነት በማቅረብ፣ የኃጢአት ይቅርታ ያስገኙለት ነበር፡፡ ነገር ግን ሕዝቡ የተሰጠውን ሕግ እንደሚገባ መጠቀምና መጠበቅ አልቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት የተነሱት ነቢያት የእስራኤልን ሕዝብ መታዘዝና አለመታዘዝ በማሳየት ከፍርድ እንዲድኑ ማስጠንቀቅ ዋና ተግባራቸው ሆኖ ነበር፡፡

 በዚህም መሠረት ከካህናት በተጨማሪ ሕዝቡን የሚያገለግሉ ነብያት እግዚአብሔር አስነሳላቸው፡፡ ሙሴ፣ ሳሙኤልና ኤልያስ እንደ መንገድ ጠራጊ (ቀደምት) ነብያት ይታያሉ፣ ነብያቱም ሕዝቡ በመንፈሳዊ፣ በማኅበራዊና በፖለቲካዊ ሕይወቱ ብርቱ ቀውስ ውስጥ ወድቆ በነበረበት ጊዜ፣  በማስተማር፣ በመምከርና በማስጠንቀቅ አገልግሎታችውን ይፈጽሙ ነበር፡፡ የትንቢት መጻሕፍት የታሪክ፣ የግጥም ቅልቅሎችና በውስጣቸውም በተጨማሪ የሕጉን መጽሐፍ በመተንተንና ከሕይወት ጋር በማዛመድ ተስፋንና ወዮላችሁ በሚል መልእክት የተሞሉ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡

 የትንቢት መጻሕፍት የተባሉት በሁለት ይከፈላሉ፣ እነርሱም ታላላቅ ነቢያት የተባሉት ከኢሳይያስ እስከ ትንቢተ ዳንኤል ሲሆኑ፣ ታናናሽ ነቢያት የተባሉት ደግሞ ከሆሴዕ እስከ ሚልኪያስ ያሉት ናቸው፤ ታላላቅና ታናናሽ ነቢያት የተባሉበት ምክንያት በጽሑፋቸው መርዘምና ማጠር ብቻ ነው፡፡ ራዕይም የትንቢት አንዱ አካል ነው፡፡ እያንዳንዱን የትንቢት መጽሐፍ በዝርዝር ስናጠና ብዙ ነገሮችን በስፋት ማየት ይቻላል፣ ለምሳሌ በራዕይ መጽሐፍ ውስጥ ሐዋርያው ዮሐንስ ሦስት ነገሮችን  በአንድ ላይ እንዲጽፍ ታዞ ነበር፡፡ አንደኛ ያየውን (ምዕራፍ 1)፣ ሁለተኛ አሁን ያለውን (ምዕራፍ 2-3)፣ ሦስተኛ ወደፊት ሊሆን ያለውን (ከምዕራፍ 4-22) በሚል ተከፋፍሎ እናገኛለን፡፡ የዮሐንስ ራዕይና ትንቢተ ዳንኤል በብዙ መልካቸው የሚመሳሰሉባቸው ብዙ ነገሮች አሉዋቸው፡፡

የነቢያት አነሣስና አገልግሎት በብሉይ ኪዳን እንዴት እንደ ጀመረ እንመልከት፡፡ የእስራኤልን ሕዝብ ታሪክ ስንመለከት ከኢያሱ ሞት በኋላ ሕዝቡ በዐመጹ እየከፋ መሄዱን ቃሉ ይነግረናል፡፡ በተለይም የመሳፍንትን መጽሐፍ ስናጠና የምናገኘው ሰው ሁሉ በፊቱ ደስ የሚለውን ያደርግ እንደነበረ፣ በመሳፍንት 21፡25 ላይ መረዳት እንችላለን፡፡ ቀጠል አድርገን ታሪካቸውን ስናጠና በኃጢአታቸው እየከፉ ከመሄዳቸው የተነሣ የእስራኤል መንግሥት፣ በሰሎሞን ኃጢአት ምክንያት የተነሣ ለሁለት ተከፈለ፡፡ አስሩ ነገዶች የሰሜኑ መንግሥት (እስራኤል) ሲባሉ፣ ሁለቱ ነገዶች ደግሞ የደቡብ መንግሥት (ይሁዳ) ተብለው ተከፋፍለው መኖር ጀመሩ፡፡ የአስሩ ነገዶች (እስራኤል) ጣዖት ከማምለክ አልፈው ልጆቻቸውን ለጣዖት መስዋዕት አድርገው እስከ ማቅረብ ስለ ደረሱ እግዚአብሔር ሊቀጣቸው አሰበ፡፡

 እግዚአብሔር ሕዝቡን ከመቅጣቱ በፊት ነቢዩ ሆሴዕን፣ አሞጽንና ዮናስ የተባሉትን ሦስት ነቢያት አስነስቶ ስለ ኃጢአታቸው እንዲወቅሷቸው አድርጎአል፤ እነርሱ ግን ከጥፋታቸው ሊመለሱ አልቻሉም፡፡ በዚህ ጊዜ የሰሜኑ መንግሥት በ722 ዓ.ዓ ላይ በአሦራውያን ተማርከው ተወሰዱ፡፡ በሰሜኑ መንግሥት ላይ የደረሰበት፣ በደቡቡ መንግሥት ላይ እንዳይደርስበትና ንስሐ እንዲገባ ከሁለት መቶ ዓመት በላይ ዘመን ተጨመረለት፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ከሰባት ያላነሱ እንደነ ኢሳይያስ፣ ሚኪያስና ኤርሚያስ ያሉ ነብያትን አስነስቶ ስለ ኃጢአታቸው እንዲወቅሷቸው አደረገ፣ እንዲመለሱም መከሩዋቸው፤ እነርሱ ግን በተሰጣቸው ዕድል ራሳቸውን አይተው ንስሐ በመግባት ሊጠቀሙበት አልቻሉም፡፡ በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር ትዕግስት በማለቁ፣ በሦስት ዙር በ606፣ 595 እና በ586 ዓ.ዓ ላይ በባቢሎናውያን ተማርከው እንዲወሰዱ አደረገ፡፡

 አሁንም እግዚአብሔር በምርኮም እያሉም አልተዋቸውም፣ በነብዩ ኤርሚያስ ምዕራፍ 29፡11 ላይ ‹‹ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ … ›› ባለው መሠረት ዳንኤልና ሕዝቅኤል የተባሉ ነቢያትን ላከላቸው (አስነሳላቸው)፡፡ ከብዙ መከራና ሥቃይ፣ ከሰባ ዓመት ምርኮ በኋላ ወደ አገራቸው ተመለሱ። ቤተ መቅደሱንና ቅጥራቸውን እንዲሠሩ ትእዛዝ ተሰጥቶአቸው፣ እነርሱ ግን ለመሥራት በተነሱ ጊዜ፣ ጠላቶች ስለ ተነሱባቸው ቤቱን የመሥራት ጊዜው አሁን አይደለም ብለው አቆሙት፡፡ በዚህም ጊዜ እግዚአብሔር እንደገና ሐጌ፣ ዘካርያስና ሚልኪያስ የተባሉትን ነቢያት አስነስቶ ሕዝቡን ወቀሳቸው፣ መከራቸው፡፡ እነርሱም ተነስተው በተባሉት መሠረት ቅጥሩንና ቤተ መቅደሱን ሠሩ፡፡

 በዚህ መሠረት ነቢያትን ስንመለከት ከምርኮ በፊት፣ በምርኮ ጊዜና ከምርኮ በኋላ የተላኩ ብለን ወይም በዘመነ አሦር፣ በዘመነ ባቢሎንና በዘመነ ፋርስ አገዛዝ ጊዜ ያገለገሉ ነቢያት ብለን በሦስት ልንከፍላቸው እንችላለን፡፡ ሁሉም ነቢያት እግዚአብሔርን ያገለገሉት በጣም አስከፊና አሳዛኝ በሆነ ታሪካዊ ወቅት ውስጥ ነበር፡፡ ስለዚህ ነቢያት የተናገሯቸውን ትንቢቶች (መልእክታቸውን) ካገለገሉበት ዐውድ አንጻር ለመገንዘብ መቻል ወሳኝነት አለው፡፡ ትቢቶቻቸውን  ስንመለከት በአብዛኛው ንስሐን፣ ፍርድንና ተስፋን የያዙ ናቸው፡፡

 ነቢያት መልእክታቸውን በትረካ፣ በግጥምና በፈሊጣዊ አነጋገሮች በመጠቀማቸው መልእክቶቻቸው በቀላሉ ላይገቡን ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም በሁለትና ሦስት ጊዜ የሚፈጸሙ የቅርብና የሩቅ ትንቢቶች ተደባልቀው ስለተነገሩ በቀላሉ መረዳት ያስቸግራል፡፡ ይህን ሐሳብ ይበልጥ ለመረዳት የሚከተሉትን  የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በጥሞና እንመልከት (እናጥናው)፡፡

 በትንቢተ ኢዩኤል 2፡28-31 ላይ ስንመለከት በሦስት ጊዜ የሚፈጸም ትንቢት ተነግሮ እናገኛለን፡፡ ‹‹ መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈሳለሁ›› የሚለው የነቢዩ ኢዩኤል ትንቢት የሚፈጸመው በሦስት በተለያዩ ጊዜያት (ዘመናት) እንደሆነ ወደፊት ከምናደርገው ምልከታችን መረዳት እንችላለን፡፡ በነገራችን ላይ ሁለቱ ሲፈጸሙ አንዱ ገና ወደፊት የሚፈጸም ነው፡፡

 1ኛ. በመጀመሪያ የቅርብ ፍጻሜውን ያገኘው አይሁዶች ከምርኮ ተመልሰው ቤተ መቅደስ መሠሩበት ጊዜ ነበር፡፡ ለዚህም ሁለት ማስረጃ ከቃሉ ማግኘት እንችላለን፡፡ በትንቢተ ሐጌ 2፡1-5 ባለው ክፍል ውስጥ ያሉት ጠቋሚ ሐሳቦች፣ የፈረሰውን ቤተ መቅደሱን ሠርተው ሲጨርሱ እግዚአብሔር በመካከላቸው ስለሚያደርገው ነገር ይናገራል፡፡ ‹‹መንፈሴም በመካከላችሁ ይኖራልና አትፍሩ›› ቁ.5  ‹‹… ይህንም ቤት በክብር እሞላዋለሁ›› ቁ.7፡፡ ‹‹ከፊተኛው ይልቅ የዚህ የሁለተኛው ቤት ክብር ይበልጣል›› ቁ.9፡፡ በትንቢተ ዘካርያስ 2፡10 ላይም ‹‹… መጥቼ በመካከልሽ እኖራለሁ›› በማለት ከምርኮ መልስ በሚሠሩት ቤተ መቅደስ ላይ፣ እግዚአብሔር በመንፈሱ አማካኝነት በክብር በመካከላቸው እንደሚኖር ያረጋግጥላቸዋል፡፡

 2ኛ. የነቢዩ ኢዩኤል ትንቢት ሁለተኛውን ፍጻሜ ያገኘው በበዓለ ኀምሳ ዕለት እንደ ነበር ሁላችንም የምንረዳ ሐቅ ሲሆን፣ ይህም የሩቅ መካከለኛ ፍጻሜ ነው፡፡ ይህ ብዙ የሚያከራክረን ሐሳብ ሊሆን አይችልም፣ ምክንያቱም ሐዋርያው ጴጥሮስ በበዓለ ኀምሳ ቀን፣ አስቀድሞ በነቢያት በተነገረው መሠረት የተፈጸመ መሆኑን፣ የኢዩኤልን ትንቢት በመጥቀስ ለሰሚዎቹ  ማስረጃ ሲሰጥ፣ ድርጊቱ የተከናወነው በወይን ጠጅ ሠክረው ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተሞልተው እንደ ሆነ ይናገራል፡፡

3ኛ. የነቢዩ ኢዩኤል ትንቢት በሦስተኛ ጊዜ የሩቅ ፍጻሜውን የሚያገኘው ጌታ በመጨረሻው ቀን ሲመጣ እንደ ሆነ ለማሳየት ጴጥሮስ ‹‹የጌታ ቀን ሳይመጣ›› የሚለውን ሐረግ ተጠቅሞበት እናገኛለን፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ ተምሳሌታዊ ንግግሮች ስለ አሉበት፣ በቁማቸው መተርጐም ስለማንችል ለመረዳት የምንቸገርባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ የፀሐይ መጨለም፣ የጨረቃ ወደ ደም መለወጥ በመሳሰሉት ላይ የተለያዩ አመለካከቶች ስለ አሉ፣ አሁን እዚህ ላይ የእኔን አመለካከት እንዲህ ነው ማለት አልፈልግም (ወደፊት የምገልጥበት ጊዜ ይኖራል)፡፡ በአጠቃላይ በቃሉ ዙሪያ ሠፋ ያለ ጥናት የሚጠይቁ ጉዳዮች ስለሆኑ፣ ሁላችንም በእነዚህ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረግን ካጠናናቸው ልንረዳቸው እንችላለን፡፡

ከአዲስ ኪዳን የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24ን፣ አንድ ተጨማሪ ምሳሌ አድርገን ወስደን እናጥናው፡፡ ይህን ክፍል ስንመለከት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመቅደስ ወጥቶ እየሄደ እያለ፣ ደቀ መዛሙርት አይሁዶች የሚመኩበትንና የሚያመልኩበትን የመቅደሱን ግንቦች አሳዩት፡፡ በዚህ ጊዜ ጌታም ‹‹እውነት እላችኋለሁ፣ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው›› በመቀጠልም ደቀ መዛሙርቱ ‹‹ንገረን ይህ መቼ ይሆናል የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው አሉት››

 ጌታም በመቀጠል ስለመምጣቱና የዓለም መጨረሻ ምልክቶች ሲናገር ሳለ፣ ሦስት ነገሮች በአንድ ላይ በማያያዝ ተናገረ፡፡ የመጀመሪያው በራሳችው በደቀ መዛሙርት ላይ ሊደርስባቸው ስላለው መከራና ስደት ተናገራቸው፡፡ በሁለተኛ በሰባ ዓመተ ምህረት ላይ በአይሁዶችና በቤተ መቅደሱ ላይ ሊደርስ ያለውን መከራ ሁሉ አመለከታቸው፡፡ በመጨረሻም ጌታ ራሱ ከመምጣቱ ከፊትና በኋላ በዳግመኛ ምጽዓቱ ጊዜ የሚፈጸሙትን ነገሮች አመልክቷቸዋል፡፡ ይህ የወንጌል ክፍል ሆኖ ከትረካ መድበን ያየነው ነው፡፡ በቅርጹ ትረካም ቢሆንም በይዘቱ ለወደፊት የሚፈጸሙ ነገሮችን የቅርብና የሩቅ የሆኑ ትንቢቶችን ይዞ እናገኘዋለን፡፡ ስለዚህ የትንቢት መጻሕፍትን ስናጠና ለየት ያለ ትኩረት ልንሰጣቸው የሚያስፈልገው ለዚህ ነው፡፡      

ቀደም ብለን እንዳልነው በሰባት የመጠየቂያ ቃላት መጠየቅ፣ የተለያዩ ምልከታዎች ማድረግ፣ የሐሳቡን መዋቅር ማየት በሚለው ሥር ሰዋስውንና ሥነ-ጽሑፉን ማየት እንዳለብን ተመልክተናል፡፡ ሥነ-ጽሑፉን ስናይ እያንዳንዱን ለየት ባለ መነጽር (ዕይታ) ማየት እንዳለብን ተነጋግረናል፡፡ በዚህ መሠረት የትንቢት መጻሕፍትን ለየት የሚያደርጋቸው የሕዝቡ  በእግዚአብሔር ላይ ያለውን ያለ መታዘዝ ዐመጽ በመውቀስ ወደ ፍርድ እንዳይገቡ ማስጠንቀቅ ዋና ተግባራቸው ነበር፡፡ ዘጠና በመቶ የሚሆነው የትንቢት መጻሕፍትዋና ይዘት (ጭብጥ) የሚያተኩረው በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ሲሆን፣ አሥር በመቶ የሚሆነው የትንቢቱ ይዘት የሚያተኩረው በወደፊት በሚሆኑ ነገሮች ላይ ነው፡፡

 በመጪ ዘመን ላይ የሚያተኩሩት ትንቢቶች ከቅርብ ዘመን ከሚፈጸሙት ትንቢቶች ጋር ተደባልቀው የተነገሩ ስለሆኑ፣  የመጪው ዘመን ትንቢቶች በአብዛኛው ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወትና አገልግሎት ጋር የተገናኙ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ነው፣ የትንቢት መጻሕፍትን ለየት ባለ ዕይታ እንድንመለከታቸው የሚያስፈልገው፡፡ በትንቢት መጻሕፍት ላይ ጥናት ስናደርግ ከፍተኛ የመመልከት ጥንቃቄ በማድረግ ወደ መተርጐምና ወደ ማዛመድ መሄድ ይገባናል፡፡

 በባለፈው እንደምናደርገው በሰባት መጠየቂያ ቃላት መጠየቅ፣ የተለያዩ ምልከታዎች ማድረግ እንደተጠበቁ ሆነው፣ ዛሬ በተመለከትነው የትንቢት መጻሕፍት በየግላችን የምንሠራው ሆኖ እንደ ተለመደው ቀርቦላችኋል፡፡ በተቻለ መጠን ትኩረት ስጡትና ሠርታችሁ በሰላም እንገናኝ፡፡

  1. በኢሳይያስ 7፡14  ላይ የተነገረውን የቅርብና የሩቁን ትንቢት ለይታችሁ አስቀምጡ፡፡
2    በዘዳግም 18፡15-19 ላይ የተነገረውን    የቅርብና የሩቁን ትንቢት ለይታችሁ በመጠቆም አውጡ፡፡
3   በሕዝቅኤል 26፡1-6 ላይ የተነገረውን የቅርብና የሩቁን ትንቢት ለይታችሁ ጻፉት፡፡

0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *