የዛሬውን ትምህርት ስለ ሕግ(ትእዛዝ) ከማየታችን በፊት ባለፈው ለተጠየቁት ጥያቄዎች የተሰጡትን መልሶች እንመልከት፡፡

  1. የመጀመሪያው ኢሳይያስ 40 በሙሉ ስንመለከተው ከተሰጡት መልሶች ውስጥ በቅርጹ የትንቢት መጽሐፍ ሆኖ እናገኘዋለን፣  በይዘቱ ግን መስመር በመስመር የተገለጠ ግጥም ነው፡፡
  2. ሁለተኛው ዘፍጥረት 1፡27 የዘፍጥረትን መጽሐፍ በቅርጹ ስንመለከትው የሕግ መጽሐፍ ሆኖ እናገኘዋለን፣ በይዘቱ ግን መስመር በመስመር የተገለጠ ግጥም ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
  3. ሦስተኛው ፊልጵስዩስ  2፡5-11 ያለው በቅርጹ የመልእክት ጽሑፍ ክፍል ሲሆን፣ በይዘቱ ግን መስመር በመስመር የተገለጠ ግጥም ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

 ሀ.  ሕግ ፡- በዛሬው ጥናታችን የሕግ መጻሕፍት ከሌሎች መጻሕፍት የሚለዩበት የራሳቸው የሆነ ባሕሪይ እንዳላቸው እንመለከታለን፡፡ እነዚህ መጻሕፍት አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት ሲሆኑ፣ ዘፍጥረት፣ ዘጸዓት፣ ዘሌዋውያን፣ ዘኍሉቅና ዘዳግም ብለን የምንጠራቸው ሲሆኑ፣ በጥቅሉም ቶራ ተብለውም ይጠራሉ፡፡ የብሉይ ኪዳን የሕግ መጻሕፍት በአብዛኛው የሕግና የትረካ ቅልቅል ናቸው፣ ለምሳሌ ዘፍጥረት ሙሉ በሙሉ የትረካ መጽሐፍ ሲሆን፣ ዘጸዓትም ግማሹ ትረካ ይዞአል፡፡ የቀሩት ሦስቱ መጻሕፍት በአብዛኛው ሕግ ቢሆኑም በውስጣቸው ትረካ ይዘዋል፡፡ በእነዚህ መጻሕፍት ውስጥ ምን ዐይነት ሕጎች እንደተሰጡና የሕግ ዝርዝሮችን ስናይ፣ የሚከተሉትን የሕግ ዐይነቶች ይዘው እናገኛለን፡፡ እነርሱም 1ኛ. ዘላለማዊ ሕግ(አሥርቱ ትእዛዛት) 2ኛ. የሥነ-ሥርዓት ሕጐች(አምልኮ) እና 3ኛ. የአስተዳደር ሕጎች(መንግስታዊ) ለእስራኤል ሕዝብ ተሰጥተውና ከታሪካቸው ጋር ተቆራኝተው፣ ተሣስረውና ተገልጸው ይገኛሉ፡፡

 ሕጉ ቢጠብቁት ትምህርትና ሕይወት የሚሰጥ፣ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹ስለዚህ ከወርቅና ከዕንቁ ይልቅ ትእዛዝህን ወደድሁ›› ብሎ እንደ ተናገረውና እንደ ዘመረው ከወርቅና ከዕንቁ ይልቅ ሕጉ የሚወደድ እንደ ሆነ እናያለን፡፡ (መዝ. 119፡127) እግዚአብሔር ከባርነት ነፃ ካወጣቸው በኋላ የሚወደድ፣ አስተማሪ፣ መካሪ፣ የሚቀድስና ወደ እግዚአብሔር የሚያስጠጋ ሕግ ሰጥቷቸው ነበር፡፡ ሕጎቹም በሦስት የተከፈሉ ነበሩ፡፡   

ዘላለማዊ ሕጎች፡- ዘላለማዊ ሕጎች የተባሉት በዘጸዓት ምዕራፍ 20-23 ላይ የተሰጡት ሲሆኑ፣ እነርሱም የማይለወጡ ሕጎች ሆነው ስለ ተቀመጡ ዘላለማዊ ተብለው ይጠራሉ፡፡ የሥነ-ሥርዓት እና የአስተዳደር ሕጎች ሲሻሩ፣ እነዚህ ዘላለማዊ (አሥር) ሕጎች ወደ አዲስ ኪዳን መጥተው በሁለት ተከፍለው ተቀምጠዋል፡፡ ጌታ ‹‹እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም›› ማቴ.5፡17 ባለው መሠረት እግዚአብሔርን ውደድ በሚለው ውስጥ አራቱ ሲካተቱ፣ ባልንጀራህን ውደድ በሚለው ውስጥ ደግሞ ስድስቱ ተካተዋል፡፡ በአዲስ ኪዳን እኛ አማኞች በተፈጸመ ‹‹የፍቅር ሕግ›› ውስጥ እንኖራለን ፡፡

 የሥነ-ሥርዓት ሕጎች፡- በዚህ የሥነ-ሥርዓት (አምልኮ) ሕጎች ውስጥ ስለ ቤተ መቅደስ አያያዝ፣ ካህናትና ሌዋውያን አገልግሎት፣ መሥዋዕት አቀራረብ፣ ሰንበት አጠባበቅ፣ … የመሳሰሉትን የያዘ ወደ 630 በላይ የሚደርሱ ትእዛዛት ለእስራኤላውያን ተሰጥተው ነበር፡፡ ዘጸአት ከምዕራፍ 25-40 እና ዘሌዋውያን ከምዕራፍ 1-27 ተመልከቱ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር በመጣ ጊዜ እነዚህ ትእዛዛት ሁሉ የሚጠይቁትን ሁሉ በመፈጸም፣ በመስቀል ላይ ስለ እኛ ኃጢአት በመሞት፣ እውነተኛ መስዋዕት ሆኖ የኃጢአታችንን ዋጋ ከፈለልን፡፡ እኛ አሁን እነዚህን ትእዛዛት መጠበቅ አይጠበቅብንም፡፡

 የአስተዳደር ሕጎች፡- የአስተዳደር ሕጎች የተባሉት እግዚአብሔር ንጉሣቸው ስለ ነበረ፣ የሚመሩበትና የሚተዳደሩበት መንግስታዊ ሕግ ሰጣቸው፡፡ የእግዚአብሔርን ንጉሥነት ትተው በራሳቸው ሕግ መተዳደር እስከ ጀመሩበት ጊዜ ድረስ፣ በእነዚህም ሕጎች ሲመሩበት ለዘመናት ቆይተዋል፡፡ ዛሬ ሁሉም ሀገሮች የየራሳቸው መንግስታዊ ሕግ ስላላቸው፣ እነዚህ ሕጎች በማንም ሀገር ላይ ተግባራዊ ሲሆኑ አናይም፡፡

 እኛም አማኞች ከእነዚህ ከተሻሩ ሕጎች እንዴት ትምህርት እንደምናገኝ ወደ ፊት ወደ መተርጎም ስንመጣ በሰፊው እንመለከተዋለን፡፡ አሁን ለጊዜው ገና መመልከት ላይ ስለ ሆነ ያለነው፣ ሕግን እንደ ሕግነቱ እንዴት መመልከት እንዳለብን እናያለን፡፡ የሕግ ጽሑፎችን በሰባት መጠየቂያ ቃላት በመጠቀም እንጠይቃለን፣ በአየናቸው የተለያዩ ምልከታዎችም፣ ምልከታ እናደርጋለን፡፡ በመቀጠልም የሥነ-ጽሑፉን ዐይነት ስንመለከት ሕግ ሆኖ ስናገኘው፣ በተለየ ዕይታ (መነፅር) ማየት ያስፈልጋል፡፡ የሕግ ጽሑፎችን ስናነብና ስናጠና የሚከተሉትን ጥንቃቄዎች ልናደርግ ይገባናል፡፡ ልንጠነቀቅባቸው የሚገቡን ነገሮች፡-

  1. የእግዚአብሔር ሕዝቦች ልዩነት ላይ፡

 በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ እሥራኤል ስትሆን፣ በአዲስ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ ቤተ ክርስቲያን ነች፡፡

በእነዚህ ጥቅሶች መሠረት ስንመለከት ሕጉ በክርስቶስ ተፈጽሞአል፡፡ ቆላ.2፡14፣ ሮሜ.10፡4፣ 2ቆሮ.3፡7-11 ስለዚህ  የብሉይ ኪዳን ሕግ በክርስቶስ ስለ ተፈጸመ በቤተ ክርስቲያን ላይ መጫን አያስፈልግም፡፡ ቤተ ክርሰቲያን የራሷ የፍቅር ሕግ አላት፡፡ በብሉይ ኪዳን አንድ ኃጢአት ቢሠራ፣ ቅድስና ቢፈልግ፣ አምላኩን ማመስገን ቢፈልግ፣ ርኩስ ነገር ቢነካ … ለሁሉም እንደ ዓይነቱና እንደ ሕጉ አንድ ሕይወት ያለው በግ ይዞ መጥቶ መሥዋዕት ማቅረብ አለበት፡፡ እኛስ ዛሬ የበግ መሥዋዕት ለማቅረብ በግ እየጐተትን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንምጣ? አረ! በፍጹም አያስፈልግም፡፡

 የሥነ-ሥርዓትና የአስተዳደር ሕጉ በክርስቶስ ስለ ተፈጸመ፣ እኛ ልንፈጽመው አይገባንም፡፡ ምንም እንኳን የተሻረ ቢሆንም፣ ምንም ትምህርት አናገኝበት ማለት አይደለም፡፡ ለትምህርታችን የተጻፈ ስለ ሆነ ብዙ ትምህርት እናገኝበታለን፡፡ ወደ ማዛመድ ስንመጣ እንዴት ተግባራዊ አድርገን ትምህርት እንደምናገኝበት ወደ ፊት እንመለከታለን፡፡

  • የቃል ኪዳኑ ቅርጽ ልዩነት ላይ፡

ሀ) በርዕሱ፡- ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን ተብለው መጠራታቸው፣ አሮጌና አዲስ በማለት ተለይተዋል፡፡ የአሮጌውን ትእዛዝ ከአዲሱ ትእዛዝ ጋር መደባለቅ አያስፈልግም፡፡ ከሁለቱም እንደየ ቦታቸው ትምህርት መውሰድ ያስፈልጋል፡፡

ለ) በታሪካዊ መሠረቱ፡- ብሉይ ኪዳን በመላእክት በኩል ለሙሴ መሰጠቱን፣ የዕብራውያን ጸሐፊ እንዲህ ሲል ይናገራል፣ ‹‹በመላእክት የተነገረው ቃል ጽኑ ከሆነ … ›› (ዕብ.2፡2) በማለት የከበረ እንደ ነበረ ይናገራል፡፡ አዲስ ኪዳን ደግሞ በክርስቶስ የተሰጠ በመሆኑ የበለጠ ጽኑ መሆኑን ያሳያል፡፡ በታሪካዊ መሠረታቸው የተለያዩ መሆናቸውን መረዳት እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡

ሐ) በሚሰጠው ትዕዛዝ፡- ብሉይ ኪዳን አድርግና አታድርግ የሚል ትእዛዝ ሲሰጥ፣ አዲስ ኪዳን ደግሞ ወድጃችኋለሁና በፍቅሬ ኑሩ የሚል ነው፡፡ ‹‹አብ እንደ ወደደኝ እኔ ደግሞ ወደድኋችሁ በፍቅሬ ኑሩ›› (ዮሐ. 15፡9)፡፡ በብዙ መልኩ በትእዛዛቸው ስለሚለያዩ ትኩረት ልንሰጣቸው ያስፈልጋል፡፡

መ) በበረከትና በመርገም፡- ሁለቱም ሕጎች በበረከትና በመርገም ይለያያሉ፡፡ ብሉይ ኪዳን አድርግና አታድርግ በሚለው ትእዛዙ የሚታዘዝ ሲባረክ፣ የማይታዘዝ ደግሞ የተረገመ ይሆናል፡፡ አዲስ ኪዳን ውስጥ ግን በረከት እንጂ መርገም የለም፡፡ የጌታን ትእዛዝ ተቀብለን ብንወደው የዘላለም ሕይወት ማግኘት ሲሆንልን፣ ባንወደው ደግሞ የዘላለም ሕይወት ማጣት ይሆንብናል እንጂ፣ በቁስል፣ በመቅሠፍት፣ በድርቅ ትመታለህ፣ ርጉምም ትሆናለህ የሚል ርግማን የለም፡፡ ስለዚህ ወደ ሕይወታችን ማዛመድ ወይም ተግባራዊ ማድርግ ስንመጣ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባናል፡፡

 ሠ) የቃል ኪዳኑ ቀጣይነት፡- ከርዕሱ እንደምንመለከተው ብሉይ ኪዳን በአዲስ ኪዳን ተተክቶአል፣ ‹‹አዲስ በማለቱ ፊተኛውን አስረጅቶአል አሮጌና ውራጅ የሆነውስ ሊጠፋ ቀርቦአል›› (ዕብ. 8፡13)፣ ‹‹ሁለተኛውን ሊያቆም የፊተኛውን ይሽራል›› (ዕብ. 10፡9)  እንደ ተባለው ብሉይ ኪዳን የተሻረ፣ ያረጀ፣ ሆኖአል፡፡ የዕብራውያን ጸሐፊ እንደሚናገረው ‹‹እርሱ (ክርስቶስ) ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ›› (ዕብ. 10፡12) በሚለው መሠረት፣ የአዲስ ኪዳን ቀጣይነት ዘላለማዊ እንደ ሆነ መረዳት እንችላለን፡፡

  • የተስፋው ልዩነት ላይ፡

በብሉይ ኪዳን የተሰጠው ተስፋ ተፈጻሚነቱ በቀጥታ ነው ወይስ በቤተ ክርስቲያን በኩል፣ ይህን መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡ እሥራኤል የተሰጠው ተስፋ በቀጥታ ነው የሚፈጸምላቸው ወይስ በክርስቶስ በኩል ለቤተ ክርስቲያን በተሰጠው ተስፋ በኩል ነው የሚፈጸምላቸው? በዚህ ላይ ትልቅ ትኩረት መስጠት አለብን፡፡  

 በዚህ ትምህርት ላይ የተለያዩ አመለካከቶች እንዳሉ የታወቀ ነው፡፡ ቢሆንም ግን እዚህ ላይ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባው ነገር ቢኖር፣ የብሉይ ኪዳን ተስፋ ምድራዊ መሆኑን ነው፡፡ ለአብረሃም የተሰጠው ተስፋ ምድራዊ ከንዓን እንዲወርስ ነበር፡፡ በእርሱ ጊዜ ባይሆንም በያዕቆብ (እስራኤል) ልጆች ጊዜ መውረስ ችለዋል፡፡

 የአዲስ ኪዳን ተስፋ ደግሞ ሰማያዊ ርስት (መንግስተ ሰማያት) ነው፡፡

 ሕግን በታሪክ፣ በትንቢትና በጥበብ መጻሕፍት (ግጥም) ውስጥ እናገኛለን፡፡  በታሪክ መጻሕፍት ውስጥ  ጸሐፊዎቹ የእስራኤል ሕዝብ ሕጉን መታዘዛቸውንና አለመታዘዛቸው፣ ብርታታቸውንና ድካማቸውን፣ ውድቀታቸውንና መነሳታቸውን ዘግበውልን እናገኛለን፡፡ በነብያት መጻሕፍት ውስጥ ነብያቶቹ የእስራኤል ሕዝብ ሕጉን ሲታዘዙ የእግዚአብሔርን በረከት እንደሚያገኙ፣ ሕጉን ሳይታዘዙ ሲቀሩና በኃጢአት ሲወድቁ እግዚአብሔር እንደሚቀጣቸው በማስጠንቀቅ መልእክታቸውን ያስተላልፉ ነበር፡፡ ወደ ጥበብ መጻሕፍት ስንመጣ ጸሐፊዎቹ ስለ ምስጉን (መልካም) ሰው እና ክፉ (ሰነፍ) ሰው በመዝሙራቸው ስለ ሕጉ እንዲህ ይላሉ፣ ‹‹በመንገዳቸው ንጹሐን የሆኑ፣ በእግዚአብሔርም ሕግ የሚሄዱ ምስጉኖች ናቸው፡፡ ምስክሩን የሚፈልጉ፣ በፍጹም ልብ የሚሹት ምስጉኖች ናቸው ዓመፅንም አያደርጉም፣ በመንገዶቹም ይሄዳሉ›› (መዝ. 119፡1-2)፡፡ የእግዚአብሔርን ሕግ በመጠበቃቸው በረከት እንደ ሆነላቸው በዝማሬአቸው ገልጠው እናገኛለን፡፡ ለዚህም መዝሙር 119 በሙሉ ብናጠናው ስለ ሕጉ ብዙ ነገሮችን ያስተምረናል፡፡

 ለእስራኤል የተሰጠውን ሕግ እንደ ወረደ ተግባራዊ ማድረግ የለብንም እንጂ ብዙ ትምህርት የምናገኝባቸው ትእዛዛቶች አሉ፡፡ ወደ ማዛመድ ስንመጣ በስፋት እንመለከተዋለን፡፡   

በባለፈው እንደምናደርገው በሰባት መጠየቂያ ቃላት መጠየቅ፣ የተለያዩ ምልከታዎች ማድረግ እንደተጠበቁ ሆነው፣ ዛሬ በተመለከትነው የሕግ ሥነ-ጽሑፍ በየግላችን የምንሠራው ሆኖ ቀርቦላችኋል፡፡ በተቻለ መጠን ትኩረት ስጡትና ሠርታችሁ በሰላም እንገናኝ፡፡

  1. ዮሐንስ ወንጌል 15፡10    ሀ. ትረካ      ለ. ሕግ   ሐ. ትንቢት   መ. ግጥም
  2. ሮሜ 2፡25                ሀ. መልእክት ለ. ሕግ   ሐ. ግጥም     መ. ትንቢት

3. መዝሙር 119፡18          ሀ. ግጥም     ለ. ሕግ   ሐ. ትንቢት   መ. መልእክት


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *