የዕለቱን ትምህርት ከማየታችን በፊት፣ በየጊዜው እንደምናደርገው አስቀድማችሁ እንድትሠሩት በተሰጣችሁ ክፍል ላይ ትኩረት በማድረግ ጥናታችንን እንቀጥላለን፡፡
የመጀመሪያው በኢሳይያስ 7፡13 ላይ ተመልከቱ ተብሎ በተሰጣችሁ ላይ ‹‹እርሱም አለ፡-እናንተ የዳዊት ቤት ሆይ፡- ስሙ በውኑ ሰውን ማድከማችሁ ቀላል ነውን? ‹‹እርሱም›› የሚለው ተውላጠ ስም ተክቶ የገባው ‹ኢሳይያስ› የሚለውን ስም ነው፡፡(በመደበኛው ትርጉም ሲተረጉሙ ‹ኢሳይያስ› ብለው ስለሆነ፣ ያለ ምንም ችግር መረዳት ይቻላል፡፡ ወደፊት ስለ ተለያዩ ትርጉሞች አጠቃቀም በሰፊው እንመለከታለን)፡፡
ሁለተኛው በኤፌሶን 4፡1 ላይ ተውላጠ ስምና ቅጽል የሆነውን ቃል አውጡ፣ ተብሎ በተሰጠው ትእዛዝ መሠረት ምን መልስ አገኛችሁ፡፡ በዚህ ሥፍራ ‹እኔ› የሚለው ተውላጠ ስም ጳውሎስን ተክቶ ሲገባ፣ በአማርኛችን ብዙ ጊዜ በግሡ ላይ የምናገኛቸው የመጨረሻ ፊደሎች ተውላጠ ስሙንና መደቡን ያመለክቱናል፡፡ ለምሳሌ መጠራታችሁ፣ እለምናችኋለሁ ‹ሁ› የሚለው ፊደል ‹እናንተ› (you) የሚለውን ተውላጠ ስም እና 2ኛ መደብ የብዙ ቁጥር መሆኑን ያመለክታል፡፡ ጳውሎስ ምን ዓይነት ሰው እንደ ነበር የሚገልጽልን ‹እስር የሆንኩ› የሚለው ቃል ‹እስረኛ› መሆኑን የሚያመለክት ሲሆን፣ ምድቡም ከንግግር ክፍሎች ‹ቅጽል› ሆኖ የዓይነት ቅጽል እንደሆነ መረዳት እንችላለን፡፡
ሦስተኛው በማርቆስ 1፡14-15 ላይ ያለውን ተመልከቱና የድርጊቱን ባለቤት፣ ግሥ፣ ተውሳከ ግሥና ቅጽል የሆኑትን አውጡ ተብሎ በተሰጠው መሠረት፣ የድርጊቱ ባለቤት- ኢየሱስ፣ ከብዙ ግሦች መካከል ዋና ግሥ – መጣ፣ ተውሳከ ግሡ – እየሰበከ፣ ቅጽሉ – ቀርባለች የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ ሌሎችም የንግግር ክፍሎችም አሉት፡፡ (ወደ መተርጐም ስንመጣ በተጨማሪ ስለ ሰዋስው ስለምናይ ለአሁኑ ይህን ያህል ካየን ይበቃናል)፡፡
3.2 የሥነ-ጽሑፍ ቅርጽ፡- በዛሬው ዕለት አዲስ የምንመለከተው፣ በሐሳብ መዋቅሩ ሥር ከምናገኘው ሁለተኛው ክፍል የሥነ-ጽሑፉን ዐይነት ማየት የሚለው ሲሆን፤ ሁለተኛው የሐሳብ መዋቅር የሚያተኩረው በቃላት ላይ ሳይሆን በውስጡ በያዛቸው የሥነ-ጽሑፍ ቅርጽ ላይ ይሆናል፡፡ የተለያዩ ሐሳቦችን በአግባቡና በዓላማ አብሮ በአንድነት ማስቀመጥ ላይም ያተኩራል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈባቸው የሥነ-ጽሑፍ ዐይነቶች አምስት ናቸው፡፡
እነርሱም፡- ሀ. ሕግ ፡ አምስቱ የኦሪት መጻሕፍት (ፔንታቱክ)
ለ. ትረካ ፡ ከኢያሱ – ዜና፣ ወንጌሎችና የሐዋርያት ሥራ
ሐ. ሥነ-ጥበብ (ግጥም) ፡ ከኢዮብ – መኃልየ መኃልይ
መ. ትንቢት ፡ ከኢሳይያስ – ሚልክያስ፣ ራዕይ
ሠ. መልእክት ፡ የጳውሎስና አጠቃላይ መልእከቶች
እነዚህን አምስት የሥነ-ጽሑፍ ዐይነቶች ሁሉ ከዚህ ቀደም ባየናቸው በሰባቱ የመጠየቂያ ቃላት በመጠቀም መጠየቅ፣ የተለያዩ ምልከታዎችን ሁሉ በመጠቀም ሁሉንም ጽሑፎች በአንድ ዓይነት መነጽር መመልከት እንችላለን፡፡ አሁን ግን እያንዳንዱን የጽሑፍ ዐይነቶች ለየት ባለ መነጽር ማየት እንደሚያስፈልግ እንመለከታለን፡፡ ይህን ሐሳብ የበለጠ ለመረዳት የምትችሉት፣ አንዳንዶቻችን መነጽራችን ለማንበቢያነትና ሰውን ለማየት ስንፈልግ የምንጠቀምበት የተለያዩ ክፍሎች አሉት፡፡ ባይፎካል የሆነ መነጽር ያለን ሰዎች ሁሉ የበለጠ ይገባናል፡፡ በምናነብበት ክፍል ሰው ማየት አንችልም፤ ሰው በምናይበት ክፍል ማንበብ እንችልም፡፡ ማየት ለምንፈልገው ነገር ቦታውን መምረጥ አለብን፡፡
እንደዚሁም የተለያዩ የጽሑፍ ዐይነቶችን በተለያየ መነጽሮች በማየት ማንበብና ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ ሕግን እንደ ሕግነቱ፣ ታሪክን እንደ ታሪክነቱ፣ ሥነ-ጥበብ (ግጥም) የሆነውን እንደ ጥበብነቱ፣ ትንቢትን እንደ ትንቢትነቱና መልእክትን እንደ መልእክትነቱ መመልከት ይገባናል፡፡ የጽሑፎቹ አቀማመጥ፣ መልእክት የማስተላለፍ ዘዴአቸው፣ ዓላማቸው፣ ስልታቸውና ቅርጻቸው ሁሉ ላይ ይለያያሉ፡፡ ስለዚህ እንደ ጽሑፎቹ ዐይነት መነጽራችንን ማስተካከል አለብን፡፡ እነዚህን የጽሑፍ ዐይነቶች አንድ በአንድ እንዴት በተለየ መነጽር ማየትና መረዳት እንደምንችል፣ ዘዴዎችን ጨምረን ምልከታዎች ማድረግ እንዳለብን በስፋት እንመለከታቸዋለን፡፡
በሥነ-ጽሑፍ ዐይነቶች ላይ ምልከታ በምናደርግበት ጊዜ በቃላቶች፣ በሐረጐች፣ በዓረፍተ ነገሮች፣ በአንቀጾች፣ በምዕራፎችና፣ በመጻሕፍት ላይ ትኩረት በምናደርግበት ጊዜ፣ ቃሉን በተገቢው መንገድ ወደ ማስተዋልና ወደ መተርጐም እንድንደርስ ያደርገናል፡፡ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፍ ሐሳብ ለመረዳትና መልእክቱን ለማግኘት ከፈለግን ምን ዐይነት ሥነ-ጽሑፋዊ ቅርጽ/ይዘት እንዳለው መለየትና ማወቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ሥራ መሆኑን አንርሳ፡፡
እያንዳንዱ የጽሑፍ ዐይነት የራሱ የሆነ ቅርጽ ስላለው፣ እያንዳንዱን የጽሑፍ ዐይነት የምንረዳበት የራሱ የሆነ መነጽር ይኑረን የምንለው ለዚህ ነው፡፡ መጻሕፍት ሁሉ በአንድ ዐይነት መንገድ አይነበቡም፣ አይተረጐሙም፡፡ የምናነበውና የምናጠናው ክፍል የሕግ፣ የታሪክ፣ የሥነ-ጥበብ፣ የትንቢትና የመልእክት ክፍል መሆኑን መረዳት ወደ ትክክለኛው ትርጉም የሚያደርስን ቀና መንገድና መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ዐይነት መንገድ ብቻ መነበብ እንደሌለበት ያስረዳናል፡፡ ቃሉ በአንድ ዐይነት መንገድ አለመጻፉ ልዩ ውበት እንዲኖረው አድርጐታል፡፡ ቃሉ መነበብና መተርጐም ያለበት እንደ ሥነ-ጽሑፋዊ ቅርጹ/ይዘቱ ነው፡፡ ‹‹የአንድ መጽሐፍ መልእከት ወይም ሐሳብ በሥነ-ጽሑፋዊ ቅርጹ ይወሰናል፤ መልእክት የሚተላለፈው በቋንቋ ብቻ ሳይሆን በሥነ-ጽሑፋዊ ቅርጽም ነው፤ እናም ሥነ-ጽሑፋዊ ቅርጽና መልእክት አይነጣጠሉም … የምናነበው መጽሐፍ መልእክቱ ከሥነ-ጽሑፋዊ ቅርጹ ሊነጠል ካልቻለ፣ ይልቁንም መልእክቱን ለመረዳት ሥነ-ጽሑፋዊ ቅርጹን መረዳት ወሳኝ ከሆነ፣ አሁን ለምናነበውና ለምናጠናው መጽሐፍ ሥነ-ጽሑፋዊ ቅርጽ ተገቢውን ሥፍራ መስጠት አለብን››፡፡ (ምኒልክ አስፋው መጽሐፍ ቅዱስና የትርጓሜ ስልቱ ገጽ 125) ስለዚህ በምንባባችንና በጥናታችን ጊዜ የሥነ-ጽሑፉን ዐይነት ላይ ትኩረት በመስጠት ምልከታ ማድረጋችን ትልቁ ሥራችን ነው፡፡ ወደ ትክክለኛው ትርጉም እንድንደርስም ይረዳናል፡፡
በባለፈው እንደምናደርገው በሰባት መጠየቂያ ቃላት መጠየቅ፣ የተለያዩ ምልከታዎች ማድረግ እንደተጠበቁ ሆነው፣ ዛሬ በየግላችን የምንሠራው የሥነ-ጽሑፍ ምልከታዎች እናደርጋለን፣ በተቻለ መጠን ጊዜ ሰጡትና ምልከታ አድርጉ፡፡
1. ኢሳይያስ 40 ሥነ-ጽሑፋዊ ቅርጹ ሀ. ታሪክ ለ. ሥነ-ጥበብ(ግጥም) ሐ. ትንቢት
2. ዘፍጥረት 1፡27 እና 2፡23 ሥነ-ጽሑፋዊ ቅርጹ ሀ. ታሪክ ለ. ሥነ-ጥበብ(ግጥም) ሐ. ሕግ
3. ፊልጵስዩ 2፡5-11 ያለው ክፍል ሥነ-ጽሑፋዊ ቅርጹ ሀ. ሕግ ለ. ሥነ-ጥበብ(ግጥም) ሐ. መልእከት
0 Comments