በአለፈው ጥናቶቻችን በተለያዩ ምልከታዎች ላይ በግላችን እንድንሠራቸው የተሰጡ ነበሩ፡፡ አንዳንዶቹ ቀለል ያሉ ሲሆኑ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ጠንከርና ጊዜ የሚጠይቁ ሆነው እንዳገኛችኋቸው አስባለሁ፡፡ የዛሬዎቹ ምልከታዎች ግን በጣም ቀላል ሳይሆኑ አይቀሩም ብዬ እገምታለሁ፡፡ ቀላል ስለሆኑ ሁላችሁም ሞክራችኋል ብዬም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

 በመጀመሪያ ሮሜ ምዕራፍ 6ን በሙሉ ምልከታ አድርገን ጥያቄና መልስ የሆኑትን እንድናወጣ ተሰጥቶ ነበር፡፡  በምልከታችን መሠረት ቁጥር 1 ላይ የመጀመሪያውን ጥያቄና መልስ እናገኛለን፡፡ ጥያቄው ‹‹እንግዲህ ምን እንላለን? ጸጋ እንዲበዛ በኃጢአት ጸንተን እንኑርን?›› መልሱ ከቁጥር 2 ጀምሮ እስከ 14 ድረስ ያለውን ይይዛል፡፡ አይደለም ብሎ መልሱን ይጀምርና ባለፈው እንደ ተነጋገርነው ጥያቄያዊ መልስም አስቀምጦአል፡፡ በቁጥር 2 ላይ ‹‹ለኃጢአት የሞትን እኛ ወደ ፊት እንዴት አድርገን እንኖራለን? ›› በማለት በቁጥር ሦስት ላይም ጨምሮ ጥያቄያዊ መልስ ይሰጣል፡፡

 ቀጣዩን ጥያቄ እንደገና ቁጥር 15 ላይ እንዲህ በማለት ያቀርበዋል፡፡ ‹‹እንግዲህ ምን ይሁን ? ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች ስላይደለን ኃጢአትን እንሥራን? ከቁጥር 16 ላይ አይደለም ብሎ ይጀምርና እስከ ቁጥር 23 ድረስ መልሱን ይሰጣል፡፡ በመካከል ቁጥር 21 ላይ ጥያቄያዊ መልስም አስቀምጦአል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ለሚጠይቃቸው ጥያቄዎች መልስ ስለሚሰጥ እኛ መልስ ለመፈለግ መጨነቅ አይጠበቅብንም፡፡

 በሁለተኛ የተሰጠው በሐዋርያት ሥራ 11፡30 ላይ ‹ና› በርናባስንና ጳውሎስን አገናኝቶአል፣ ‹ም› ወደ ሽማግሌዎቹ የተላከው ገንዘብ በሁለቱ እጅ (ኃላፊነት) እንደሆነ ታመለክታለች፡፡ በ15፡6 ላይ ደግሞ እንዲሁ ‹ና› ሐዋርያትና ሽማግሌዎችን አያይዞአል፣ ‹ም› ለመማከር የተሰበሰቡት ሐዋርያት ብቻ ሳይሆኑ ሽማግሌዎችም ጭምር እንደሆኑ ታሳያለች፣ ቁጥር 22፣ በሮሜ 8፡1-11 ላይ ‹ና፣ ስለ፣ እንግዲህ፣ እንደ፣ ቢሆን፣ ቢኖር፣ ግን፣ ነገር ግን፣ … የሚሉት  ቃላት ሁሉ አገናኝ ናቸው፡፡

 በመጨረሻ በማቴዎስ 1፡21-23 ባለው ክፍል ልንመለከታቸው የተጠየቀው የግሥ ጊዜያት ነው፡፡ በዚህ ክፍል ላይ ምልከታ ስናደርግ የምናገኘው፤ በብሉይ ኪዳን በነብዩ ኢሳይያስ የተነገረ ለወደፊት የሚፈጸም ትንቢት ሲሆን፣ ማቴዎስ ደግሞ ትንቢቱ እየተፈጸመ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ ለእኛ ደግሞ ትንቢቱ ስለ ተፈጸመ ኃላፊ ነው፡፡ በዛሬው ዘመን በአገራችን ሳይሆን፣ በጐረቤት አገር ለአጭር ጊዜ በሄድኩበት፣ ክርስቶስ ከእኛ ይወለዳል ብለው የሚጠብቁና እምነት ያላቸው ቡድኖች በኮሌጃችን አጠገብ አጋጥሞኛል፡፡ ከወጣት ጀምሮ እስከ አሮጊቶች ያሉ ክርስቶስ ከእኛ ይወለዳል ብለው፣ ሳያገቡ በድንግልና ሆነው ይጠብቃሉ፡፡ የሚወለደውም አንድ ጊዜ በኬንያ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በኢትዮጵያ ነው እያሉ ሐሳባቸውን ይለዋውጣሉ፡፡ በሳምንት ሁለት ቀን ተራ በተራ ሆነው ወንጌልን ለማሰራጨት በሰርቢስ መኪናቸው ሲወጡ በተደጋጋሚ በዓይኔ አይቻለሁ፡፡ ይኸው ሠላሳ ዓመት አለፈው እስከ አሁን ድረስ ክርስቶስ አልተወለደም፡፡ የዚህ እምነት ጀማሪዎች ይህን የትንቢት ቃል ሲያነቡና ሲያጠኑ የግሥ ጊዜያቱን አልተመለከቱም፡፡ በዚህ ምክንያት ስሕተት ላይ ወድቀዋል፡፡ (ስለ ትንቢት  ወደ ፊት በሠፊው እንመለከታለን)፡፡

     13) መጠን፡-

         በዛሬው ዕለት የመጨረሻዎቹን ሦስት ምልከታዎች እናደርጋለን፡፡ በመጀመሪያ ምልከታ የምናደርገው ‹መጠን› (proportion) በሚለው ላይ ይሆናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን በምናጠናበት ጊዜ ከሚገጥሙን ነገሮች አንዱ፣ ጸሐፊው ለአንድ ነገር የሚሰጠው መጠን (ሥፍራ) የበዛ ወይም ያነሰ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህም መጠኑ በዛ ብሎ ሲገኝ ትኩረት የተሰጠው ዋናው ቁም ነገር መሆኑን ያመለክታል፡፡ ለምሳሌ የዘፍጥረትን መጽሐፍ ዋና ዓላማ ለመረዳት ጥናት ሳናደርግ፣ ዋና ዓላማው የእግዚአብሔርን መኖርና ፈጣሪነት ለማሳወቅ ነው ልንል እንችላለን፡፡ የዘፍጥረትን መጽሐፍ ዋና ሐሳብ ምን እንደሆነ ለመረዳት ምልከታዎችን አድርገን፣ የምናገኘው ውጤት በሠንጠረዥ ይህን ይመስላል፡፡

ሰዎችመግቢያአብርሃምይስሐቅያዕቆብዮሴፍ
ምዕራፍ1-1112-2521-2627-3637-50

በዚህ ሠንጠረዥ መሠረት ዘፍጥረትን ስንመለከተው ጸሐፊው ሰፊ መጠን (ሥፍራ) የሰጠው ለማን እንደሆነ መረዳት አያስቸግረንም፡፡ መግቢያ ብለን ባስቀመጥነው በዚህ አስራ አንድ ምዕራፎች ውስጥ ለፍጥረት፣ ለሰይጣን፣ ለአዳምና ሔዋን፣ ለኖኅ፣ ለማቱሳላ፣ ለሄኖክ … ለመሳሰሉት ታላላቅ ሰዎችና ድርጊቶች የተሰጠው ሥፍራ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ለአራቱ ሰዎች የተሰጠው የምዕራፍ መጠን በጣም ሠፊ እንደሆነ እንመልከት፤ ለአብርሃም 12፣ ለይስሐቅ 5፣ ለያዕቆብ 9፣ ለዮሴፍ 13 ምዕራፍ ተሰጥቶአቸው እናገኛለን፡፡

     በዚህ ጽሑፍ ጸሐፊው ስለ እግዚአብሔር መኖር ማስረጃ ለመስጠት አይሞክርም፣ በእግዚአብሔር መኖር እርግጠኛ ሆኖ በዘፍጥረት 1፡1 ላይ ‹‹በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ›› ብሎ ይጀምራል፡፡ ጸሐፊው ትልቅ ትኩረት የሰጠው ለአራት ሰዎች እንደሆነ ማየት አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ እነዚህ አራት ሰዎች ከየት መጡ ተብሎ የሚጠየቅ ጥያቄ እንዳይኖር በመጀመሪያዎቹ አስራ አንድ ምዕራፎች ውስጥ የእግዚአብሔር እጅ ሥራዎች እንደሆኑ በማሳየት፣ የሰውን ልጅ ጅማሬና ውድቀት በማስረዳት፣ እግዚአብሔር በእነዚህ አራት ሰዎች የዓለም መድኃኒት የሆነውን ክርስቶስን ከዚህ ትውልድ ለማምጣት የመረጣቸውና ያዘጋጃቸው መሆኑን መግቢያው ያሳየናል፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን በምናጠናበት ጊዜ፣ ጸሐፊው በጽሑፉ ውስጥ ለአንድ ነገር የሰጠው የጽሑፉ መጠን፣ ዋና ሐሳቡን ለመረዳት በጣም አስፈላጊና ጠቃሚ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ስለዚህ ቃሉን ስናጠና ጸሐፊው ለአንድ ነገር የሰጠው መጠን/ሥፍራ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ልንሰጠው ያስፈልጋል፡፡

 14) ማብራሪያ፡-

         ከዚህ በመቀጠል ምልከታ የምናደርገው ማብራሪያ (Illustration) በሚለው ላይ ይሆናል፡፡ ጸሐፊው ለአንባቢዎቹ አንድን ነገር በይበልጥ እንዲገባቸውና እንዲረዱት የሚሰጠው ማብራሪያ፣ ገለጻና ማስረጃ፣ ክፍሉን ለመረዳት እርዳታ ያደርጋል፡፡ የፊልጵስዩስን መልእክት በምዕራፍ ሁለት ላይ ሙሉ ምልከታ እናድርግና ዋና ሐሳቡን ለመረዳት እንሞክር፡፡ የፊልጵስዩስ መልዕክት ጸሐፊ ሐዋርያው ጳውሎስ ሲሆን፣ መልእክቱን የጻፈው ከእስር ቤት ሆኖ እንደሆነ ጽሑፉ ራሱ ያስረዳል፡፡ ከጽሑፉ እንደምንረዳው ጳውሎስ እስረኛ ቢሆንም፣ በሁለት ምክንያት እጅግ ደስ ብሎታል፣ የመጀመሪያው በጌታ ባገኘው ሰላም ሲሆን፣ ሁለተኛ የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ገንዘብ አዋጥተው ስለ ላኩለት ነበር፡፡ ከዚህ የተነሣ በመልአክቱ ውስጥ አስራ አንድ ጊዜ ደስ ብሎኛል ደስ ይበላችሁ እያለ ጽፎ እናገኛለን፡፡

 በፊልጵስዩስ 2፡2 ላይ ‹‹በክርስቶስ አንዳች ምክር ቢሆን፣ የፍቅር መጽናናት ቢሆን፣ የመንፈስ ኅብረት ቢሆን፣ ምሕረትና ርኅራሄኄ ቢሆኑ፣ ደስታዬን ፈጽሙልኝ፣ በአንድ አሳብ ተስማሙ፣ አንድ ፍቅር፣ አንድም ልብ፣አንድም አሳብ ይሁንላችሁ›› በማለት መልእክቱን ጽፎላቸው እናነባለን፡፡ በዚህ ዓረፍተ-ነገር ውስጥ ‹ደስታዬን ፈጽሙልኝ› የሚሉት ቃላቶች ደስታውን ሙሉ ያላደረጉበት ችግሮች እንዳሉ ያመለክቱናል፡፡ ችግሮቹ በቁጥር 3 እና 4 ላይ ተጠቅሰው እናገኛለን፡፡ ወገናዊነት፣ ራስን ከሌላው ማስበለጥና የራስን ጥቅም ብቻ ማስቀደም ናቸው፡፡ ታዲያ በዚህ ችግር ውስጥ የወደቁት እነማን ናቸው ብለን ስንጠይቅ መልሱን የምናገኘው በምዕራፍ 4፡3-4 ላይ ይሆናል፡፡

 በዚህ ክፍል ውስጥ ስንመለከት ኤዎድያንና ሲንጤኪን የተባሉ ሁለት ሴት አገልጋዮች የችግሩ መንስኤ እንደሆኑ እናያለን፡፡ ጳውሎስ ስለ እነዚህ ሴቶች ሲመሰክር እንዲህ ይላል ‹‹ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት ከቀሌምንጦስና ደግሞ ከእኔ ጋር አብረው ከሠሩት ከሌሎች ጋር በወንጌል ከእኔ ጋር አብረው ተጋድለዋልና›› በማለት የእምነት ጀግኖች እንደሆኑ ይመሰክርላቸዋል፡፡ አሁን ግን ከላይ በተጠቀሱት ችግሮች ውስጥ ወድቀዋል፡፡

 ስለዚህ ከዚህ ችግር ውስጥ እንዲወጡ አራት ማብራሪያዎች፣ ምሳሌዎች፣ ማስረጃዎች (Illustration) ያቀርብላቸውና ከእነርሱ እንዲማሩ ያደርጋል፡፡ ክብር እያለው፣ ክብር እንደሌለው ከሆነው ክርስቶስ ትህትናን፣ ከራሱ ከጳውሎስ ለሌላው መሥዋዕት መሆንን፣ ከጢሞቴዎስ ስለ ሌሎች እየተጨነቁ ማገልገልንና ከአፍሮዲጡ ሌሎችን በማገልገል እስከ ሞት መድረስን እንዲማሩ ያሳስባቸዋል፡፡ ከቁጥር አንድ እስከ አራት ያለውን ዋና ሐሳብ ለማብራራት አራት ምሳሌ የሚሆኑ አገልጋዮችን አቅርቦላቸው እናገኛለን፡፡ ዋናውን ሐሳብ በማብራሪያ አስደግፎ በማቅረብ፣ ከችግራቸው ለመውጣት ወደ ውሳኔ እንዲመጡ ያደርጋቸዋል፡፡ (አንድ እህት ክፍል ውስጥ እንደምታስተምረው መጽሐፍህን እንደዚያ ሆኖ አላገኘሁትም እንዳለቺኝ፣ ይህን ክፍል እንደሚገባው አልገለጽኩትም)፡፡ ቢሆንም ግን ስለ ማብራሪያ (Illustration) ትንሽ ብልጭታ ያገኛችሁ ይመስለኛል፡፡

    15. ዕድገት፡-

     ብዙ ምልከታዎች ቢኖሩም ለጊዜው እዚህ ላይ ማቆም እገደዳለሁ፤ ወደፊት በመጽሐፍ ሲወጣ ሁሉን ምልከታዎች ጨምሬ አወጣቸው ይሆናል፣ ብዬ አስባለሁ፡፡ አሁን የመጨረሻውን ምልከታ ካደረግን በኋላ ወደ ሦስተኛው ዓይነት ምልከታ ‹‹የሐሳቡን መዋቅር›› ወደ ማየት እንገባለን፡፡

ዕድገት (Progression) አንድ ነገር ከትንሽ ወደ ትልቅ እያደገ ሲሄድ ወይም ከትልቅ ወደ ትንሽ እየቀነሰ ሲመጣ ዕድገት ይባላል፡፡ በሁለቱም ለውጥ ሲያሳይ የመጨመር ወይም የመቀነስ ዕድገት ሲያሳይ በውስጡ ቁም ነገር/ዋና ሐሳብ ይዞአል ማለት ነው፡፡ በዘፍጥረት ምዕራፍ 13፣ 14 እና 19 ላይ ምልከታዎችን ስናደርግ ስለ ሎጥ የጥፋት ሕይወት እያደገ መምጣት እንመለከታለን፡፡ በመጀመሪያው ምዕራፍ 13፡10 ላይ ከአብርሃም ጋር መለያየት ያደርጋል፣ 14፡12 ላይ ሎጥ ተማርኮ ይወሰዳል፤ 19፡23-26 ላይ የእሳት ዲን ዘንቦ፣ ሚስቱ የጨው ዐምድ ሆና ቀረችበት፡፡ በዚህ ሥፍራ የጥፋቱ ዕድገት እየጨመረ መሄዱን መረዳት እንችላለን፡፡ በንባባችንና በጥናታችን እየጨመረ ወይም እየቀነሰ የሚሄድ ነገር ካለ ዕድገት ማሳየቱን መረዳት ቁም ነገሩን/ዋናውን ሐሳብ ለመረዳት እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡

  እንደ ተለመደው ከዚህ በላይ ላደረግናቸው ምልከታዎች በቤታችን ሁላችንም የምንሠራውን ቀጥዬ አቅርቤአለሁ፡፡                                 

  1. ሉቃስ ወንጌሉን ሲጽፍ ሠፊ ሥፍራ(መጠን) የሰጠው ለየትኛው የክርስቶስ ታሪክ ነው?
  2. ሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 15ን በድግግሞሽ፣ ጠቅላላ/ዝርዝርና ተከታታይ በሚለው ምልከታ አድርገናል፤ አሁን ደግሞ ማብራሪያ በሚለው ምልከታ አድርጉና ማብራሪያው፣ ምሳሌው፣ ማስረጃው የትኛው እንደሆነ አውጡ፡፡

ዕብራውያን ከምዕራፍ 1-5 ባለው ክፍል ላይ ምልከታ በማድረግ ያለውን ዕድገት ተመልከቱ፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *