ማስታወሻ
Teleko.org (የተልዕኮ) ድህረ ገጽ፣ ቴሌግራም ቻናል እና ፌስ-ቡክ ውድ ተከታታዮች ከሁሉ አስቀድሜ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለሁላችሁ ይሁን እያልኩ ሰላምታዬን አቀርባለሁ፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች ላለፉት ጥቂት ወራት ያህል ስትከታተሉት የነበረው የኦን ላይን አገልግሎት መቋረጡ ይታወቃል፡፡ ብዙዎቻችሁም የተቋረጠበትን ምክንያት እየደወላችሁ እንዲሁም በአካል ጭምር ስትጠይቁ ለነበራችሁ ጌታ ይባርካችሁ እያለኩ፡-
በመጀመሪያ ዌብ ሳይቱ የተቋረጠበት ዋናው ምክንያት ይህ አገልግሎት ለብዙዎች መጠቀሚያ ሆኖ እንዲያገለግል ለማድረግ አድማሱን ለማስፋት ሲሆን፤ በተጨማሪም ሰሞኑን ሀገራችንን ጨምሮ ዓለም ላይ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በዓለም ዙሪያ ብዙ አገልግሎቶች እንዲቋረጡ ማስገደዱ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ብዙ ያደጉት ሀገራትን ስንመለከት ሁሉም ሰው ከቤት እንዳይወጣ ቢደረግም ብዙ የንግድ፣ የመዝናኛ፣ የት/ቤት ሆነ የመንፈሳዊ አገልግሎቶች ቴክኖሎጂን በመጠቀም እንዲቀጥል መደረጉ ይታወቃል፡፡ በሀገራችንም የማስ ሚዲያውን በተቀናጀ መንገድ በመጠቀም ምን ያህል ሰዎችን በያሉበት መድረስ እንደምንችል ያሳየ ነው፡፡ ከዚህም ማየት የምንችለው እኛም ከምን ጊዜውም በላይ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የተለያዩ ሰዎች በየግል ኮምፕዩተሮቻቸው እና በየማስታወሻ መዝገብ ላይ ሰፍረው የሚገኙ፣ ለትውልድ መተላለፍ የሚገባቸውን ጠቃሚ ትምህርቶች እና ጽሑፎች ወጥነት ባለው መልኩ ብዙዎችን በሚደርስ እና በሚያሳትፍ ለማድረግ መዋቅሩን ለማስፋት እና ለማስተካከል ሲኖን ጌታም ረድቶን ዝግጅታችንን ስላጠናቀቅን በያዝነው ሳምንት ውስጥ የቀድሞ አገልግሎታችንን እንደምንቀጥል እያሳወቅን፡፡ በሀሳብ፣ በጸሎት አብረን በመሆን ይህን አገልግሎት እርስ በእርስ በመተጋገዝ የእግዚአብሔርን መንግሥት አብረን እንድናሰፋ ይሁን፡፡
በኢሳይያስ 65፡24 ላይ ‹‹ሳይጠሩ እመልስላቸዋለሁ፣ ገናም ሲናገሩ እሰማለሁ›› ብሎ እንደተናገረው በሀገራችን አብያተ ክርስቲያናት በታወጀውን ጾም ጸሎት ከልብ በአንድነት ሆነን ጌታ ሰምቶን ዕንባችን በእርሱ ይታበስ ዘንድ እምነታችን ነው፡፡
በመጨረሻም እንኳን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ መታሰቢያ በሰላም አደረሳችሁ እያልን፣ አሁን አገልግሎታችንን በጌታ ዕርዳታ ካቆምንበት መጀመራችንን በደስታ እንገልጻለን፡፡ መልካም የዕረፍትና የጥናት ጊዜ ይሁንላችሁ ወቅቱ አብዛኛዎቻችን በቤት ውስጥ ለትንሽ ጊዜ ማሳለፋችን አስፈላጊ በመሆኑ፣ ሁላችንም ቤታችን መሽገን በመንፈስ እና በሐሳብ አብረን የጌታን ቃል የምንካፈልበት ጊዜ እንዲሆንልን ምኞታችን ነው፡፡
0 Comments