ባለፈው ጥናታችን ሦስት የሚሆኑ ምልከታዎችን ተመልክተን፣ በግላችሁም የምትሠሩት እንደ ተሰጣችሁ የሚታወቅ ነው፡፡ በመጀመሪያ የተሰጣችሁ በተመሳሳይ መልካቸው የሚወዳደሩትንና ሁለተኛው በዚሁ ክፍል ውስጥ የሚነፃፀሩትን እንድታወጡ ነበር፡፡ የሠራችሁትን ከምታገኙት መልስ ጋር አስተያዩት፣ በዚህ ክፍል ውስጥ ባለፈው እንደ ተመለከትነው፣ ሁለት ነገሮችን ለማወዳደር የሚጠቅማችሁ ‹‹እንደ›› የሚለው ቃል ነው፡፡ በዚህ ቃል ምንና ምንን አወዳደራችሁ? ጸሐፊው ያነፃፀረው ሁለት ነገሮችን ሲሆን ከማወዳደር ጀምሮ ወደ ማነፃፀር ነው የመጣው፡፡
በ1ኛ ጴጥሮስ ምዕራፍ 1፡18-19 ‹‹ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፣ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ፡፡›› በዚህ ክፍል ውስጥ ፀሐፊው ሁለት ነገሮችን በተመሳሳይ መልካቸው ያወዳድራል፡፡ የክርስቶስ ደም ፤ ከበግ ደም ጋር፣ እንዲሁም ከብርና ወርቅ ጋር (ይህን ጸሐፊው አላወዳደረውም የምንባቡ ሐሳብ ይበልጥ ግልጽ እንዲሆንልን ያወዳደርነው ነው፡፡ እንዲሁ ስናየው ብርና ወርቅ የከበረ ነው፣ በብሉይ ኪዳንም አይሁዶች ለነፍሳቸው ማስተሰሪያ እንዲሆን ብርና ወርቅ በሰቅል ያቀርቡ ነበር) ይወዳደራል፡፡ ጸሐፊው ይህን የከበረውን የክርስቶስ ደም ከሚጠፋው ብርና ወርቅ ጋር ያነፃፅራል፡፡ የከበረ የነበረውን ብርና ወርቅ ‹‹በሚያልፍ›› በሚለው ቃል የከበረ መሆኑን ያፈርሰዋል፡፡ ስለዚህ ጸሐፊው ለአንባቢዎቹ የሚያስረዳው ከለመዱት ከብሉይ ኪዳን የመዋጀት ሥርዓት በበለጠ በክርስቶስ ደም መዋጀታቸውን ያሳያቸዋል፡፡
ሁለተኛው የምትመለከቱት የተሰጣችሁ ማቴዎስ 5፡17-48 ያለው ክፍል ነው፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ የተደጋገሙ ነገሮች እንዳገኛችሁ እርግጠኛ ነኝ፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ ስንመለከት የተለያዩ ነገሮች መግደል፣ ማመንዘር፣ ፍቺ፣ መሐላ፣ በቀልና ጠላትን መውደድ የሚሉት ተጠቅሰው ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ስድስት የተለያዩ ነገሮችን የሚያገናኛቸው ምንድን ነው? የሚያገናኛቸውን ካላወቅን፣ ምንባቡን አልተረዳነውም ማለት ነው፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ የተደጋገሙት ነገሮች የክፍሉን ዋና ሐሳብ ያመላክቱናል፡፡ የተደጋገሙት ‹‹እንደ ተባለ ሰምታችኋል›› ‹‹እኔ ግን እላችኋለሁ›› የሚሉት ሐሳቦች ናቸው፡፡ በተለይም ‹‹እንደ ተባለ ሰምታችኋል›› የሚለውን ሐሳብ ወስደን ምን ሰምተው ነበር? ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ በዚህም አንዳንድ መረጃዎችን ተጠቅመን የምናገኘው ሐሳብ፣ የአይሁድ ሊቃውንት በሚሽናህና በሚድራሽ ላይ የጻፏቸውን ይሆናል፡፡ እነዚህ መጻሕፍት በሙሴ የተጻፉትን ሕጎች የሚያብራሩ ማብራሪያዎችና በቃል ሲተላለፉ የነበሩትን አጠቃለው የጻፉባቸው ናቸው፡፡ ጌታ እነዚህን በቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ ቆይተው በኋላ ላይ በመጽሐፍ የተጻፉትን ነው፣ ‹‹እንደ ተባለ ሰምታችኋል›› እያለ የተናገረው፡፡ ከብሉይ ኪዳን ጌታም ሆነ ሐዋርያቶች ሲጠቅሱ በሕግ፣ በነብያትና በመዝሙራት ወይም የነብዩ ስም ተጠቅሶ ይነገራል እንጂ፣ እንደ ተባለ ሰምታችኋል ብለው ተጠቅመው አያውቁም፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ በትክክለኛውና ትክከለኛ ባልሆነው ሕግ መካከል ልዩነት እያደረገ መናገሩ ነው፡፡ ስድስቱንም ሐሳቦች የሚያገናኛቸውና ዋናውን ሐሳብ የሚጠቁሙት ‹‹እንደ ተባለ ሰምታችኋል›› የሚሉት ቃላቶች ናቸው፡፡
- የሚከታተሉ፡-
በዛሬው ጥናታችን ሦስት ምልከታዎችን ጨምረን እንመለከታለን፡፡ በምናነበውና በምናጠናው ክፍል ውስጥ የተለያዩ ነገሮች ተከታትለው ከተገኙ ወደ ዋናው ሐሳብ የሚያደርሱን ጠቋሚዎች ይሆናሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ሉቃስ 15፡1-32 ላይ ያለውን ታሪክ እንመልከት፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ ተከታታይነት ያላቸው ሦስት ድርጊቶች እናገኛለን፡፡ ድርጊቶቹ የበግ፣ የድሪምና የልጅ መትፋት ናቸው፡፡ ሁሉም የጠፉ በመሆናቸው አንድ እውነት ብቻ ያስተላልፋሉ፡፡ ሦስት በመሆናቸው የተለያየ እውነት ያስተላልፋሉ ማለት አይደለም፡፡ አንድን እውነት በማከታተል ያሳያሉ፡፡ ያ የሚያስተላልፉት/የሚያሳዩት እውነት ምንድን ነው? ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ በዚህ ክፍል ሦስቱም የጠፉ በመሆናቸው የተነሳ ሐሳቡ ተደጋግሞ ይገኛል፡፡ ስለዚህ የሚደጋገም ለሚለውም ምልከታችን ምሳሌ ሊሆነንም ይችላል፡፡
እነዚህን ሦስት ማስረጃዎች (Illustration) ብቻቸውን ይዘን ብንሄድ፣ ጸሐፊው በክፍሉ ሊያስተላልፍ የፈለገውን ሐሳብ ማግኘት አንችልም፡፡ ዋና ሐሳቡ ያለው ቁጥር 1 እና 2 ላይ ስለሆነ ተከታትለው የተቀመጡት ማስረጃዎቹ ትርጉም አልባ ይሆናሉ፡፡ ዋና ሐሳቡ ያለው ሁለቱ ቁጥሮች ላይ ነው፡፡ ‹‹ቀራጮችና ኃጢአተኞችም ሁሉ ሊሰሙት ወደ እርሱ ይቀርቡ ነበር፡፡ ፈሪሳውያንና ጻፎችም፡-ይህስ ኃጢአተኞችን ይቀበላል ብለው እርስ በርሳቸው አንጐራጐሩ፡፡›› የሚለው ዋና ሐሳቡ ነው፡፡ ይህን ማንጐራጐር በቃላት አውጥተው አልተናገረትም ነገር ግን በልባቸው ነው ያሰቡት፡፡ ጌታም በልባቸው ያሰቡትን አውቆ ሦስቱን ማስረጃዎች በማከታተል ተናገረ፡፡ መልእክቱም ቀራጮችና ኃጢአተኞች ለእኔ እንደ ጠፋው በግ፣ ድሪምና ልጅ ውድና ተወዳጅ ናቸው ማለቱ ነው፡፡ ሦስቱም ምሳሌዎች(ማስረጃዎች) የሚያስተላልፉት አንድ እውነት ነው፡፡ (ይህ ክፍል ጥሩ ትምህርት ስለሚሰጥ ‹ማብራሪያ› በሚለው ምልከታ 14 ላይ እንደገና እናየዋለን)
- ድርጊት/ውጤት፡-
በመቀጠል የምንመለከተው አንድ ነገር ሲፈጸም ድርጊት(መንስዔ)ና ውጤት ይኖረውና እንደገና ደግሞ ሌላ ውጤትና ድርጊት ይኖረዋል፡፡ ዮሐንስ 3፡16 ላይ ስንመለከት እነዚህን በቀላሉ መረዳት እንችላለን፡፡ ‹‹በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና፡፡›› በዚህ ጥቅስ ውስጥ ዋናውን ሐሳብ ለመረዳት ከፈለግን ድርጊትና ውጤት የሆነውን ማውጣት ያስፈልገናል፡፡ ድርጊቱ- እግዚአብሔር ዓለምን ወዶአል የሚለው ሲሆን፣ ውጤቱ እግዚአብሔር ልጁን ሰጠ የሚለው ነው፡፡ ውጤቱ ተመልሶ ድርጊት ይሆንና ሌላ ውጤት ይኖረዋል፡፡ በእግዚአብሔር ልጅ ማመን ድርጊት ይሆንና ውጤቱ የዘላለም ሕይወት ማግኘት ይሆናል፡፡
- ጠቅላላ/ዝርዝር፡-
አንዳንድ ምንባቦችን በሰባቱ መጠየቂያ በመጠየቅ ዋናውን ሀሳብ ማግኘት ሲቻል፣ አንዳንዱን ደግሞ የተለያዩ ምልከታዎች በማድረግ ማግኘት ይቻላል፡፡ አንዳንድ ምንባቦች በመጀመሪያ አጠቃላዩን ቀጥሎም ዝርዝሩን ያቀርባሉ፡፡ ዋናውን ሐሳብ ወይም አጠቃላዩን እንደ መግቢያ፣ ማስተዋወቂያና ዝግጅት አድርጎ ይጠቀምበታል፡፡ በ1ኛ ጴጥሮስ 5፡1-5 ላይ ያለውን ብንመለከት ቁጥር 1 ለክፍሉ ሐሳብ መግቢያ፣ ማስተዋወቂያ አድርጎ ሲያቀርበው፣ ከቁጥር 2-5 ባለው ክፍል ዝርዝር ሐሳቦችን ያቀርባል፡፡ ከጥቂት ጥቅሶች ሰፋ ወዳለው ሄደን አንድ ክፍል፣ ከሮሜ መጽሐፍ ከምዕራፍ 12-16 ያለውን እንመልከት፡፡ ምዕራፍ 12፡1-2 ያለው ጠቅላላ ሐሳብ ሲሆን ከምዕራፍ 12፡3 እስከ ምዕራፍ 16 መጨረሻ ድረስ ያለው ክፍል ዝርዝር ሐሳብ ነው፡፡
በሚቀጥለው ጽሑፍ እስከምንገናኝ የሚከተሉትን ክፍሎች በመጠየቂያ ቃላት ጠይቁ፣ እንዲሁም ምልከታ አድርጉ፡፡ 1. ‹‹ተከታታይ›› ለሚለው ማቴዎስ 13 ን በሙሉ ተመልከቱና ተከታታይ የሆነውን አውጡ፡፡
2. ‹‹ድርጊትና ውጤት›› ለሚለው ቲቶ 2፡11-12 ተመልከቱና ድርጊትና ውጤት የሆነውን ለዩ፡፡ 3. ‹‹ጠቅላላና ዝርዝር›› ለሚለው በድግግሞሽ ያያችሁትን ክፍል ማቴዎስ 5፡17-48 ተመልከቱና አጠቃላይና ዝርዝሩን ለዩ፡፡
0 Comments