ባለፈው በምዕራፍ አንድና ሁለት ጥናታችን ኢየሱስ ከነብያትና ከመላእክት እንደሚበልጥ ተመልክተናል፡፡ አሁን ደግሞ ምዕራፍ ሦስትንና አራትን ስናጠና ኢየሱስ ከሙሴና ከኢያሱ እንደሚልጥ እንመለከታለን፡፡ ብሉይ ኪዳን በሙሉ በሙሴ ላይ ተሰቅሏል (ተመሥርቷል) ማለት ስሕተት ላይሆን ይችላል፡፡ ኦሪት/ሕግ፣ ሥነ ሥርዓትና ከባርነት የመውጣት ዕድላቸው ከሙሴ ጋር ተያይዟል፡፡ ያወጣቸውና በምድረ በዳ የመራቸው ሙሴ ራሱ ነበረ፡፡ ግን እርሱና ያ ትውልድ ከነዓን ባለማመናቸው ምክንያት ሊገቡ አልቻሉም፡፡ ስለዚህ የተገባላቸውን ተስፋ ሳይወርሱ ሞቱ፡፡ የገጠመው ውጥረት ትምህርታዊም መንፈሳዊም ነበረ፡፡ እግዚአብሔር የገባላቸውን ቃል ኪዳን ይፈጽምልናል ብለው ሕዝቡ ሳይረዱ ስለቀሩ ለመፈጸም ራሳቸውን አሳልፈው ለመስጠት አልፈቀዱም፡፡ እግራቸው በአንድ ቦታ ልባቸው በሌላ ነበረ፡፡ ስለዚህ የዕብራውያን ክርስቲያኖችም እንደ አባቶቻቸው ወደ እውነተኛው ዕረፍት ሳይገቡ እንዳይቀሩ ይመክራቸዋል፡፡

 እነዚህ ሰዎች (አንባቢዎቹ) ኃጢአት አልሠሩም፡፡ ስለ ኃጢአት አልተወቀሱም፡፡ ነገር ግን በልባቸው ያወላውሉ ነበር፡፡ ወደ ቤተ መቅደስ ሥነ ሥርዓት ሊመለሱ ይፈልጉ ነበር፡፡ ሙሴ ለብሉይ ኪዳን መገለጥ ማዕከላዊ ሆኖ ቢገኝም፣ ኢየሱስ ከእርሱ የበለጠ ሥፍራ አለው፡፡ ሙሴ ለመራው ትውልድ ለማድረግ ያልቻለውን፣ ኢየሱስ ለዚህ ትውልድ ለማድረግ ችሏል፡፡ ሙሴ ዕረፍት ሊሰጥ አልቻለም፣ ኢየሱስ ግን ዕረፍትን ሰጥቷል፡፡ ባለመታዘዛቸው ምክንያት ያ ትውልድ የተሰጣቸውን ተስፋ ለመውረስ አልቻሉም፡፡ ይህ አማራጭ ከአይሁድ ምኵራብ ራሳቸውን ለለዩት ለእነዚህ ክርስቲያኖች አስፈላጊ አይደለም፡፡ ኢየሱስ ከሙሴ እጅግ በጣም ስለሚበልጥ ወደ ጉዞአቸው መድረሻ ያለ ምንም ጉዳት ሊመራቸው ይችላል፡፡ በመንገድ ላይ ወድቆ የመቅረት አማራጭ ለክርስቲያን የማያስፈልግ አማራጭ ነው፡፡ ለመሆኑ እውነተኛ ድነትን ያገኘ ሰው ወድቆ ይቀር ይሆን? ትምህርቱን አንቀጽ በአንቀጽ ለማየት ሙከራ እናደርጋለን፡፡

 3፡1-6 ኢየሱስ ከሙሴ ይበልጣል፡– እምነትና ድፍረት የሚሉት ቃላት የአንባቢያንን ጉድለት ይገልጻሉ፡፡ ኢየሱስ ሊቀ ካህናችን ብቻ ሳይሆን፣ ልጅ ከአገልጋይ እንደሚበልጥ ሁሉ ከሙሴ እንኳ ይበልጣል፡፡ ሙሴ በእግዚአብሔር ቤት እንደ ሎሌ (አገልጋይ) ሲያገለግል፣ ኢየሱስ በቤቱ እንደ ልጅ በማገልገሉ ከሙሴ መብለጡን ያሳያል፡፡ በምዕራፍ 2፡14-18 በተገለጠው አንፃር እንኳ ኢየሱስ ታማኝ ነበር፡፡ የእነዚህ አንባቢያን ታማኝነት ቁ.1 ተመልከቱ ቁ.12 ተጠንቀቁ ቁ.13 ተመካከሩ የሚሉትን ቃላት ስንመለከት ወደ አጠያያቂ ደረጃ ተቃርቦ ነበር፡፡

 በዚህ ክፍል ስንመለከት የተሻለ ተስፋ አላቸው፣ ስለዚህ ያንን ማመን አለባቸው፡፡ ሙሴና ኢያሱ ታላቅ መሪዎች ነበሩ፣ ነገር ግን ለሕዝብ የልብ ዕረፍት ሊሰጡአቸው አልቻሉም፡፡ በዘዳግም መጽሐፍ ምዕራፍ 18፡16 ላይ በተነገረው ቃል መሠረት ይህ ዕረፍት ለእኛ የተሰጠ መሆኑን ትንቢቱ ይመሰክራል፡፡ ኢየሱስ የአእምሮና የነፍስ ዕረፍት ሊሰጥ ቀርቧል ብለው ይመሰክራሉ፡፡ በተለይም በማቴዎስ 11፡፡28-30 ላይ ጌታም ራሱ የነፍስ ዕረፍት እንደሚሰጥ ይናገራል፡፡ ለዚህም የነፍስ ዕረፍት ያገኘን ሁላችን ምስክሮች ነን፡፡ ጸሐፊው በዚህ ክፍል ኢየሱስ ከሙሴ በተሻለ ዕረፍት እንደሚሰጥ ያስተምራል፡፡

 3፡7-19 ለእግዚአብሔር ሕዝብ ስለተሰጠ ዕረፍት፡-

 እንቢተኞች ነበሩ፡-3፡7-11 ሳይታመኑ የቀሩትም ምን ሆኑ? የመዝ. 94፡7-11 ጸሐፊው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ እርሱን በመጥቀስ ጸሐፊው ቀጥተኛ ጥያቄ ያቀርብላቸዋል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለዕብራውያን አማኞች ይናገራል፡፡ ማዳመጥ አለባቸው፡፡ የእስራኤል ሕዝብ እንቢተኞች በመሆናቸው ዕረፍትን ሊያገኙ አልቻሉም፣ የእግዚአብሔርን ተስፋዎች አልወረሱም፡፡ የሙሴ ትውልድ ከነዓን የመግባት ተስፋ የነበረው ቢሆንም፣ ያልገቡት የእግዚአብሔርን ተስፋ ቃል ጨብጠው ባለመያዛቸው ነበረ፡፡ ጸሐፊው የአይሁድ ክርስቲያኖች ጌታ ኢየሱስን ክደው ወደ ድሮው የሕግ እምነታቸው እንዳይመለሱ ያስጠነቅቃቸዋል፡፡ በአዲስ ኪዳን ይህን ዕረፍት ሰጪው ከሙሴ ይበልጣል፣ ስለዚህ የእኛ ተስፋ የተሻለ ነው፡፡ እኛም በዚህ ዘመን ያለን አማኞች፣ እነዚህን ተስፋዎች ባንይዝ በሕይወታችን ላይ ሐዘንና ጉዳትን እናስከትላለን፡፡  

 መታዘዝ ይኖርባቸዋል፡- 3፡12-15 ልባችንን መጠበቅ አለብን፣ ካልተጠበቀ እልከኛና ከቅን መንገድ ፈቀቅ የሚል ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ እንዳይሆን እርስ በእርሳችን መረዳዳት አለብን፡፡ በእምነት እያደግን እንድንሄድ የመተጋገዝ ግዴታ አለብን፡፡ ታምነን እንድንኖር ተጠርተናል፡፡ ያን ተስፋ በእጃችን እስክንጨብጠው ድረስ በሀሳብ መዋዠቅ አይገባንም፡፡

 አለመታዘዝ አሰናከላቸው፡-3፡16-19 እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ሕጉን ሰጣቸው፣ እነርሱም ሕጉን ለመጠበቅ ቃል  ገቡ፡፡ ነገር ግን ወደ ከነዓን ለመግባት እምቢ አሉ፡፡ ወደ ከነዓን ያለ መግባታቸው ምክንያት አለመታዘዛቸው ነበረ፡፡ አለመታዘዝ ምንድን ነው? እግዚአብሔር የተናገረውን አያደርግም የማለት ሀሳብ ነው፡፡ ይህን ሀሳብ የሚያብራሩ አባባሎች ብዙዎች ናቸው፡፡ ስለ መንፈሳዊ ሕይወታቸው ምንም አይናገርም፡፡ የእግዚአብሔርን ተስፋዎች መውረስ ሲገባቸው አልወረሱም፣ በረከቶቹንም አላገኙም፡፡ ዛሬም ብዙ ክርስቲያኖች በኢየሱስ ላይ ያላቸውን እምነት ቤተ ሰባቸውን በመፍራት፣ ገንዘብና ሥልጣን ለማግኘት ሲሉ ይተዋሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች ጊዜአዊ የሆነ ደስታ፤ ሰላምና ብልፅግና ቢያስገኙልንም በኋላ ላይ ፍርድ ያስከትሉብናል፡፡ እኛም በእነዚህ ነገሮች ላለመያዝና ያለመታዘዝ በሕይወታችን እንዳይኖር፣ ጥንቃቄ ልናደርግና ታማኞች ሆነን ልንመላለስ ይገባናል፡፡

  እውነተኛ ዕረፍት፡- 4፡1-7 አሁን ባየነው በምዕራፍ ሦስት ላይ ጸሐፊው ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ሁለት በጣም አስፈላጊ  የሆኑ ምክሮችን በመስጠት ወደ ምዕራፍ አራት ይሸጋገራል፡፡ ምክሮቹም በየቀኑ እየተገናኙ መመካከርና እምነታቸውን አጽንተው እንዲጠብቁት የሚሉት ናቸው፡፡ አሁን ልንዘው የምንችል የዕረፍት ተስፋ አለን፡፡ ትኩረቱ በተሰጠው ተስፋ ላይ ነው፣ ገና አለ፡፡ እስራኤላውያን ተስፋውን ሳይወርሱት እንደ ቀሩ ሁሉ የዕብራውያን ክርስቲያኖችም ሊያጡት ይችላሉ፣ በማለት ጸሐፊው ስለ ሠጋ የተሰጠውን ተስፋ መያዝ እንዳለባቸው ያሳስባቸዋል፡፡ እኛም ተስፋ በመሆኑ መቀበል አለብን፡፡ ዛሬ ብሎ በዳዊት ሲናገር የመጨረሻው ዕረፍት ገና እንደ ቀረ ያሳያል፡፡ ለእስራኤል በዕብራውያን 4 ላይ ዕረፍት ከነዓን መግባት ነበር፡፡ ሰንበት እንደ ምሳሌ ብቻ ተጠቅሶአል፡፡ እውነተኛው ዕረፍት ግን የነፍስ ዕረፍት በጌታ ማግኘት ነው፡፡

 የዕረፍት ትርጉም ፡- 4፡8-11 የእግዚአብሔር ዕረፍት ምን ዓይነት ዕረፍት ሊሆን ይችላል ? ‹‹እግዚአብሔርም የሠራውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ፈጸመ›› ሲል የእቅዱ መከናወን ነው እንጂ ሥራ አለመሥራቱ አይደለም፡፡ ከዘፍጥረት 2፡2 የተጠቀሰው የዕረፍቱ ዓይነት ይህ ነው፡፡ የዕቅድ መከናወን ካለ ዕረፍት አለ ማለት ነው፡፡ ሁለት አማራጮች ብቻ አሉ፡- በኢየሱስ የተገኘውን ዕረፍት መቀበል ወይም ወድቆ መቅረት፡፡ ከሁለት አንዱን የግድ መምረጥ አለብን፡፡ የድነታችን ሥራ በጌታ ስለ ተሠራልን፣ ድነትን ለመሥራት መሯሯጥ የለብንም፡፡ እርሱን በማመን ወደ ዕረፍቱ ለመግባት እንትጋ፡፡ እርፍ! እንበል፡፡ ወደፊትም በሰማይ ለሚጠብቀን ዕረፍትም ዋስትና ነው፡፡

 የእግዚአብሔር ቃል፡-4፡12-13 ከፍ ብሎ ከተጠቀሰው እንዴት ተያይዘዋል ? ከብሉይ ኪዳን ተጠቅሰው የቀረቡት ጥቅሶች በዕብራውያን አማኞች ችግር ላይ ያተኩራሉ፡፡ የችግሩ መፍትሔ ምን እንደ ሆነ ይገልጣሉ፡፡ ምክንያትን በመፍጠር ረገድ አዋቂዎች ነበሩ፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ልባችንን ቢመረምር መነሾውንና መድኃኒቱን ይሰጣል፡፡ እውነተኛ እምነት የሚለካው ቃሉን በመታዘዝ፣ ምን ያህል ኢየሱስን በመምሰላችንና እስከ መጨረሻው ድረስ እምነታችንን  በታማኝነት  በመጠበቃችን ነው፡፡ ቃሉ ሕያውና የሚሠራ ስለሆነ ሕይወታችንን እንዲሠራው ለቃሉ ጊዜ እንስጥ፣ እናንብበው፣ እናጥናው፡፡

4፡14-16 የኢየሱስ ሊቀ ካህንነት፡– የዕብራውያን አማኞች ችግር ተገልጦአል፡፡ ድክመታቸው እምነታቸውን የመልቀቅ ዝንባሌ ነበረ፡፡ ከእግዚአብሔር ምህረትና ጸጋ ያስፈልጋቸው ነበረ፣ ተሰናክለውም ይሆናል፡፡ የአይሁድ ሊቀ ካህን ሊያጽናናቸው ምንም አቅም የለውም፣ ነገር ግን ኢየሱስ ይችላል፡፡ በእምነት ወደ ጸጋው ዙፋን ቢቀርቡ ሊረዳቸው እንደሚችል ያሳያቸዋል፡፡ ኢየሱስ የመለኰታዊ መገለጥ ሁሉ መጨረሻ ነው፡፡ ስለ ማንኛውም አማራጭ ማሰላሰል ወደኋላ እንደማፈግፈግ ነው፡፡ ጳውሎስ ለቆላስይስ ቤተ ክርስቲያን በምዕራፍ 2፡16 ላይ ተመሳሳይ ምክር ሰጥቶ ነበር፡፡ እንዲህ በማለት ‹‹እንግዲህ በመብል ወይም በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም  ስለ ሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ፤ እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና፣ አካሉ ግን ክርስቶስ ነው››፡፡ ብርቅ ከሆነው ክርስትና የእኛ የሆነውን ዕረፍት እንቀበል፡፡ ፍጹም ሰው የሆነና የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ ብቸኛው ሊቀ ካህን፣ አማላጅ እርሱ ስለ አለን፣ ተስፋ ተሰጥቶናልና ተቀብለነዋል ማለት ይገባናል፡፡ ለእኛ የተሰጠውን ተቀብለን ልንደሰትበት ይገባናል፡፡ የቀድሞ ሊቀ ካህናት ፍጹማን አልነበሩም፡፡ የእኛ ሊቀ ካህን ይታዘዛል፣ ፍጹም ይቅርታ ሊሰጠን ይችላል፡፡ እነዚህ ሁለት ነጥቦች ክህነቱ ፍጹም መሆኑን ያሳያሉ፡፡ በክርስቶስ በሚገኘው ፍጹም ዕረፍት ውስጥ እንዲገቡና እንዲጸኑ ያሳስባቸዋል፡፡ ከዚህ ትምህርት ብዙ ጠቃሚ የሆኑ ትምህርቶችን ማግኘት እንችላለን፡፡ ሥራችንንና አስተሳሰባችንን መመርመርና በጌታ ተጠያቂዎች መሆናችንን መገንዘብ ያስተምረናል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የነፍሳችን ሐዋርያና ሊቀ ካህን በመሆኑ፣ ከሙሴና ከኢያሱ ይበልጣል፤ ስለዚህ በሙሉ ልባችን ይህን እውነት ተቀብለን፣ ክርስቶስን እየተመለከትን በእምነት መመላለስ ይጠበቅብናል፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *