የዕብራውያንን መልእክት በሚገባ ለመረዳት ከምዕራፍ ሰባት መጀመር እንዳለብን በቀደመው ጽሑፍ አይተናል፡፡ ለምንድን ነው ከመሐል መጀመር ያለብን? ብለን ስነጠይቅ፣ በዚህ ክፍል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሦስት ምክንያት እንዴት ብቸኛ ሊቀ ካህን እንደሆነ ያስረዳናል፡፡ እግዚአብሔር ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ሊቀ ካህን አድርጎ የሾመበትን ዋናውን ሐሳብ በምዕራፍ 7 ቁ. 20-21 ባለው ክፍል ላይ እንገኛዋለን፡፡ በእነዚህ ሁለት ቁጥሮች ስለ ሊቀ ካህንነቱ ሦስት ታላላቅ እውነቶች ተገልጸው እናገኛለን፡፡ እነርሱም 1ኛ) እንደ መልከ ጼዴቅ ካህን መሆኑ፣ 2ኛ) ለዘላለም ካህን መሆኑና፣ 3ኛ) በመሐላ ካህን  መሆኑ የሚሉት ሀሳቦች ኢየሱስን ብቸኛው ሊቀ ካህን የሚያደርጉት የመጽሐፉ ዋና ቁልፍ እውነቶች ናቸው፡፡

ይህን ምዕራፍ ስናጠና በመጀመሪያ መነሳት ያለብን መልከ ጼዴቅ ማን ነው? ከሚለው ጥያቄ መጀመሩ መልካም ነው፡፡ መልከ ጼዴቅ በዘፍጥረትና በመዝሙር መጻሕፍቶች ተጠቅሶ እናገኘዋለን፡፡ መልከ ጼዴቅ ከሌዊ የሚበልጥ ታላቅ ካህን ነበር፡፡ እያንዳንዱ የአይሁድ ካህን ከሌዊ ቤተ ሰብ መሆን ነበረበት፡፡ በአይሁድ ሃይማኖት ውስጥ ሕጋዊ ሰውነት ያለው ክህነት ይህ ብቻ ነበር፡፡ በምዕራፍ 7 ላይ ያለው ሌላው የመልከ ጼዴቅ ክህነት ከሌዊ ክህነት የበለጠ መሆኑን ያሳያል፡፡

 በተለያዩ ምክንያቶች መልከ ጼዴቅ ከሌዊ የበለጠ ካህን ነበር፡፡ ኢየሱስ ደግሞ ከመልከ ጼዴቅ ይበልጣል፡፡ የኢየሱስ ክህነት ምንም የመልከ ጼዴቅ ዓይነት ቢሆንም ከእርሱ ይበልጣል፡፡ የሌዊና የመልከ ጼዴቅ ክህነት በጣም ልዩ በመሆናቸው ሁለቱንም ለማነጻጻር ያስቸግራል፡፡ መልከ ጼዴቅ ከሌዊ ወገን አልነበረም፣ ኢየሱስም አልነበረም፣ ከይሁዳ ነገድ ነበር፡፡

          መልከ ጼዴቅ ማን ነበረ? ቁ. 1-3 አእምሮን ማራኪ የሆነው  የመልከ ጼዴቅ ታሪክ የሚገኘው በዘፍጥረት 14፡17-20 ውስጥ ነው፡፡ ከታሪኩ፡- መልከ ጼዴቅ መለኰታዊ ፍጡር ነበረ ለማለት አንችልም፡፡ አብርሃምን እንደ ባረከና አብርሃምም አሥራት እንደ ሰጠው መገንዘብ ጠቃሚ ነው፡፡ መልከ ጼዴቅ የሳሌም (በንጉሥ ዳዊት ኢየሩሳሌም ተባለች) ካህንም ንጉሥም ነበረ፡፡ ካህንና ንጉሥ ከሆነ ሰው ነው፣ ሰው ከሆነ ደግሞ እናት አባት አሉት፡፡ ቁጥር 3 ለማለት የሞከረው እናትና አባቱ እነማን እንደ ነበሩ፣ ከየትኛው ወገን እንደ ነበረና መቼ እንደ ተወለደ፣ እንዴትና መቼ እንደ ሞተ ምንም አልተገለጸም፡፡ ስለ ሞቱ የተጠቀሰ ነገር ባለመኖሩ እስካሁን ድረስ ሊቀ ካህን ሆኖ የሚኖር ይመስላል፡፡ ቢያስመስለውም ሰው ከሆነ ሞቷል፡፡ ጸሐፊው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ከመልከ ጼዴቅ ጋር በሦስት ዋና ዋና መንገዶች ያመሳስለዋል፡፡ 1) ካህንና ንጉሥ የሚለውን አጣምረው መያዛቸው፣ 2) የአመራር ሥርዓታቸው ሰላምና ጽድቅ በመሆኑና፣ 3) ሁለቱም ዘላለማዊ በመሆናቸው (የመልከ ጼዴቅ ዘላለማዊነት በምሳሌነቱ) ነው፡፡

          መልከ ጼዴቅ ከሌዊ ነገድ ነበረ? ቁ. 4-10 በአይሁድ ሥነ ሥርዓት የሌዊ ወገን አሥራትን ለመሰብሰብ ታዝዞ ነበረ፡፡ የሌዊ ነገድ ከአብርሃም የወጣ ነው፡፡ መልከ ጼዴቅ ከሌዊ አሥራት ከተቀበለ ከሌዊ ይበልጣል ማለት ነው፡፡ መልከ ጼዴቅ የይሁዳ ሰው ሳይሆን ኢያቡሳዊ ነበር፡፡ ቢሆንም ግን የሌዊ ነገድ በአብርሃም ዕቅፍ ሆነው የመልከ ጼዴቅ ክህነት ብልጫ እንዳለው አሥራት በመስጠት መሰከሩ፡፡ አብርሃምን፣ የተስፋ ቃል የነበረውን ስለ ባረከና አሥራት ስለ ተቀበለው ከእርሱ የበለጠ መሆኑን ያሳያል፡፡ ትንሹም በታላቁ እንዲባረክ ክርክር የሌለበት የብሉይ ኪዳን ሥርዓት ነበር፡፡  

            ኢየሱስ እንዴት ካህን ሊሆን ይችላል? ቁ.11-14 በጸሐፊው አቀራረብ ክህነቱና ሕጉ (ኦሪቱ) ተያይዘዋል፣  ምክንያቱም ክህነቱ ከሕጉ ጋር የተሰጠ ስለሆነ የማይነጣጠሉ ናቸው፡፡ እንግዲህ ክህነቱ ከተለወጠ ሕግ የግድ መለወጥ አለበት፡፡ ሌላ ካህን ለምን አስፈለገ? የሌላው አገልግሎት ጐዶሎና ፍጹም ስላልነበረ ነው፡፡ ኢየሱስ ከይሁዳ ወገን ስለ ነበረ፣ ከሌዊ ነገድም ስላልነበረ፣ በሕጉ መሠረት ሊቀ ካህን ለመሆን በፍጹም አይችልም ነበር፡፡ ኢየሱስ ከላይ በምዕራፍ 7፡20-21 ላይ ባየናቸው ሦስት ነጥቦች ምክንያት ልዩ ካህን ሆነ፣ በአዲስ ካህን መምጣት ምክንያት አሮጌው ክህነትም ሕጉም ተሽሯል፡፡ አዲሱን ካህን ሞት ሊያሸንፈው በፍጹም አይችልም፣ አልቻለምም፡፡ በዚህ ምክንያት ለሰው ልጆች ደህንነትን ሊያስገኝና ወደ ባሰ ኃጢአት እንዳንገባ ጠበቃችን ሆኖልናል፡፡

ኢየሱስ ሊቀ ካህን የሆነባቸውን ምክንያቶች ጸሐፊው በአራት ተጨማሪ ማስረጃዎች ያረጋግጣል፡፡

1) ከትንቢት የተገኘው ማስረጃ፡- ቁ. 15-19፣ መዝ.110፡4 በሙሴ ሕግ መሠረት የተሾሙ ካህናት ሁሉ እንደ ሌላ ሰው ይሞቱ  ነበር፡፡ መዝሙር 110፡4 ግን የኢየሱስ ክህነት የማይለወጥ መሆኑን ይናገራል፡፡ እንደ አሮን ሳይሆን እንደ መልከ ጼዴቅ ነው፡፡ በመዝሙር በተነገረው ትንቢት መሠረት የኢየሱስ አገልግሎት እንኳ በጣም የበለጠ ሆነ፣ ሕያው ነውና፣ የሚቀርቡትን ሁሉ ይቀበላቸዋል፣ ያበረታታቸዋል፣ ያጸድቃቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት አዲሱ ሕግ ሲመጣ የቀድሞው ጥቅመ ቢስ ሆነ፡፡ እኛ በአዲሱ ሊቀ ካህንና በአዲሱ ሕግ ሥር እንገኛለን፡፡

2) ከመሐላ የተገኘ ማስረጃ፡- ቁ.20-22 መዝ.110፡4 የመሐላ ጥቅም ምንድር ነው? በጸሐፊው ሀሳብ መሐላ እውነትን ማረጋገጫና የሙግት ፍጻሜ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ የፊተኛው ክህነት አስፈላጊ በመሆኑ ምክንያት ብቻ ተቋቁሞ ነበር፡፡ መዝ. 110፡4 በቀጥታ ክርስቶስን ያመለከተ መሆኑን ምንም አልተጠራጠረም፡፡ አሁን አዲስ ነጥብ ቀርቧል፣ የተሻለው ቃል ኪዳን በኢየሱስ ተሰጥቷል፡፡ በብሉይም በአዲስ ኪዳንም መሐላ ለእውነት ከሆነ አልተከለከለም፡፡ ስለዚህ የኢሱስን ሊቀ ካህንነት አባቱ በመሐላ ስላጸደቀለት፣ የአዲስ ኪዳን መሥራችና ዋስ (ተያዥ) ሆኖልናል፡፡ ጸሐፊው የዕብራውያን አማኞች ይህን እውነት እንዲረዱ ሲል ነው መልእክቱን የሚጽፍላቸው፡፡

3) ከአለመሞት የተገኘ ማስረጃ፡- ቁ.23-25 ካህን ምን ዓይነት ሰው ነው? እግዚአብሔርን ወደ ሰው ያቀርባል፣ ሰውንም ወደ እግዚአብሔር ያቀርባል፡፡ ከሌዊ ነገድ የነበሩ ካህናት እንደ ማንኛውም ሰው ኃጢአተኛና የሚሞቱ ነበሩ፡፡ ኢየሱስ ግን አሁንም ሕያው ነው፣ ዘላለማዊ ነው፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ሞትን ድል አድርጎ በመነሣቱና ሕያው በመሆኑ ብቸኛው ዘላለማዊ ሊቀ ካህናችን ሊሆን ችሎአል፡፡ በቁ.25 ስንት ነገር ለማድረግ እንደሚችል ተገንዘቡ፡፡ ያድነናል፣ ያማልደናል፣ ለጸሎታችን መልስ ይሰጣል፣ በሕይወት ዘላለም ይኖራል፡፡

4) ከፍጹም መሥዋዕት የተገኘው ማስረጃ፡- ቁ. 26-28 የአይሁድ ሊቀ ካህን ሥራ አልቋል፣ አሁን ሌላ ካህን አለን፣ እርሱም  ሀ. ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ፣ ለ. ከሰማያት ከፍ ከፍ ያለ፣ ሐ. ለዘላለም ስለሚኖር ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱ ራሱ ፍጹም ስለሆነ ሊያቀርብ የሚችለው አገልግሎት እክል የሌለበት ነው፡፡ ፍጹም የሆነ መሥዋዕት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አቀረበ፣ እንደ ብሉይ ኪዳን ካህናት፣ ለራሱ ሳይሆን ለእኛ አቀረበልን፡፡ ሥራው የተፈጸመ በመሆኑ ሁልጊዜ የሊቀ ካህኑን የቃጭል ድምፅ ለመስማት መጓጓት የለብንም፡፡ የዕብራውያን አማኞች ይህን ድምጽ ለመስማት የናፈቁ ይመስላሉ፡፡ ስለዚህ የእኛ ብቸኛው ሊቀ ካህን ፍጹም መሥዋዕት በማቅረቡ ከመልከ ጼዴቅ እንደሚበልጥና ማስረጃውን እንዲቀበሉ ያሳስባቸዋል፡፡ አሜን!

1. ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በብሉይ ኪዳን ከተገለጡት ካህናት ሁሉ ይበልጣል፣ ከሰንበት፣ ከቤተ መቅደስና ከሰሎሞን መብለጡን እርሱ ራሱ ገልጾ ነበር፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ነው፣ የሰውን ድካምና የእግዚአብሔርን ጻድቅነት ስለሚረዳ፣ እውነተኛ አስታራቂ ሊቀ ካህናችን እርሱ ነው፡፡ እርሱን አውቀን ወደ ኋላ መመለስ የማይታሰብ ነገር ነው፡፡ ምን ለማግኘት እርሱን እንተዋለን? ምንም !

2. የብሉይ ኪዳን ሕግ አልፏል፣ ቦታው ግን ባዶ አይደለም፡፡ በቦታው ሌላ ተሰጥቷል፡፡ ሕጉ ባያልፍ ኖሮ ሌላ ሊመጣ ባልቻለም ነበር፣ አዲስ ኪዳንም የለም ማለት ነበር፡፡ ጥምቀትና የጌታ ራት የአዲሱ ኪዳን ሥርዓትና ምልክቶች ናቸው፡፡

3. ኢየሱስ ሕያው ብቸኛ ሊቀ ካህን ሆኖ ያገለግላል፡፡ የሌሎች አገልግሎት በሞት ምክንያት ተቋርጦአል፡፡ ሕያው ሆኖ ማገልገሉ ከማስረጃዎቹ አንደኛው ነው፡፡ያማልደናል፣ ኃይል ይሰጠናል፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *