ባለፈው ጽሑፍ የተመለከትነው ጸሐፊው ማን እንደሆነና የመጽሐፉን ይዘት ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ስለ መልእክት ተቀባዮቹ እንመለከታለን፡፡ መልእክቱ የተጻፈው ለዕብራውያን አማኞች እንደሆነ ገምተናል፡፡ ዕብራውያን የተባሉት የአብርሃም ልጆች ናቸው፡፡ (አብርሃም ይስሐቅን፣ ይስሐቅ ያዕቆብን፣ ያዕቆብ አሥራ ሁለቱን ነገዶች ወለዱ) ለአሥራ ሁለቱ ነገዶች ዕብራውያን፣ እስራኤላውያን፣ አይሁድ የሚሉት ሦስቱም ለእነርሱ የተሰጡ መጠሪያ ናቸው፡፡ (ዘፍ. 14፡13፣ 32፡28) የክርስትና እምነት የተጀመረው በእስራኤል አገር እንደ ሆነና ብዙዎች ዕብራውያን በክርስቶስ እንዳመኑ እናውቃለን፡፡ በበዓለ ኀምሳ ቀን ‹‹ከሰማይ በታች ካሉ ሕዝብ ሁሉ በጸሎት የተጉ አይሁድ በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር›› (የሐዋ. 2፡5) ‹‹… አይሁድ በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሁላችሁ…›› (ቁ፣14) ‹‹የእስራኤል ሰዎች ሆይ፡- ይህን ቃል ስሙ…›› (ቁ.22) ‹‹ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ፣ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ››(ቁ.41) ‹‹… ቃሉን ከሰሙት ብዙዎች አመኑ የወንዶችም ቍጥር አምስት ሺህ ያህል ሆነ›› (ቁ.4፡4) በማለት ቃሉ በሚገልጸው መሠረት፣ የመጀመሪያዎቹ አማኞች አይሁዶች ስለ ነበሩ፣ መልዕክቱ የተጻፈላቸው የዕብራውያን አማኞች እንደ ነበሩ መረዳት እንችላለን፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ የዕብራውያን አማኞች የት እንደ ነበሩ መልእክቱ አይነግረንም፡፡ የቀሩት ብዙዎቹ መልእክቶች ሁሉ አድራሻ ሲኖራቸው፣ የዕብራውያን መልእክት ግን አድራሻ የለውም፡፡

የመልእክቱ ተቀባዮች ክርስቲያኖች ከመሆናቸው የተነሣ በመከራ ውስጥ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ ጸሐፊው መልእክቱን የጻፈው ለመላው ቤተ ክርስቲያን ሳይሆን ልዩ ችግር ለገጠመው ክፍል ነበረ፡፡ ከክርስቲያኖች ጋር የነበራቸውን ኅብረት በማቋረጥ ከመከራው የማምለጥ ሀሳብ ነበራቸው፡፡ ወደ ብሉይ ኪዳን ሥርዓት ተመልሰው እንደገና ከአይሁዶች ጋር ለመቀላቀል ፈልገው ነበር፡፡

ስደቱን ያስነሱባቸው ዘመዶቻቸው የሆኑት አይሁዶች ነበሩ፣ የሮም ቄሣር ኔሮ ያነሣሣው ስደት ገና ባይጀምርም ዋዜማው ደርሷል፡፡ ከችግር የተነሣ ከክርስቲያኖች አንድነት ተገልለው ወደ ቀድሞ ኅብረት እንዲመለሱ ተፈተኑ፡፡ በልባችን አምነን እምነታችንን ለማንም አንገልጠውም የማለት ሀሳብ ነበራቸው፡፡ በአሮጌውና በአዲሱ መካከል ያለውን ግንኙነት በሚገባ አልተረዱትም፣ ደግሞ የይቅርታ ማግኛውን ትተው ይቅርታ ወደማይገኝበት ሥርዓት ቢመለሱ በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ መገኘታቸውን አልተገነዘቡም፡፡ የአይሁድ ሊቀ ካህን የፍጹም ይቅርታ ዋስትና ሰጪ እንደነበረ ሁሉ ኢየሱስ በተሻለ መንገድ ሊቀበላቸውና ሊያጽናናቸው ሰው ሆኖ መምጣቱን አልተረዱም፡፡

እነዚህ አማኞች የት እንደነበሩ የተለያየ አመለካከት ይሰጣል፡፡ 1ኛ. በኢየሩሳሌም 2ኛ. በእስክንድርያ (ግብፅ) 3ኛ. በኢጣሊያ ብለው የሚያስተምሩ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች አሉ፡፡ መጽሐፉ በትክልል የት እንዳሉ ስለማይናገር ሦስቱም ሀሳቦች የመልእክቱን ይዘት አይለውጡትም፡፡ መልእክት ተቀባዮቹ የት እንዳሉም ባይታወቅም የነበሩበትን ሁኔታ ከመጽሐፉ ውስጥ ጠቋሚ ሀሳቦች ማግኘት እንችላለን፡፡ ጸሐፊውና መልእክት ተቀባዮቹ በሚገባ እንደሚተዋወቁ መረዳት ይቻላል፡፡

  • ከሰሙት ወንጌል ለመወሰድ የቀረቡ (2፡1-4)          
  • ባለ ማመን ልባቸውን እልከኛ ያደረጉ (3፡15)           
  • የሕፃንነት ሕይወት የሚታይባቸው (5፡11-12          
  • በጌታ መታመናቸውን የጣሉ (10፡35)
  • በነፍሳቸው ዝለው የደከሙ (12፡3-4)
  • ቃሉን መስማት የሰለቹ (12፡25)
  • ሰው ምን ይለኛል የሚሉ (13፡6)

እኔ ጸሐፊው ጳውሎስ ነው ካልኩኝ ዘንድ፣ መልእክት ተቀባዮቹ በሮም ነበሩ ማለት ይቀለኛል፤ ምክንያቱም ‹‹ከኢጣሊያ የሆኑት ሰላምታ ያቀርቡላችኋል›› ስለሚል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያ እስራቱ  ጊዜ በሮም ተቀምጦ ለሁለት ዓመት ያህል እስረኛ ሆኖ ቅዱሳንን እንዳገለገለ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የመጨረሻው ምዕራፍ ይነግረናል፡፡ ከእስራቱ ከተፈታ በኋላ ከጻፋቸው ጽሑፎች የዕብራውያን መልእክት አንዱ ነው፡፡ በሮም ለሚኖሩ ብሉይ ኪዳንን ለሚያውቁ ጥቂት የአይሁድ ምሁራን ልዩ ትምህርት ያስፈልጋቸው ስለ ነበርና፣ ብዥ ያለባቸውን ነገር ለማጥራት እንደ ጻፈላቸው እገምታለሁ፡፡

ጌታን በማመናቸው ምክንያት ከፍተኛ ተቃውሞና ስደት ደርሶባቸዋል፡፡ ከዚህም የተነሳ አዲሱን እምነታቸውን ትተው ወደ ድሮ እምነታቸው ለመመለስ የሚያወላውሉና በጥርጣሬ ላይ ያሉ ይመስላሉ፡፡ ጸሐፊው እነዚህ ክርስቲያኖች ክርስትናን ትተው ወደ ድሮው የአይሁድ ሃይማኖት ከሄዱ የሚከተላቸውን ችግር ያመለክታቸዋል፡፡

መልእክቱ መቼ ተጻፈ? ለሚለው ሀሳብም የተለያዩ ሀሳቦችም ይቀርባሉ፡፡ ቢሆንም ግን በ66 እና በ70 ዓ.ም መካከል እንደ ተጻፈ በውስጡ ባሉት መረጃዎች መረዳት ይቻላል፡፡ ደራሲው በ70 ዓ.ም ስለ ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሱ መፍረስ የተናገረው ምንም ነገር የለም፡፡ በብሉይ ኪዳን ሥነ ሥርዓት ሊቀ ካህን ምን ያህል አስፈላጊ እንደነበረ ዘሌዋውያን 16 ያሳየናል፡፡ ያለ ካህን አገልግሎት፣ ሥነ ሥርዓቱ ትርጉም የለሽ በሆነ ነበር፡፡ እነዚህ አይሁድ ክርስትናን ከተቀበሉ በኋላ እንደገና ካላመኑት አይሁድ ጋር ለመቀላቀል ፈለጉ፡፡ ምናልባት የክርስቲያኖች ጉባዔ ትንሽና በከተማው ውስጥ ብዙ ተቀባይነት ያላገኙ ይሆን ይሆናል፡፡ የአይሁድ ሊቀ ካህን በኢየሱስ ተተክቶ እንደሆነ የአይሁድ ጉባዔ ምን ጥቅም አለው? ጊዜ ያለፈበት ነው፡፡ በምዕራፍ 8፡13 ላይ በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበረውን ሥርዓት እስከ አሁን ቢጠቀሙበትም በአዲሱ የሚተካበት ጊዜ መቅረቡን ያመለክታቸዋል፡፡ በምዕራፍ 7 ላይ ጸሐፊው ሊያስረዳቸው የሚፈልገው ነጥብ ይህ ነው፡፡ ዘመን የማይሽረው ብቸኛው ሊቀ ካህን መገኘቱን በስፋት በመተንተን ያበስራቸዋል፡፡

   የዕብራውያንንመጽሐፍ በሚገባ ለመረዳት ማጥናት የምንጀምረው ከምዕራፍ ሰባት ይሆናል፣ ምክንያቱም የመጽሐፉ ዋና ሐሳብ (እምርት) ያለው እዚያ ስለሆነ፡፡ የምዕራፍ ሰባት ሐሳብ በሚገባ ከገባን በሌሎች ምዕራፎች ላይ ያሉት ሐሳቦች ሁሉ በቀላሉ ይገቡናል፡፡ አከፋፈሉንም ከዚህ በታች ባሉት በሰባት ርዕሶች ከፍለን በዝርዝር (ጥቅስ በጥቅስ) ሳይሆን ጠቅለል ባለ  መልኩ እንደሚከተለው እናያቸዋለን፡፡

         አከፋፈሉ፡- ምዕ 7   መልከ ጼዴቅና ኢየሱስ                                   

                     ምዕ 1 – 2 ኢየሱስ ከመላእክት ይበላጣል                           

                      ምዕ 3 –4 ኢየሱስ ከሙሴ ይበልጣል                              

                     ምዕ 5 – 6 ኢየሱስ ከአሮን ይበልጣል  

  ምዕ 8 – 9  የተሻለ ቃል ኪዳን

ምዕ 10 – 11  የተሻለ ተስፋ                      

ምዕ 12 – 13  የተሻለ ኑሮ


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *