በእነዚህ ጽሑፎች ውስጥ ያነሳሁት ዋና ቁም ነገር ለሐዋርያት የተሰጠው ታላቁ ተልዕኮ ከኢየሩሳሌም ተነስቶ ከግብ መድረስ አለመድረሱን ማሳየት ሲሆን፣ በመቀጠልም ይህ ተልዕኮ የኢየሩሳሌምና የአንጾኪያ አብያተ ክርስቲያናት ተቀብለውት የት እንዳደረሱት መዳሰስ ነበረ፡፡ በዚህም ዳሰሳ ያየነው የሁለቱም ብርታታቸውና ድካማቸው ምን እንደ ነበረ ማየትና ከእነርሱ ተምረን ልናስተካክል በምንችለው ላይ እርምጃ እንድንወስድ ነው፡፡ የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን ከጌታ የተሰጣትን የመንፈስ ቅዱስ ተስፋ በመቀበል ታላቁን ተልዕኮ ለመወጣት ያደረገችውን ጥረት፣ በመከራ ውስጥ ሆነው ወንጌልን መመስከራቸው፣ የነበራቸው ሕብረትና የጸሎት ሕይወት፣ ድሆችን የመርዳት ትጋታቸው፣ ለጌታ የነበራቸው መሰጠትና ያላቸውን እየተው ለወንጌል ሲሉ ከአገር ወደ አገር እየዞሩ ወንጌሉን ማሠራጨታቸው ብርታታቸውን አሳይቶናል፡፡
ሐዋርያት በሕግ ታሰረው፣ ወገናዊ ሆነው፣ ታላቁን ተልዕኮ ወገናዊ ማድረጋቸው፣ ስደተኛና ያልተሰደዱ፣ ከተሜና ገጠሬ፣ የተማረና ያልተማረ በማለት በተፈጠረ ችግር፣ ለስምና ለዝና ሲሉ ባደረጉት አስመሳይነት ታይቶባቸዋል፡፡ ጳውሎስም በገላትያ 2፡11-14 ላይ ‹‹…እንደ ወንጌል እውነት በቅንነት እንዳልሄዱ ባየሁ ጊዜ በሁሉ ፊት ኬፋን (ጴጥሮስ):- አንተ አይሁዳዊ ሳለህ በአይሁድ ኑሮ ያይደለ በአሕዛብ ኑሮ ብትኖር፣ አሕዛብ በአይሁድ ኑሮ ሊኖሩ እንዴት ግድ አልሃቸው? አልሁት::›› በማለት ጴጥሮስና በርናባስ በአይሁድና በአሕዛብ ፊት ያሳዩትን ግብዝነት (ማስመሰል፣ ወገንተኝነት) ፊት ለፊት በመቃወም እንደ ገሠጻቸው ይናገራል፡፡ አማኞችም በቤተ ክርስቲያን በዓላማ ባለመገናኘት የተደረገ የአገልጋዮች መለያየትና ሳይለወጡ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመግባት የጸጋ ስጦታን ለመለማመድና የመሪነት ስፍራ ለመያዝ ያደረጉት ጥረት እና የመሳሰሉት ድካማቸውን ያመለክቱናል፡፡
የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን የተሰጣትን ታላቁን ተልዕኮ ለአይሁድም ለአሕዛብም ማድረስ ሲገባት፣ በጎጂ ልማዳዊ ባሕል እስራት ተይዛና ግርግዳ ሠርታ ብትቆይም፣ የአንጾኪያን ቤተ ክርስቲያን ለውጥና ዕድገት በማየት፣ ተልዕኮዋን በመፈተሽና ታላቁ ተልዕኮ በሌሎች በስፋት ሲተገበር በማየታቸው ከሃያ ዓመት በኋላ ወደ መንፈሳዊ ብስለት በመምጣት፣ ያቆሙትን ግርግዳ አፍርሰው ወደ አሕዛብ ወንጌሉን ይዘው ወደ ተለያየ አገር በመሄድ፣ ብዙዎች ሐዋርያት መሥዋዕት ሆነው እንዳለፉ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ይነግረናል፡፡ ለምሳሌ፣ ቶማስ ወደ ሕንድ፣ ማቴዎስ ወደ ኢትዮጵያ፣ ሌሎቹም በተለያየ አገር ለወንጌል ሥራ ተበታትነው ባሉበት መሬት ለመሬት እየተጎተቱ፣ ቆዳቸው እንደ ከብት እየተገፈፈ፣ በሰይፍ እየተሰየፉ መሥዋዕት ሆነው አልፈዋል፡፡ ወደ ብስለትና መረዳት ሲመጡ በዚህ መንገድ አልፈዋል፡፡ ይህ መረዳታቸውና ብስለታቸው ግን ቶሎ ሊመጣ አልቻለም፣ ምክንያቱም መንፈሳዊ ዕድገት ቅጽበታዊ አይደለምና ነው፣ እንደ አንድ ሕፃን ልጅ እድገት ጊዜ ይወስዳል፣ ከቃሉም ጋር ይበልጥ መተዋወቅ ያስፈልጋል፤ ከጌታ ጋር የቆይታ ጊዜና መሰጠትንም ይጠይቃል፡፡
በመጀመሪያው ጽሑፌ ላይ እንደገለጽኩት ሉቃስ የተረከልን ‹‹ውሾች›› የተባሉት አሕዛብ ወንጌልን እንዴት እንደ ተቀበሉ መተረክ ሲሆን፣ ይህ የእርሱ የመልእክቱ ዋና ዓላማ የተመሠረተበት ነበር፡፡ የሉቃስ ትኩረት የጳውሎስን አገልግሎትና የአሕዛብን መዳን በስፋት መተንተን ነበር፤ ቢሆንም፣ ይህ ማለት ሌሎቹ ሐዋርያት ምንም አልሠሩም ማለት አይደለም፡፡ የሠሩትንና ታሪካቸውን በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ማግኘት እንችላለን፡፡
የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ግን ታላቁን ተልዕኮ ተቀብላ በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳ፣ በሰማርያ እና በዓለም ዳርቻ ይዛ በመውጣት ከኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ይልቅ ቀዳሚነቱንና ሚስዮናዊነቷን ይዛ ትገኛለች፡፡ እኛም ዛሬ ያለንበት ሁኔታ ብዙ ፈተና የተጋረጠበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ የሐዋርያት ችግር/ፈተና አሕዛብን ከወንጌሉ ማግለል ሲሆን፣ የተሃድሶ ዘመን (የእነሉተርና መሰሎቹ) ችግር ሁለቱም አማኞች ሆነው አንዱ ሌላውን የእኔን አስተምህሮ ካልተቀበልክ ብለው በማውገዝ፣ በማሠቃየት፣ በመግደልና ሬሳ በማቃጠል መልካሙን የወንጌል ታሪክ ጥላሸት በመቀባት አበላሽተውት አልፈዋል፡፡ አማኙን አማኝ ሲያፈናቅለው፣ ሲገድለው፣ ወንጌል ከድል በኋላ እየተባለ ባለበት ሁኔታ፣ ምን ዓይነት የወንጌል ታሪክ ሠርተን እናልፍ ይሆን? መቼም አይቀሬው ሞት ወደ እያንዳንዳችን መምጣቱ የታወቀ ነው፡፡ ከሐዋርያት ያነሰ ወይስ የበለጠ ስሕተት ሠርተን እናልፍ ይሆን? ከእነርሱ ብርታትና ድካም ተምረን ተልዕኮውን የት እንዳደረስነው ራሳችንን በመጠየቅና በመፈተሽ የወንጌልን አደራ እንድንወጣ መጸለይና በችግሮቻችን ላይ እርምጃ ልንወስድ ይገባናል፡፡ እኛ እርምጃ ካልወሰድን ጌታ የሚወስደው እርምጃ ከባድና አስከፊ ይሆንብናል፡፡ ዛሬ በተሰጠን ጊዜ ተንቀሳቃሽ እንጂ፣ ውዝፍ አማኝ (ቤተ ክርስቲያን) እንዳንሆን ጌታ ይርዳን! አሜን፡፡
0 Comments