ጳውሎስ የኤፌሶንን ሽማግሌዎች ተሰናብቶ ወደ ኢየሩሳሌም እየሄደ ባለፈው ጽሑፍ ተመልክተን ነበር፡፡ በመቀጠልስ ጳውሎስ ምን አድርጎ ይሆን? የት ከተማ ሄዶ ይሆን? ወንጌልን ሲሰብክ ምን ደርሶበት ይሆን? ያለበትን ሁኔታ ለማወቅ ጉጉት አላደረባችሁም? ጳውሎስ በየመንገዱ ማለት በከተሞች በጢሮስ ሰባት ቀን በአካ አንድ ቀን ቆይቶ፣ ቀጥሎም በቂሣርያ በደረሰ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ እንደሌለበት በፊልጶስ ቤት ተቀምጦ ሳለ፣ አራት ትንቢት የሚናገሩ ልጃገረድ የሆኑ ሴቶች ተናገሩለት፡፡ ቢሆንም ግን፣ ሊቀበላቸው ፈቃደኛ ባልሆነ ጊዜ፣ የተልዕኮውን ጌታ በመተማመን “የጌታ ፈቃድ ይሁን ብለን ዝም አልን” ይላል ሉቃስ፡፡
እነጳውሎስም ወደ ኢየሩሳሌም ሲደርሱ የሽማግሌዎች ሰብሳቢ ወደ ሆነው ያዕቆብ ቤት በገቡ ጊዜ ሽማግሌዎች ሁሉ ተሰብስበው መጡ፡፡ “ሰላምታም ካቀረበላቸው በኋላ በእርሱ ማገልገል እግዚአብሔር በአሕዛብ (ከአይሁድ ውጭ) መካከል ያደረገውን እያንዳንዱን ተረከላቸው፡፡ “እነርሱም በሰሙ ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡” አሉትም፣ “ወንድም ሆይ፣ በአይሁድ መካከል አምነው የነበሩት ስንት አእላፋት እንደ ሆኑ ታያለህ፤ ሁላቸውም ለሕግ የሚቀኑ ናቸው” (21፡19-20)፡፡
ይህንንም ብለው ከአራት ሰዎች ጋር የመንጻት ሥርዓት እንዲፈጽም አደረጉት፡፡ “ሰባቱ ቀንም ይፈጸም ዘንድ ሲቀርብ ከእስያ የመጡ አይሁድ በመቅደስ አይተውት ሕዝብን ሁሉ አወኩና፡- የእስራኤል ሰዎች ሆይ፣ እርዱን፤ ሕዝብን ሕግንም ይህንም ስፍራ ሲቃወም ሰውን ሁሉ በየስፍራው የሚያስተምረው ሰው ይህ ነው፤ ጨምሮም የግሪክን ሰዎች ደግሞ ወደ መቅደስ አግብቶ ይህን የተቀደሰ ስፍራ አርክሶአል ብለው እየጮኹ እጃቸውን ጫኑበት” (21፡27-28)፡፡ ጳውሎስ ከፍተኛ በሆነ ተቃውሞ ውስጥ ገብቶ እየደበደቡት ሳለ፤ ሻለቃው ደርሶ ከድብደባው አድኖት በቁጥጥሩ ሥር አድርጎ እስረኛ አደረገው፡፡
ሦስተኛውን የወንጌል ጕዞ ጨርሶ ወደ አንጾኪያ ደርሶ ዘገባ ሳያቀርብ፣ በኢየሩሳሌም እስረኛ ሆኖ ሳለ፣ ሕዝቡ ሊገድሉት ከፍተኛ ዓመፅ ባስነሱ ጊዜ፣ ሻለቃው ለሞት ወይም ለእስራት የሚያበቃ ምንም ነገር ሊያገኝበት እንዳልቻለ ገልጾ ከደብዳቤ ጋር ወደ ቂሣርያ አገረ ገዥ ወደ ፊልክስ ላከው፡፡ ፊልክስም ጉቦ ይሰጠኛል እያለ ሲጠብቅ ባለማግኘቱ ሁለት ዓመት አቆይቶት በምትኩ ሌላ አገረ ገዥ ፊስጦስ ተተካ፡፡ ይህንንም ያደረገው አይሁድን ደስ ለማሰኘት ነበር (ሐዋ.21፡31-33፤ 23፡26-30፤ 24፡22-27)፡፡
ዛሬም ጉቦ ባለ መስጠታችን በእስር ቤት ልንጣል፣ ንብረታችን ሊወሰድ፣ ጉዳያችን ላይፈጸምና ያለ ፍርድ ልንገላታ እንችላለን፡፡ መልካም ማድረግ ብዙ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ጳውሎስ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ ጌታ በአጠገቡ ሆኖ እንዳበረታው እኛንም ስለሚያበረታን፣ በእርሱ ታምነን እንሰማራ፡፡
“በሁለተኛውም ሌሊት ጌታ በአጠገቡ ቆሞ፡- ጳውሎስ ሆይ፣ በኢየሩሳሌም ስለ እኔ እንደ መሰከርክ እንዲሁ ሮሜም ትመሰክርልኝ ዘንድ ይገባሃልና አይዞህ አለው” (ሐዋ. 23፡ 11)፡፡ ጳውሎስ በሻለቃው ሉስዮስ፣ በሊቀ ካህናቱ ሐናንያ፣ በአገረ ገዥው ፊልክስና ፊስጦስ፣ እንዲሁም በንጉሡ አግሪጳ ፊት እየቀረበ በሚከራከርበት ጊዜ ሁለት ነገሮችን ተጠቅሞአል፡፡ 1ኛ) የሮማዊ ዜግነት እንዳለው በመናገሩ፣ ከከፋ ሥቃይና እስራት ሊጠበቅ ችሎአል፡፡ ጌታም ወደ ደህንነት ሲጠራው ሊጠቀምበት የፈለገውም በዚህ ምክንያት ነበር፡፡ 2ኛ) ወደ ቄሣር ይግባኝ መጠየቁ፣ በሕግ ያገኘውን መብቱን በሚገባ ተጠቅሞበታል (ሐዋ.22፡24-29፤ 25፡11-12፤ 26፡32)፡፡
ጳውሎስ ለሞትም ሆነ ለእስራት የሚያበቃው ምንም ነገር እንዳላገኙበት እነፊስጦስ በድጋሚ ከመሰከሩ በኋላ፣ ይግባኝ በማለቱ ብቻ ወደ ቄሣር እስረኛ ሆኖ እንዲሄድ ተወሰነበት (ሐዋ.27፡1)፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም እስረኛ ሆኖ አራተኛውን የወንጌል ጕዞ በብዙ ችግር ከሦስት ወር በላይ በመጓዝ ወደ ሮም ከተማ ደርሰው ከጠባቂው ወታደር ጋር አብሮ እንዲቀመጥ ተፈቀደለት (28፡16)፡፡ ምንም እንኳን እንደ ሌሎቹ ጕዞዎቹ በነጻነት ማገልገል ባይችልም፣ በተከራየው ቤት ተቀምጦ ለሁለት ዓመት ያህል የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበከ እንደ ኖረ ሉቃስ ይነግረንና፣ ይፈታ አይፈታ ምንም ነገር ሳይነግረን ደብዳቤውን ይዘጋዋል (28፡30-31)፡፡ የጳውሎስ የእስር ቤት ደብዳቤዎች እየተባሉ የሚጠሩት የኤፌሶን፣ የፊልጵስዩስ፣ የቆላስይስና የፊልሞና ደብዳቤዎች የተጻፉት በዚህ ጊዜ እንደሆነ ብዙዎች የመጽሐፍ ቅዱስ አዋቂዎች ይስማሙበታል፡፡ ስለዚህ ጳውሎስ የእስራቱን ጊዜ ያሳለፈው በመስበክና በማስተማር ብቻ ሳይሆን፣ ደብዳቤዎችንም በመጻፍ እንደሆነ መረዳት እንችላለን፡፡ ከአዲስ ኪዳን 27 መጻሕፍት ውስጥ 13ቱን የጻፈው እርሱ ነው፡፡ ስለዚህ ምንም ያባከነው ጊዜ አልነበረውም፡፡ ይህ ሁሉ በአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን (ተንቀሳቃሽዋ) በሚስዮናዊነቷ የተገኘ ውጤት ነው፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ጳውሎስን ባትቀበለውና ባታቅፈው ኖሮ ይህ ውጤት ሊገኝ አይችልም ነበር፡፡ ዛሬም ውጤታማ የሆኑ አገልጋዮችን ቤተ ክርስቲያን አቅፋ፣ ለወንጌል አገልግሎት ልታሰማራቸው ይገባል፡፡ አገልጋዮችም በቤተ ክርስቲያን በመታቀፍ ፍሬአማ አገልግሎት ልንሰጥ ይጠበቅብናል፡፡ ለዚህም ሁሉ የተልዕኮው ጌታ በአጠገባችን ሆኖ ጸጋውን ያብዛልን፡፡
0 Comments